1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ስጋቱ እያየለ የመጣው እገታ በኦሮሚያ ክልል

ማክሰኞ፣ ጥቅምት 13 2016

በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ አከባቢዎች በታጠቁ አካላት የሚፈጸሙ እገታዎች ነዋሪዎችን ማማረራቸውን እንደቀጠሉ ነው፡፡ ሌሊት ከሚኖሩበት ቀዬ እየታገቱ ተወስደው በመቶ ሺዎች አልም በሚሊየን የሚቆጠር ገንዘብ እንደሚጠየቁም ነዋሪዎች ተናግረዋል። የእገታዉ አሁን አሁን መልኩን ቀያይሮ በርካታ ቦታዎችን ማዳረሱም ተጎጂዎችተመልክቷል፡፡

ኦሮሚያ ክልል፤ ጉጂ ዞን
በኦሮሚያ ክልል፤ ጉጂ ዞን ምስል Private

በታጋቾች ሌሊት ከሚኖሩበት እየታገቱ ተወስደው በመቶ ሺዎች አልያም በሚሊየን የሚቆጠር ገንዘብ የሚጠየቁ ነዋሪ ቤተሰቦች፤ ጉዳዩ የጸጥታ እጦቱ ፈታኝ ገጽታ መሆኑን ገልፀዋል

This browser does not support the audio element.

በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ አከባቢዎች በታጠቁ አካላት የሚፈጸሙ እገታዎች ነዋሪዉን ማማረሩ እንደቀጠለ ነው፡፡ ሌሊት ከሚኖሩበት ቀዬ እየታገቱ ተወስደው በመቶ ሺዎች አልያም በሚሊየን የሚቆጠር ገንዘብ እንደሚጠየቁ የሚናገሩት የታጋች ቤተሰቦች፤ እገታዉ የጸጥታ እጦቱ ፈታኝ ገጽታ መሆኑንም ነዋሪዎች አማረዋል። አሁን አሁን ደግሞ እገታዉ መልኩን ቀያይሮ በርካታ ቦታዎችን ማዳረሱንም የእገታዉ ሰለባ የሆኑ ነዋሪዎች ተናግረዋል።

ለደህንነታቸው ሲባል ስማቸው እንዳይጠቀስና ድምጻቸውም እንዳይሰማ ጠይቀው አስተያየታቸውን የሰጡን በምስራቅ ሸዋ ዞን የአደአ ወረዳ ጊጬ ጋራ-ባቦ ቀበሌ ነዋሪ በየሰበብ አስባቡ ተስፋፍቷል ያሉት የእገታ አሁን የነዋሪዎች ዋነና ስጋት መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ አስተያየት ሰጪው በቅርቡ ከዚሁ ቀበሌ አንድ ሰው ተገድለው ሌሎች ሶስት በሌሊት ታግተው ተወስደው በነፍስ ወከፍ በመቶ ሺህ ብር ከፍለው መውጣታቸውንም አመልክተዋል፡፡ ሌለው ከምእራብ ሸዋ ዞን አደዓ በርጋ ወረዳ አስተያየት የሰጡን በተመሳሳይ ሁኔታ ለደህንነታቸው የሰጉ አስተያየት ሰጪ በወረዳው ጃሎ ከሚባል አከባቢ በቅርቡ እንኳ በአንድ ሌሊት የተወሰዱ 10 ሰዎች ገደማ ከመቶ ሺኅ እስከ ሚሊየን ተጠይቀው ከፍለው መውጣታቸውን ይገልጻሉ፡፡በኦሮሚያ ክልል የሰዎች መታገት ነዋሪዎችን አማሯል

ከዚሁ ዞን ደንዲ ከተባለ ወረዳ ቤተሰብ ደጋግሞ እንደታገተባቸው ገልጸው አስተያየታቸውን የሰጡን የጊንጪ ከተማ ነዋሪ የእገታ ተግባራቱ እየተለመደ ከመምጣቱም የህብረተሰቡን የመንቀሳቀስ ብሎም ወጥቶ የመግባትን ጉዳይ አደገኛ ያሉት ሁኔታ ውስጥ ከቷል፡፡ “የታጠቁ አካላት ትንሽ መሸት ሲል ታጥቀው ወደ ሰው ቤት ይገባሉ፡፡ የሚወስዱት ከብት ወይም ሌላ ንብረት አይደለም፡፡ ከቤተሰብ አባላት አንዱን ይዘው ይሄዱና ትንሽ ቆይተው በመደወል ገንዘብ ይጠይቃሉ፡፡ ከአንድ ሰው እስከ 500 ሺህ ብር ይጠየቃል፡፡” 

አስተያየት ሰጪው በዚህ አከባቢ በተለይም ከኦሎንኮሚ ከተማ ወደ በቾ በሚወስደው መንገድ ፍንጫአ-ቦሬቲ በሚባል ቀበሌ ችግሩ ይከፋል ነው የሚሉት፡፡ በብዛት የሚታገቱት በእጃቸውም ቆጥረው የማያውቁትን ገንዘብም የሚጠየቁት የአከባቢው አርሶአደር መሆናቸውን በማንሳት ይህን ተግባር የፈሩ መተዳደሪያ እርሻቸውን ትተው ወደ ከተማም እየፈለሱ ነው ብለዋል፡፡ “የሚዘረፉት ገበሬዎች ናቸው፡፡ አሁን በዚህ የተማረሩት ዘመድ ያለው ወደ ዘመዱ ከከተማ ቤት ያለውም ወደዚያው እየሸሹ ነው፡፡ አሁን ከሰሞኑ እንኳ በአንድ ምሽት ስምንት ሰዎች ታግተው ተወስደው ዘረፋው ተፈጽሞባቸዋል፡፡”ምዕራብ ጎንደር ውስጥ በትንሹ 5 ሰዎች በታጣቂዎች ታግተዋል

አስተያየት ሰጪው እንደሚሉት መክፈል ያልቻለ አሊም ምክፈል ያልፈለገ ወዲያው ይገደላል ነው የሚሉት፡፡ የአጋቾችንም ማንነት ተጠይቀው ሀሳባቸውን ያጋሩን አስተያየት ሰጪው ማንነታቸውን በውል መግለጽ አዳጋች ቢሆንም ዘረፋን መተዳደሪያ ያደረጉ ግን መስላል ብለዋል፡፡ አስተያየት ሰጪው መንግስት ህዝብን አወያይቶ አንዳች መፍትሄ እንዲያመጣም ተማጽነዋል፡፡ ሌላው ከሰሜን ሸዋ ዞን ሰላሌ ደራ ወረዳ አስተያየታቸውን የሰጡን ነዋሪም ሀሳባቸውን ቀጠሉ፤ “የእገታው መክፋት አሁንም ችግር ውስጥ ከቶናል፡፡ ገንዘብ አለው ተብሎ የሚገመት ሁሉ ይታገታል፡፡ ለወሬውም አይመችም፡ መቶ ሁለት መቶ ሺኅ እና ከዚያም በላይ ይጠይቃሉ፡፡ አጋቾቹ በብዛት ሌሊቱን ነው የሚንቀሳቀሱት፡፡”

መንግስት በክልሉ በመሰል ተግባራት የሚከሰው እራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት በሚል የሚንቀሳቀሰውና መንግስት ሸነ ያለውን የሽምቅ ውጊያ ታጣቂን ነው፡፡ ታጣቂ ቡድኑ በፊናው ውንጀላውን በማጣጣል በገለልተኛ አካል ይጣራልኝ ሲል ነው የሚደመጠው፡፡ በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን የጠየቅናቸው የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶ/ር ለገሰ ቱሉ የችግሩን መኖር መንግስታቸው እንደሚገነዘብ ያስረዳሉ፡፡ስርቆት፣ ዘረፋ፣ እገታና ሥርዓተ አልበኝነት በትግራይ

ሚኒስትሩ ድርጊቱን የሚፈጽሙ “በህጋዊ መንገድ የተመረጠን መንግስት በሃይል ከስልጣን ለመጣል የሚያልሙ ያሏቸው የታጠቁ አካላትም” ናቸው ብለዋል፡፡ ሚኒስትሩ አክለውም መንግስት የህግ የበላይነትን ለማስከበር ሲል በየአከባቢው የሚወስዳቸው ወታደራዊ እርምጃዎችን መቋቋም የተሳናቸው ታጣቂ የሽምቅ ውጊያ ተዋጊዎቹ እራሳቸውን ወደ “ውንብድና” ቀይረው ህብረተሰቡን ያሰቃያሉ ነው ያሉት፡፡ ህብረተሰቡ ከመንግስት ጋር በትብብር ከሰራ የተሻለ ውጤት እንደሚመዘገብ በአስተያየታቸው አክለዋል፡፡ በኢትዮጵያ መንግስት እና በኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት መካከል ልዩነቶችን በሰላማዊ መንገድ ለመቋጨት በሚል ባለፈው ዓመት ሚያዚያ ወር ውስጥ በታንዛንያ የተጀመረው የሰላም ድርድር የተስፋ ጭላንጭሎች የታዩበትና ቀጣይነትም የሚኖረው ነው ቢባልም አሁን ላይ በክልሉ ያለው የጸጥታ ሁኔታ እንደተወሳሰበ ስለመቀጠሉ ይነገራል፡፡

ስዩም ጌቱ

አዜብ ታደሰ

ነጋሽ መሐመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW