1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ስጋትን ስላጫረው የአዲስ አበባው የመሬት መንሸራተት የአስተዳደሩ ምላሽ

ሥዩም ጌቱ
ሐሙስ፣ መስከረም 8 2018

በአዲስ አበባ በተለምዶ ብርጭቆ ሚኪላንድ ኮንዶሚኒየም እና አስኮ-አዲስ ሰፈር ተብለው በሚጠሩ አከባቢዎች የመሬት መሰንጠቅና ናዳ በከተማ አስተዳደሩ ቅርብ ክትትል ውስጥ መሆኑ ተነግሯል፡፡ በአደጋው የሰዎች ሕይወት ባይጠፋም በመሬት ናዳው የንብረት ጉዳት መከሰቱን ተከትሎ የከተማ አስተዳደሩ የአጭር እና ረጅም ጊዜ እልባቶችን እያበጀሁ ነው ብሏል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሥራ አስኪያጅ ወንድሙ ሴታ
“ከኢትዮጵያ ጂኦሎጂካል ኢንስቲትዩት የተውጣጡ የባለሙዎች ቡድን ባለፉት ሁለት ሳምንታት የአደጋውን መንስኤ ስያጠኑ” እንደነበር የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሥራ አስኪያጅ ወንድሙ ሴታ ተናግረዋል። ምስል፦ Seyoum Getu/DW

ስጋትን ስላጫረው የአዲስ አበባው የመሬት መንሸራተት የአስተዳደሩ ምላሽ

This browser does not support the audio element.

ዶይቼ ቬለ በትናትናው እለት በስፍራው ተገኝቶ በመመልከት ዘገባ የሰራበት የአዲስ አበባ ከተማ አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 13 እና 14 በተለምዶ ብርጭቆ ፋብሪካ እና አዲስ ሰፈር በሚባሉ አከባቢዎች ያጋጠመው የመሬት መሰንጠቅና መሸሽ የአከባቢው ነዋሪዎች ትልቅ ስጋት መሆኑ ተነግሯል፡፡

የአደጋ ምልክቱ ከነሃሴ ወር አጋማሽ ጀምሮ መታየቱን በተለይም ለዶይቼ ቬለ የተናገሩት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ዋና ስራ አስከያጅ ኢንጂነር ወንድሙ ሴታ፤ የአደጋ ምልክቱ ከታየበት ጊዜ ጀምሮ የሚመለከታቸው የከተማ አስተዳደሩ መዋቅሮች ክትትል ስያደርጉ ቆይተዋል ብለዋል፡፡ ለዚህም በመጀመሪያ የአደጋውን መንስኤ ወደ መለየት ተገብቶ ስለተገኘው ውጤት ማብራሪያ ሰጥተውናል፡፡

“ከኢትዮጵያ ጂኦሎጂካል ኢንስቲትዩት የተውጣጡ የባለሙዎች ቡድን ባለፉት ሁለት ሳምንታት የአደጋውን መንስኤ ስያጠኑ ነበር” ያሉት ኢንጂነር ወንድሙ ለተከሰተው የመሬት መሸሽ አንደኛው ምክንያት አከባቢው ላይ ከሚገኘው ከአራት ሺህ በላይ አባወራዎች ከሚኖሩባቸው 123 የጋራ መኖሪያ ህንጻዎች የሚወጣው ፍሳሽ በአግባቡ የተሰራ ባለመሆኑ የሚወጣው ፍሳሽ ወደ ወንዝ ከመሄድ ይልቅ ወደ መሬት መስረጉ ነው ብለዋል፡፡

ከጋራ መኖሪያ ቤቶቹ በተጨማሪ አከባቢው ላይ ከሚገኝ ሚኪሊሊላንድ ትምህርት ቤት የሚወጣው ፈሳሽም በተገቢው ወደ ማፋሰሻ ከመግባት ይልቅ ወደ ሜዳ የሚፈስ መሆኑም በአከባቢው ላይ የሚገኘውን አስፓልት ከጥቅም ውጪ ማድረጉን አስረድተዋል፡፡

ከነዚህ ከማፋሰሻው ስርዓት እጦት በተጨማሪ የጋራ መኖሪያ ህንጻዎቹ በሚሰሩበት ወቅት በዘፈቀደ ወደ ተዳፋታማው ወንዝ ዳርቻ ስገፋ የነበረው የተከማቸ አፈር እንዲሁም ከአፈሩ ስር የሚገኙ አለታማ የመሬት ገጽታ እና አከባቢው ላይ ከሚበዛው የትራፍክ እንቅስቃሴ ጋር ተዳምሮ ለመሬት መሸሹ መንስኤዎች ስለመሆናቸውም በተደረገው ጥናት ፍንጭ መገኘቱም ነው የተነገረው፡፡

እስካሁን የደረሰው ጉዳት

እስካሁን በመሬት ስንጥቃትና መሸሽጋር ተያይዞ በሰው ህይወት ላይ አደጋ አለመድረሱን ያመለከቱት የአዲስ አበባ ከተማ ዋና ስራ አስከያጁ፤ በንብረት ላይ የደረሱትን ጉዳቶች ግን ዘርዝረዋል፡፡ “አከባቢው ላይ የሚገኝ የአንደኛ እና መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የኋላ አጥር ሙሉ በሙሉ ወድቋል” ያሉት ኃላፊው በትምህርት ቤቱ ቅጥር ጊቢ ውስጥ በነበረው የተማሪዎች መመገቢያ ማዕከል ላይ ጉዳት መድረሱን አስረድተዋል፡፡

በአዲስ አበባ በተለምዶ ብርጭቆ ፋብሪካ እና አዲስ ሰፈር በሚባሉ አከባቢዎች ያጋጠመው የመሬት መሰንጠቅና መሸሽ የአከባቢው ነዋሪዎች ትልቅ ስጋት መሆኑ ተነግሯል፡፡ምስል፦ Seyoum Getu/DW

በዚሁ አቅራቢያ የሚገኝ የአስፓልት መንገድ በሰው ቁመት ልክ በሸሸው መሬት መደርመሱንና በሌላኛው የተዳፋታማው ወንዙ አቅጣጫ ወረዳ 14 ውስጥ የሚገኝ አንድ የእመነት ተቋማት ውስጥ የሚገኙ የተወሰኑ ክፍሎች በተከፈለው የመሬት መሰንጠቅ አደጋ ማስተናገዳቸውን አብራርተው ገልጸዋል፡፡

ከአደጋው በኋላስ በከተማ አስተዳደሩ ምን መፍትሄ ተወሰደ?

ከአደጋው መስተዋላ በኋላ ከአደጋ ጊዜ ሰራተኞች እና የሚመለከታቸው የስራ ኃላፊዎች ጋር በመሆን ህዝቡን ግንዛቤ ከማስጨበጥ ጀምሮ ነዋሪዎችን ከስጋት ስፍራው የማስወጣት ስራ መከወኑንም ዋና ስራ አስከያጁ ኢንጂነር ወንዲሙ ጠቁመዋል፡፡ “በተለይም ብሎክ 13 በሚባል ህንጻ ላይ የሚኖሩ 150 ሰዎች የሚሆኑ 29 አባወራዎች ህንጻውን ለቀው እንዲወጡና ጉዳት እንዳይደርስ የማሸግና ሰዎች በዚያ እንዳይንቀሳቀሱ ተደርጓል” ነው ያሉት፡፡

ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ከተማ አስተዳደሩ ጀመረውን የወንዝ ዳር ልማትን አተናክሮ መቀተል ሲሆን አሁን ላይ አደጋው በተከሰተበት ስፍራ እንደ አጭር ጊዜ መፍትሄ የእርከን ስራ በመስራት ለአፈር ጥበቃው ተስማሚ ተክሎችን መትከል ብሎም በመሬቱ ውስጥ የተከማቹትን ውሃ ወደ ማፋሰሻው ማስገባት ነው ተብሏልም፡፡

ከዚሁ ጋር ተያይዞ በቅርቡ አዲስ አበባ ውስጥ በተከታታይ የተከሰቱትን የጎርፍ አደጋዎችአስመልከተውም አደጋውን ለመከላከል አስቀድሞም ስራ ተሰርተው ነበር ያሉት የከተማ አስተዳደሩ ዋና ስራ አስከያጅ፤ በጎርፍ የሚመጡ ተረፈምርቶች የወንዞች ማፋሰሻ በዘጉባቸው አከባቢዎች ላይ ግን አደጋው እንዲከሰት ምክንያት መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ሥዩም ጌቱ

እሸቴ በቀለ

ዮሐንስ ገብረእግዚዓብሔር

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW