ስጋት ያስከተለው የአዋሽ ወንዝ ሙላት
ዓርብ፣ ነሐሴ 29 2012
ከአፍ አስከ ገደፉ እየተጥለቀለቀ ያለው የአዋሽ ወንዝ በኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን መርቲ-የጁ ወረዳ በትምህርት ቤት ላይ የከፋ ጉዳት ማድረሱን የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህርት ለዶይቼ ቨሌ ተናገሩ። የወንዙ በዚህ ደረጃ መሙላት ፍጹም ታይቶ የማይታወቅ ነው ያሉት ወ/ሮ ሰዓዳ ከድር ከትምህርት ቤቱም ውጭ የአርሶ አደሮች ማሳ ላይ ውሃው ጉዳት ማድረሱን አድርሷል፤ አከባቢው በውሃ ሙላት ተከቦም ደሴት ሆኗልም ነው ያሉት። አሁን ከመርቲ የጁ ወደ የትኛውም ስፍራ የሚወስዱ መንገዶች በውኃ መሸፈኑን፤ በዚህ የሚቀጥል ከሆነም ጎርፍ ወደ ሰዎች መኖሪያ መግባቱ አይቀሬ ነውም ይላሉ። በአከባቢው የሚገኘው የላይኛው አዋሽ ተፋሰስ አግሮ ኢንደስትሪ በበኩሉ እስካሁን በካምፕና በነዋሪዎች ላይ የጎርፍ አደጋው እንዳይከሰት ጥረት ቢደረግም ከ70 ሄክታር በላይ የጥጥ አንዲሁም 30 ሄክታር የሚገመት የብርቱካን እርሻ በውኃ መዋጡን አስታውቋል። የኢንደስትሪው የውኃ ክፍል ኃላፊ አቶ መንክር ግርማ ከዚህ በፊት በታሪክ ጎርፍ ደርሶበት የማያውቀው ስፍራ ሁሉ በውኃ እየተሸፈነ መሆኑን ገልጸዋል። ከቆቃ ግድብ የሚለቀቅ ውኃ ለአከባቢው በጎርፍ መጥለቅለቅ ጉልህ ድርሻ ቢኖረውም የአከባቢው ገባር ወንዞች በውል አለመጠናታቸው ደራሽ ውሃውን የማይገመት ማድረጉንም ኃላፊው ተናግረዋል፡፡ ዝርዝሩን የአዲስ አበባው ዘጋቢያችን ስዩም ጌቱ ልኮልናል።
ዓለምነው መኮንን
ሸዋዬ ለገሠ
ነጋሽ መሐመድ