ስፓሩሊና ፤ በርካታ ሚሊዮን ብር የሚታፈስበት የውሃ ውስጥ ምርት
ረቡዕ፣ ሐምሌ 17 2016
የሥነ- ምግብ ሳይንስ ተመራማሪዎች እንደሚሉት በዓለም ላይ በአሁኑ ወቅት ባህር ውስጥ የሚገኙ ምግቦች /Sea Foods/ ለጤና ተስማሚ በሆነው የንጥረ ነገር ይዘታቸው ተፈላጊነታቸው እያደገ መጥቷል። ከዚህ በተጨማሪ ለመድሃኒት ቅመማ እና ለተጨማሪ አልሚ ምግብነትም ይውላሉ።
ከነዚህም መካከል በአልሚ ምግብ ይዘቱ ከፍተኛ መሆኑ የሚነገርለት ውሃ ውስጥ የሚገኘው እና በተለምዶ የውሃ አረንጓዴ የምንለው ፤በሳይንሳዊ ስሙ ማይክሮ አልጌ /ስፓይሩሊና/ አንዱ ነው።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከፍተኛ ትኩረት እና ሰፊ ጥናቶች እየተደረገበት የሚገኘው «ስፓይሩሊና» ወደ ሰማያዊ የሚያደላ አረንጓዴ ቀለም ያለው የአልጌ አይነት ሲሆን፤ለገበያ የሚቀርበው በቤተ-ሙከራ ቁጥጥር በሚደረግበት አካባቢ በማሳደግ ነው።
በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ የተፈጥሮ ሳይንስ ትምህርት ክፍል ከፍተኛ ተመራማሪ የሆኑት ዶክተር ሀብቴ ጀቤሳ በዚህ ዙሪያ ምርምር አድርገዋል። እሳቸው እንደሚሉት ስፒሩሊና በፕሮቲን፣ በቫይታሚን እና በማዕድናት የበለፀገ እና ህዋሳትን ከጉዳት የሚከላከል የ«አልጌ» አይነት ነው።
ከዚህ ቀደም በአሜሪካን ሀገር በዚህ ኢንደስትሪ ውስጥ ሲሰሩ መቆየታቸውን የገለፁት ዶክተር ሀብቴ በዚህ ወቅትም ስፓሩሊና በርካታ ጠቀሜታዎች እንዳሉት በተግባር አይተዋል። ይህንን ጠቀሜታውን ወደ ኢትዮጵያ ለማምጣትም ከሌሎች የሙያ አጋሮቻቸው ጋር በመሆን ስፓይሩሊና በኢትዮጵያ ስለሚመረትበት ሁኔታ ጥናት ሲያደርጉ ቆይተዋል።ይህ ጥናታቸው ፍሬ አፍርቶም፤ በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የባዮ እና ኢመርጂንግ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ከኦሮሚያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር በኢትዮጵያ የመጀመርያ የሆነው የማይክሮ አልጌ /ስፓይሩሊና/ የምርምር እና የማምረቻ ማዕከል በቅርቡ ተመርቋል።
ይህ የምርምር ማዕከል ለሶስት ዓመታት ጥናት ሲደረግበት የቆየ ሲሆን፣በቅርቡ ግንባታው ተጠናቆ ፤በዝዋይ አዳሚ ቱሉ የግብርና ተቋም ለአገልግሎት ክፍት መደረጉን ዶክተር ሀብቴ ያስረዳሉ።በዚህም ኢትዮጵያ ለስፓሮሊና ምርት ተስማሚ ሀገር መሆኗን ማረጋገጥ ተችሏል።
ስፓሩሊና የያዙ ታላቅ ሀይቆች በመካከለኛው አፍሪካ በቻድ እና በኒጀር ሀይቆች እንዲሁም፤ በምስራቅ አፍሪካ በታላቁ የስምጥ ሸለቆ ይገኛሉ። በኢትዮጵያ እና በኬንያ ሐይቆች ውስጥም ትልልቅ የስፓሩሊና ዝርያዎች መኖራቸውን መረጃዎች ያሳያሉ።ያም ሆኖ በርካታ የአፍሪቃ ሀገራት ስፓሩሊናን በውድ ዋጋ ከውጭ በመግዛት ወደ ሀገር ያስገባሉ።ኢትዮጵያም ለአንድ ኪሎ ግራም ከ60,000 ብር በላይ በማውጣት ከህንድ፣ ቻይና እና አውሮፓ ስፓሩሊናዎችን በማስመጣት ጥገኛ የነበረች ሲሆን፤ በሀገር ውስጥ ማምረት ከዚህ ጥገኝነት ለመላቀቅ እና ወደ ውጭ በመላክ የውጭ ምንዛሬ ለማግኘት ይጠቅማል።መረጃዎች እንደሚያሳዩት በአሁ ወቅት ስፓሩሊና በኪሎ 20,000 ብር፤ በኩንታል ደግሞ እስከ 2 ሚሊዮን ብር በከፍተኛ ዋጋ ይሸጣል።
በሌላ በኩል ስፓሩሊና ለሰው ልጅ ከሚያስፈልጉት ንጥረ ነገሮች ውስጥ ከ90 በመቶ በላይ የያዘ ሲሆን፤ በአለም ላይ በአንድ ህዋስ ውስጥ አምስቱን ንጥረ ነገሮች ማለትም ፕሮቲን፣ ቫይታሚን፣ ስብ፣ ማዕድናት እና ካርቦሃይድሬትን በመያዝ ብቸኛው «ማይክሮአልጌ» ነው። ይህም እንደ ባለሙያው በኢትዮጵያ የሚታየውን ደካማ የአመጋገብ ስርዓት ለማስተካከል ይረዳል።የዉሓ አረንጓዴ እንደምግብ
ኢትዮጵያን ጨምሮ ከሰሃራ በታች ያሉ ሀገራት በአሁኑ ስዓት ከፍተኛ የሆነ የህፃናት መቀንጨር ይታያል የሚሉት ባለሙያው የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ሳቢያ በልጆች አካል እና አዕምሮ ላይ ጉዳት እያደረሰ ነው።ከክብደት በታች የሆኑ ህፃናትም ውልደትም ከ38 እስከ 42 በመቶ እንደሚደርስ ጥናቶች እንደሚያሳዩ ገልፀዋል። ከዚህ በተጨማሪ የምግብ ዋጋ ማሻቀብ እና እሳቸው «እየበሉ መራብ» የሚሉት የተመጣጠነ ምግብ እየተበላ ነገር ግን ተገቢውን የንጥረ ነገር ይዘት አለማግኘትም በሀገሪቱ ሌላው ችግር ነው።
ከዚህ አንፃር የተመጣጠነ ምግብ ችግሮችን በመቅረፍ በአካል እና በአእምሮ የዳበረ ትውልድ ለማፍራት እንደ ስፓሩሊና ያሉ አማራጭ የተመጣጠነ የምግብ ይዘት ማግኛ ዘዴዎችን መጠቀም ጠቀሜታው ከፍተኛ መሆኑን ባለሙያው ገልፀዋል።ስለሆነም እንደ ሰርቶ ማሳያ በቅርቡ በአዳሜ ቱሉ የተጀመረውን የማምረቻ ማዕከል ለማስፋፋት እና የሚፈለገውን ምርት ለማግኘት ባለሀብቶች በዘርፉ መዋዕለ ንዋይ ማፍሰስ እንደሚገባቸው አሳስበዋል።
ስፒሩሊና የአልካላይንነት ፀባይ ባላቸው ሀይቆች ውስጥ በፍጥነት እና በብዛት የሚያድጉ ሲሆን፤ ብዛታቸው ከፍተኛ ሲሆን እና አልሚ ምግቦች ሲያጡ ደግሞ ይሞታሉ። አዲስ ወቅታዊ ዑደት የሚጀምረውም የበሰበሱ አልጌዎች ምግብ የሚሆን ንጥረ ነገር ሲለቁ ወይም ብዙ ንጥረ ነገሮች ወደ ሀይቁ ሲገቡ ነው። ይህ የእድገት ዑደት ፈጣን በመሆኑ ደግሞ የምርቱ ሂደቱም ፈጣን ነው። ይህም ምርት ለመስጠት ወራት ወይም አመታት ከሚፈልጉት ተለምዷዊ ሰብሎች በተለየ መልኩ ስፓሩሊና ከመጀመሪያው ምርት በኋላ በየዕለቱ ምርት መሰብሰብ እንደሚቻል ባለሙያው ተናግረዋል።
ከዚህ በተጨማሪ ስፓሩሊና የሚያድገው በሞቃታማ የአየር ክልል ውስጥ ሲሆን፤፤ የካርቦን ልቀትን በመቀነስም ለአካባቢ ጥበቃ ተስማሚ መሆኑን ዶክተር ሀብቴ ገልፀዋል።አንድ ግራም ስፓሮሊና ሁለት ግራም የካርቦንዳይ ኦክሳይድ ልቀት በመቀነስ ከአማዞን ደን ያልተናነሰ ጥቅም አላት የሚሉት ባለሙያው በአካባቢ ላይ ያለው አሉታዊ ተጽዕኖ ዝቅተኛ በመሆኑ በሰምጥ ሸለቆ በሚገኙ በፓርኮች ውስጥ ማምረት ጉዳት እንደሌለው አብራርተዋል።
በ8.2 ሚሊዮን ብር በአዳሚ ቱሉ ግብርና ማዕከል መገንባቱ የሚነገረው፤ አዲሱ የስፓሩሊና ምርምር እና የማምረቻ ማዕከል በ1,200 ካሬ ሜትር ስፋት ያለው ሲሆን ዶክተር ሀብቴ እንደገለፁት ለመጀመሪያ ጊዜ በወር 30 ኪ.ግ ማምረት ተችሏል።ስለሆነም ይህ ስራ ቀጣይነት እንዲኖረው የሚመለከታቸው አካላት ትኩረት እንዲሰጡት አሳስበዋል።ተስፋ የተጣለበት የባሕር ውስጥ ማሳ
ተመራማሪዎች እንደሚሉት ስፓሩሊና በአጠቃላይ አስደናቂ የምግብ ማሟያ እና አማራጭ የሕክምና ምንጭ ነው። ዶክተር ሀብቴ እንደሚሉት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢትዮጵያ ይህ የስፓሩሊና ጠቀሜታ እየታወቀ በመምጣቱ ፤ በበይነመረብ እየገዙ የሚጠቀሙ ሰዎች አሉ። ነገር ግን ስፓሩሊና ከጠቀሜታው ባሻገር በአደገኛ ንጥረ ነገሮች እና መርዛማ ብረቶች የመበከል እድል አለው እና፤ በሰው ልጆች ጤና ላይ ጉዳት ሊያስከትልም ይችላል። ስለሆነም ጥራቱን የጠበቀ መሆኑን ማረጋገጥ አልያም የጤና ባለሙያ በማማከር ተገቢ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚያስፈልግም በባለሙያዎች ይመከራል።
ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ።
ፀሐይ ጫኔ
እሸቴ በቀለ