1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ስፔንን ለድል ያበቁት የዘር ሐረጋቸው ከአፍሪቃ የሚመዘዝ ተጨዋቾች

ሰኞ፣ ሐምሌ 8 2016

ስፔን በትናንትናው ዕለት እንግሊዝን በአውሮጳ እግር ኳስ ዋንጫ ፍጻሜ 2 ለ1 ድል ነስታ ስትቦርቅ ፥ የዘር ሐረጋቸው ከአፍሪቃ ከሚመዘዝ ቤተሰብ የተወለዱ ሁለት ተጨዋቾች ታላቅ አስተዋጽኦ አበርክተዋል ። ላሚን ያማል እና ኒኮ ዊሊያምስ ። ሁለቱም ከድሉ ዋዜማና 2 ቀን በፊት ልደታቸውን አክብረው ነበር ።

Deutschland Berlin | UEFA EURO 2024 Finale | Spanien gewinnt EURO 2024
ምስል Andre Weening/Orange Pictures/Imago Images

ሁለቱም ከድሉ ዋዜማና 2 ቀን በፊት ልደታቸውን አክብረው ነበር

ስፔን በትናንትናው ዕለት እንግሊዝን በአውሮጳ እግር ኳስ ዋንጫ ፍጻሜ 2 ለ1 ድል ነስታ ስትቦርቅ ፥ የዘር ሐረጋቸው ከአፍሪቃ ከሚመዘዝ ቤተሰብ የተወለዱ ሁለት ተጨዋቾች ታላቅ አስተዋጽኦ አበርክተዋል ።  ላሚን ያማል እና ኒኮ ዊሊያምስ ። ላሚን ከኢኳቶሪያል ጊኒ እና ሞሮኮ ወላጆች ነው የተወለደው ። ሌላኛው የስፔን ድንቅ፦ ኒኮ ዊሊያምስ ደግሞ የተወለደው አሰቃቂውን  የሰሐራ በረሃ አቋርጠው ስፔን አዲስ ሕይወት ከጀመሩ ጋናውያን ቤተሰቦች ነው ።

የስፔን ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን የእንግሊዝ አቻውን በዩሮ 2024 ፍጻሜ 2 ለ1 አሸንፎ ዋንጫ ወስዷልምስል Kai Pfaffenbach/REUTERS

ላሚን ያማል እና ኒኮ ዊሊያምስ

ያም ብቻ አይደለም ግቦቹም ሆኑ የአውሮጳ ዋንጫ ድሉ ለሁለቱም ተጨዋቾች የልደት ቀን ስጦታ ሆኖም ነው የቀረበው ማለት ይቻላል ። ላሚን ያማል 17ኛ የልደት ቀኑን ባከበረ በነጋታው ስፔን እንግሊዝን 2 ለ1 አሸንፋ ለአውሮጳ ዋንጫ ድል እንድትበቃ አስችሏል ። ቀዳሚዋን ግብ በ47ኛው ደቂቃ ላይ ኒኮ ዊሊያምስ እንዲያስቆጥር አመቻችቶ የሰጠው ይኸው በዩሮ ታሪክ ትንሹ ተጨዋች ላሚን ነው ። ቀዳሚዋን ግብ ያስቆጠረው ኒኮ ዊሊያምስ 22ኛ የልደት በዓሉን ያከበረው ከዋንጫ ጨዋታው ሁለት ቀን ቀደም ብሎ ዓርብ ዕለት ነበር ።

ባለ ረጅም ፀጉሩ ወጣት ሊዮኔል ሜሲ ከጨቅላው ላሚኔ ያማል ጋር ከ17 ዓመታት በፊት ። እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2007 የባርሴሎናውን ኮከብ ለማግኘት በተደረገ እጣ የላሚኔ ያማል ወላጆች አሸንፈው ነበር ከሊዮኔል ሜሲ ጋ ፎቶ የተነሱት ። አሁን ላሚኔ ያማልም ሆነ ሊዮኔል ሜሲ ሁለቱም በየአኅጉራቸው ሃገራቸውን ለድል አብቅተዋል ።ምስል Joan Monfort/AP Photo/picture alliance

ላሚን ያማል ከሊዮኔል ሜሲ ጋ ፎቶ

ሌላው አስደማሚ ነገር፦ ላሚን ያማል የዛሬ 17 ዓመት ጨቅላ ሳለ ቤተሰቦቹ በደረሳቸው የእጣ አጋጣሚ ላሚን ከሊዮኔል ሜሲ ጋ ፎቶ እንዲነሳ መደረጉ ነው ። የያኔው ባለ ረጅም ፀጉሩ የ20 ዓመቱ ወጣት ሊዮኔል ሜሲ እና ጨቅላው ላሚኔ ያማል እጅግ ተደስተው ሲስቁ ይታያል በፎቶው ። የሊዮኔል ሜሲ አርጀንቲና የደቡብ አሜሪካውን ኮፓ አሜሪካ ዋንጫ ትናንት አንስታለች ። እነ ላሚን ያማል ደግሞ ትናንት ። ሁለቱን የዛሬ 17 ዓመታት እንዲህ ያስፈገጋቸው ከ17 ዓመታት ወዲህም በተመሳሳይ ቀን ይደገማል ብሎ ማን አሰበ? #DWSports 

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ታምራት ዲንሳ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW