1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ስፖርት፤ ሐምሌ 16 ቀን፣ 2010 ዓ.ም

ሰኞ፣ ሐምሌ 16 2010

ነገሩ ጡዘት ላይ ሳይደርስ የረገበ የመሰለው ያለፈው ግንቦት ወር ላይ ነበር። ኾኖም ውስጥ ውስጡን ሲብላላ ቆይቶ ጀርመን ከዓለም ዋንጫ በሽንፈት ከተሰናበት በኋላ ግን ውጥረቱ እንደ አዲስ አይሏል።

WM 2018 Deutschland Südkorea Mesut Özil
ምስል picture-alliance/Photoshot/L. Ga

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

This browser does not support the audio element.

ነገሩ ጡዘት ላይ ሳይደርስ የረገበ የመሰለው ያለፈው ግንቦት ወር ላይ ነበር። ኾኖም ውስጥ ውስጡን ሲብላላ ቆይቶ ጀርመን ከዓለም ዋንጫ በሽንፈት ከተሰናበት በኋላ ግን ውጥረቱ እንደ አዲስ አይሏል። ለጀርመን ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ተሰልፎ የሚጫወተው ሜሱት ኦዚል ከቱርክ ፕሬዚዳንት ጋር የተነሳው ፎቶግራፍም ነበር የውጥረት ውዝግቡ ሰበብ፤ ዳሰነዋል። በፎርሙላ አንድ የመኪና ሽቅድምድም የብሪታንያው ሌዊስ ሐሚልተን ጀርመናዊ ተፎካካሪውን በገዛ ሀገሩ ድል ነስቷል። የሁለቱ አሽከርካሪዎች ፉክክር ግን ተጠናክሮ ቀጥሏል። ኢትዮጵያዊቷ አትሌት በሳምንቱ መገባደጃ በተከናወነ የሩጫ ውድድር ስትመራ ቆይታ በስተመጨረሻ በስህተት ውድድሩ ያለቀ መስሏት ሳትጨርስ በማቋረጧ የማሸነፍ ዕድሉን ከእጇ አስወጥታለች።

ሰሞኑን በስፖርቱ ዓለም እጅግ አነጋጋሪ የኾነው በተጨዋቾች ማንነት ላይ የሚሰጡ አስተያየቶች እና የሚያስከትሉት ውዝግብ ነው። ለጀርመን ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ተሰልፎ ይጫወት በነበረው ሜሱት ኦዚል ላይ የደረሰውም የዚህ ውዝግብ ውጤት ነው። ሜሱት ኦዚል ከቱርክ ቤተሰቦች ጀርመን ሀገር ጌልዘንኪርሸን ከተማ ውስጥ የተወለደ የሦስተኛው ትውልድ ዘመነኛ ነው። ሜሱት ጀርመን ውስጥ የተወለደ ቢሆንም  ቅሉ በጀርመን ቀኝ ዘመም ፖለቲካ አራማጆች እና አቀንቃኞቻቸው ደረሰብኝ ባለው የዘር መድልዎ የተነሳ ግን ከእንግዲህ ለጀርመን ብሔራዊ ቡድን ተሰልፎ  እንደማይጫወት ዐሳውቋል።

ምስል picture-alliance/augenklick/firo Sportphoto

የጀርመን ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ተሰላፊ የነበረው፤ የአርሰናሉ አማካይ ላይ የደረሰው ምንድን ነው? ነገርዬው የተከሰተው ግንቦት ወር ላይ ነው። በወቅቱ ሜሱት ኦዚል እና ሌላኛው የጀርመን ብሔራዊ ቡድን ተሰላፊ  ኢካይ ጉንዶዋን ከኤቨርተኑ አጥቂ ቼንክ ቶሱን ጋር በመሆን የቱርኩ ፕሬዚዳንት ሬቺፕ ጣይብ ኤርዶሃንን መሀል አድርገው ፎቶግራፍ ይነሳሉ። ለንደን ውስጥ የተነሱትን ፎቶግራፍም የቱርኩ ገዢ ፓርቲ ለምርጫ ቅስቀሳ ይጠቀምበታል። ፓርቲው የምርጫው አሸናፊ ኾኖ ወጥቷል። ፕሬዚዳንት ኤርዶሃን እና ፓርቲያቸው ከከሸፈው መፈንቅለ መንግሥት በኋላ በወሰዷቸው መጠነ ሰፊ ርምጃዎች በምዕራባውያን ዘንድ ከፍተኛ ትችት አስከትሎባቸው ቆይቷል። 

በእርግጥ ምዕራባውያኑ ጀርመንን ጨምሮ ማለት ነው በገፍ የሚመጡባቸውን ፍልሰተኞች እንዲገቱላቸው ሲሉ ዲሞክራሲን ጨፍልቀዋል ሲሉ ከሚተቿቸው የቱርኩ ፕሬዚዳንት ጋር ለመሥራት ላይ ታች ሲሉ ነበር። ስደተኞችን እዛው ቱርክ ውስጥ እንዲያስቀሩላቸውም ሲሉ ፕሬዚዳንቱን በገንዘብ ክፍያም በዲፕሎማሲ ጫናም ሊያሳሳድሩባቸው ሲጥሩም ተሰተውሏል። ተጨዋቾቹ ግን ከቤተሰቦቻቸው ሀገር ፕሬዚዳንት ጋር ፎቶግራፍ ሲነሱ ትችቱ ከጥግ እስከ ጥግ አስተጋብቷል። በተለይ የቀኝ ዘመም አክራሪ ፖለቲከኞች ተጨዋቹ ከእንግዲህ «ጀርመን አይደለም» እና «ከሀገራችን ይውጣልን» የሚሉ ቅስቀሳዎችንም አካሂደውበታል።  ከግንቦት ወር አንስቶ ሲገፋው የቆየው ትችት እና ጫና ትናንት ሜሱት ኦዚልን ከመጨረሻው ውሳኔ ላይ አድርሶታል።

እናም ሜሱት ኦዚል፦«እጅግ በተሰበረ ልብ፤ ለረዥም ጊዜ ሳስብበት ከቆየሁ በኋላ አሁን እየኾነ ባለው ነገር የተነሳ ዘረኝነት እና ክብር አልባ ጉዳዮችን እያስተናገድኩ ከእንግዲህ የጀርመን ብሔራዊ ተጨዋች ኾኜ መቀጠል አልችልም።» ብሏል።

ምስል picture-alliance/Pressefoto ULMER

ሜሱት ኦዚልን ጨምሮ ሦስተኛ ትውልድ የደረሱት ጀርመን ሀገር ውስጥ የሚኖሩ የቱርክ ዝርያ ያላቸው ነዋሪዎች ቁጥር 3 ሚሊዮን ይገመታል። እናም ተጨዋቹ «የጀርመንነት ስሜት» አይሰማኝም የሚል ቃል ማውጣቱ በተለይ አዲሱ ትውልድ ላይ የሚኖረው ተጽዕኖ ከፍተኛ ነው። ሜሱት ኦዚል እና ኢካይ ጉንዶዋን ከቱርኩ ፕሬዚዳንት ጋር ፎቶግራፍ ሲነሱ  የጀርመንን ዲሞክራሲ ችላ ብለዋል ሲሉ በርካታ የጀርመን ፖለቲከኞች  ተችተዋል።  ሜሱት ኦዚል ግን እንደውም ከቱርኩ ፕሬዚዳንት ጋር ፎቶ ባይነሳ ኖሮ «የቤተሰቦቹ ትውልድን እንዳለማክበር ይቆጠር» እንደነበር ገልጧል። የተበራከተበትን ትችት አስመልክቶ ሲናገር፦ «ስናሸንፍ ጀርመናዊ ነኝ፤ ስንሸነፍ ግን መጤ» ሲል ተቺዎቹን ተችቷል።

ከዚሁ ከጀርመን ሳንወጣ በፎርሙላ አንድ የጀርመን የመኪና ሽቅድምድም ብሪታንያዊው  ሌዊስ ሐሚልተን አሸንፏል። ለሌዊስ  የትናንቱ  ድል ልዩ ኾኖ ተመዝግቧል። ድሉ የተገኘው አንድም በተፎካካሪው ሠባስቲያን ፌትል ሀገር በተደረገ ውድድር ነው። በሌላ መልኩ ደግሞ ከመርሴዲስ ጋር በዓመት የ40 ሚሊዮን ፓውንድ ውል በፈረመ ማግስት ያገኘው ድል ኾኖ ተመዝግቦለታል።  በእርግጥም መርሴዲስ ያን ያኽል ብር መክፈሉ ትክክል እንደነበር ማሳያም ነው ለሌዊስ ሀሚልተን የትናንቱ ድል። በእስካሁኑ አጠቃላይ ውጤት መሰረት ሌዊስ ሐሚልተን 188 ነጥብ ሰብስቦ ሠባስቲያን ፌትልን በ17 ነጥብ እየመራ ይገኛል። ትናንት ከውድድር ውጪ የኾነው ሠባስቲያን አጠቃላይ ነጥቡ 171 ነው። በትናንቱ ሽቅድምድ ቫልተሪ ቦታስ ሌዊስ ሐሚልተንን ተከትሎ 2ና ወጥቷል። የ3ና ደረጃን ያገኘው የፌራሪው ኪም ራይከነን ነው።

ሌላው በሳምንቱ አነጋጋሪ ከነበሩ የስፖርታዊ ክንውኖች መካከል ለንደን ውስጥ በተካሄደው የ3000 ሜርትር የሩጫ ፉክክር ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ላይ የደረሰው ይጠቀሳል። |ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ፋንቱ ወርቁ ቅዳሜ ዕለት ለንደን ውስጥ ባከናወነችው ውድድር ከፊት ቀዳሚ የነረች ቢኾንም ውድድሩ ሊጠናቀቅ 200 ሜርትር ሲቀረው ግን ውድድሩን የጨረሰች መስሏት በመቆሟ ድሉ ከእጇ አምልጧል። የ19 ዓመቷ አትሌት ሌሎች ሯጮች ወደ ውድድሩ ማብቂያ መስመር ሲሮጡ ግራ በመጋባትም ስትመለከት ተስተውላለች። በዚህ ውድድድር የኬኒያዋ ሊሊያን ካሳዪት ሬንጌሩክ በአንደኛነት ስታሸንፍ፤ የኔዘርላንዷ ሱዛን ክሩሚንስ ሁለተኛ ኾናለች። ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ፋንቱ ወርቁ  ውድድሩን ያሸነፈች መስሏት ሳትጨርስ ቀርታለች ሲሉ የተለያዩ መገናኛ ዘዴዎች ዘግበዋል። በውድድሩ ስታቋርጥም የሚያሳይ አጠር ያለ ቪዲዮ በኢንተርኔት ይገኛል።

የተጨዋቾች ዝውውር ዜና። የእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ሊጀመር ጥቂት ሳምንት ብቻ ነው የሚቀረው። በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥም በተለይ አርሰናል፣ ሊቨርፑል እና ዌስትሀም ለተጨዋቾች ዝውውር ከፍተኛ ወጪ ፈሰስ እንዳደረጉ ተዘግቧል።

ምስል picture-alliance/AP Photo/J. Meyer

አርሰናል አምስት ቁልፍ ተጨዋቾች አግኝቷል። አርሰናል አማካዩ ሉቃስ ቶሬራን ከሳምፕዶሪያ ያስመጣው በ26 ነጥብ 5 ሚሊዮን ፓውንድ ነው። ለባየር ሌቨርኩሰኑ ቤርንድ ሌኖ 19 ነጥብ 2ሚሊዮን  ፓውንድ አውጥቷል። የቦሩስያ ዶርትሙንዱ ሶቅራጥስ ፓፓስታቶፖሉስ 17 ነጥብ 7 ሚሊዮን፤ እንዲሁም የሎሬን ተጨዋች የነበረው ማቴዎ ጉዌንዶዚ 8 ሚሊዮን ፓውንድ ተከፍሎባቸዋል።

ሊቨርፑል ለተጨዋቾች ዝውውር በጥቅሉ 176 ሚሊዮን ፓውንድ ማውጣቱ ተነግሯል።  ለሮማው አሊሰን 65 ሚሊዮን፤ ለላይፕሲሹ ናቢ ኪዬታ 52 ነጥብ 8 ሚሊዮን፤ ለሞናኮው ፋቢንሆ 40 ሚሊዮን እንዲሁም ለስቶክ ሲቲው ሼርዳን ሻቂሪ 13 ነጥብ 5 ሚሊዮን ፓውንድ አውጥቷል።

ዌስትሀም በበኩሉ በ80 ሚሊዮን ፓውንድ ግድም  አምስት ተጨዋቾችን ያስመጣ ሲሆን ሁለት ተጨዋቾችን በነጻ አግኝቷል። በነፃ የመጡት ተጨዋቾች የፉልሀሙ ሪያን ፍሬድሪክ እና የአርሰናሉ ጃክ ዊልሼር ናቸው።  ዌስትሀም ዘንድሮ ለላትሲዮው ፌሊፕ አንደርሰን 33 ነጥብ 5 ሚሊዮን አውጥቷል። የቱሉሴውን ኢሳ ዲዮፕ ያስመጣው በ22 ሚሊዮን ነው።  ለቦሩስያ ዶርትሙንዱ አንድሪ ያርሞሌንኮ 17 ነጥብ 5 ፤ ለስዋንሲ ሲቲው ሉካስ ፋቢያንስኪ 7 ሚሊዮን እንዲሁም ለኮሪንቲያንሱ ባልቡዌና 3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ፓውንድ ፈሰስ አድርጓል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሐመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW