1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ስፖርት፤ ሐምሌ  2 ቀን፣ 2010 ዓ.ም

ሰኞ፣ ሐምሌ 2 2010

የሚሸነፉ የማይመስሉ ኃያል ቡድኖች የተገነደሱበት፣ የተናቁት የገነኑበት፤ ገሚሱ በደስታ ሲቦርቅ በርካቶች በእንባ ተራጭተው የተመለሱበት የዓለም ዋንጫ ሊጠናቀቅ ተቃርቧል። የፈረንሳይ የሩብ ፍጻሜ ጨዋታን ከፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኤማኑዌል ማክሮ ጋር በቤተመንግሥት ተጋብዞ የመመልከት ዕድሉን ያገኘ ትውልደ ኢትዮጵያዊ ታዳጊ ወጣትን እንግዳችን አድርገናል።

Biruk Sisay in Paris
ምስል DW/H. Tiruneh

የሚሸነፉ የማይመስሉ ኃያል ቡድኖች የተገነደሱበት፣ የተናቁት የገነኑበት፤ ገሚሱ በደስታ ሲቦርቅ በርካቶች በእንባ ተራጭተው የተመለሱበት የዓለም ዋንጫ ሊጠናቀቅ ተቃርቧል። ለግማሽ ፍጻሜ ከደረሱት ቡድኖች ጥንካሬዋን ያስመሰከረችው ፈረንሳይ የሩብ ፍጻሜ ጨዋታን ከፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኤማኑዌል ማክሮ ጋር በቤተመንግሥት ተጋብዞ የመመልከት ዕድሉን ያገኘ ትውልደ ኢትዮጵያዊ ታዳጊ ወጣትን እንግዳችን አድርገናል። ከፈረንሳይ በተላከልን ዘገባ ተካቷል።  የዓለም ዋንጫ በሚከናወንባት ሩስያ የሥራ ዕድል ብሎም በእግር ኳስ ቡድኖች ታቅፈው ሊጫወቱ እንደሚችሉ ቃል የተገባላቸው ናይጀሪያውያን ከሩስያ መውጪያው ጠፍቷቸው ሲዳክሩ ተስተውለዋል።  እግር ኳስ ለመመልከት ሄዶ ወደ ሀገሩ መመለስ ያልቻለ ናይጀሪያዊ ወጣት በሩስያ ስለገጠመው የሚለው አለ። የሜዳ ቴኒስ እና የፎርሙላ አንድ ውጤቶችንም እንመለከታለን።

የዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማሕበራት ፌዴሬሽን (FIFA) 21ኛው የዓለም ዋንጫ ሩስያ ውስጥ ሊጠናቀቅ ጥቂት ቀናት ብቻ ቀርተውታል። ወደ ዋንጫ ጨዋታው ለማለፍ በነገው ዕለት ፈረንሳይ ቤልጂየምን ትገጥማለች። እንግሊዝ እና ክሮሺያ ረቡዕ ዕለት ይፋለማሉ። ተሸናፊዎች ቅዳሜ የደረጃ ጨዋታ ያከናውናሉ። እንዲሁም ለዋንጫ የሚደረገው የፍጻሜው ፍልሚያ ለእሁድ ቀጠሮ ተይዞለታል።

ፈረንሳይ ነገ የምትገጥማት ጎረቤቷ ቤልጂየምን በግማሽ ፍጻሜው ካሸነፈች በ20 ዓመት ውስጥ ለሦስተኛ ጊዜ ለፍጻሜ ቀረበች ማለት ነው።  ዋንጫውን ይወስዳሉ ተብለው ከፍተኛ ግምት ተሰጥቷቸው ከነበሩት ቡድኖች ቀዳሚዋ ብራዚልን ያሰናበተችው ቤልጂየም «ወርቃማ ዘመኗ» ነው በተባለበት በአሁኑ ወቅት ለፍጻሜ ለመድረስ ከፍተኛ ግምት ተሰጥቷታል።

ምስል DW/H. Tiruneh

እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ1966 ለእንግሊዝ ተሰልፎ ሄትትሪክ የሠራው የ76 ዓመቱ አዛውንት ጄኦፍ ሑርስት በጋሬት ሳውዝጌት የሚሰለጥነው የእንግሊዝ ቡድን ለፍጻሜ እንደሚደርስ እምነቱ እንደኾነ ተናግሯል። እንግሊዝ ረቡዕ እለት በግማሽ ፍጻሜው የሩስያ መዲና ሞስኮ ውስጥ የምትገጥመው ክሮሺያን ነው። የእንግሊዝ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ዐይነ ጥላው ተገፎለት ከነገ በስትያ ክሮሺያን ካሸነፈ ከ52 ዓመት ወዲህ ዋንጫ ሲያነሳ የመጀመሪያው ተብሎ ይነገርለታል። ከግማሽ ምዕተ ዓመት በፊት ምዕራብ ጀርመን ላይ ሦስት ግቦችን በማከታተል ሔትትሪክ የሠራው ጄኦፍ ሑርስት ያ ታሪክ እንደሚጻፍ ጠንካራ እምነት አለው።

ፈረንሳይ በበኩሏ ዘንድሮ ለዋንጫ ለመድረስ የተቃረበችው ከኹለት ዐሥርተ ዓመት ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው። እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ1998 ፈረንሳይ ድል ስትቀዳጅ የቡድኑ አባል የነበረው ቲዬሪ ኦንሪ ነገ ፈረንሳይን ከሚገጥመው የቤልጂየም ቡድን ጋር ተሰልፎ ነው የመጣው። ቲዬሪ የቤልጂየሙ አሰልጣኝ  ሮቤርቶ ማርቲኔዝ ሁለተኛ ረዳት ኾኖ የሀገሩ ቡድንን ሊፋለም ነገ ወደ ቅዱስ ፔተርስበርግ ያቀናል። ቲዬሪ ኦንሪ የሀገሩ ቡድንን ድል ነስቶ በረዳትነት ከሚያሰለጥነው የቤልጂየም ቡድን ጋር ይቦርቅ ይኾን? ነገ አብረን የምናየው ይኾናል።

ምስል Reuters/C. Hartmann

በሩስያው የዓለም ዋንጫ ወደ ግማሽ ፍጻሜ ለማለፍ ባለፈው ዐርብ ፈረንሳይ ኡራጓይን 2 ለ0 አሸንፋ ነው እዚህ የደረሰችው። ያን ጨዋታ የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኤማኑዌል ማክሮ በኤሌዜ ቤተመንግሥት የተመለከቱት በፓሪስ እና አካባቢዋ ከሚገኙ የእግር ኳስ ቡድኖች እና ትምህርት ቤቶች ከተውጣጡ ቁጥራቸው ወደ 300 ከሚጠጋ ታዳጊ ወጣት ወንድ እና ሴት ስፖርተኞች ጋር ነበር። ከፕሬዚዳንት ማክሮ ጋር ቤተመንግሥት  ታድመው ጨዋታውን እንዲመለከቱ ከተጋበዙት መካከልም ከኢትዮጵያዊ ቤተሰብ ፈረንሳይ ውስጥ የተወለደው የ13 ዓመቱ ታዳጊ ብሩክ ሲሳይ መሀፔ አንዱ እንደነበር የፈረንሳዩዋ ወኪላችን ሀይማኖት ጥሩነህ ዘግባለች። ታዳጊውን በስልክ አነጋግራም ቀጣዩን ዘገባ ከፓሪስ ልካልናለች። 

ከፓሪስ የተጠናቀረውን ዘገባ ያቀረበችልን ሀይማኖት ጥሩነህ ነች። ሊጠናቀቅ ጥቂት ቀናት የቀሩት የሩስያ የዓለም ዋንጫን በሚል በርካታ ናይጀሪያውያን ሩስያ ገብተው ችግር ውስጥ መውደቃቸው ተገልጧል። ቁጥራቸው ከ150 እስከ 200 የሚጠጉ ናይጀሪያውያን የዓለም ዋንጫ ጨዋታዎችን ለመመልከት እና ሥራ ለማግኘት በሚል ሩስያ ውስጥ ይገኛሉ። ታዲያ አብዛኛዎቹ የተገባላቸው ቃል መክኖ በችግር ላይ እንደሚገኙ ይናገራሉ። የዓለም ዋንጫው ከመጀመሩ ቀደም ብሎ ናይጀሪያ ውስጥ የሚገኙ የጉዞ ወኪሎች እና ተገቢ ያልኾነ ትርፍ ለማጋበስ የቋመጡ ግለሰቦች ናይጀሪያውያንን በባዶ ተስፋ አታለው ወደ ሩስያ እንደላኳቸውም ናይጀሪያውያኑ ተናግረዋል። አንዳንዶቹ ከአየር ማረፊያ እንደወጣችሁ ሥራ ታገኛላችሁ ተብሎ ቃል ቢገባልንም መጠለያና ምግብ እንኳን ተቸግረናል ሲሉ ይደመጣሉ። ከእነዚህ መካከል ስሙን መግለጥ ያልፈለገው ናይጀሪያዊ ያለበትን ችግር እንዲህ ያብራራል።

ምስል Getty Images/AFP/A. Isakovic

«ከናይጀሪያ ነው የመጣኹት፤ ሩስያ የመጣኹት የዓለም ዋንጫን ለመመልከት ነበር። በእውነቱ ለመኖር የሚያስችለኝን ነገር ማድረግ ተስኖኛል። ከእንግዲህ እዚህ መቆየት ስለማልችል መመለስ ነው የምፈልገው። ማንም የሚረዳን የለም። ወደ ኤምባሲያችን ሄጄ ስላለኹበት ኹኔታ መናገር ነበረብኝ። እናም አማራጭ ሰብአዊ የነጻነት ሕይወት ወደ ሚል ድርጅት ተልኬያለሁ። እናም ጽሕፈት ቤታቸውን ጎብኝቻለሁ። የምተኛበትን ቦታ ሰጥተውኛል። ለዚያም ይከፍሉልኛል። የመመለሺያዬ ቀን እስኪቀየር ድረስ እዚያ መቆየት አለብኝ። ኤምባሲው በምፈልገው መልኩ አልረዳኝም። ግን ወደ አማራጭ ሰብአዊ የነጻነት ሕይወት ድርጅት ልከውኛል። እናም እንደ ናይጄሪያዊ ኤምባሲዬ ጋ ብሄድም እኔን ከመርዳት ይልቅ ወደ ሌላ ድርጅት መላካቸው በእውነቱ አበሳጭቶኛል።»

ወደ ሩስያ በማቅናት ሥራ በቀላሉ ታገኛላችሁ ተብለው እንደተታለሉ ከገለጡት ባሻገር እዚያ ስትደርሱ በአንዱ የእግር ኳስ ቡድን ታቅፋችሁ እንደ እነሮናልዶ ትጫወታላችሁ ተብለው የተሞኙ እንዳሉም የገለጡ አሉ። አብዛኛዎቹ ግን የተሰጣቸውን ባዶ ተስፋ ታቅፈው ወደ ናይጀሪያ መመለሱን በናፍቆት ይጠባበቃሉ።

በብሪታንያ ግራንድ ፕሪ የፎርሙላ አንድ የመኪና ሽቅድምድም ብሪታንያዊው ሌዊስ ሐሚልተን አልተሳካለትም። ኾኖም ጀርመናዊው ሠባስቲያን ፌትልን ተከትሎ በኹለተኛነት ያጠናቀቀበትን የትናንቱን ውጤት እንደ ድል እንደሚቆጥረው ገልጧል።

ምስል Getty Images/Ryan Pierse

በእርግጥም በኪም ራይከነን ፌራሪ ተገጭቶ መጥፎ አጀማመር የነበረው ሌዊስ በ10ኛው ዙር ላይ ስድስተኛ ደረጃ ነበረው። እናም ሁሉም የተሽከርካሪዎቻቸውን ጎማ ለመቀየር ጥግ ሲይዙ ፍጥነቱን የጨመረው ሐሚልተን በስተመጨረሻ ስልቱ ሰምሮለት ሦስተኛ መኾን ችሏል። የማታ ማታ ከፊቱ የነበረው የቡድኑ አባል ቫልተሪ ቦታስን ጥሶ በማለፍ በኹለተኛነት ማጠናቀቅ ችሏል። ያም በመኾኑ ከሠባስቲያን ፌትል ጋር ያለው የነጥብ ልዩነት በስምንት ብቻ እንዲወሰን አድርጓል። በአጠቃላይ መሪው ሠባስቲያን ፌትል171 ነጥብ ሲኖረው ሌዊስ ሐሚልተን  በ163 ይከተላል። ኪም ራይከነን በ116 ሦስተኛ ደረጃ ይዟል።

በዌንብልደን የሜዳ ቴኒስ ግጥሚያ ስዊዘርላንዳዊው ሮጀር ፌዴሬር  6-0 7-5 6-4  በኾነ ውጤት አድሪያን ማናሪኒን አሸንፏል። ሴሬና ዊሊያምስ በበኩሏ ኢቭጌኒያ ሮዲናን  6-2 6-2 አሸንፋለች። ሮጀር ፌዴሬርም ሴሬና ዊሊያምስም ወደሩብ ፍጻሜ አልፈዋል። 

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ኂሩት መለሰ

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW