1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ስፖርት፤ ሐምሌ 23 ቀን፣ 2010 ዓ.ም

ሰኞ፣ ሐምሌ 23 2010

በጋና 5 ለ0 የተረታውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ሊያሰለጥኑ የተረከቡት አዲስ አሰልጣኝ ማን ናቸው? የሪዮ ኦሎምፒክ የብር ሜዳሊያ ተሸላሚው ኢትዮጵያዊ አትሌት ፈይሳ ሊሌሳ ያሸንፋል ተብሎ በተጠበቀበት የቦጎታው ግማሽ ማራቶን ውድድር ሌላ ያልተጠበቀ ኢትዮጵያዊ ተፎካካሪ ታሪክ ሠርቷል።

Africa Cup Fans
ምስል P. Pabandji/AFP/Getty Images

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

This browser does not support the audio element.

በጋና አቻው 5 ለ0 የተረታውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ሊያሰለጥኑ የተረከቡት አዲስ አሰልጣኝ ማን ናቸው? ገና በቅጡ ያልተሰባሰበው ብሔራዊ ቡድን ወደሚቀጥለው የካሜሩኑ የአፍሪቃ ዋንጫ ለማስገባትስ ልምዳቸው ምን ይመስላል? የስፖርት ተንታኝ አነጋግረናል። የሪዮ ኦሎምፒክ የብር ሜዳሊያ ተሸላሚው ኢትዮጵያዊ አትሌት ፈይሳ ሊሌሳ ያሸንፋል ተብሎ በተጠበቀበት የቦጎታው ግማሽ ማራቶን ውድድር ሌላ ያልተጠበቀ ኢትዮጵያዊ ተፎካካሪ ታሪክ ሠርቷል። በተመሳሳይ የውድድር ዘርፍ በሴቶች ድሉ ከኢትዮጵያውያት እጅ አልወጣም። በፎርሙላ አንድ የመኪና ሽቅድምድም የብሪታንያው ሌዊስ ሐሚልተንን የሚያስቆመው አልተገኘም። በሀንጋሪው የትናንቱ ፉክክር የመርሴዲሱ አሽከርካሪ ሌዊስ ዳግም ድል ተቀዳጅቷል። 

ካሜሩን የዛሬ ዓመት በምታሰናዳው 32ኛው የአፍሪቃ ዋንጫ እግር ኳስ ውድድር ላይ ለመሳተፍ ሁለተኛ ዙር የማጣሪያ ጨዋታዎች ተቃርበዋል። በመጀመሪያ ዙር ውድድር ባለፈው ዓመት ኢትዮጵያ በጋና  ቡድን 5 ለ0 መሸነፏ ይታወሳል።  ኢትዮጵያ በምድብ  «ረ»  ከጋና፣ ሴራሊዮን እና ጎረቤት ኬንያ ጋር ነው የተደለደለችው። ምድቡን ጋና በ3 ነጥብ እና 5 ንጹህ ግብ ክፍያ ትመራለች። ኬንያን 1 ለ0 ያሸነፈችው ሴራሊዮን ተመሳሳይ 3 ነጥብ ይዛ በግብ ክፍያ ተበልጣ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ናት። 5 የግብ ዕዳ ያለባት ኢትዮጵያ  ከኬንያ በታች የመጨረሻ ደረጃ ላይ ነው የምትገኘው።  

ምስል Reuters/B. Szabo

የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ማለትም ዋልያዎቹን ወደ አፍሪቃ ዋንጫ ውድድር ለማስገባት ኃላፊነቱ የተጣለው አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ ላይ ነው።  ጳጉሜ ወር ላይ ሐዋሳ ከተማ ውስጥ በሚደረገው ሁለተኛ ዙር ውድድር የዋሊያዎቹን የአፍሪቃ ዋንጫ ተፋሳትፎ ግብ ለማሳካት አዲሱ አሰልጣኝ ብቃታቸው ምን ይመስላል? በብሥራት 101.1 ኤፍ ኤም የትሪቡን ስፖርት ዋና አዘጋጅ ፍቅር ይልቃል፦ «በተለይ የየመን ብሔራዊ ቡድንን በእስያ ዋንቻ ውድድር ለመጀመሪያ ጊዜ በማሳለፍ የሚታወቁ ናቸው» ብሏል። «ከዚያ ባሻገር ደግሞ ኢትዮጵያ ውስጥ የእግር ኳስ አስተማሪ ናቸው። በተለያዩ የአፍሪቃ ሃገራት ልምዶችን አካብተዋል። ኢትዮጵያ ውስጥም የተለያዩ ሥልጠናዎችን በመስጠት የአፍሪቃ እግር ኳስ ችግር ምንድን ነው? የሚለውን በተደጋጋሚ ለወጣት አሰልጣኞች ጭምር የሰጡ ኢንስትራክተር ናቸው» ሲል አክሏል። ያም ብቻ አይደለም በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ምክትል አሰልጣኝ ኾነው የሠሩ በመኾናቸው «የተሻሉ ሥራ ይሠራሉ ብዬ እገምታለሁ» ብሏል ፍቅር። አሰልጣኙ አጠቃላይ ችሎታቸውም ጥሩ መኾኑን ገልጧል። 

ካሜሩን በምታሰናዳው የአፍሪቃ እግር ኳስ ዋንጫ ዘንድሮ 16 ቡድኖች ብቻ ሳይኾኑ 24 ቡድኖች ሊያልፉ እንደሚችሉ የአፍሪቃ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን በእንግሊዝኛ ምኅፃሩ (CAF) ገልጧል። ኾኖም 24 ቡድኖችን ለማሳተፍ ካሜሩን ስታዲየም ግንባታዎችን ጨምሮ ለውድድሩ ግብዓት የሚሆኑ ነገሮችን በአፋጣኝ እንድታስተካክል በካፍ በኩል ተነግሯታል። ካሜሩን በተባለችው መሰረት መሰረተ አውታሮችን እያቀላጠፈች መኾኑን ለማረጋገጥ የካፍ ልዑክ ለሦስተኛ ጊዜ የፊታችን ቅዳሜ ወደ ካሜሩን ያቀናል። ካሜሩን ቃሏን ካልጠበቀች ከውድድር አዘጋጅነትም ልትሰረዝ ትችላለች ተብሏል። 

ምስል picture-alliance/dpa/B. Thissen

ከእግር ኳስ ውድድር ርእሰ ጉዳይ ሳንወጣ፦ የእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ሊጀምር ሁለት ሳምንታት በቀረበት በአሁኑ ወቅት ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በተደረጉ ዓለም አቀፍ የአሸናፊዎች ውድድሮች ቅዳሜ ዕለት ሊቨርፑል ማንቸስተር ዩናይትድን 4 ለ1 አሸንፏል።  ትናንት ማንቸስተር ሲቲ የጀርመኑ ኃያል ባየር ሙይንሽንን 3 ለ2 ድል አድርጓል። ከእንግሊዙ ቶትንሀም ጋር ሁለት እኩል አቻ የወጣው የስፔኑ ባርሴሎና በፍጹም ቅጣት ምት 5 ለ3 አሸንፏል። የስፔን ሌላኛው ቡድን አትሌቲኮ ማድሪድ ግን ዛሬ  በፈረንሳዩ ፓሪስ ሰንጀርሜን 3 ለ2  ተረትቷል።

የቀድሞው የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን አጥቂ ዋይኔ ሩኒ ለዲሲ ቡድን የመጀመሪያ ግቡን ባስቆጠረበት ጨዋታ አፍንጫውን ተሰብሯል። የ32 ዓመቱ ሩኒ ጉዳቱ የደረሰበት ቡድኑ ከኮሎራዶ ጋር ባደረገው ግጥሚያ ነው። ሌላኛው ለአሜሪካው ኤል ኤ ጋላክሲ ተሰልፎ የሚጫወተው የቀድሞው የስዊድን ቡድን አጥቂ፣ የ36 ዓመቱ ዝላታን ኢብራሒሞቪች ሦስት ግቦችን በተከታታይ በማስቆጠር ሔትትሪክ ሠርቷል። የዝላታን ግቦች እየተመራ የነበረው ቡድኑ ኦርላንዶ ሲቲን 4 ለ3 በኾነ ውጤት እንዲያሸንፍ አስችለዋል።

በኮሎምቢያ መዲና ቦጎታ ትናንት በተከናወነው የግማሽ ማራቶን የሩጫ ፉክክር ኢትዮጵያዊው አትሌት በተስፋ ጌታሁን ድል አድርጓል። በተስፋ በአንደኛነት የጨረሰው 1:05:08 በመሮጥ ነው። በውድድሩ ያሸንፋል ተብሎ እጅግ ተጠብቆ የነበረው፤ በሪዮ ኦሎምፒክ የብር ሜዳሊያ ባለቤቱ ሌላኛው ኢትዮጵያዊ አትሌት ፈይሳ ሊሌሳ ትናንት ሁለተኛ ኾኗል። የሦስተኛ ደረጃ ያገኘው ዝነኛው የኬንያው አትሌት ዲክሰን ቹምባ ነው። በተመሳሳይ የሴቶች ግማሽ ማራቶን  ሩጫ ድሉ ለኢትዮጵያዊቷ ነጻነት ጉደታ ኾኗል። የዓለም ሻምፒዮን ባለድሏ ነጻነት 1:11:32 ሮጣ ነው አንደኛ የወጣችው። እሷን ተከትላ የሁለተኛ ደረጃ ያገኘችው ኬኒያዊቷ ብርጊድ ኮስጌ ናት። ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት ደጊቱ አዝመራው የሦስተኛ ደረጃን ይዛለች።

ምስል Getty Images/AFP/O. Morin

በፎርሙላ አንድ የመኪና ሽቅድምድም የብሪታንያው አሽከርካሪ ሌዊስ ሀሚልተን ዳግም ድል ቀንቶታል። ሌዊስ ትናንት በተቀዳጀው የሀንጋሪ ግራንድ ፕሪ ሽቅድምድም ከተፎካካሪው ጀርመናዊ አሽከርካሪ ሰባስቲያን ፌትል ጋር ያለውን አጠቃላይ የነጥብ ልዩነት 24 አድርሶታል።  ሌዊስ ሐሚልተን አጠቃላይ ነጥቡ 213 ሲኾን፤ ሰባስቲያን ፌትል  189 ነጥብ አለው። ኪሚ ራይከነን በ146 ይከተላል። ጀርመናዊው የፌራሪ አሽከርካሪ «ግልጽ በኾነ መልኩ አንዳች ነገር እንዳቀድነው አልሄደም» ሲል የትናንት ሽንፈቱን ተቀብሏል። የመርሴዲሱ አሽከርካሪ ሌዊስ ሐሚልተን ቀሪ የበጋ ወር ረፍቱን በድል ስሜት እንደሚያጣጥም ገልጧል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሰ

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW