1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ስፖርት፤ መስከረም 15 ቀን፣ 2010 ዓ.ም. 

ሰኞ፣ መስከረም 15 2010

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትረምፕ ከአሜሪካ የብሔራዊ እግር ኳስ ሊግ ተጨዋቾች ጋር እሰጥ አገባ ይዘዋል። ተጨዋቾቹ ዘረኝነትን በመቀፍ በጋራ ተነስተዋል። ፕሬዚዳንቱ ደግሞ ተጨዋቾቹ ይሰናበቱልኝ ጥሪ አስተጋተዋል። በበርሊን ማራቶን ያሸንፋሉ ተብለው ከተጠበቁ 3 አትሌቶች ሁለቱ ውድድሩን ሲያቋርጡ አንደኛው ድል ቀንቶታል። ቀነኒሳ አቋርጧል።

Deutschland Berlin Marathon
ምስል Reuters/M. Dalder

This browser does not support the audio element.

በጀርመን ቡንደስሊጋ ቦሩስያ ዶርትሙንድ አጀማመሩ የሰመረ ይመስላል። እንደ አጀማመሩ ከዘለቀም በሻምፒዮንስ ሊግ ፍልሚያ ከሪያል ማድሪድ ጋር በሚያደርገው ጨዋታም አይበገሬ ሊሆን ይችላል ተብሏል። በሳምንቱ መጨረሻ በተደረጉ የእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ የእግር ኳስ ግጥሚያዎች እንደ ማንቸስተር ሲቲ ኃያል በትር የሰነዘረ ቡድን የለም።  ማንቸስተር ሲቲ ተጋጣሚውን 5 ለ0 ድባቅ መቷል። የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትረምፕ ከአሜሪካ የብሔራዊ እግር ኳስ ሊግ ተጨዋቾች ጋር እሰጥ አገባ ገብተዋል። ተጨዋቾቹ ዘረኝነትን በመቀፍ በጋራ ተነስተዋል። ፕሬዚዳንቱ ደግሞ ተጨዋቾቹ ይሰናበቱልኝ ጥሪ በተለመደው የትዊተር ገጻቸው አስተጋተዋል።

በቅድሚያም አትሌቲክስ

በትናንቱ የበርሊን ማራቶን የሩጫ ውድድር ሦስት የዓለማችን ፈጣን ሯጮች ብርቱ ፉክክር ያደርጋሉ ተብሎ ተጠብቆ ነበር፤ ሁለት ኬንያውያን እና አንድ ኢትዮጵያዊ። ኬንያዊው የኦሎምፒክ ባለድል ኤሊውድ ኪፕቾንጌ ውድድሩን በድል ሲያጠናቅቅ የሀገሩ ልጅ ዊልሰን ኪፕሳንግ እና ሌላኛው ዋነኛ ተፎካካሪው ይኾናል ተብሎ የተጠበቀው ቀነኒሳ በቀለ ግን ውድድራቸውን አቋርጠዋል። 

ምስል Reuters/H. Hanschke

በበርሊኑ ማራቶን አትሌት ኤሊውድ ኪፕቾንጌ የጠበቃቸው ቀርተው ያልጠበቀው አዲስ አትሌት ኢትዮጵያዊው ጉዬ አዶላ ተፈታትኖ አስደንቆታል ሲሉ የተለያዩ የአውሮጳ የስፖርት መገናኛ አውታሮች አትሌቱን አወድሰዋል። ኬኒያዊው ውድድሩን በአንደኛነት ያጠናቀቀው 2 ሰአት ከ3 ደቂቃ  ከ32 ሰከንድ በመግባት ነው። ጉዬ አዶላ ለጥቂት  በ14 ሰከንዶች ብቻ ተቀድሞ ሁለተኛ ደረጃ ማግኘት ችሏል። የሦስተኛ ደረጃን በ2:06:12 በመሮጥ የተቆናጠጠው ሌላኛው ኢትዮጵያዊ አትሌት ሞስነት ገረመው ነው። 

በሴቶች የበርሊን ማራቶን የሩጫ ፉክክር ኢትዮጵያዊቷ ሩቲ አጋ በ18 ሰከንዶች ብቻ ተቀድማ ሁለተኛ ደረጃን አግኝታለች።  ውድድሩን በአንደኛነት ያጠናቀቀችው ኬንያዊቷ ግላዲስ ቼሮኖ ናት። የሮጠችውም  2:20:23 ነው። የሀገሯ ልጅ ቫለሪ አያባይ ብርቱ ፉክክር በማድረግ በሩቲ አጋ ለጥቂት በ12 ሰከንድ ተበልጣ ሦስተኛ ኾናለች። ኢትዮጵያዊቷ ሔለን በቀለ የአራተኛ ደረጃን አግንታለች።  

እግር ኳስ

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ የሳምንቱ መጨረሻ ግጥሚያዎች እንደ ማንቸስተር ሲቲ ኃያል ብትሩን ያሳረፈ ቡድን የለም። ማንቸስተር ሲቲ ክሪስታል ፓላስን አይቀጡ ቅጣት  የቀጣው 5 ለ0 በሆነ ሰፊ ልዩነት በማሸነፍ ነው። ቸልሲም የግብ ክልሉን ሳያስነካ ስቶክ ሲቲን 4 ለ0 ኩም አድርጎ ሸኝቷል። ሊቨርፑልና ማንቸስተር ዩናይትድም ቀንቷቾዋል። ሊቨርፑል ላይስተር ሲቲን 3 ለ 2 ሲረታ፤ ማንቸስተር ዩናይትድ ሳውዝሐምፕተንን ያሸነፈው 1 ለ0 ነው። 

ምስል Reuters/C. Recine

የሊቨርፑሉ ግብ ጠባቂ ሲሞን ሚኞሌት ባለቀ ሰአት የፍጹም ቅጣት ምት በማዳን ቡድኑን ባይታደግ ኖሮ ሊቨርፑል በላይስተር ሲቲ ዳግም ነጥብ በጣለ ነበር። ሊቨርፑል የቅዳሜ ድሉ ለአራት ጊዜያት ድል አልባ የነበረው ጉዞውን ቀይሮለታል። ከ25 ዓመታት ወዲህ ደግሞ ከሜዳ ውጪ በተደረጉ 3 ተከታታይ ጨዋታዎች 10 ግብ ሲቆጠርበት የመጀመሪያው ኾኗል። የሊቨርፑል አሰልጣኝ ዬርገን ክሎፕ ቡድናቸው ነገ ከስፓርታክ ሞስኮው ጋር ለሚያደርገው የሻምፒዮንስ ሊግ ሁለተኛ ጨዋታ ወደ ሜዳ የሚገቡት በሳሳ የተከላካይ ክፍላቸው ስጋት ተውጠው ነው። 

በቅዳሜው ሌላ የፕሬሚየር ሊግ ጨዋታ ዋትፎርድ ስዋንሲ ሲቲን 2 ለ1 አሸንፏል። ትናንት በተደረገ ጨዋታ ደግሞ ብሪንግቶን ኒውካስልን 1 ለ0 በማሸነፍ በአንድ ደረጃ መሻሻል አሳይቷል። አርሰናል ከዌስት ብሮሚች ጋር ዛሬ ይጋጠማል። 

ቡንደስ ሊጋ

በጀርመን ቡንደስሊጋ ስድስት ጨዋታዎች ቦሩስያ ዶርትሙንድ መሪነቱን አስጠብቋል። በተለይ ቅዳሜ ዕለት ቦሩስያ ሞይንሽን ግላድባኅን 6 ለ1 በኾነ ሰፊ ልዩነት ማሸነፍ ችሏል። በዚህ አያያዙ ቦሩስያ ዶርትሙንድ በነገው የሻምፒዮንስ ሊግ ግጥሚያ ለስፔኑ ኃያል ሪያል ማድሪድ ብርቱ ተገዳዳሪ መኾኑ አይቀርም።  

ዶርትሙንዶች ከቡንደስ ሊጋው ጫፍ የሚያወርዳቸው አልተገኘም። ዘንድሮ አጀማመራቸው ድንቅ የሚባል ነው።  ይህን ብቃት ታዲያ አሁን መተግበር የሚጠበቅባቸው በሻምፒዮን ሊጉ የሚገጥሙት የስፔኑ ኃያል ሪያል ማድሪድ ላይ ነው።

ምስል picture-alliance/augenklick/firo Sportphoto

በሲግናል ኢንዱንዳ ስታዲየም የሚገናኙት ሁለቱ ኃያላን ቡድኖች ከባድ ፉክክር ያሳያሉ ተብሎ ተጠብቋል። ሁለቱ ቡድኖች በስድስት የውድድር ዘመኖች ለአምስት ጊዜያት ተገናኝተው ያውቃሉ። በአጠቃላይ ውድድሩ ሪያል ማድሪድ በጠበበ መልኩ ቦሩስያ ዶርትሙንድን ይበልጣል። ይሁንና ግን ቦሩስያ ዶርትሙንድ ዘና የሚያስብለው ነገር አላጣም። ከሪያል ማድሪድ ጋር በሜዳው ባደረጋቸው ግጥሚያዎች እስካሁን ድረስ አንድም ጊዜ ተሸንፎ አያውቅም። ዶርትሙንድ በሜዳው ሪያል ማድሪድን ለሦስት ጊዜያት ያሸነፈ ሲሆን፤ ሦስት ጊዜ ደግሞ አቻ መውጣት ችሏል። 

የሳምንቱ ማሳረጊያ ቦሩስያ ሞይንሽን ግላድባኅን 6 ለ 1 ያንኮታኮተው ቦሩድያ ዶርትሙንድ እስካሁን በድል ጎዳና ላይ እየተረማመደ ነው።  ከስድስት የቡንደስ ሊጋውእ ግጥሚያ አምስቱን ድል በማድረግ አንዱን አቻ ወጥቷል።  በደርጃ ሠንጠረዡ 16 ነጥብ የሰበሰው ቦሩስያ ዶርትሙንድ 19 ግቦችን 1 የግብ እዳ አስተናግዷል።

ዶናልድ ትራምፕና የአሜሪካ እግር ኳስ ውዝግብ

በዩናይትድ ስቴትስ የተለያዩ ግዛቶች ስፖርተኞች እና ታዋቂ ሰዎች የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ላይ ተቃውሞዋቸውን እያሰሙ ነው። ተቃውሞዋቸውም ዘረኝነትን በማውገዝ ነው።  በዋናነት ተቃውሞውን ያሰሙት ስፖርተኞች የአሜሪካ የብሔራዊ እግር ኳስ ሊግ ተጨዋቾች ናቸው።  የተቃውሞው ሰበብም ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ተቃውሞ የሚያሳይ ማንኛውም የብሔራዊ እግር ኳስ ሊግ ተጨዋች ሊሰናበት ይገባል የሚል አስተያየት በትዊተር የማኅበራዊ መገናኛ ገፃቸው ላይ ካሰፈሩ በኋላ ነው።  ፕሬዚዳንቱ በበርካታ ስፖርተኞች የተዛመተው እና ከጨዋታ በፊት የብሔራዊ መዝሙሩ ሲሰማ የሚታየው ተቃውሞ "ከዘር ጋር አንዳችም ግንኙነት የለውም" ብለዋል።  

ምስል picture-alliance/AP Photo/B. Anderson

ትናንት በተከናወኑ 14 ጨዋታዎች ብቻ 150 ተጨዋቾች አንድም በአንድ እግራቸው ሸብረክ ብለው በመንበርከክ አለያም እጅ ለእጅ በመያያዝ ተቃውሟቸውን ፕሬዚዳንቱ ላይ አንፀባርቀዋል።  ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በበኩላቸው «ታላቅ የኔነት ስሜት ለብሔራዊ መዝሙራችን እና ለሀገራችን።  እጅ አቆላልፎ መቆም ጥሩ ነው።  መንበርከክ ተቀባይነት የለውም።  መጥፎ ገፅታ» ብለዋል በተለመደው የትዊተር መልእክታቸው። እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር ከ2016 ወዲህ ስፖርተኞች በስፋት እና በጋራ ያሳዩት ተቃውሞ ተብሎለታል።  

በነገው የሻምፒዮንስ ሊግ ግጥሚያዎች ማንቸስተር ሲቲ ከሻካታር ዶኒዬትስክ፤ ሞናኮ ከፖርቶ ቶትንሀም ከአፖል ኒኮሲያ፤ ሴቪያ ከማሪቦር፤ ላይፕትሲሽ ከቤሲክታስ እንዲሁም ናፖሊ ከፊዬኑርድ ይገናኛሉ። ሁሉም የሻምፒዮንስ ሊግ ግጥሚያዎች በተመሳሳይ ሰአት ከምሽቱ 3 ሰአት ከ45 ደቂቃ ነው የሚከናወኑት። 

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አርያም ተክሌ


 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW