1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ስፖርት፤ መስከረም 29 ቀን፣ 2010 ዓ.ም. 

ሰኞ፣ መስከረም 29 2010

ግብጽ ከ27 ዓመታት በኋላ ለዓለም ዋንጫ የማለፍ ሕልሟ ዕውን ሲሆን፤ ጀርመን በድል ጎዳና እየገሰገሰች ነው። በአንጻሩ የአርያን ሮበን የሆላንድ ቡድን ሕልም ግን ደመናው ላይ ሊበታተን በንፋስ እየተገፋ ነው። ሆላንድ ማጣሪያውን ለማለፍ ስዊድን ላይ 7 ንጹህ ግቦች ማስቆጠር ይጠበቅበታል። ብዙዎች የማይሆን ብለውታል።

Fußball 2018 World Cup Qualifications - Africa - Egypt vs Congo
ምስል Imago/Xinhua

This browser does not support the audio element.

በሳምንቱ ማሳረጊያ ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ በቺካጎ ማራቶን ድል ስትቀዳጅ በርካታ ሃገራት ለዓለም ዋንጫ እግር ኳስ ማጣሪያ ተፋልመዋል። ግብጽ ከ27 ዓመታት በኋላ ለዓለም ዋንጫ የማለፍ ሕልሟ ዕውን ሲሆን፤ ጀርመን በድል ጎዳና እየገሰገሰች ነው። በአንጻሩ የአርያን ሮበን የሆላንድ ቡድን ሕልም ግን ደመናው ላይ ሊበታተን በንፋስ እየተገፋ ነው። ሆላንድ ማጣሪያውን ለማለፍ ስዊድን ላይ 7 ንጹህ ግቦች ማስቆጠር ይጠበቅበታል። ብዙዎች የማይሆን ብለውታል። ብሪታንያዊው የመርሴዲስ አሽከርካሪ ሌዊስ ሐሚልተን ዳግም ድል ተቀዳጅቷል። ጀርመናዊው ተፎካካሪው የፌራሪ አሽከርካሪ ሰባስቲያን ፌትል በመጥፎ አነዳድ በተከታታይ ሲበለጥ ትናንት ለሦስተኛ ጊዜ መሆኑ ነው። 

አትሌቲክስ

ኢትዮጵያዊቷ የኦሎምፒክ ባለድል ጥሩነሽ ዲባባ በቺካጎ ማራቶን ትናንት አንደኛ ደረጃን ስትቀዳጅ ድሉ በማራቶን የመጀመሪያው ኾኖ ተመዝግቦላታል። በወንዶች ፉክክር ደግሞ አሜሪካዊው ጋለን ሩፕ አንደኛ በመውጣት ከ35 ዓመታት ወዲህ በቺካጎ ማራቶን ያሸነፈ የዩናይድ ስቴትስ ተወላጅ ተብሎለታል። ሁለቱም አትሌቶች እያንዳንዳቸው አንድ መቶ ሺህ ዶላር ማለትም 2 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር ግድም ተሸላሚ እንደሚኾኑ ተገልጧል። 

ምስል Reuters

በሴቶች የቺካጎ ማራቶን ሩጫ ጥሩነሽ ዲባባ በ2:18:31 ስትገባ፤ የኬንያዋ አትሌት ብሪጊድ ኮስጌይ እና አሜሪካዊቷ ጆርዳን ሐሴይ ከሁለት ደቂቃ ግድም በኋላ ተከትለው በመግባት ሁለተኛ እና ሦስተኛ ወጥተዋል። 

በወንዶች ዘርፍ የቺካጎ ማራቶን አሜሪካዊ አትሌት ያሸነፈው እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ1982 ዓመት ነበር፤ በአትሌት ግሬግ ማየር። ከዚያ በኋላ የዛሬ 18 ዓመት ካህሊድ ካኖቺ ለሞሮኮ ሮጦ ካሸነፈ በኋላ የዛሬ 17 እና 15 ዓመት በተከታታይ ማለትም በ2000 እና 2002 ለዩናይትድ ስቴትስ ሮጦ ማሸነፍ ችሏል። ጋለን ሩፕ ዘንድሮ በአንደኛነት ድል በመቀዳጀት ለሦስት ዐሥርተ ዓመት የራቀውን የቺካጎ ማራቶን ወደ ዩናይትድ ስቴትስ አስመልሷል። 

እግር ኳስ

ከሰኔ 7 እስከ ሐምሌ 8 ቀን 2010 ዓ.ም. ድረስ ሩስያ በምታከናውነው የዓለም ዋንጫ የእግር ኳስ ጨዋታ ለመሳተፍ ሃገራት በተለያየ የየዓለም ክፍላት ተፋልመዋል። አፍሪቃውያን ባከናወኑት የማጣሪያ ጨዋታ ግብጽ ናይጀሪያን ተከትላ ለሩስያው የዓለም ዋንጫ ማለፏን አረጋግጣለች። ፈርኦኖቹ የሚል መጠሪያ ያለው የግብጽ እግር ኳስ ብሔራዊ ቡድንን ባለቀ ሰአት ለድል ያበቃው የሊቨርፑሉ አጥቂ ሞ ሳላህ ነው። ሞ ኮንጎ ላይ ትናንት ባለቀ ሰአት በፍጹም ቅጣት ምት ያስቆጠራት ሁለተኛ ግብ ፈርኦኖቹን ከ17 ዓመት ወዲህ ወደ ዓለም ዋንጫ ውድድር እንዲመለሱ አስችሏቸዋል። ግብጽ ሰኔ ወር ላይ ሩስያ ውስጥ ለሚከናወነው ውድድር ማለፏን ያረጋገጠችው ገና አንድ ጨዋታ እየቀራት ነው። ግብጾች ትናንት በአሌክሳንድሪያ የግድ ማሸነፍ የነበረባቸው ኡጋንዳ እና ጋና ቅዳሜ እለት አቻ በመውጣታቸው ነበር።

ምስል Reuters/K. Pfaffenbach

በሌላ ስፍራ በተከናወኑ ግጥሚያዎች ፖላንድ በ10 ጨዋታዎች 25 ነጥብ በመሰብሰብ ለዓለም ዋንጫ ማለፏን አረጋግጣለች። የሮበርት ሌቫንዶቭስኪ ድንቅ ግብ ታክሎበት ሞንቴኔግሮን 4 ለ2 ያሸነፈው የፖላንድ ቡድን በሁለተኛ ደረጃ የሚከተለው ዴንማርክን በአምስት ነጥብ ይበልጣል። የዴንማርክ ቡድን በቶትንሀሙ ክርስቲያን ኤሪክሰን በኩል አንድ ግብ ማስቆጠር ቢችልም ከሩማንያ ጋር በአቻ ተለያይቷል። 
ትናንት የአዘርባጃን ተጋጣሚውን 5 ለ1 ያርበደበደው የጀርመን ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን በ10 ተከታታይ ጨዋታዎች በማሸነፍ አዲስ ታሪክ አስመዝግቧል። ቡድኑ እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር ከ2016 የአውሮጳ ዋንጫ ወዲህ ተሸንፎ አያውቅም። ትናንት ከተከላካይ ክፍል በመምጣት ለጀርመን ቡድን ግብ ያስቆጠረው ተከላካዩ አንቶኒዮ ሩዲገር የጀርመን ቡድን ሦስት የተሟሉ ቡድኖች ሊወጣው እንደሚችል ተናግሯል።

«ከፍተኛ ብቃት ነው ያለን። የመጀመሪያ የሚባለው ቡድን ብቻ ሳይሆን በሁለተኛ እና ሦስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ቡድናችንም ብቃት አለው። በአንደኛ ዲቪዚዮንና በሻምፒዮንስ ሊግ ተሰልፈው የተጫወቱ ብዙ ወጣት ተጨዋቾች አሉን። አዎ፤ እዚህ ቡድን ላይ ከፍተኛ ብቃት ይታያል።»

የጀርመን ብሔራዊ ቡድን ተደጋጋሚ ድሎችን ማስመዝገቡን ተከትሎ አሠልጣኙ ዮኣኂም ሎይቭ ቡድናቸው ትናንት ዘና ብሎ ወደ ሜዳ እንዲገባ አድርገዋል። ቡድኑ የመጨረሻ ልምምድ በሚያደርግበት ወቅትም ደጋፊዎች ወደ መለማመጃ ስፍራው እንዲገቡ ተፈቅዶላቸዋል። የጀርመን ቡድን እንዲህ እጅግ ዘና ያለባቸው ጊዜያት በርካታ አይደሉም። አሠልጣኝ ዮኣኂም ሎይቭ አዘርባጃንን ትናንት ከመግጠማቸው ቀደም ብሎ በሰጡት መግለጫ  ቡድናቸው እንደተለመደው ኃያል ሆኖ ወደ ሜዳ እንዲገባ ማዘጋጀታቸውን ገልጠው ነበር።

ምስል Imago/Jan Huebner

«በማጣሪያው ላይ ስኬት ካስመዘገብን በኋላ ቡድናችን ትንሽ አረፍ እንዲል ትንፋሽ እንዲወስድም አድርጌያለሁ። አሁን በድጋሚ ጠንከር እንዲል እፈልጋለሁ።» በእርግጥም የጀርመን ብሔራዊ ቡድን ተጋጣሚው አዘርባጃን ላይ አንድ ግብ ካስቆጠረ በኋላ የግብ ክልሉን እንዳሻው ተመላልሶበታል። የሌዮን ጎሬትስካ በተረከዝ ከመረብ የተቆጠረችውን ግብ ጨምሮ፤ በ54ኛው ደቂቃ በዛንድሮ ቫግነር፤ በ64ኛው ሩዲገር እንዲሁም በ65ኛው ደቂቃ ላይ በድጋሚ በሊዮን ጎሬትስካ በተቆጠሩት አራት ግቦች የጀርመን ቡድን ሲመራ ቆይቷል። በ81ኛው ደቂቃ ላይ ኤምሬ ቻን ባስቆጠራት ድንቅ ግብ የጀርመን ቡድን አዘርባጃንን 5 ለ1 ድል ማድረግ ችሏል። 

ለአዘርባጃን ብቸኛዋን ግብ ያስቆጠረው ሼይዳዬቭ ነው። ሙስጣፊ በጉዳት ሜዳ ላይ እንደወደቀ በፍጥነት ወደ ግብ ክልሉ ያመራው ሼይዳዬቭ የጀርመኑ ተከላካይ አንቶኒዮ ሩዲገርን ጨምሮ ሌሎች ተጨዋቾችን ትንፋሽ አሳጥቶ በማታለል ያስቆጠራት ግብ የተጨዋቹ የግል ብቃት የተመሰከረባት ናት። 

በጀርመን ቡድን ውስጥ አዳዲስ ተጨዋቾች መሰለፍ ችለዋል። ግብ ጠባቂው ማኑኤል ኖየርን ተክቶ የገባው በርንድ ሌኖ የመጀመሪያዋና ብቸኛዋ ግብ ጀርመን ላይ ለመቆጠሯ ተጠያቂ ተደርጓል በቀላሉ ሊያድናት ይችል ነበር በሚል። ማኑኤል ኖየር ባለፈው መስከረም ወር ላይ ድጋሚ ከደረሰበት ጉዳት በቅጡ ማገገም የሚችለው ከስድስት ወራት በኋላ መሆኑን ከባየርን ሙይንሽን ቡድን ቴሌቪዥን ጋር ባደረገው ቃለ መጠይቅ አስታውቋል። የዓለማችን ምርጡ ግብ ጠባቂ ከተጠቀሰው ጊዜ ቀደም ብሎ ተሽሎት ለዓለም ዋንጫ ይሰለፍ እንደሁ ወደፊት የሚታይ ነው። አሰልጣኙ በበኩላቸው በአጭሩ፦ «ማኑኤል ኖየር በሚቀጥለው ዓመት በተቻለ ፍጥነት ልምምድ ጀምሮ ጨዋታ ያከናውናል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ» ብለዋል።

ምስል picture-alliance/dpa/Revierfoto

 ተከላካዮቹ ኒክላስ ሱይሌ እና ሽኮድራን ሙስጣፊ መጎዳትም ለአሠልጣኝ ዮአኺም ሌላ ምኞት የማይሰጥ ነገር ይመስላል።  የሌዮን ጎሬትስካ መጠንከር እና ሁለት ግቦችን ማስቆጠር ግን ዘና ሳያደርጋቸው አይቀርም። ሌዮን በዚህ አያያዙ በሩስያው የዓለም ዋንጫ 23ቱ የቡድኑ አባላት ውስጥ መግባት ብቻ ሳይሆን ከ11ዱ ምርጦች ውስጥ ለመካተት የሚሳካለት ይመስላል። 

የጀርመን ጎረቤት ኔዘርላንድ ተስፋ ግን ስዊድን ሉግዘንበርግን 8 ለ0 በማንኮታኮቷ እጅግ ተመናምኗል።  ኔዘርላንድ ቤላሩስን 3 ለ1 ማሸነፏ በምድቡ የሦስተኛነት ደረጃን እንድታገኝ አስችሏታል፤ በሁለተኛ ደረጃ ላይ በምትገኘው ስዊድን ግን በ3 ነጥብ ትበለጣለች። ያም ብቻ አይደለም ስዊድን እጅግ በሰፋ የግብ ልዩነት ትበልጣለች። ኔዘርላንድ ወደ ሩስያው የዓለም ዋንጫ ለመግባት ስዊድንን በ7 ግብ ልዩነት ማሸነፍ ይጠበቅባታል። የኔዘርላንድ አምበል አሪየን ሮበን፦ «ይኽ ሊሆን የማይችል ነው» ብሏል። «ሲበዛ ያማል ግን ምን ታደርገዋለህ ያ የስፖርቱ አንድ አካል ነው» ሲል ለሮይተርስ ተናግሯል። «እስከ መጨረሻዋ ሰአት ድረስ ተስፋ ሳንቆርጥ መቀጠላችን ግን ግልጽ ነው» ያለው አርየን ሮበን ስዊድንን በሰፋ ልዩነት ማሸነፍ ግን ሊሆን የማይችል ነገር ነው ሲል አክሏል።

የጀርመን አትሌቶች ከሀገሪቱ የኦሎምፒክ ስፖርት ኮንፌዴሬሽን (DOSB) ሙሉ ለሙሉ በመነጠል አዲስ ነጻ ድርጅት ለማቋቋም ከጫፍ መድረሳቸው ተገልጧል። የጀርመን አትሌቶች  ኮሚቴ ሊቀ-መንበር ማክሲሚሊያን ሐርቱንግ  ለጀርመን ማሰራጫ ARD እንደተናገሩት «አትሌቶች የራሳቸውን ድምጽ የሚያሰማላቸው ተቋም ይሻሉ። እናም የምናቋቁመው ሌላ ድርጅት  የአትሌቶችን ምልከታ ነጻ በኾነ መልኩ ለማንጸባረቅ ይረዳናል» ብለዋል። አዲስ የሚቋቋመው ተቋም፦ «የጀርመን አትሌቶች» የሚል መጠሪያ እንደሚኖረው፤ ከስድስት ቀናት በኋላም ኮሎኝ ከተማ ውስጥ በሚደረገው የአትሌቶቹ ተወካዮች ስብሰባ ላይ ውሳኔ እንደሚተላለፍ ተገልጧል። 

ምስል Getty Images/M. Thompson

የመኪና ሽቅድምድም
በጃፓን ግራንድ ፕሪ የመኪና ሽቅድምድም ብሪታንያዊው ሌዊስ ሐሚልተን ዳግም አሸናፊ ኾነ። የመርሴዲስ አሽከርካሪው ሌዊስ ለድል የበቃው ሱዙካ ውስጥ በተደረገው ውድድር ነው። ጀርመናዊው የፌራሪ አሽከርካሪ ተቀናቃኙ ሰባስቲያን ፌትል በጊዜ እጅ ለመስጠት ተገዷል። 

የትናንትናውን ጨምሮ ለሦስት ተከታታይ ጊዜያት ማሸነፍ የቻለው ሌዎስ ሐሚልተን አጠቃላይ ውድድሩን አሁን በ59 ነጥብ ልዩነት በመቅደም ይመራል። ውድድሩ ሊጠናቀቅ የቀረው አራት ተከታታይ ሽቅድምድሞች ብቻ ነው። ሰባስቲያን ፌትል በውድድሩ መሪ ኾኖ መዝለቅ የቻለው እስከ አራተኛው ሳምንት ውድድር ድረስ ብቻ ነው። የዓለም መገናኛ አውታሮች ብሪታንያዊው አሽከርካሪ ሌዊስ ሐሚልተን የፎርሙላ አንድ የመኪና ሽቅድምድምን በማሸነፍ ለ4ኛ ጊዜ ዋንጫውን ማንሳቱ የማይቀር ነው ሲሉ ከወዲሁ ዘግበዋል።   

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW