1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ስፖርት፤ መጋቢት 10 ቀን፣ 2010 ዓ.ም 

ሰኞ፣ መጋቢት 10 2010

በአፍሪቃ የኮንፌዴሬሽን ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታ አዲስ መጪው ወላይታ ዲቻ አንጋፋው የግብጽ የእግር ኳስ ቡድን ዛማሌክን ከውድድር አሰናብቶ ጉድ አሰኝቷል። ሌላኛው የኢትዮጵያ አንጋፋ ቡድን ቅዱስ ጊዮርጊስ ግን በኡጋንዳው ካምፓላ ካፒታል ሲቲ አውቶሪቲ (KCCA) ከቻምፒየንስ ሊግ ተሰናብቷል።

UK Mohamed Salah
ምስል Reuters/L. Smith

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

This browser does not support the audio element.

በአፍሪቃ የኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ አዲስ መጪው ወላይታ ዲቻ አንጋፋው የግብጽ የእግር ኳስ ቡድን ዛማሌክን ከውድድር አሰናብቶ ጉድ አሰኝቷል። ሌላኛው የኢትዮጵያ አንጋፋ ቡድን ቅዱስ ጊዮርጊስ ግን በኡጋንዳው ካምፓላ ካፒታል ሲቲ አውቶሪቲ (KCCA) ከቻምፒየንስ ሊግ ተሰናብቷል።  ግብጻዊው ሞሐመድ ሳላኅ ገኖ በወጣበት ጨዋታ ሊቨርፑል ዋትፎርድን አደባይቷል። ኃያሉ ባየር ሙይንሽን በዘንድሮ የውድድር ዘመን ከ19ኝ ጨዋታዎች ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ  ሽንፈት ቀምሷል። ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ሱሌ ዑቱራ በሎስ አንጀለስ ማራቶን ድል ተቀዳጅታለች።  

ዛማሌክን ድል የነሳው ወላይታ ድቻ 

በአፍሪቃ አኅጉራዊ እግር ኳስ ጨዋታዎች ለዘጠኝ ጊዜያት ዋንጫ በእጁ ያስገባው የግብጹ አንጋፋ ቡድን ዛማሌክ ትናንት ጉድ ኾኗል። የግብጹ ዛማሌክን ድል አድርጎ ከውድድር ያስወጣው ደግሞ ለኮንፌዴሬሽኑ ግጥሚያ አዲስ የኾነው የኢትዮጵያው ወላይታ ድቻ ነው ። 

ወላይታ ድቻን ንቀው ወደ ሜዳ የገቡት የግብጹ ዛማሌክ አዲሱ አሰልጣኝ ኤሃብ ጋላል ወላይታ ድቻን እንደሚያሸንፉ እርግጠኛ ነበሩ። አሰልጣኙ ከጨዋታው በፊት ተጠይቀው ሲመልሱ፦ «ግብጽ ውስጥ በሰፋ ልዩነት እንደምናሸንፍ እርግጠኛ ነኝ» ብለው ነበር። ያም ብቻ አይደለም፦ «ተጋጣሚያችን እዚህ ግባ የሚባል ቡድን አይደለም» ሲሉም በንቀት ነበር መልስ የሰጡት። ነገሩ «የናቁት ይወርሳል» ኾነና የአፍሪቃ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫን፤ ለአምስት ጊዜያት፤  የአኅጉሩ ሱፐር ካፕን ለሦስት ጊዜያት በድል ያጠናቀቀቅው ዛማሌክ በወላይታ ድቻ ከማጣሪያው ተሰናብቷል። በነገራችን ላይ ዛማሌክ ከ8 ዓመት በፊትም የአፍሪቃ ቡድኖች የአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫንም በእጁ ያስገባ ቡድን ነበር። ምናልባትም የአሰልጣኙ ከልክ ያለፈ ልበ-ሙሉነት ከእዚህ ሁሉ ተደጋጋሚ ድል የመነጨም ሊኾን ይችላል። 

ምስል picture-alliance/blickwinkel/McPhoto

ወላይታ ድቻ ዛማሌክን ትናንት አሸንፎ ከውድድሩ ማስወጣቱ ደጋፊዎቹን ሲያስቦርቅ ግብጻውያንን ለሐዘን ዳርጓል፤ ያ ብቻ ግን አይደለም።  የዛማሌክ ሽንፈት በግብጽ የእግር ኳስ ማኅበረሰብ ዘንድ እሰጥ አገባም አስነስቷል። የዛማሌክ ቡድን ሊቀ-መንበር ሞርታዳ ማንሱር ለሽንፈታቸው ተጠያቂው የሀገሪቱ የስፖርት ሚንሥትር ነው ሲሉ አምርረው ተናግረዋል።  
ሊቀመንበሩ ከጨዋታ በኋላ ባደረጉት ቃለ-መጠይቅ፦«ቡድናችንን ላደባዩት ለሚንሥትር ካህሌድ አብደል አዚዝ ምሥጋና ይግባቸውና ዛሬ ተሸንፈናል» ብለዋል። «በካዝናው ከ200 ሚሊዮን የግብጽ ፓውንድ በላይ ያለው ቡድን ለተጨዋቾቹ የአየር መጓጓዣ እና የሆቴል ክፍያ መጠየቁ አመክኖዋዊ ነውን?» ሲሉ ጠይቀዋል። ሚንሥትር መሥሪያ ቤቱ ለዛማሌክ ቡድን የገንዘብ ነክ አስተዳደር ውሳኔ ኮሚቴ እንዲዋቀር በመወሰኑ ቦርዱ ለቡድኑ አስፈላጊ ወጪዎችን ማስፈጸም እንደተሳነውም ተዘግቧል። 

የዛማሌክ ዋነኛ ተቀናቃኝ አል አህሊ ባለፈው ሳምንት የግብጽ ሊግ ዋንጫን ማሸነፉ በራሱ ለዛማሌክ ተጨማሪ ራስ ምታት ሳይኾን አልቀረም።  የዛማሌክ ቡድን ሊቀመንበር  የትናንቱን ሽንፈት በተመለከተ ለሚንሥትሩን ጥያቄ አቅርበዋል። «ሚንሥትሩን የምጠይቀው፤ ለአል አኅሊ ብለው ዛማሌክን እያንኮታኮቱ ነውን?» ብለዋል። አልአህሊን ለመጥቀም የተደረገ ነው ሲሉ የግብጽ የስፖርት ሚንሥትርን ወቅሰዋል።  በዚህም አለ በዚያ ግን የዛማሌክ ጉዞ ንቆት ወደ ሜዳ በገባው ወላይታ ዲቻ ድል በአጭሩ ተቀጭቷል።   

የወላይታ ድቻ የትናንት ድል ዛሬም አብይ መነጋገሪያ ኾኗል። የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት፦ «የግብጹ ዛማሌክ አስደንጋጭ እልቂት ደርሶበታል»  ሲል አትቷል።  የግብጹ አህራም በበኩሉ፦ «ከኮንፌዴሬሽን ዋንጫ በፍጹም ቅጣት ምት የተሰናበተው የግብጹ ዛማሌክ ለድንጋጤ ተዳርጓል» ሲል ዘግቧል። «ዛማሌክ ተንኮታኮተ» እና መሰል ዘገባዎችንም የግብጽ ጋዜጦች አስነብበዋል። 

ዛማሌክ ትናንት በአኅመድ ማድቦሊ ሁለት ግቦች ቢመራም በ52ኛው ደቂቃ ላይ ለወላይታ ድቻ አንድ ጎል በማስቆጠር በአጠቃላይ ድምር ሦስት እኩል እንዲኾን ያደረገው አብዱልሰመድ ዓሊ ዑስማን ነው። እናም ወደ ፍጹም ቅጣት ምቱ አመሩ። በፍጹም ቅጣት ምቱ የወላይታ ድቻ ተጨዋቾች በተረጋጋ  መልኩ ያስቆጠሯቸው ግቦች የፍጹም ቅጣት ምት ብቃታቸው የታየበት ነበር።  የዛማሌክ አይማን ሄፍኒ እና ሞሀመድ አብደል አዚዝ አራተኛውን እና አምስተኛውን ፍጹም ቅጣት ምት ማስቆጠር ተስኗቸው ድል የወላይታ ድቻ ኾኗል።  የመጨረሻዋን ፍጽም ቅጣት ምት የወላይታ ድቻ ግብ ጠባቂ አጨናግፎ ደጋፊዎቹን አስፈንጥዟል። 

ምስል picture-alliance/dpa/B. Thissen

ከዛማሌክ ባሻገር የኮንፌዴሬሽን ዋንጫን አምስት ጊዜያት ማሸነፍ የቻለው የቱኒዝያው ክለብ አፍሪቃም በሞሮኮው ሬኔሳንስ ቤርካና በደርሶ መልስ 4 ለ1 መሸነፉ ብዙዎችን አስደምሟል። የቱኒዚያው አንጋፋ ቡድን «ክለብ አፍሪቃ» በኮንዴሬሽን ዋንጫ ባለፈው ዓመት ለፍጻሜ ደርሶ በአስደናቂ ኹኔታ የተሸነፈው በደቡብ አፍሪቃው ሱፐር ስፖርት ዩናይትድ ቡድን ነበር። እንደ ዛማሌክ ሁሉ እሱም ቅዳሜ ዕለት የኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ጉዞውን ገትቷል።  

ቅዳሜ እለት በአፍሪቃ የሻምፒዮንስ ሊግ ግጥሚያ ቅዱስ ጊዮርጊስ በኡጋንዳው ካምፓላ ካፒታል ሲቲ አውቶሪቲ (KCCA) በደርሶ መልስ 1 ለ0 ተሸንፎ 16ቱ ቡድኖች ውስጥ መግባት ተስኖታል። የጨዋታው ኹለተኛ አጋማሽ በተጀመረ 2ኛ ደቂቃ ላይ በሙዛሚሩ ሻባን የተቆጠረችው ብቸኛ ግብ ቅዱስ ጊዮርጊስን ከውድድሩ አሰናብታለች። 

አትሌቲክስ
24,000 ሯጮች በተሳተፉበት የሎስ አንጀለሱ የማራቶን ሩጫ ፉክክር ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ሱሌ ዑቱራ በአንደኛነት አሸናፊ ኾናለች። በትናንቱ የማራቶን ሩጫ ውድር ሱሌ በድል ያጠናቀቀችበት ጊዜ 2 ሰአት ከ33 ደቂቃ ከ50 ሰከንድ ነው። በመጨረሻዎቹ  ደቂቃዎች  በቡድን ከሚሮጡ አትሌቶች መሀል ተፈትልካ በመውጣት አንደኛ የወጣችው ሱሌን ተከትላ በሁለተኛነት ያጠናቀቀችው ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት ተወዳዳሪ ፀሓይ ደሳለኝ ናት። ፀሓይ ሱሌን ተከትላ ኹለተኛ የወጣችው ከሱሌ በ8 ሰከንድ ብቻ ተበልጣ ነው። ኬኒያዊቷ ሔለን ጄፕኩርጋት 13 ሰከንድ ተበልጣ ሦስተኛ ወጥታለች። 

በወንዶቹ የሎስ አንጀለስ የማራቶን ሩጫ ፉክክር ኬኒያዊው ዌልደን ኪሩይ በአንደኛነት አሸንፏል። ዌልደን አንደኛ የወጣው  2 ሰአት ከ11 ደቂቃ ከ48 ሰከንድ ሮጦ በመግባት ነው። ኢትዮጵያዊው አትሌት ገብረጻድቅ አድኃነ በ10 ሰከንዶች ብቻ ለጥቂት ተበልጦ በሁለተኛነት አጠናቋል። የዓምና አሸናፊው ኬኒያዊው ኤሊሻ ባርኖ በበኩሉ በገብረጻድቅ በ16 ሰከንዶች ተበልጦ ሦስተኛ ኾኗል።  ሣንታ ሞኒካ ፒየር ላይ በተጠናቀቀው የሎስአንጀለሱ የማራቶን ሩጫ አሸናፊዎች እያንዳንዳቸው የ23 ሺህ ዶላር ተሸላሚ መኾናቸው ተዘግቧል። 
እግር ኳስ
በጀርመን ቡንደስ ሊጋ ኃያሉ ባየር ሙይንሽን በዘንድሮ የውድድር ዘመን ከ19 ጨዋታዎች ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ሽንፈት ደርሶበታል። ባየር ሙይንሽንን ለመጀመሪያ ጊዜ ያሸነፈው ላይፕሲሽ ሲኾን ውጤቱም 2 ለ1 ነው።  በናቢ ኬይታ እና በቲሞ ቬርነር ግቦች ነው ላይፕሲሽ ለድል የበቃው። ለባየር ሙይንሽን ጨዋታው በተጀመረ 12ኛው ደቂቃ ላይ የእለቱን ቀዳሚ ብቸኛ ግብ ያስቆጠረው ዛንድሮ ቫግነር ነው። ላይፕሲሽን አሸናፊ ያደረገችውን ግብ በ56ኛው ደቂቃ ላይ ያስቀጠረው ቲሞ ቬርነር የማሸነፊያዋን ግብ ማስቆጠሩ ብቻ አይደለም ልዩ ስሜት የፈጠረበት። 

ምስል picture alliance/Cordon Press/E. Ivanova

«ባየርን ላይ ብቻ ግብ ማስቆጠሩ በራሱ ደስ የሚል ነገር ነው። በዛ ላይ ደግሞ ማሸነፉ ሲጨመርበት ይበልጥ ደስ ይላል። ዛሬ ዚበዛ በድንቅ ኹናቴ  ነው የተጫወትነው።  ባየርንን ፋታ ነስተን በማጥቃት ነው የተጫወትነው። ሌላው ደግሞ የግድ ሊነገርለት የሚገባው፤ ከ1 ለ0 መመራት ተነስተን ነው ጨዋታውን የገለበጥነው። አንድ እጅግ ጥሩ ቡድን ማድረግ የሚገባውን ነው ያደረግነው።  በዚያ በእውነቱ ልንኮራ ይገባል።»

በቡንደስሊጋ

በቡንደስሊጋው ባየርን ከ19ኝ ጨዋታዎች ወዲህ ትናንት ለመጀመሪያ ጊዜ ሽንፈት ቢገጥመውም የደረጃ ሰንጠረዡን በ17 ነጥብ ልዩነት እየመራ ይገኛል።  ባየርን ሙይንሽንን የሚከተለው ሻልከ 49 ነጥብ አለው። 48 ነጥብ የሰበሰበው ቦሩስያ ዶርትሙንድ በባየር ሙይንሽን በ18 ነጥብ ተበልጦ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። 

ምስል Reuters/M. Rietschel

ኮሎኝ ከ190 ቀናት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ድል ቀንቶት ከደረጃ ሰንጠረዡ የመጨረሻ ግርጌ አንድ ከፍ ብሏል። 18ኛ ደረጃ ቦታውንም ቅዳሜ ዕለት በሔርታ ቤርሊን 2 ለ1 ለተሸነፈው ሐምቡርግ አስረክቧል። ሊጠናቀቅ 7 ጨዋታዎች በሚቀሩት ቡንደስ ሊጋ ኮሎኝ ወራጅ ቃጣናው ጠርዝ ላይ ከሚገኘው ማይንትስ የሚበለጠው በ5 ነጥብ ብቻ ነው። ያም በመኾኑ የትናንቱ የባየር ሌቨርኩሰን ላይ የተቀዳጀው የ2 ለ0 ድል ተደምሮለት ከወራጅ ቃጣናው ለመውጣት ተስፋ እንዲሰንቅ አድርጎታል። ሻልከ፣ ዶርትሙንድ እና ፍራንክፉርትን በተከታታይ ያሸነፈው ባየር ሌቨርኩሰን ለኮሎኝ እጅ ሰጥቷል። ከኮሎኝ እና ባየር ሌቨርኩሰን ግጥሚያ ቀደም ብሎ 400 ግድም የሚኾኑ የእግር ኳስ ጠበኞች በፈጠሩት ግርግር በርካታ ሰዎች ተጎድተዋል። 

ፕሬሚየር ሊግ

በፕሬሚየር ሊጉ ግጥሚያ ግብጻዊው ሞሐመድ ሳላህ ከሦስተኛ ግብ ውጪ ለሊቨርፑል አራት ግቦችን በተከታታይ አስቆጥሮ ደጋፊዎቹን አስፈንጥዟል። ለሦስተኛውም ግብ ቢኾን ኳሷን ለሮቤርቶ ፊርሚኖ  አመቻችቶ የሰጠው ይኸው ሞሐመድ ሳላህ ነው። ሊቨርፑል ዋትፎርድን 5 ለ0 ድባቅ በመታበት የእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ጨዋታ ግብጻዊው ኃያልነቱን አስመስክሯል።  31 ጨዋታዎችን ያከናወነው ቡድኑም በ63 ነጥብ በደረጃው ሦስተኛ እንዲኾን አስችሎታል። አንድ ተስተካካይ ጨዋታ የሚቀራቸው መሪው ማንቸስተር ሲቲ እና ማንቸስተር ዩናይትድ በ81 እና በ65 ነጥብ ከሊቨርፑል በላይ ይገኛሉ። ተመመሳሳይ ተስተካካይ ጨዋታቸውን የሚያከናውኑት ቶትንሀም እና ቸልሲ ደግሞ  በ61 እና 56 ነጥብ አራተኛ እና አምስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።

ምስል imago/Action Plus/D. Blunsden

ላሊጋ

በስፔን ላሊጋ ክሪስቲያኖ ሮናልዶ በአራት ግቦች በተንበሸበሸበት በትናንቱ የሪያል ማድሪድ እና ጂሮና ግጥሚያ ሉቃስ ቫስጌስ እና ጋሬት ቤልም ሁለት ግቦችን ከመረብ አሳርፈዋል። ለጂሮና ክሪስቲያን ስቱዋኒ ሁለት ጁዋንፔ ደግሞ አንድአስቆጥረዋል። በድምሩ ሪያል ማድሪድ 6 ለ3 በኾነ ሰፊ ልዩነት ድል አድርጓል። እንዲያም ኾኖ ሪያል ማድሪድ በሊዮኔል ሜሲ እና ፓኮ ብቸኛ ግቦች አትሌቲኮ ቢልባዎን ትናንት 2 ለ0 ድል የነሳው ባርሴሎና ላይ ግን ለመድረስ ብዙ ይቀረዋል። በላሊጋው ሦስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ሪያል ማድሪድአትሌቲኮ ማድሪድ በ4 እንዲሁም በመሪው ባርሴሎና በ15 ነጥቦች ይበለጣል። 

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ኂሩት መለሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW