ስፖርት፤ መጋቢት 26 ቀን፤ 2008 ዓ.ም.
ሰኞ፣ መጋቢት 26 2008በጀርመኑ ቡንደስ ሊጋ ለረዥም ጊዜ በጉዳት ከውድድር ውጪ የነበረው የባየር ሙይንሽኑ ፍራንክ ሪበሪ በመጀመሪያ ውድድሩ አየር ላይ ወደ ጎን ተንሳፎ ድንቅ ግብ ማስቆጠር ችሏል። አትሌት መሰረት ደፋር በካሊፎርኒያው የ5 ሺህ ሜትር የሩጫ ውድድር አሸናፊ መሆን ችላለች። በሜዳ ቴኒስ ውድድር ሠርቢያዊው ኖቫክ ጄኮቪች በተደጋጋሚ በማሸነፍ ግስጋሴውን እየቀጠለ ነው።
ዩናይትድ ስቴትስ ካሊፎርኒያ ውስጥ በተከናወነው የካርልስባድ የ5 ሺህ ሜትር የሩጫ ውድድር የሁለት ጊዜያት የኦሎምፒክ ባለድሏ መሠረት ደፋር አሸናፊ ሆነች። መሠረት 5 ሺህ ሜትሩን አጠናቃ አንደኛ የወጣችው 15 ደቂቃ ከ02 ሰከንድ በመሮጥ ነው። ኬኒያዊቱ ካሮሊን ኪፕኪሩይ 11 ሰከንድ ዘግይታ በመከተል ሁለተኛ ወጥታለች። የኔዘርላንዷ ሱዛን ኩይጄከን በ15 ደቂቃ ከ28 ሰከንድ በመግባት የሦተኛነቱን ደረጃ አግኝታለች።
በወንዶች ተመሳሳይ የሩጫ ውድድር ደግሞ ኬንያውያኑ አንደኛ እና ሁለተኛ በመሆን ተከታትለው ገብተዋል። ኢትዮጵያዊው ደበሌ ገዝሙ 13 ደቂቃ ከ38 ሰከንድ በመሮጥ ሦስተኛ ለመሆን ችሏል።
በፕሬሚየር ሊጉ በርካታ ቡድኖች 32ኛው ውድድራቸውን አከናውነዋል። ሊቨርፑል እና ኤቨርተን ግን ሁለት ተስተካካይ ጨዋታ ይቀራቸዋል። አንድ አንድ ተስተካካይ ጨዋታ የሚቀራቸው ደግሞ፦ አርሰናል፣ ማንቸስተር ሲቲ፣ ማንቸስተር ዩናይትድ፣ ዌስትሐም ዩናይትድ፣ ቸልሲ፣ ዌስትብሮሚች፣ ዋትፎርድ፣ ክሪስታል ፓላስ፣ ሰንደርላንድ እና ኒውካስል ዩናይትድ ናቸው።
ማንቸስተር ዩናይትድ ኤቨርተንን አንድ ለዜሮ በማሸነፍ ለአውሮጳ ሊግ ለመሳተፍ የሚያበቃውን ደረጃ ለጊዜው ተቆጣጥሯል። በአንድ ነጥብ የሚበልጠው እና 54 ነጥቦችን የሰበሰበው ማንቸስተር ሲቲ በርመስን 4 ለ0 በማደባየት ለሻምፒዮንስ ሊግ ማጣሪያ ለማለፍ የሚያበቃውን የአራተኛነት ደረጃ ይዟል። አርሰናል ዋትፎርድን 4 ለ0 በማንኮታኮት ለሻምፒዮንስ ሊግ በቀጥታ ለማለፍ ሁኔታዎችን አመቻችቷል። በ58 ነጥቡ በደረጃ ሠንጠረዡ ሁለተኛ ከሆነው ቶትንሐም ሆትስፐር ላይ ደረስኩብህ እያለው ነው። በአራት ነጥብ ብቻ ነው የሚበለጠው። ቶትንሐም ሆትስፐር ቅዳሜ እለት ከሊቨርፑል ጋር ባደረገው ግጥሚያ ነጥብ ጥሏል። ሊቨርፑል ለአውሮጳ ሊግ ማጣሪያ የነበረው ተስፋ ባያከትምም የጠበበ ይመስላል። ቸልሲ አስቶን ቪላን 4 ለ0 አንበርክኮ ነጥቡን 44 ማድረስ ችሏል። ሆኖም በአንድ ነጥብ ከሊቨርፑል ዝቅ ብሎ 9ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
መሪው ላይስተር ሲቲ ትናንት ባደረገው ጨዋታ ሳውዝ ሐምፕተንን አንድ ለባዶ አሸንፏል። ቀበሮዎቹ በሚል ስያሜ የሚታወቁት ላይስተር ሲቲዎች ዘንድሮ የዋንጫው ባለቤት ለመሆን የቆረጡ ይመስላሉ። በተጨዋቾቻቸው ጥንካሬ እና ጉጉት ደስተኛ የሆኑት የቡድኑ አሠልጣኝ ክላውዲዮ ራኒዬሪ በተደጋጋሚ ለማሸነፋቸው እምብዛም እዩኝ እዩኝ ሲሉ አልታዩም። ይልቁንስ ለጋዜጠኞች ሲናገሩ፦ «ይኽ የጨዋታ ክፍለ-ጊዜ ለእኛ ሲበዛ ምትሃታዊ ነው። የሚቀጥለው ክፍለ-ጊዜ እንደአሁኑ አይሆንም» ሲሉ ተደምጠዋል። አያይዘውም «በተቻለ መጠን የአቅማችንን ለማድረግ እንጥራለን። አንዳንድ ቡድኖች 3-0, 4-0 ሊያሸንፉ ይችላሉ። እኛ 1-0 ለማሸነፍ ነው የምንታገለው። የራሳችን መንገድ ላይ ነው ማተኮር የሚገባን» ብለዋል። በእርግጥም ላይስተር ሲቲ ከቀሪ ስድስት ጨዋታዎቹ አራቱን ካሸነፈ የፕሬሚየር ሊጉ ዋንጫ ባለቤት ይኾናል።
እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር ከ1888 አንስቶ የፕሬሚየር ሊግን ጨምሮ ለ73 ጊዜያት በእንግሊዝ ከፍተኛ ዲቪዚዮን ተሳታፊ የነበረው ቦልተን ዋንደረርስ ደግሞ አሁን ከሚገኝበት የሁለተኛ ዲቪዚዮን ሻምፒዮንስሺፕ ዝቅ ብሎ ወደሚገኘው ወደ ሦስተኛው ዲቪዚዮን ሊግ ዋን ሊያሽቆለቁል ነው። ቦልተን ዋንደረርስ 26 ነጥብ ይዞ የመጨረሻ 24ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ወራጅ ቃጣና ውስጥ ከሚገኙት ከኤም ኬ ዶንስ እና ከቻርልተን በ11 እና በ9 ነጥብ ርቋል። ቦልተን ዋንደረርስ በደህናው ጊዜ የኤፍ ኤ ካፕ ዋንጫን ለአራት ጊዜያት ወስዷል። ዘንድሮ ቡድኑ ቀን ጥሎት ወደ ሦስተኛ ዲቪዚዮን ሊያሽቆለቁል የመጨረሻ ትንፋሹን እያጣጣረ ነው። ቦልተን ዋንደረርስ በ1888 የእንግሊዝ እግር ኳስ ሊግን ከመሰረቱት 12 ቡድኖችም አንዱ ነበር። ከእዛው ከእንግሊዝ ሳንወጣ የለንደኑ ሐኪም ማርክ ቦናር ለ150 ስፖርተኞች ኃይል ሰጪ መድኃኒት ይሰጡ እንደነበር በድብቅ ካሜራ መጋለጣቸውን የእንግሊዙ (The sunday Times)ጋዜጣ ዘግቧል።
በጀርመን ቡንደስ ሊጋ በደረሰበት የጉልበት አደጋ ባለፈው የውድድር ዘመን በርካታ ጨዋታዎች ላይ መሰለፍ ያልቻለው የባየር ሙይንሽኑ የክንፍ ተጨዋች ፍራንክ ሪቤሪ ትናንት ዳግም ወደ ሜዳ ሲመለስ አስደናቂ ግብ ማስቆጠር ችሏል። ጎትሰ ወደ ግብ አክርሮ የመታትን ኳስ የአይንትራኅት ፍራንክፉርቱ ግብ ጠባቂ ገጭቶ ሲመልስ ፍራን ሪቤሪ ወደ ጎን አየር ላይ ተንሳፎ በመምታት ከመረብ አሳርፏታል። በዚህች ብቸኛ ግብ መሪው ባየር ሙይንሽን ነጥቡን 72 አድርሷል።
አይንትራኅት ፍራንክፉርት ከሐኖቨር ጋር ወራጅ ቃጣናው ውስጥ ይገኛል። ቬርደር ብሬመንን 3 ለ2 ያሸነፈው ቦሩስያ ዶርትሙንድ በደረጃ ሰንጠረዡ 67 ነጥብ ይዞ ሁለተኛ ነው። ትናንት በቦሩስያ ሞይንሽን ግላድባኅ 5 ለ0 ድባቅ የተመታው ሔርታ ቤርሊን በ48 ነጥቡ ይዞ ሦስተኛ ደረጃ ይዟል።
በስፔን ላሊጋ መሪው ባርሴሎና ቅዳሜ እለት በሪያል ማድሪድ 2 ለ1 ተሸንፏል። ለሪያል ማድሪድ ካሪም ቤንዜማ እና ክሪስቲያኖ ሮናልዶ ግብ አስቆጥረዋል። የባርሴሎና ብቸኛ ግብ የተቆጠረችው በጄራርድ ፒኬ ነው። አትሌቲኮ ማድሪድ 70 ነጥብ አለው። ሪያል ማድሪድ ነጥቡን 69 አድርሷል። በደረጃ ዘንጠረዡ ግርጌ የሚገኙት ሌቫንቴ እና ስፖርቲን ጂዮን ዛሬ ይጋጠማሉ። 19ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ስፖርቲን ጂዮን በወራጅ ቃጣና ውስጥ በሚገኘው በጌታፌ የሚበለጠው በአንድ ነጥብ ነው። ሌቫንቴ በ24 ነጥቡ የመጨረሻው 20ኛ ደረጃ ላይ ተንጠልጥሏል።
በፎርሙላ አንድ የመኪና ሽቅድምድም የማርሴዲስ አሽከርካሪው ኒኮ ሮዝበርግ ትናት ለድል በቅቷል። ሌላኛው የማርሴዲስ አሽከርካሪ ሌዊስ ሐሚልተን አጀማመሩ ላይ በፈጸመው ስህተት ሦስተኛ ሆኗል። በፌራሬ የተወዳደረው ኪሚ ሬይከነን ሁለተኛ ወጥቷል።
በሚያሚው የሜዳ ቴኒስ ውድድር ሠርቢያዊው ኖቫክ ጄኮቪች ማሸነፍ ችሏል። ማሸነፍ ብቻም አይደል በሜዳ ቴኒስ ከዓለማችን ከፍተኛ ገንዘብ በመሰብሰብም ክብር ወሰን መስበር ችሏል። ኖቫክ ጄኮቪች እስካሁን በማሸነፍ የተሸለመው ወደ 100 ሚሊዮን ዶላር ከፍ አድርጎታል።
አርጀንቲናዊው የኳስ ጥበበኛ ሊዮኔል ሜሲን ጨምሮ 20 ምርጥ የዓለማችን እግር ኳስ ተጨዋቾች በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ወደ ውጭ ሀገር በሕገ-ወጥ መንገድ ማሸሻቸውን የፓናማ ሠነድ የተሰኘው ያፈተለከ መረጃ አጋለጠ። 11 ሚሊዮን የሚጠጉ መረጃዎችን ያቀፈው ሠነድ ከአውሮጳ እግር ኳስ ማኅበራት ኅብረት ኃላፊነት በሙስና ቅሌት የታገደውን ሚሼል ፕላቲኒን እና የሊዮኔል ሜሲ አባትንም አካቷል።
በሥልጣን ላይ የሚገኙ እና የቀድሞ ባለሥልጣናት የነበሩ 12 የዓለም መሪዎች እና 128 ታዋቂ ፖለቲከኞች፤ እንዲሁም ባለሥልጣናት ይገኙበታል ተብሏል። ከዓለም መሪዎቹ መካከል የጁዶ ስፖርት እንደሚያዘወትሩ የሚነገርላቸው የሩስያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲንም ሠነዱ ውስጥ ሰፍረዋል። የፓናማ ሠነድ ያፈተለከው እምብዛም ዕውቅና ከሌለው እና ጠንካራ ከሆነው፤ መቀመጫውን ፓናማ ካደረገው ሞሳክ ፎኔስካ ከተሰኘው የሕግ አገልግሎት ሰጪ ድርጅት ነው።
ማንተጋፍቶት ስለሺ
አዜብ ታደሰ