ስፖርት፤ ሚያዝያ 16 ቀን፣ 2009 ዓ.ም.
ሰኞ፣ ሚያዝያ 16 2009የማራቶን ሩጫ ውድድሮች በሳምንቱ ማሳረጊያ በተለያዩ የአውሮጳ ሃገራት ተከናውነዋል። የለንደኑ ማራቶን ግን ከሁሉም ጎልቶ ወጥቷል። በተለይ በኦሎምፒክ ውድድሮች የሦስት ወርቅ ሜዳሊያ ባለድሉ ቀነኒሳ በቀለ እና በሪዮ ኦሎምፒክ ሁለተኛ ሲወጣ እጆቹን ከፍ አድርጎ በማጣመር የመንግሥት ተቃውሞ ያደረገው ፈይሳ ሊሌሳ ተወዳዳሪ መኾናቸው የበርካቶችን ቀልብ ስቦ ነበር። አርጀንቲናዊው የኳስ ጥበበኛ ሊዮኔል ሜሲ ለባርሴሎና 500ኛ ግቡን ዋነኛ ተፎካካሪው ሪያል ማድሪድ ላይ አስቆጥሯል። ዘንድሮ በፕሬሚየር ሊጉ ያልተሳካላቸው የአርሰናል አሰልጣኝ አርሰን ቬንገር ማንቸስተር ሲቲን ድል አድርገው ለኤፍ ኤ ካፕ ፍጻሜ ደርሰዋል። በቡንደስ ሊጋው መሪው ባየር ሙይንሽን ነጥብ ጥሏል፤ እንዲያ ምኾኖ ተከታዩ ላይፕትሲሽን በስምንት ነጥብ ርቆ ይገኛል።
ትናንት በለንደን ከተማ በተከናወነው የማራቶን ሩጫ ውድድር ኬንያውያን አትሌቶች በወንድም በሴትም ድል ተቀዳጅተዋል። በውድድሩ ላይ ከሚገኙ አትሌቶች መካከከል በተለይ በወንድ ተፎካካሪዎች ዘንድ አትሌት ቀነኒሳ በቀለ እና ፈይሳ ሊሌሳ የበርካታ መገናኛ ብዙኃንን ትኩረት ስበው ቆይተው ነበር።
በውድድሩ ፍጻሜ አትሌት ቀነኒሳ በቀለ በኬንያዊው አትሌት ዳንኤል ዋንጂሩ ለጥቂት ተቀድሞ ሁለተኛ ወጥቷል። ብርቱ ተፎካካሪ ይኾናል ተብሎ ግምት የተሰጠው ሌላኛው ኢትዮጵያዊ አትሌት ፈይሳ ሊሌሳ በ12ኛነት አጠናቋል።
ፈይሳ ሊሌሳ በሪዮ ኦሎምፒክ ውድድር ወቅት ሁለት እጆቹን ከፍ አድርጎ በማጣመር መንግሥት ላይ ተቃውሞ ማሰማቱ እና ቀነኒሳ በቀለ ያን በተመለከተ በእንግሊዝኛ ተጠይቆ የሰጠው ምላሽ በዩትዩብ ከተለቀቀ በኋላ አነጋጋሪ ኾኖ ቆይቷል። አትሌት ፈይሳ ሊሌሳ በሪዮ ኦሎምፒክ ወቅት እንዳደረገው ሁሉ ትናንትም ሁለት እጆቹን ከፍ አድርጎ በማጣመር ተቃውሞን አሳይቷል።
ከኬንያዊው አትሌት በ9 ሰከንዶች ተበልጦ ሁለተኛ የወጣው አትሌት ቀነኒሳ በቀለ በውጤቱ ደስተኛ አለመኾኑን ገልጧል። «ሁለተኛ መውጣት ያናድዳል። ጡንቻዬ ላይ እና ቀኝ ባቴ ላይ ኅመም ተሰምቶኛል። የአሯሯጥ ዘዬዬንም መቀየር ነበረብኝ» ሲል ከውድድሩ በኋላ ለጋዜጠኞች ተናግሯል። ቀነኒሳ ወደ ውድድሩ ሲገባ በዴኒስ ኬሚቶ የተያዘውን የ2:02.57 የዓለም ክብረ-ወሰን ለመስበር በማለም ነበር። ኬንያዊው ዳንኤል ዋንጂሩ የለንደኑ ማራቶንን በድል ያጠናቀቀው 2 ሰዓት ከ5 ደቂቃ ከ48 ሰከንድ በመሮጥ ነው።
በሴቶች ውድድር በብዙዎች ዘንድ ዋነኛ ተፎካካሪ ይኾናሉ ተብለው የተጠበቁት ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ እና ኬኒያዊቷ ማሪ ኪታኒ እንደተባለውም ተከታትለው ገብተዋል። አትሌት ጥሩነሽ በውድድሩ መገባደጃ አካባቢ እጇን ሆዷ ላይ ስታስደግፍ፤ እና ፍጥነቷን በመቀነስ ሊያስመልሳት ሲተናነቃት ታይቷል። ማሪ ኪታኒ አንደኛ የወጣችው የሴቶች ብቻ የዓለም ክብረ-ወሰንን ጭምር በመስበር ነበር። ሮጣ የገባችውም 2 ሰዓት ከ17 ደቂቃ ከ1 ሰከንድ ነው፡፡ ጥሩነሽ ዲባባ ከኬኒያዊቷ በሃምሳ ስድስት ሰከንድ ዘግይታ ሁለተኛ ወጥታለች። ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት አሰለፈች መርጊያ በሦስተኛነት ስትጨርስ አንደኛ ከወጣችው ኬኒያዊት 6 ደቂቃ ከ7 ሰከንድ ዘግይታ ነበር። ትግስት ቱፋ ስምንተኛ ሆናለች፡፡ የለንደን ማራቶን ያለፈው ዓመት ውድድር አሸናፊ ኬኒያዊቷ ጄሚማ ሱምጎንግ አበረታች ንጥረ ነገር ደሟ ውስጥ ተገኝቷል በመባሉ በዘንድሮው ውድድር ተሳትፋ የዓምና ድሏን ለማስጠበቅ አልቻለችም ተብሏል።
በለንደኑ የማራቶን ሩጫ ኢትዮጵያውያኑ በኬንያውያን ቢበለጡም በጀርመን ሀምቡርግ ትናንት በተካሄደ የማራቶን ውድድር ግን ጸጋዬ መኮንን አሸናፊ ኾኗል። ጸጋዬ የዓለም ክብረ-ወሰንን ባለቤቱን ዩጋንዳዊ ጥሎ በመግባት ነበር ለድል የበቃው፡፡ ጸጋዬ ውድድሩን በአንደኛነት ለማጠናቀቅ የፈጀበት ጊዜ 2 ሰዓት ከ7 ደቂቃ ከ26 ሰከንድ ነው። ድል የነሳውም በኦሎምፒክ መድረክ አሸናፊ የነበረውን ስቴፈን ኪፕሮች ነው፡፡ በሀምቡርግ ማራቶን የሴቶች ፉክክር ፖርቹጋላዊቷ ጄሲካ አውግስቶ ድል ቀንቷታል። ኢትዮጵያዊቷ መገርቱ ኢፋ ከአራት ደቂቃ በኋላ ተከትላት በመግባት ሁለተኛ ወጥታለች፡፡ በኦስትሪያ ቬይና በተደረገ የማራቶን ውድድርም ኬንያውያት አትሌቶች አንደኛ እና ሁለተኛ በመውጣት ድል ተቀዳጅተዋል። ኢትዮጵያዊቷ ሮዛ ደረጄ እና ሹኮ ጌኔሞ የሦስተኛ እና አራተኛ ደረጀ አግኝታለች፡፡
እግር ኳስ
በፕሬሚየር ሊግ ተደጋጋሚ ሽንፈት ያስተናገደው አርሰናል በኤፍ ኤ ካፕ አሰልጣኙ አርሰን ቬንገርን ለመካስ ግስጋሴ ላይ ነው። በፕሬሚየር ሊጉ አራተኛ ደረጃ ላይ ሰፍሮ በሰባት ነጥብ የሚርቀው ማንቸስተር ሲቲን አርሰናል ትናንት በኤፍ ኤ ካፕ የግማሽ ፍጻሜ ፍልሚያ ድል ያደረገው 2 ለ 1 ነበር። አርሰናል ለኤፍ ኤ ካፕ ፍጻሜ የሚፋለመው የፕሬሚየር ሊጉ መሪ ከኾነው ቸልሲ ጋር ነው። ውድድሩ የሚከናወነውም ከአንድ ወር ከሦስት ቀን በኋላ ነው።
በፕሬሚየር ሊጉ ሰባተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው አርሰናል በአሰልጣኝ አርሰን ቬንገር ዘመን ለመጀመሪያ ጊዜ ከሻምፒዮንስ ሊግ ውድድር ሊወጣ ይችል ይኾናል ተብሏlል። የአርሰናል አማካይ ተጨዋች አሮን ራምሴይ ግን ቡድናቸው ከኤፍ ኤ ካፕ ዋንጫ ባሻገርም ለሻምፒዮንስ ሊግ ማጣሪያ የማለፍ ዕድሉ እንዳላከተመ ተናግሯል። «ሰባት ጨዋታዎች ይቀሩናል፤ ስለዚህ የመጨረሻዎቹ አራቱ ቡድኖች ውስጥ ለመግባት እንሞክራለን» ብሏል። ከቡድኑ እና ከደጋፊዎቻቸው ጫና የበረታባቸው አሰልጣኝ አርሰን ቬንገርን በተመለከተም፦ «በዚህ የጨዋታ ዘመን አሳፍረነዋል፤ የኤፍ ኤ ካፑን ዋንጫ ለእሱም ለእኛም ስንል ማሸነፍ እንፈልጋለን» ብሏል።
በፕሬሚየር ሊጉ መሪው ቸልሲ በ75 ነጥብ ይመራል። ቶትንሀም በ71 ይከተላል። ሊቨርፑል 66 ነጥብ ይዞ በሦስተኛ ደረጃ ላይ ሰፍሯል። ማንቸስተር ሲቲ በ64 ነጥብ ማንቸስተር ዩናይትድ ደግሞ በ63 አራተኛ እና አምስተኛ ኾነው ይከታተላሉ። ከሊቨርፑል በስተቀር አራቱም ሁለት ተስተካካይ ጨዋታዎች ይቀሯቸዋል።
የቸልሲው አማካኝ ንጎሎ ካንቴ የእንግሊዝ እግር ኳስ ማኅበር የዓመቱ ምርጥ ተጨዋች ሽልማትን አግኝቷል። ኤደን ሐዛርድ፤ ሀሪ ኬን፤ ሮሜሉ ሉካኩ፤ ዝላታን ኢብራሂሞቪች እና አሌክሲስ ሳንቼዝ ለሽልማት ውድድሩ በእጩነት ቀርበው ነበር። ሁሉንም ልቆ ዘንድሮ ተሸላሚ የኾነው ንጎሎ ካንቴ ነው። የ27 ዓመቱ ንጎሎ ካንቴ ወደ ቸልሲ ቡድን የመጣው ካለፈው የውድድር ዘመን አሸናፊ ላይስተር ሲቲ ነው።
በጀርመን ቡንደስ ሊጋ ከትናንት በስትያ ከማይንትስ ጋር ሁለት እኩል በመለያየት ነጥብ የተጋራው ባየር ሙይንሽን በ70 ነጥብ እየመራ ይገኛል። ትናንት ከሻልከ ጋር አንድ እኩል አቻ የተለያየው ላይፕትሲሽ 62 ነጥብ ይዞ በደረጃው 2ኛ ነው። ዶርትሙንድ ቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅን 3 ለ2 አሸንፏል፤ በ56 ነጥብ ሦስኛ ኾኖ ይከተላል።
በስፔን ላሊጋ ባርሴሎና ሪያል ማድሪድን 3 ለ2 ድል ነስቷል። ሪያል ማድሪድ በባርሴሎና 2 ለ1 እየተመራ ባለበት ኹኔታ ሠርጂዮ ራሞስ በቀይ ከሜዳ መሰናበቱ ቡድኑን እንደጎዳው ሠርጂዮ ራሞስ ተናግሯል። ባርሳ 3 ለ2 ለማሸነፉ የእኔ መውጣት «ወሳኝ» ነበር ብሏል። ሠርጂዮ ራሞስ በ77ኛው ደቂቃ ላይ ከሜዳ የተሰናበተው ሊዮኔል ሜሲ ላይ አደገኛ ታክል በመግባቱ ነበር።
በእርግጥ ሜሲ በሁለት እግሮቹ ዘሎ ሊደርስበት ይችል ከነበረው ከባድ ጉዳት አምልጧል። ሠርጂዮ ራሞስ በቀይ መሰናበቱን በመቃወም ለጥቂት ጊዜ ከዳኛው ጋር በመጨቃጨቅ ከሜዳው ወጥቷል።
የባርሴሎና ተከላካይ ጌራርድ ፒኬንም ለመተናኮል ሞክሯል። በእግር ኳስ ዘመኑ ለ22ኛ ጊዜ ትንንት ከሜዳ የተሰናበተው ሠርጂዮ ራሞስ የዳኛውን ውሳኔ «እጅግ የበዛ» ብሎታል። «ልጎዳው አስቤ አልነበረም፤። እኔ ኳስ እንደሚገባኝ ያ ቢጫ እንጂ ቀይ የሚያሰጥ አልነበረም» ሲልም ሊዮኔል ሜሲ ላይ አስቦበት እና ዘግየት ብሎ ምንም አይነት የሰውነት ንክኪ እንዳይኖር ተጠንቅቆ መንሸራተቱን ተናግሯል። በደረጃ ሠንጠረዡ ባርሴሎና በግብ ክፍያ ሪያል ማድሪድን በልጦ አንደኛ ኾኗል።
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ነጋሽ መሐመድ