1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ስፖርት፤ ሚያዝያ 8 ቀን፣ 2010 ዓ.ም 

ሰኞ፣ ሚያዝያ 8 2010

እድሜያቸው ከ17 ዓመት በታች ተጨዋቾች በሚሳተፉበት የአፍሪቃ እግር ኳስ ውድድር የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ድል መሰረዙ ተዘግቧል። በ47ኛው የኢትዮጵያ አትሌቶች የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮን 1237 ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ይሳተፋሉ። የሊቨርፑል ቡድን አጥቂ ግብጻዊው ሞሐመድ ሣላኅ ከሻምፒዮንስ ሊግ ውጪ የሚታየኝ ነገር የለም ብሏል።

Brasiliens' Ronaldinho Gaucho
ምስል picture-alliance/V.R.Caivano

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

This browser does not support the audio element.

ነገ በሚጀምረው 47ኛው የኢትዮጵያ አትሌቶች የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮን 1237 ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ይሳተፋሉ። እድሜያቸው ከ17 ዓመት በታች የኾኑ ተጨዋቾች በሚሳተፉበት የአፍሪቃ እግር ኳስ ውድድር ደግሞየኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ድል መሰረዙ ተዘግቧል። በሻምፒዮንስ ሊግ ግማሽ ፍጻሜ በሚቀጥለው ሳምንት ማክሰኞ ሮማን የሚገጥመው ሊቨርፑል ቡድን አጥቂ ግብጻዊው ሞሐመድ ሣላኅ ሻምፒዮንስ ሊግ ውጪ የሚታየን ነገር የለ ም ብሏል። ሣላኅ በፕሬሚየር ሊጉ በኮከብ ግብ አግቢነት እየመራ ነው። የሞሐመድ ሣላኅ ቡድን ከሻምፒዮንስ ሊግ ያሰናበተው ማንቸስተር ሲቲ በፕሬሚየር ሊጉ የዋንጫ ባለቤት መኾኑን አረጋግጧል። በጣሊያን ሴሪኣ ጁቬንቱስ ዋንጫውን ለመጨበጥ ጫፍ ደርሷል።

አትሌቲክስ

47ኛው የኢትዮጵያ አትሌቶች የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮን ከነገ ጀምሮ እስከ ፊታችን እሁድ ድረስ ሊከናወን ቀጠሮ ተይዞለታል። ይህንኑም የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በድረ-ገጹ ዐስታውቋል። በውድድሩ ከሚሳተፉ ታዋቂ አትሌቶች መካከል፦ ኢማና መርጊያ፣ ሙክታር እድሪስ፤ አማን ወጤ፣ ሰለሞን ባረጋ፣  ጌታነህ ሞላ፣ ሩቲ አጋ፣ ጉዳፍ ጸጋዬ፣ ጫልቱ ሹሚ እና ሌሎችም ይገኙበታል። 

ምስል picture-alliance/AP/R. Vieira

1237 ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በሚሳተፉበት በዚህ ውድድር 500ዎቹ ሴት አትሌቶች ናቸው። የዘንድሮ ተወዳዳሪዎች ብዛት ከዓምናው በ28 ዝቅ ብሏል። ለውድድሩ ከ2,1 ሚሊዮን በላይ ብር በጀት መመደቡም ዐርብ እለት ውድድሩን አስመልክቶ በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ መገለጡን የፌዴሬሽኑ የፌስቡክ ገጽ ላይ ሰፍሯል። 

እግር ኳስ

እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2020 ኢትዮጵያ ለምታዘጋጀው ቻን የአፍሪቃ እግር ኳስ ዋንጫ ቅድመ-ዝግጅቶችን ለመመልከት የካፍ ገምጋሚዎች ኢትዮጵያ መግባታቸው ተዘግቧል። ገምጋሚዎቹ ኢትዮጵያ ውድድሮቹ ይካሄዱባቸዋል ያለቻቸውን ስታዲየሞች እየተዘዋወሩ ይገመግማሉ። ስታዲየሞቹ የአደይ አበባ፣ የባሕር ዳር፣ የመቀሌ፣ የአዋሳ፣ እና የድሬዳዋ ናቸው።   

በሌላ ዜና ዕድሜያቸው ከ17 ዓመት በታች የኾኑ ተጨዋቾች በሚሳተፉበት ውድድር ተሳታፊ የኾነው ቀይ ቀበሮዎቹ በመባል የሚጠራው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ውጤት መሰረዙ ተዘግቧል። የኢትዮጵያ ቡድን የሶማሊያ ቡድንን በትናንትናው ዕለት 3 ለ 0 አሸንፎ ነበር። ኾኖም ቡድኑ ዕድሜያቸው ከ17 ዓመት በላይ የኾኑ ሦስት ተጨዋቾችን አሰልፏል በመባሉ ውጤቱ በቅጣት ተገልብጦ ሶማሊያ 3 ለ0 እንዳሸነፈች መቆጠሩን  የሩዋንዳው ኒው ታይምስ በትዊተር ገጹ ይፋ አድርጓል።

የኢትዮጵያ ቡድን የ5 ሺህ ዶላር ቅጣት እንደተላለፈበትም ይኸው ዘገባ ይገልጣል። ይኽን አስመልክቶ ለማረጋገጥ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ጁነዲን ባሻ ጋር ከሁለት ሰአት በፊት ደውለን ነበር። ስታዲየም እየገቡ የነበረ በመኾኑ አመቺ ባይኾንም በአጭሩ ቀጣዩን ለዶይቸ ቬለ ተናግረዋል። «እኔ ያለሁት ሀገር ውስጥ ነው። እዛ እየተነጋገሩ ነው፤ ቅድም ሁሉ ተነጋግረን በኔ በኩል የተነገረኝይኼ ነገር መጣ እንደገና ውይይት ላይ ናቸው። ውሳኔ ሊሰጥ ነው ተብሎ ነው የተደወለልኝ። ምንም የወጣ ነገር የለም። »

ምስል picture-alliance/blickwinkel/McPhoto

በውድድሩ እድሜያቸው ከ17 ዓመት በላይ የኾኑ 12 ተጨዋቾችን አሰልፏል የተባለው የዛንዚባር ቡድን በሴካፋ ከውድድሩ ተባሯል። የኢትዮጵያ ቡድን ምን እንደሚጠብቀው ዐልታወቀም። 

የሚታወቀው ነገር ቡሩንዲ ባዘጋጀችው የምስራቅና መካከለኛው አፍሪቃ የእግር ኳስ ውድድር ለመሳተፍ ወደ መዲናዪቱ ቡጅንቡራ ያቀናው የኢትዮጵያ ቡድን በመቀጠል በምድቡ ከሚገኘው ከጎረቤት ኬንያ ቡድን ጋር ለመጋጠም ለነገ ቀጠሮ እንደተያዘለት ነው።  

በመክፈቻ ውድድሩ የኬንያ ቡድን አዘጋጇ ቡሩንዲን ሙዪንጋ ስታዲየም ውስጥ በደጋፊዎቿ ፊት 4 ለ0 በማደባየት ጥንካሬውን አሳይቷል። የኬንያ ቡድን የመጀመሪያ ግቡን በ13ኛው ደቂቃ ከመረብ ያሳረፈው በክሪስቶፈር ራይላ ነው። ኒኮላስ ኦሞንዲም አንድ አስቆጥሯል። ኢሳያህ አብዋል በበኩሉ በ54ኛው እና 79ኛው ደቂቃ ላይ ሁለት ግቦችን ከመረብ ማሳረፍ ችሏል። ቅዳሜ፤ ሚያዝያ 6 ቀን የጀመረው ውድድር በሁለተኛ ሳምንቱ  ዐርብ ሚያዚያ 20 ይጠናቀቃል።

የብራዚሉ ኮከብ ሮናልዲንሆ ትናንት በአዲስ አበባ ስታዲየም በአድናቂዎቹ ፊት በመገኘት የኢትዮፕያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን መለያን በመልበስ ታዳሚዎቹን አስደስቷል። ከታዳሚዎቹ ያገኘነው ድጋፍም በትዊተር ገጹ አስደማሚ ብሎታል።  ሮናልዲንሆ የአውሮጳ ሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫ ይዞ ኢትዮጵያ የተገኘው ለ2 ቀናት ነበር። 

ፕሬሚየር ሊግ

በፕሬሚየር ሊጉ ኮከብ ግብ አግቢው የሊቨርፑሉ አጥቂ ሞሐመድ ሣላህ ከምንም በላይ ለሻምፒዮንስ ሊግ ቅድሚያ እንደሚሰጥ ተናገረ። ሞሐመድ ሣላህ ሊቨርፑል ቅዳሜ ዕለት በርመስን 3 ለ0 ባሸነፈበት ጨዋታ ያስቆጠራት ግብ ዘንድሮ በፕሬሚየር ሊጉ 30ኛ ግቡ ኾና ተመዝግባለታለች። ሣላህም ወርቃማውን ጫማ ለማጥለቅ ኮከክብ ግብ አግቢነቱን በአምስት ግቦች ልዩነት እንዲመራ አስችሎታል ።  

ምስል Reuters/D. Staples

ቅዳሜ ዕለት በማንቸስተር ሲቲ 3 ለ1 የተሸነፈው ቶትንሀም ቡድን አጥቂ ሔሪ ኬን በ25 ከመረብ ያረፉ ግቦች ሞሐመድ ሣላህን ይከተላል። የማንቸስተር ሲቲው ሠርጂዮ አጉዌሮ 21 ግቦች አሉት፤ ሦስተኛ ነው። ማንቸስተር ሲቲ የዘንድሮውን ዋንጫ ከወዲሁ የሚወስድ መኾኑ ተረጋግጧል። በደረጃ ሠንጠረዡ 6ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው አርሰናል ትናንት በኒውካስል 2 ለ1 ተሸንፏል። ከምንም በላይ በርካቶችን ያስደመመው ግን በደረጃ ሠንጠረዡ 2ኛ ላይ የሚገኘው ማንቸስተር ዩናይትድ 20ኛ የመጨረሻ ደረጃ ላይ በሚገኘው ዌስት ብሮሚች ትናንት 1 ለ0 መሸነፉ ነበር። በዚህም ውጤት አንድ ተስተካካይ ጨዋታ እየቀረው ከሊቨርፑል በ1 ነጥብ በመብለጥ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

ሻምፒዮንስ ሊግ 

ማንቸስተር ዩናይትድ ከነገ በስተያ ተስተካካይ ጨዋታውን የሚያከናውነው ሊቨርፑል 3 ለ0 ድል ካደረገው በርመስ ጋር ነው። ቶትንሀምም ታች 13ኛ ከሚገኘው ብሪንግቶን ጋር ነገ ተስተካካይ ጨዋታውን ያከናውናል። 67 ነጥብ ይዞ በሊቨርፑል በ3 ነጥብ ይበለጣል። ቶትንሀም የነገው ጨዋታ አሸንፎ በነጥብ ቢስተካከልም የሊቨርፑል የግብ ክፍያ ላይ ግን መድረስ አይችልም። 

ላሊጋ

ባርሴሎናን ባልተጠበቀ መልኩ 4 ለ1 ያንኮታኮተው ሮማ የነገ ሳምንት ማክሰኞ የሚፋለመው በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ዘንድሮ ዋንጫ ማንሳቱ የተረጋገጠለት ቡድንን ካሰናበተው ሊቨርፑል ጋር ነው። ሊቨርፑል በሻምፒዮንስ ሊግ ሩብ ፍጻሜ የደርሶ መልስ ድምር ውጤት ማንቸስተር ሲቲን 5 ለ1 በኾነ ድምር አሸንፎ ነው ለግማሽ ፍጻሜ የደረሰው። ከሮማ እና ከሊቨርፑል ግጥሚያ በበነጋታው ረቡዕ የጀርመኑ ኃያል ባየር ሙይንሽን ሪያል ማድሪድን ይገጥማል። 

በቡንደስሊጋው መሪው ባየር ሙይንሽን እንደለመደው በሰፋ ልዩነት ተጋጣሚውን አደባይቷል። ቅዳሜ ዕለት በባይር ሙይንሽን የ5 ለ1 ከባድ ቅጣት በተራው የቀመሰው ቦሩስያ ሞይንሽን ግላድባኅን ነው። ዘንድሮም የቡንደስሊጋውን ዋንጫን እንደሚያነሳ ከወዲሁ ያረጋገጠው ባየር ሙይንሽን ፕሬዚዳንት ዑሊ ሆይነፍ በትናንት ወዲያው ግጥሚያ እንደተዝናኑ ተናግረዋል።

ምስል picture-alliance/dpa/M. Balk

«እስከ መጀመሪያዎቹ ዐሥር ደቂቃዎች ድረስ እጅግ በጣም ደስ የሚል ነበር። በቃ እንደው ዝም ብለህ የምትዝናናበት። ለእኛ መቼም ብዙም ሳንጨነናነቅ መጫወታችን ደስ የሚል ነበር። አጨናናቂው ግጥሚያ ማክሰኞ ይጠብቀናል»

ባየር ሙይንሽን ከነገ በስትያ በጀርመን እግር ኳስ ማኅበር ዋንጫ ግማሽ ፍጻሜ ግጥሚያ ከባየር ሌቨርኩሰን ጋር ተቀጣጥሯል። በበነጋታው ሻልከ አይንትራኅት ፍራንክፉርትን ይገጥማል። ባየር ሙይንሽን በሚቀጥለው ሣምንት በሻምፒዮንስ ሊጉ ግማሽ ፍጻሜ ከሪያል ማድሪድ ጋር ይፋለማል።  

ሪያል ማድሪድ በስፔን ላሊጋ ትናንት ማላጋን 2 ለ  1 አሸንፏል። በተመሳሳይ ውጤት መሪው ባርሴሎና ቅዳሜ ዕለት ቫሌንሺያን 2 ለ1 ድል አድርጓል። በ11 ነጥብ ርቀት ባርሴሎናን የሚከተለው አትሌቲኮ ማድሪድ ሌቫንቴን ትናንት 3 ለ0 ድል አድርጓል። 71 ነጥብ የሰበሰበው አትሌቲኮ ማድሪድ ሪያል ማድሪድን በ4 ነጥብ ይበልጠዋል። 

ምስል Getty Images/Bongarts/S. Widmann

ሴሪኣ

በጣሊያን ሴሪኣ ደግሞ ትናንት ሣምፕዶሪያን 3 ለ0 የሸኘው ጁቬንቱስ የዘንድሮውን ዋንጫ በእጁ ለማስገባት ጫፍ ደርሷል። በሴሪኣው ከጁቬንቱስ በ6 ዝቅ ያለ 78 ነጥብ የያዘው ናፖሊ ከሚላን ጋር ዜሮ ለዜሮ መውጣቱ ነው ለጁቬንቱስ ዋንጫ የማግኘት እድሉን ያሰፋው።  

ጁቬንቱስ የፊታችን ረቡዕ ክሮቶኔን ካሸነፈ እና ናፖሊ በሜዳው በኡዲኒዜ ከተሸነፈ የእሁዱ ጨዋታ ለጁቬንቱስ ዋንጫ የማግኘት ግስጋሴ ማሳረጊያ ይኾናል። 27 ነጥብ ብቻ ይዞ በሴሪኣው 18 ደረጃ ላይ ወራጅ ቃጣና ጫፍ ላይ የሚገኘው ክሮቶኔ ልምድ ላካበተው ጁቬንቱስ የሚከብደው አይኾንም። 84 ነጥብ የሰበሰበው ጁቬንቱስ እሁድ ከተከታዩ ናፖሊ ጋር በሚያደርገው ግጥሚያ የዋንጫ ባለድልነቱ ይለይለታል። በዚህ ግጥሚያ ጁቬንቱስ ድል ከቀናው በሴሪኣው በታሪኩ 34ኛ የሚኾነውን ዋንጫ ይጨብጣል ማለት ነው። 

ማተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሐመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW