1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ስፖርት፤ ሰኔ 17 ቀን፣ 2011 ዓ.ም

ሰኞ፣ ሰኔ 17 2011

በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች የእግር ኳስ ግጥሚያዎች እየተከናወኑ ነው። ግብፅ የአፍሪቃ ዋንጫን በማስተናገድ ላይ ትገኛለች። እድሜያቸው ከ21 ዓመት በታች የአውሮጳ እግር ኳስ ተጨዋቾች ሳን ማሪኖ እና ጣሊያን ከትመዋል።

Frauenfußball-WM - England - Kamerun
ምስል picture-alliance/empics/J. Walton

በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች የእግር ኳስ ግጥሚያዎች እየተከናወኑ ነው። ግብፅ የአፍሪቃ ዋንጫን በማስተናገድ ላይ ትገኛለች። እድሜያቸው ከ21 ዓመት በታች የአውሮጳ እግር ኳስ ተጨዋቾች ሳን ማሪኖ እና ጣሊያን ከትመዋል። በሴቶች የዓለም ዋንጫ ግጥሚያ ጀርመን እና ፈረንሳይ ወደ ሩብ ፍጻሜው ማለፋቸውን አረጋግጠዋል። የሴቶች የዓለም ዋንጫ እግር ኳስ ውድድር፤ የአውሮጳ ከ21 ዓመት በታች የእግር ኳስ ግጥሚያን እንዳስሳለን።

እምብዛም ደጋፊዎች በስታዲየም ያልታዩበት የአፍሪቃ እግር ኳስ ዋንጫ ዐርብ እለት በአስተናጋጇ ግብጽ እና ዚምባብዌ ውድድር ተጀምሯል። በእርግጥ መዲናይቱ ካይሮ ዓለም አቀፍ ስታዲየም ውስጥ ግብጽ ዚምባብዌን 1 ለ0 ባሸነፈችበት የመክፈቻ ውድድር ከ75 ሺህ በላይ ታዳሚ ተገኝቷል።  በበነጋታው ግን በዛው በተመሳሳይ ስታዲየም ውስጥ የዲሞክራሲዊ ኮንጎ ሪፐብሊክ እና የኡጋንዳ ግጥሚያ ሲከናወን ተመልካች ባዶ ነበር ማለት ይቻላል። በእለቱ ኡጋንዳ ተጋጣሚዋን 2 ለ0 አሸንፋለች። ናይጀሪያ ቡሩንዲን 1 ለ0 በረታችበት የቅዳሜ ሌላኛው ግጥሚያም ቢኾን ስታዲየሙ ውስጥ ለመታደም የተገኙ ተመልካቾች እጅግ ጥቂት ነበሩ።

ምስል Reuters/S. Salem

በትናንትና ግጥሚያዎች፦ሞሮኮ ናሚቢያን 1 ለ0፤ ሴኔጋል ታንዛኒያን እንዲሁም አልጄሪያ ኬንያን 2 ለ0 አሸንፈዋል። ውድድሩ ቀጥሎ የዛሬ ተጋጣሚዎች ኮትዲቯር ከደቡብ አፍሪቃ፤ ቱኒዝያ ከአንጎላ፤ ማሊ ከሞሪታንያ ናቸው። በነገው እለት ጋና ከቤኒን እንዲሁም ካሜሩን ከጊኒ ቢሳዎ ይፋለማሉ።

በነገራችን ላይ የካሜሩን ብሔራዊ ቡድን ሴት እግር ኳስ ተጨዋቾች በዓለም ዋንጫ ሩብ ፍጻሜ ለማለፍ ባደረጉት ግጥሚያ ትናንት በእንግሊዝ ቡድን 3 ለ0 ሽንፈት ገጥሟቸዋል።   ሁለተኛዋ ግብ ስትቆጠር ግን ብዙዎችን ያስደመመ ክስተት ተፈጠረ። ሁለተኛውን ግብ የመስመር ዳኛዋ ከጨዋታ ውጪ ሲሉ ባንዲራቸውን ዘረጉ። ግቡ በቪዲዮ ተረጋግጦ የመሀል ዳኛዋ ሲያጸድቁት ግን የካሜሩን ተጨዋቾች ግብ ጠባቂዋን ጨምሮ አንጫወትም በማለት መሀል ሜዳ ላይ ተሰብስበው  ለተወሰነ ደቂቃ ጨዋታው ተቋረጠ። ካሜሮኖችን ዳግም ግራ ያጋባ ነገር ተከሰተ። ካሜሮኖች ያስቆጠሩት ግብ በቪዲዮ ተጣርቶ ከጨዋታ ውጪ ተብሎ ተሰረዘ።

ምስል picture-alliance/empics/J. Walton

የካሜሩን ተጨዋቾች ማመን አልቻሉም። ከትንሽ ውዝግብ በኋላ ግን ጨዋታው ቀጥሎ እንግሊዝ ሦስተኛዋን ግብ አስቆጠረች። ካሜሮኖችን ያወዛገበው ጨዋታ በእንግሊዝ አሸናፊነት ተጠናቋል። ቅዳሜ እለት በሩብ ፍጻሜው ግጥሚያ ናይጀሪያን 3 ለ0 ያሸነፈችው ጀርመን እንደ እንግሊዝ ሁሉ ወደ ሩብ ፍጻሜው ማለፍ ችላለች። ትናንት ብራዚልን 2 ለ1 በማሸነፍ በብዙዎች ዘንድ ተወዳጅነት ያተረፈችው ማርታ እና ጓደኞቿን ያስቀረችው ፈረንሳይም  ወደ ሩብ ፍጻሜ አልፋለች። አውስትራሊያን 4 ለ1 ያሸነፈችው ኖርዌይም ወደ ሩብ ፍጻሜ ካለፉት ውስጥ ትገኛለች። በሩብ ፍጻሜው የምትገጥመው የእንግሊዝን ቡድን ነው። በዛሬው እለት ከሚደረጉ ጨዋታዎች መካከል ዋንጫውን ዳግም ልትወስድ ትችላለች ተብላ የምትጠበቀው ዩናይትድ ስቴትስ ከስፔን፤ ስዊድን ከካናዳ ጋር ይጋጠማሉ። ነገ ደግሞ ጣሊያን ከቻይና እንዲሁም ኔዘርላንድ ከጃፓን ጋር ይፋለማሉ።  

እድሜያቸው ከ21 ዓመት በታች የኾኑ ተጨዋቾች በሚሳተፉበት የአውሮጳ እግር ኳስ ላይ የጀርመን ቡድን ከኦስትሪያ አቻው ጋር አንድ እኩል ሲለያይ፤ ዴንማርክ ሰርቢያን 2 ለ0 አሸንፋለች። ዛሬ ማታ ክሮሺያ ከእንግሊዝ እንዲሁም ፈረንሳይ ከሩማንያ ጋር ይጋጠማሉ። እስካሁን የስፔን ቡድን ብቻ ለግማሽ ፍጻሜው አልፏል። ዛሬ እና ሐሙስ ከሚከናወኑት አራት ግጥሚያዎች በኋላ የፊታችን እሁድ የፍጻሜው ጨዋታ ይከናወናል።

ምስል Reuters/J. P. Pelissier

በትናንቱ የፎርሙላ አንድ የፈረንሳይ ውድድር የመርሴዲስ አሽከርካሪዎች ድል ቀንቷቸዋል። ሌዊስ ሐሚልተን በስምንት ውድድሮች ለስድስተኛ ጊዜ በድጋሚ ማሸነፍ ችሏል። ቫልተሪ ቦታስ ሁለተኛ፣ ቻርለስ ሌክሌርክ እና ማክስ ፈርሽታፓን ሦስተኛ እና አራተና ሲወጡ ሰባስቲያን ፌትል የአምስተኛ ደረጃን አግኝቷል። በእስካሁኖቹ ውድድሮች አጠቃላይ 187 ነጥብ የሰበሰበው ሌዊስ ሐሚልተን ቀዳሚ ሲኾን፤ በ151 ነጥቡ የሚከተለው የመርሴስ ቡድን አጋሩ ቫልተሪስ ቦታስ  ነው። የፌራሪ አሽከርካሪው ሰባስቲያን ፌትል በአጠቃላይ 111 ነጥቡ የሦስተኛ ደረጃን ይዟል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሐመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW