1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ስፖርት በጎርጎሮሣውያኑ 2008 ዓ.ም.

ሰኞ፣ ታኅሣሥ 27 2001

ባለፈው ሣምንት አጋማሽ ላይ የተሰናበተው የጎርጎሮሣውያኑ ዘመን 2008 ዓ.ም. በዓለማችን በርከት ያሉ ዓበይት የስፖርት ውድድሮች የተካሄዱበትና አስደናቂ ውጤቶችም የተመዘገቡበት ነበር።

ሃይሌ ገ/ሥላሴ በበርሊን ማራቶን
ሃይሌ ገ/ሥላሴ በበርሊን ማራቶንምስል AP

የቤይጂንጉ ኦሎምፒክ ከነዚሁ ታላቁ ነበር። በአፍሪቃና በአውሮፓም ማራኪ የነበሩ የክፍለ-ዓለማቱ የእግር ኳስ ዋንጫ ውድድሮች ተካሂደዋል። 2008 ዓ.ም. ድንቁ የኢትዮጵያ አትሌት ሃይሌ ገ/ሥላሴ የበርሊንን ማራቶን ከሁለት ሰዓት አራት ደቂቃ በታች በሆነ ጊዜ በማሽነፍ የመጀመሪያው አትሌት ሆኖ ታሪክ ያስጻፈበትም ነበር።

ባለፈው ሣምንት የተገባደደው የጎርጎሮሣውያኑ 2008 ዓ.ም. ዓለምን በምግብና በነዳጅ ዘይት ምርቶች የዋጋ ንረት ሲንጥ፤ የኤኮኖሚ ዕድገትን ክፉኛ በሚፈታተን በፊናንስ ቀውስ ሲያንገዳግድ ቢገሰግስም በስፖርቱ ዓለም ግን ድንቅ ዕርምጃ በታየበት ሁኔታ ነው’። ገና በጅምሩ በወርሃ ጥርና የካቲት ጋና ያስተናገደችው የአፍሪቃ ዋንጫ ፍጻሜ ውድድር ተመልካችን እጅግ የሚማርክ የማጥቃት አጨዋወት ስልት ያመዘነበት ሆኖ ዓለምአቀፍ አድናቆትን በማትረፍ ይጠናቀቃል። በውድድሩ የአፍሪቃ እግር ኳስ ታላቅ የወደፊት እመርታ ማድረጉ እንደገና ሲከሰት በአውሮፓም ጨዋታዎቹን በቴሌቪዥን አማካይነት የተከታተለው የኳስ አፍቃሪ ቁጥር ከመቼውም የላቀ ነበር።

በውድድሩ በመጀመሪያው ማጣሪያ በአንድ ምድብ ተደልድለው የነበሩት ግብጽና ካሜሩን ለፍጻሜ ሲደርሱ ግብጽ 1-0 በማሸነፍ ቀደም እንዳለው ሻምፒዮና ሁሉ የዋንጫ ባለቤት ትሆናለች። ውድድሩ በአራት ከተሞች ሲካሄድ ጋና ያደረገችው ዝግጅት ከዚያን ቀደም በክፍለ-ዓለሚቱ አቻ ያልታየለት ነበር። የጋናው የአፍሪቃ ዋንጫ ድል ለግብጽ በጠቅላላው ስድስተኛው ሲሆን አስተናጋጇ አገር ሶሥተኛ፤ አይቮሪ ኮስትም አራተኛ በመሆን ውድድሩን መፈጸማቸው ይታወሣል። በውድድሩ በጠቅላላው 32 ግጥሚያዎች ሲካሄዱ 99 ጎሎች ተቆጥረዋል። ይህም በአንድ ጨዋታ በአማካይ ከሶሥት ጎል በላይ መሆኑ ነው።
714 ሺህ ተመልካቾች ደግሞ በስታዲዮሞች በመገኘት ግጥሚያዎቹን በቀጥታ ተከታትለዋል። የውድድሩ ጎል አግቢ አምሥት በማስቆጠር የካሜሩኑ ሣሙዔል ኤቶ፤ ድንቅ በመባል የተመረጠው ተጫዋችም የግብጹ ሆስኒ-አብድ-ራቦ ነበሩ። የአፍሪቃ እግር ኳስ በዚያ መጠን ቀልጥፎና አይሎ መታየቱ በሚቀጥለው ዓመት ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ በሚካሄደው የዓለም ዋንጫ ፍጻሜ ውድድር ምናልባትም የክፍለ-ዓለሚቱን የመጀመሪያ ድል ለማየት ተሥፋን የሚያዳብር ነው። ምኞቱን ዕውን ማድረጉ ቀላል አይሁን እንጂ የማይቻል አይደለም። እርግጥ አፍሪቃውያን ተጫዋቾች ዛሬ ደርሰው ከሚገኙበት በቴክኒክ የረቀቀ አጨዋወት ባሻገር የአውሮፓና የላቲን አሜሪካ ተፎካካሪዎቻቸውን ዲሲፕሊን እስከዚያው መውረስ መቻል ይኖርባቸዋል።

ይሄው የአፍሪቃ ዋንጫ ፈታ ያለ የማጥቃት አጨዋወት ስልት በዓመቱ አጋማሽ ከግንቦት እስከ ሰኔ ወር በአውስትሪያና በስዊትዘርላንድ የጋራ አስተናጋጅነት በተካሄደው የእውሮፓ እግር ኳስ ዋንጫ ፍጻሜ ውድድርም ደግሞ የተከሰተ ነበር። ውድድሩ ሰሥት ሣምንታት ያህል ሲካሄድ ከከረመ በኋላ ሰኔ 29 ቀን. 2008 ዓ.ም. ስፓኝና ጀርመን በቪየናው ኤርንስት-ሃፕል ስታዲዮም የዋንጫ ተጋጣሚዎች ሆነው ይቀርባሉ። ስፓኝ ድንቅ አጥቂዋ ፌርናንዶ ቶሬስ በ 33ኛዋ ደቂቃ ላይ ባስቆጠራት ጎል የዋንጫ ባለቤት ትሆናለች።

ጀርመን ከ 12 ዓመታት በኋላ የምድቧ ሁለተኛ በመሆን ሩብ ፍጻሜውን አልፋ እንደገና ወደ ፍጻሜው ብትገሰግስም ቶሬስን፣ ዴቪድ ቪያንና ራሞስን የመሳሰሉትን የስፓኝ ኮከቦች ለማቆም አትችልም። በውድድሩ አንዲት ግጥሚያ እንኳ ሳትረታ ለፍጻሜ የደረሰችው ስፓኝ ከ 44 ዓመታት በኋላ ለሁለተኛ ጊዜ የአውሮፓ ዋንጫ ባለቤት ትሆናለች። የቡድኑ በረኛና አምበል ኢከር ካሢላስ በ 51 ሺህ ተመልካች ፊት ዋንጫውን ሲቀበል ደጋፊዎቹ ቡድኑን ያወደሱት በደመቀ ሁኔታ ነበር። የስፓኝ ብሄራዊ ቡድን በውድድሩ ሂደት ባሣያቸው ግሩም ጨዋታዎች የተመልካችን ቀልብ በሰፊው ለመሳብ በቅቷል። እርግጥ በሩብና ግማሽ ፍጻሜ ቀደም ብለው ቢሰናከሉም ሆላንድ፣ ሩሢያና ቱርክ ያሳዩት ማራኪ ጨዋታም ግሩም ትውስት ሆኖ የሚቀጥል ነው። በአንጻሩ ኢጣሊያ፣ ፈረንሣይ፤ ክሮኤሺያ፤ በአጀማመሩ ጠንክራ የታየችው ፖርቱጋልም እንደተጠበቀው ሣይሆኑ ቀርተዋል።

በተሰናበተው 2008 ዓ.ም. በዓለም የስፖርት መድረክ ላይ ከሁሉም በላይ ታላቁ እርግጥ የቤይጂንጉ ኦሎምፒክ ነበር። 29ኛው የዘመናችን የኦሎምፒክ ጨዋታ ከሁለት መቶ ከሚበልጡ ሃገራት የተውጣጡ 11 ሺህ አትሌቶች የተሳተፉበት እስካሁን ከታዩት ሁሉ ተወዳዳሪ ያልተገኘለት ነበር። ምንም እንኳ የቻይና የቲቤት ፖሊሲ በዋዜማው በዓለም ዙሪያ የፖለቲካ ተቃውሞን ቢቀሰቅስም እጅግ የደመቀ ዝግጅቱና አጠቃላይ ሂደቱ ለአስተናጋጇ አገር ዕውቅናን አትርፎ ነው ያለፈው። ሕዝባዊት ቻይና በዝግጅት ብቃት ብቻ ሣይሆን 51 የወርቅ፤ በጠቅላላይ 110 ሜዳሊያዎችን በማግኘት ከአሜሪካ ቀድማ አንደኛ ለመሆን በቅታለች።

በቤይጂንጉ ኦሎምፒክ እንዳይረሱ ሆነው ድንቅ በሆነ ውጤት ታሪክ ያስመዘገቡ ግሩም አትሌቶችም አልታጡም። ከነዚሁ መካከል በተለይም ስምንት የወርቅ ሜዳሊያ የሰበሰበው አሜሪካዊው ዋናተኛ ማይክል ፌልፕስና የአጭር ሩጫው መንኮራኩር ጃማይካዊው ኡሤይን ቦልት ቀደምቶቹ ነበሩ። የነዚህ ሁለት አትሌቶች ውጤት የሚያስደንቀው ፌልፕስ ከስምንት ሰባቱን ወርቅ፤ ኡሤይን ቦልትም በሶሥቱም ውድድር በመቶ፣ በሁለት መቶና በአራት ጊዜ መቶ ሜትር የዱላ ቅብብል በአዲስ የዓለም ክብረ-ወሰን ማሸነፋቸው ነው። ማይክል ፌልፕስ በዚሁ የአገሩ ልጅ ማርክ ሽፒትስ ከ 36 ዓመታት በፊት በሚዩኒክ ኦሎምፒክ ሰባት ወርቅ በማሸነፍ ያስቀመጠውን ክብረ-ወሰን ሲሰብር የቦልትም ልዕልና ዓለምን ጉድ ማሰኘቱ አልቀረም። ብልት መጣ፤ ቦልት አሸነፈ! ዘጋቢዎች ሌላ የሚሉት ነገር አልነበራቸውም!

በመካከለኛና ረጅም ርቀት ሩጫ ደግሞ የቤይጂንግን ኦሎምፒክ አድማስ የተለየ ውበት የሰጡት እንደተጠበቀው የአፍሪቃ አትሌቶች ነበሩ። ኢትዮጵያ ሃይሌ ገ/ ሥላሴ በአየር ብክለት ስጋት በማራቶን ባለመሳተፉ ምናልባትም አንዱንና ዋነኛውን ሜዳሊያ ብታጣም በሌላ በኩል ቀነኒሣ በቀለና ጥሩነሽ ዲባባ በአምሥትና አሥር ሺህ ሜትር አስደናቂ በሆነ ድርብ ድል ክሰዋታል። የቤይጂንጉ ኦሎምፒክ በአጠቃላይ ሲታይ ለሁለቱ ተፎካካሪ የአፍሪቃ አገሮች ለኬንያና ለኢትዮጵያ የሰመረ ነበር። በተለይ ኬንያውያን ፓሜላ ጀሊሞን በመሳሰሉት ወጣት ኮከቦች አማካይነት የወቅቱን ልዕልናዋን አስመስክራለች። ለኬንያ ከሁሉም በላይ ታላቁ ስኬት እርግጥ በኦሎምፒክ ታሪክ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ የማራቶን ድል መቀዳጀቷ ነበር።

ወርሃ-ነሐሴ እንዲህ ሲል አለፈ። የቤይጂንግ ኦሎምፒክም ታሪክ ሆነ! ተከታዩ መሥከረም ደግሞ ሃይሌ ገ/ሥላሴ የማራቶን ጌታነቱን ለማስመስከር ሲጠብቀው የቀየው የቅርብ አጋጣሚ ነበር። ጌትነቱን ለማረጋገጥም አልተሳነውም። ምኞቱ በ 35ኛው የበርሊን ዓለምአቀፍ ማራቶን ዕውን ይሆናል። ሃይሌ አንድ ዓመት ቀደም ሲል በዚያው አስመዝግቦት የነበረውን የራሱን የማራቶን ክብረ-ወሰን በማሻሻል ከሁለት ሰዓት አራት ደቂቃ በታች በመሮጥ የመጀመሪያው አትሌት ይሆናል። ታዓምር ነው! አኩሪ አትሌት!

ያለፈው ዓመት በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት 16ኛው የመላው አፍሪቃ የአትሌቲክስ ውድድር የተካሄደበትም ነበር። ለአዲስ አበባ ታላቁ አሕጉር-አቀፍ ዝግጅት ሲሆን አበበ ቢቂላን የመሳሰሉ የአፍሪቃ የጥንት አትሌቶችም ተዘክረውበታል።

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW