1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ታኅሣሥ 10 2009

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ቸልሲ 11ኛ ተከታታይ ጨዋታውን በማሸነፍ ታሪክ ሠርቷል። ከተፎካካሪዎቹ ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነትም አስፍቷል። አርሰናል ትናንት ነጥቡንም ደረጃውንም ለማንቸስተር ሲቲ አስረክቦ ዛሬ ተስተካካይ ጨዋታውን ከሚያከናውነው ከሊቨርፑል ስር ለመሆን ተገዷል።

Deutschland Darmstadt 98 gegen FC Bayern München
ምስል imago/J. Huebner

ስፖርት ታህሳስ 10፣ 2009 ዓም

This browser does not support the audio element.

በኢትዮጵያ ፕሬሚየር ሊግ ስድስተኛ ዙር የእግር ኳስ ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ ዳግም አቻ ወጥቷል። አዳማ ከነማ እና ደደቢት በነጥብ ተስተካክለውታል። ወደ ወላይታ ያቀናው ኢትዮጵያ ቡና  አንድ እኩል ወጥቶ ተመልሷል። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ቸልሲ 11ኛ ተከታታይ ጨዋታውን በማሸነፍ ታሪክ ሠርቷል። ከተፎካካሪዎቹ ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነትም አስፍቷል። አርሰናል ትናንት ነጥቡንም ደረጃውንም ለማንቸስተር ሲቲ አስረክቦ ዛሬ ተስተካካይ ጨዋታውን ከሚያከናውነው ከሊቨርፑል ስር ለመሆን ተገዷል። በጀርመን ቡንደስ ሊጋ በደረጃ ሰንጠረዡ መሪው ባየር ሙሽይንሽንም ተከታዩ ላይፕትሲሽም ማሸነፍ ችለዋል፤ በግብ ልዩነት ብቻ ይለያያሉ።  

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ሊቨርፑል ዛሬ 17ኛ ተስተካካይ ጨዋታውን ያከናውናል።  ካሸነፈ በጎርጎሪዮሱ ቀመር የሚከበረውን ገና የሚያሳልፈው በደረጃ ሰንጠረዡ ሁለኛ ሆኖ ነው። ለዛሬው ጨዋታ ሊቨርፑል ወደ ኤቨርተን የሚያናቀናው «ለጦርነት ነው» ሲል አጥቂው ዲቮክ ኦሪጊ ተናግሯል።

ምስል Reuters/E. Keogh

የ21 ዓመቱ ወጣት የሊቨርፑል አጥቂ ኦሪጊ ያለፉት አምስት ጨዋታዎች ላይ ግብ ማስቆጠር የቻለ ጠንካራ ተጨዋች ነው። ለዛሬው ጨዋታ ወደ ኤቨርተን የሚያቀኑት በራስ መተማመን እንደሆነ ተናግሯል። «ዛሬ ጦርነት ነው የሚኾነው» ሲል ለጋዜጠኞች የተናገረው ቤልጂጋዊው የሊቨርፑል አጥቂ፥ «የዛሬውን ጨዋታ ማሸነፍ እንፈልጋለን» ብሏል። «መቼም ጨዋታው ቀላል አይሆንም። ጨዋታው በአንድ ከተማ ቡድኖች የሚከናወን ደርቢ በመሆኑ ለየት ያለ ነው የሚሆነው። ለእኛ ትልቅ እና ወሳኝ ግጥሚያ ነው» ሲልም አክሏል።

34 ነጥብ ያለው ሊቨርፑል መሪው ቸልሲ ላይ ለመድረስ ከዛሬው በተጨማሪ ሌሎች ሁለት ጨዋታዎችን ማሸነፍ ይገባዋል። 43 ነጥብ የሰበሰበው ቸልሲ አያያዝ ግን ለዚያ የሚመች አይመስልም። ቸልሲ በፕሬሚየር ሊጉ የአንድ የጨዋታ ዘመን 11 ተከታታይ ጨዋታዎችን በሙሉ በማሸነፍ የቡድኑን አዲስ ታሪክ አስመዝግቧል። 

ከትናንት በስትያ ክሪስታል ፓላስን 1 ለ0 ያሸነፈው ቸልሲ የደረጃ ሠንጠረዡን በ7 ነጥብ መምራት ችሏል። ቡድናቸው 11 ጨዋታዎችን በተከታታይ ካሸነፈ በኋላ የቸልሲ አሠልጣኝ አንቶኒዮ ኮንቴ፦ «አሁን ደህና እንቅልፍ ማግኘት እችላለሁ» ሲሉ ተናግረዋል። አንቶኒዮ ኮንቴ ቡድናቸው ቸልሲ በሜዳው መስከረም ወር ላይ በሊቨርፑል 2 ለ1 እንዲሁም ከሜዳው ውጪ በአርሰናል 3 ለ 0 ከተሸነፈ ወዲህ «እንቅልፍ አጥተው» አጨዋወታቸውን እንዳሻሻሉም ተናግረዋል። 

በደረጃ ሰንጠረዡ ቸልሲን የሚከተለው ማንቸስር ሲቲ 36 ነጥብ አለው። አርሰናል በ34 ነጥብ አራተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ትናንት በርንሌይን 2 ለ1 የረታው ቶትንሀም ሆትስፐር 33 ነጥብ ይዟል።ማንቸስተር ዩናይትድ ዌስት ብሮሚችን 2 ለ0 በማሸነፍ  በ30 ነጥብ ስድስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

ምስል Reuters/M. Rehle

ወደ ቡንደስ ሊጋ እና የአትሌቲክስ ዜና ከማለፋችን በፊት የኢትዮጵያ ፕሬሚየር ሊግ ስድስተኛ ዙር ጨዋታዎችን በተመለከከተ ያደረግነውን ቃለ መጠይቅ እናሰማችሁ። በብሥራት 101.1 የስፖርት ፕሮግራም ዋና አዘጋጁ ጋዜጠኛ ማርቆስ ኤልያስ እስካሁን የተደረጉ ጨዋታዎች ይዘት ምን ይመስሉ እንደነበር በመግለጥ ይጀምራል።

«ኅዳር 3 ነው የተጀመረው ስድስተኛው ሳምንት ላይ ደርሷል። እስካሁን  በተከናወኑ  ጨዋታዎች  ሁለተኛው ሳምንት ላይ ሁለት ጨዋታዎች በተለያዩ ምክንያት አልተከናወኑም። ስድስተኛው ሳምንት ጨዋታ ሙሉ ለሙሉ የተከናወነው ትናንትና ነው። ትናንትና ስምንት የሚደርሱ ጨዋታዎች  በአዲስ አበባ እና» በሌሎች ከተሞች መከናወናቸውን ገልጧል። «የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ወደ ድሬዳዋ ተጉዞ ድሬዳዋ ከነማን 2 ለ0 በሆነ ውጤት ነው ማሸነፍ የቻለው» ያለው ማርቆስ ከዚያ ውጪ ጨዋታዎቹ በሚከናወኑባቸው ጊዜያት «ይኽ ነው የተባለ ነገር» እንደሌለ ተናግሯል።

በጀርመን ቡንደስሊጋ መሪው ባየር ሙይንሽን ዳርምሽታድትን ትናንት 1 ለ ባዶ በማሸነፍ የመሪነት ደረጃውን በ36 ነጥብ አስጠብቋል።  በ8 ነጥብ የተውሰነው ዳርምሽታድት የደረጃ ሰንጠረዡ ጥግ 18ኛ ላይ ይገኛል። ከዳርምሽታድት ጋር ዘንድሮ ወደ ቡንደስ ሊጋው ያደገው ኢንግሎሽታድት ትናንት ባየር ሌቨርኩሰንን 2 ለ 1 ድል አድርጎ ከባየርሙይንሽን ጋር በተመሳሳይ ነጥብ ሆኖም በግብ ክፍያ ይበለጣል።

ምስል Reuters/R.Orlowski

ሆፈንሃይም እና ሔርታ ቤርሊን ተመሳሳይ 27 ነጥብ ይዘው 3ኛ እና 4ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ። ሔርታ ቤርሊን ቅዳሜ ዕለት በላይፕሲሽ 2 ለባዶ ተሸንፏል። ሆፈንሀይም ዐርብ እለት ከዶርትሙንድ ጋር 2 ለ2 ነበር የተለያየው። ዶርትሙንድ በተመሳሳይ 26 ነጥብ አይንትራኅት ፍራንክፉርትን አስከትሎ 5ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። 

በሙስና ተጠርጥረው ለጊዜው ከሥራ የታገዱ የዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማኅበር (IAAF) ሦስት ከፍተኛ አመራር የተጣለባቸው እገዳ እንደሚቀጥል ተገለጠ።  የማኅበሩ የፕሬዚዳንት ጽ/ቤት  ኃላፊ ኒክ ዳቪስ፤ ባለቤታቸው ጄን ቦልተር ዳቪስ እና ፒየር ይቬ ጋርኒየር አበረታች መድኃኒት የተጠቀሙ የሩስያ አትሌቶችን ስም ደብቀዋል በሚል ነው የታገዱት። ለ180 ቀናት  የተጣለው እገዳ ለሚቀጥሉት 44 ቀናት የጸና እንደሚሆን ተገልጧል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሐመድ

    

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW