1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ስፖርት፤ ታኅሣሥ 2 ቀን፣ 2010 ዓ.ም.

ሰኞ፣ ታኅሣሥ 2 2010

በሴካፋ የእግር ኳስ ውድድር የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ወደ ግማሽ ፍጻሜ ለማለፍ የነበረችው ጭላጭል ተስፋ ዛሬ ተዳፍናለች። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ማንቸስተር ዩናይትድ በሜዳው መሸነፉን ተከትሎ ለተፈጠረው ግጭት ቡድኖቹ በአስቸኳይ ዝርዝር ማብራሪያ እንዲሰጡ እስከ ረቡዕ ድረስ ጊዜ ተሰጥቷቸዋል።

Fußball Auslosung Achtelfinale Champions League Paarungen
ምስል Getty Images/AFP/F. Coffrini

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

This browser does not support the audio element.

በጀርመን ቡንደስ ሊጋ መሪው ባየር ሙይንሽን ምርጥ ተጨዋቾችን መሰብሰቡን አሁንም ቀጥሏል። ባየርን ሙይንሽን አሁን ደግሞ ዐይኑን የጣለው በባየር ሌቨርኩሰኑ የብሔራዊ ቡድን ተሰላፊ ግብ ጠባቂ ላይ ነው። በስፔን ላሊጋ የባርሴሎናው ሊዮኔል ሜሲበኮከብ ግብ አግቢነቱ እየገሰገሰ ነው።

የምሥራቅ እና መካከለኛው አፍሪቃ እግር ኳስ ማኅበር ምክር ቤት (Cecafa) እግር ኳስ ጨዋታ ሊጠናቀቅ ጥቂት ቀናት ብቻ ይቀሩታል። በውድድሩ ተሳታፊ የነበረው የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ወደ ግማሽ ፍጻሜው ለማለፍ የነበረችው ቀጭን ተስፋ ዛሬ ተበጥሳለች። ብሔራዊ ቡድኑ ትናንት ከዩጋንዳ ጋር ባደረገው ጨዋታ ዕድሉን አሳልፎ ሰጥቷል። ጨዋታውን ለመዘገብ ኬንያ የሚገኘው የሶከር ኢትዮጵያ ድረ-ገጽ መራኄ አርታኢ ኦምና ታደለ የትናንቱን ጨዋታው እንዲህ ቃኝቶቶታል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን ለመደገፍ ከኢትዮጵያ ወደ  ኬንያ ካቀኑ 11 ደጋፊዎች መካከልም አንዱ የሆኑት አቶ ፍሬው ለብሔራዊ ቡድኑ «የግብ ጠባቂ ችግር ነው ያለበት» ሲሉ ድክመቱን ነቅሰው ተናግረዋል።

ምስል Reuters/A. Couldridge

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ የእግር ኳስ ግጥሚያ ትናንት በሜዳው ሽንፈት የገጠመው የማንቸስተር ዩናይትድ ቡድን አሰልጣኝ ከማንቸስተር ሲቲ አሰልጣኝ ጋር መጋጨታቸውን በተመለከተ እስከ ረቡዕ ድረስ ማብራሪያ እንዲሰጡ በእንግሊዝ የእግር ኳስ ማኅበር ተጠይቀዋል። የማንቸስተር ዩናይትድ አሰልጣኝ  ጆዜ ሞሪንሆ  ቡድናቸው በፕሬሚየ ር ሊጉ መሪ ማንቸስተር ሲቲ 2 ለ 1 ከተሸነፉ በኋላ የሲቲው አሰልጣኝ ሚኬል አርቴታን በውሃና ወተት መያዣ ዕቃ መፈንከታቸው ተገልጧል።  ማንቸስተር ዩናይትድ ተጨዋቾች በድል አድራጊው ማንቸስተር ሲቲ ፈንጠዝያ ባለመደሰታው ወደ መልበሻ ክፍል መተላለፊያ ላይ ጸብ መፈጠሩ ተዘግቧል። በትናንትናው  ድል መሪው ማንቸስተር ሲቲ ከተከታዩ ማንቸስተር ዩናይትድ ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ወደ 11 ከፍ አድርጎታል። ማንቸስተር ሲቲ የፊታችን ረቡዕ የሚገጥመው በወራጅ ቃጣናው ከታች ሁለተኛ ደረጃ ላይ ከሚገኘው ስዋንሲ ሲቲ ጋር ነው። ማንቸስተር ዩናይትድከቸልሲ በ3 ነጥብ በልጦ በያዘው 35ነጥቡ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። 

30 ነጥብ ይዞ አራተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ሊቨርፑል ትናንት በግብጻዊው አጥቂው ሞሐመድ ሳላህ ግብ በሜዳው ከኤቨርተን ጋር አቻ ተለያይቷል።  የሊቨርፑሉ አሰልጣኝ ዬይርገን ክሎፕ ወሳኝ ተጨዋቾችን ባለማሰለፋቸው ለቀረበባቸው ቅሬታ ተጨዋቾችን እያቀያየሩ ማሰለፋቸው ወደፊትም የሚቀጥል መሆኑን አስረግጠዋል። በትናንቱ ወሳኝ ጨዋታ ፊሊፕ ኮቲንሆ እና ሮቤርቶ ፊርሚኖ አለመሰለፋቸው ብርቱ ነቀፌታ አስከትሎባቸዋል።  ትናንት ከሳውዝሀምፕተን ጋር እንድ እኩል የተለያየው አርሰናል በአውሮጳ ሊግ 32 ቡድኖች ድልድል የሚገጥመው የስዊድኑ  ኦስተርሱንድ ቡድንን ነው።

ምስል picture-alliance/Citypress24

በጀርመን ቡንደስሊጋ የባየር ሌቨርኩሰኑ ዋና ኃላፊ ሩዲ ፎለር መገናኛ አውታሮች የጀርመኑ ግብ ጠባቂ በጥር ወር ውስጥ ወደ ኃያሉ ባየር ሙይንሽን ሊያቀና ነው መባሉን «ዘብራቃ ወሬ» ሲሉ ነቀፉ። ባየር ሙይንሽን በጀርመን ቡንደስ ሊጋ ብቃት ያላቸው ተጨዋቾችን በመሰብሰብ ይታወቃል። ባየር ሙይንሽን አይንትራኅት ፍራንክፉርትን ከትናንት በስትያ  አሸንፎ የያዘው 3 ነጥብን ጨምሮ ባሰባሰበው 35 ነጥብ ከተከታዩ ላይፕሲሽ ቡድን በ8 ነጥብ ይበልጣል። ላይፕሲሽ ከሻልከ በአንድ ነጥብ በልጦ 27 ነጥብ ይዞ ባየር ሙይንሽንን ይከተላል።

በስፔን ላሊጋ ግጥሚያ በደረጃ ሰንጠረዡ ስድስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ቪላሪያልን ትናንት 2 ለ0 ያሸነፈው  ባርሴሎና 39 ነጥብ  ይዞ ይመራል።  ቫለንሺያ በ34 ነጥብ ይከተላል።  አትሌቲኮ ማድሪድ በአንድ ነጥብ ዝቅ ብሎ ደረጃው ሦስተኛ ነው። የመሪው ባርሴሎና አጥቂ ሊዮኔል ሜሲ በ14 ግቦች በኮከብ ግብ አግቢነት እየመራ ይገኛል። የቫለንሺያው ሲሞን ዛዛ በ10 ግቦች ሲከተል፤ የሴልታ ቪጎው ኢያጎ አስፓስ 9 ግቦች አሉት፤ ሦስተኛ ነው።  ኢስፓኞላ ከጊሮኛ ዛሬ ማታ ይጋጠማሉ።

የሻምፒዮንስ ሊግ 16 ቡድኖች ድልድል ዛሬይፋ ኾኗል ሪያል ማድሪድ እና ፓሪስ ሴን ጀርሜን በሚያደርጉት ግጥሚያ ክርስቲያኖ ሮናልዶ እና የቀድሞ የቡድኑ አባል ኔይማር ይፋጠጣሉ። ቸልሲ የአምስት ጊዜ የሻምፒዮንስ ሊግ ባለድል ከሆነው ባርሴሎና ጋር የሚያደርገው ግጥሚያም እጅግ የሚጠበቅ ነው።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አርያም ተክሌ

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW