1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ስፖርት፤ ኅዳር 15 ቀን፣ 2012 ዓ.ም

ሰኞ፣ ኅዳር 15 2012

​​​​​​​በጀርመን ቡንደስ ሊጋ መሪው ቦሩስያ ሞይንሽን ግላድባኅ ከታች ዲቪዚዮን ባደገው ኡኒዮን ቤርሊን በጨዋታ ተበልጦ 2 ለ0 መሸነፉ ብዙዎችን አስደምሟል። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ሊቨርፑልን ከስር ከስር በነጥብ ሲከተል የከረመው ማንቸስተር ሲቲ ቦታውን ለላይስተር ሲቲ አስረክቧል።

Deutschland Dortmund - Paderborn | Frust
ምስል Imago-Images/ActionPictures/P. Schatz

በጀርመን ቡንደስ ሊጋ መሪው ቦሩስያ ሞይንሽን ግላድባኅ ከታች ዲቪዚዮን ባደገው ኡኒዮን ቤርሊን በጨዋታ ተበልጦ 2 ለ0 መሸነፉ ብዙዎችን አስደምሟል። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ሊቨርፑልን ከስር ከስር በነጥብ ሲከተል የከረመው ማንቸስተር ሲቲ ቦታውን ለላይስተር ሲቲ አስረክቧል። ድምፁን አጥፍቶ የቆየው ላይስተር ሲቲ በፕሬሚየር ሊጉ የሁለተኛ ደረጃን ተቆናጧል። ትናንት ስለተጠናቀቀው የ14ኛው የአዲስ  አበባ ከተማ ዋንጫ ቃለ መጠይቅ ይኖረናል። በዳቪስ ካፕ የሜዳ ቴኒስ የፍጻሜ ፍልሚያ ስፔናውያን ድል ተቀዳጅተዋል።

እግር ኳስ

ወደ እንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ እና የጀርመን ቡንደስሊጋ ግጥሚያዎች ከመሻገራችን በፊት ለሀገር ውስጥ የእግር ኳስ ጨዋታዎች ቅድሚያ እንስጥ። በምሥራቅ እና መካከለኛው አፍሪቃ ሃገራት ግጥሚያ ከኤርትራ አቻው ጋር የተደለደለው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ብሔራዊ ቡድን የፋይናንስ ችግር እንዳለበት እየተነገረ ነው። ዕድሜያቸው ከ17 ዓመት በታች ተጨዋቾች በሚሳተፉበት እና ኡጋንዳ ካምፓላ ውስጥ በሚከናወነው ውድድር አስተናጋጇ ኡጋንዳ፤ ቡሩንዲ እና ኤርትራ በሚገኙበት ምድብ የተደለደለው የኢትዮጵያ ቡድን በውድድሩ ለመሳተፍ የፋይናንስ ድጋፍ እንደሚያስፈልገው ምንጮቻችን ገልጠውልናል።

ምስል Getty Images/AFP/J. Batanudde

ከሀገር ውስጥ የእግር ኳስ ዜና ሳንወጣ፦ በተደጋጋሚ ጊዜያት በደጋፊዎቻቸው መካከል ግጭት ሲፈጠርበት የቆየው የፋሲል ከነማ እና የመቀሌ 70 እንደርታ ግጥሚያ አዲስ አበባ ውስጥ እንደሚከናወን ተገልጧል። የሁለቱ ቡድኖች የአሸናፊዎች አሸናፊ ፍልሚያ መከናወን የነበረበት ባለፈው ጥቅምት 23 ነበር። የፍጻሜ ግጥሚያው ለኅዳር 16 ቀን 2012 መቀጠሩ ነው የተነገረው።

የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ

ይኽ በእንዲህ እንዳለ የ14ኛው የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ የፍጻሜ ግጥሚያን ቅዱስ ጊዮርጊስ ቡድን ሰበታ ከተማን ትናንት 2 ለ1 ድል በማድረግ ዋንጫውን ወስዷል። አራት የአዲስ አበባ ከተማ እንዲሁም አራት የክልል ቡድኖችን በማስተናገድ ለሁለት ሳምንት በዘለቀው ጨዋታ የቅዱስ ጊዮርጊሱ ሰልሃዲን ሰዒድ 4 ግቦችን ከመረብ በማሳረፍ ኮከብ ግብ አግቢ ኾኗል። በአጠቃላይ ውድድሩ ሰበታ ከተማ የስፖርታዊ ጨዋነት አሸናፊ ለመኾኗን በቅቷል። በአጠቃላይ ጨዋታዎች የታደሙ ተመልካቾች ቁጥር 173,484 እንደነበር ከአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የደረሰን መረጃ ያመለክታል በውድድሮቹ የጸጥታ ጉዳይ ትኩረት እንደተደረገበት የፌዴሬሽኑ ፕሬዚደንት ኢንጂነር ኃይለ-ኢየሱስ ፍስሃ ለዶይቸ ቬለ (DW)ተናግረዋል። በድረገጽ 60 በመቶ የቲኬት ሽያጭ ማድረጋቸውን እንዲሁም ጨዋታዎቹ የቴሌቪዥን ሽፋን እንዲኢደርጉ ማስቻላቸውንም አክለዋል።

ምስል Imago/Zink

በውድድሩ ስምንት ቡድኖች ማለትም ከአዲስ አበባ፦ አሸናፊው ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ኢትዮጵያ ቡና፤ መከላከያ እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ ተሳታፊ ነበሩ። ከክልል ቡድኖች ደግሞ፦ በሁለተኛ ደረጃ ያጠናቀቀው ሠበታ ከተማ ከኦሮሚያ፤ ባሕርዳር ከተማ ከአማራ፤ ወልቂጤ ከተማ ከደቡብ ክልል፤ እንዲሁም ወለዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ከትግራይ ናቸው።  የውድድሩ ኮከብ አሰልጣኝና ተጨዋች ምርጫ ውጤት በቀጣይ ቀናት ይፋ እንደሚኾን የአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጠቅሷል።

ቡንደስ ሊጋ

በጀርመን ቡንደስ ሊጋ መሪው ቦሩሲያ ሞይንሽንግላድባኅ ሲንገዳገድ ቦሩስያ ዶርትሙንድ ፍርክርኩ ወጥቷል። የባየር ሙይንሽኑ ግብ አዳኝ ሮበርት ሌቫንዶቭስኪ ደግሞ ግብ ማስቆጠር ተስኖት አምሽቷል። ባየር ሙይንሽን ዱስልዶርፍን 4 ለ0 ባሸነፈበት የቅዳሜው ጨዋታ ዮሹዋ ኪሚሽ፤ ኮሬንቲን ቶሊሶ፤ ሠርጌይ ግናብሬ እና ፊሊፕ ኮቲንሆ ግብ አስቆጥረዋል።

ምስል imago images/J. Huebner

ከመሪው ቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅ በአንድ ነጥብ ብቻ ተበልጦ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ለሚገኘው ባየር ሙይንሽን ጊዜያዊ አሰልጣኝ ሐንሲ ፍሊክ ቡድኑን በዋና አሰልጣኝነት ሊይዙት ይገባል የሚሉ የቡድኑ ደጋፊዎች ተበራክተዋል። ተመሳሳይ 24 ነጥብ ያለው ላይፕሲሽ በደረጃ ሰንጠረዡ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ሲገኝ ቅዳሜ ዕለት ኮሎኝን 4 ለ1 ድል አድርጓል።

ቦሩስያ ዶርትሙንድ ከታች ባደገው ቡድን ፓዴርቦን በመጀመሪያው አጋማሽ 3 ለ0 ሲመራ ቆይቶ በስተመጨረሻ አቻ የኾነው ዐርብ ዕለት ነው። ዶርትሙንድ በሜዳው ነጥብ መጣሉ ደጋፊዎቹን እጅግ አበሳጭቷል። ጫና የበረታባቸው አሰልጣኝ ሉቺየን ፋቭሬ አንድ ዕድል ተሰጥቷቸዋል። ጥሩው ነገር በሻምፒዮንስ ሊጉ ቀጣዩ ተፋላሚያቸው የእነ ሊዮኔል ሜሲ ባርሴሎና መኾኑ ነው። በሻምፒዮንስ ሊጉ ከነገ በስተያ ከቦሩስያ ዶርትሙንድ እና ባርሴሎና ግጥሚያ ባሻገር ሌላኛው የጀርመን ቡድን ላይፕሲሽ ቤኔፊካን ይገጥማል። ነገ ደግሞ ባየር ሙይንሽን ሮተር ሽቴርንን ይፋለማል።  የጣሊያኑ ናፖሊ እና የእንግሊዙ ሊቨርፑል የረቡዕ ግጥሚያም የሚጠበቅ ነው።

ፕሬሚየር ሊግ

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ሊቨርፑል ግስጋሴውን እንደቀጠለ ነው። እንደተለመደው ከትናንት በስትያም ተጋጣሚው ክሪስታል ፓላስን 2 ለ1 አሸንፎ ነጥቡን 37 አድርሷል። የሁለቱም ቡድኖች ማራኪ በነበረው ግጥሚያ ማንቸስተር ሲቲ ቸልሲን 2 ለ1 ቢያሸንፍም፤ በደረጃ ሰንጠረዡ ግን ከላይስተር ሲቲ በአንድ ነጥብ ዝቅ ብሎ ሦስተኛ ነው።  ብራይተንን 2 ለ 0 የረታው ላይስተር ሲቲ 29ነጥብ ሰብስቦ በሁለተኛ ደረጃ ሊቨርፑልን ይከተላል፤ ከመሪው ሊቨርፑል በ8 ነጥብም ይበለጣል።

የቶትንሐም ሆትስፐር አዲሱ አሠልጣኝ ሆዜ ሞሪኞ ምስል picture-alliance/AP Photo

በአሠልጣኝ ሆዜ ሞሪኞ የሚመራው ቶትንሐም ሆትስፐር ቅዳሜ ዕለት ዌስትሐም ዩናይትድን 3 ለ2 አሸንፏል። ለ11 ወራት ግድም ከእግር ኳስ አሰልጣንነት ርቀው ለቆዩት ሆዜ ሞሪኞ ድሉ እንደጥሩ ጅማሬ ተቆጥሮላቸዋል።

የሜዳ ቴኒስ

ካለፈው ሰኞ እስከ እሁድ ድረስ ሲከናወን የቆየው የዳቪስ ካፕ የሜዳ ቴኒስ ፍጻሜ በስፔናውያን ድል አድራጊነት ተጠናቋል። ስፔናውያን በሀገራቸው በማድሪድ የተከናወነውን የዘንድሮ የፍጻሜ ግጥሚያ ያሸነፉት 12,500 ተመልካቾች በታደሙበት ውድድር ነው።

በአዲስ መልክ በተዋቀረው ግጥሚያ ራፋኤል ናድል ካናዳን እሁድ እለት 2 ለ0 ድል ከማድረጉ አስቀድሞ ስምንት የተለያዩ ግጥሚያዎችን በስድስት ቀናት የዳቪስ ካፕ በማከናወን ራሱን ለጉዳት አጋልጦ ነበር። ራፋኤል ናዳል በግሉ አምስት ውድድሮችን፤ እና በቡድን ሦስት ግጥሚያዎችን ከአንድ ሳምንት ባነሰ ጊዜ ውስጥ በማከናወን ብርታቱን አሳይቷል።

ምስል Reuters/S. Vera

ስፔናዊው የሜዳ ቴኒስ ዝነኛ ተጨዋች ራፋኤል ናዳል በዳቪስ ካፕ የፍፃሜ ግጥሚያ ትናንት ድል ሲቀዳጅ ለስድስተኛ ጊዜ ነው። በራፋኤል ናዳል እይታ ግን በትናንትናው የዳቪስ ካፕ ፍጻሜ ወሳኙ ሰው የሀገሩ ልጅ ሮቤርቶ ባውቲስታ አጉት ነው። ምክንያቱ ደግሞ ባለፉት ቀናት ሮቤርቶ አባቱ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተውም ቢኾን ለድል መብቃቱ ነው። ራፋኤል በሀገሩ ልጅ መደመሙን በዚህ መልኩ ነው የገለጠው።

«እኔ ስምንቱን ጨዋታዎች አሸንፌያለሁ። ኾኖም በዚህ የዳቪስ ካፕ ግጥሚያ ወሳኙ ሰው ሮቤርቶ ነው። ለእኔ እሱ ያደረገው ማንም ሰው ሊያደርገው የማይችል ነው ማለት ይቻላል። እንዴት እንደማብራራው እንጃ። በቀሪ ሕይወቴ በሙሉ አብነቴ ይኾናል። አባቱ በመሞታቸው መሄድ ነበረበት። ከዚያ ቅዳሜ ዕለት ተመልሶ መጥቶ ከእኛ ጋር አብሮ ከተለማመደ በኋላ ዛሬ በከፍተኛ ብቃት ለመጋጠም ዝግጁ ኾኗል። ይኽ ፈጽሞ የማይታመን ነው።»

ራፋኤል ናዳል ዴኒስ ሻፖቫሎቭን 6 ለ3 እና 7 ለ6 በጥቅሉ 2 ለ0 ከማሸነፉ በፊት ባውቲስታ አጉት ፌሊክስ አውገር አሊያሲሜን 1 ለ0 እየመራ ነበር። ማሸነፉን እንዳረጋገጠም ጣቱን ወደ ሰማይ ጠቁሞ በእንባ እንደተዋጠ ደጋፊዎቹን አመስግኗል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ተስፋለም ወልደየስ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW