1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ስፖርት፤  ኅዳር 17 ቀን፣ 2010 ዓ.ም

ሰኞ፣ ኅዳር 17 2011

በደቡብ አሜሪካ ውስጥ ትናንት ሊከናወን ቀጠሮ ተይዞለት የነበረው የኮፓ ሊበርታዶሬስ የፍጻሜ ግጥሚያ በደጋፊዎች ኹከት ላልተወሰነ ጊዜ በድጋሚ ተራዝሟል። ኮፓ ሊበርታዶስ (የነጻነት ዋንጫ) በደቡብ አሜሪካ ዘንድ ልክ እንደ አውሮጳው ሻምፒዮንስ ሊግ የሚቆጠር የእግር ኳስ ፍልሚያ ነው።

Argentinien Copa Libertadores - Finale
ምስል picture-alliance/dpa/J. Romero

ስፖርት፣ ህዳር 17 ቀን፣ 2011 ዓም

This browser does not support the audio element.

የኢትዮጵያ ብስክሌት ፌዴሬሽን የብስክሌት ተፎካካሪዎቹን አስመራ ጎዳናዎች ላይ እንዲወዳደሩ አድርጓል። ትናንት በተጠናቀቀው ሽቅድምድም ኢትዮጵያውያን በሴት እና በወንድ በተለያዩ የእድሜ ዘርፎች ተወዳድረዋል። መነሻውን ከምንሊክ አደባባይ አድርጎ ከቀናት በኋላ አስመራ የሚጠናቀቅ የብስክሌት ውድድርም በትናንትናው እለት ተጀምሯል። ስለውድድሩ ዓላማ እና ቀጣይነት የኢትዮጵያ ብስክሌት ፌዴሬሽን ዳይሬክተር ለDW ማብራሪያ ሰጥተዋል። የጀርመን ቡድደስሊጋ፣ የእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ እና የስፔን ላሊጋ የሳምንቱ መጨረሻ ግጥሚያዎችንም እንዳስሳለን። በዓለም ዙሪያ በርካቶች ሲጠብቁት የነበረው የደቡብ አሜሪካ «ሱፐርክላሲኮ» የፍጻሜ ግጥሚያ በደጋፊዎች ኹከት ዳግም ለሌላ ቀን ተላልፏል። ዝርዝር ዘገባ ይኖረናል።  አብራችሁን ቆዩ!

የኢትዮጵያ እና የኤርትራ የሠላም ወዳጅነትን በማሰብ በሚል ኢትዮጵያውያን ብስክሌተኞች ወደ አስመራ ጉዞ ጀምረዋል። ለጊዜው ቁጥራቸው 19 የኾኑ ብስክሌተኞች ትናንት ጉዟቸውን የጀመሩት አዲስ አበባ ከዳግማዊ ምንሊክ አደባባይ ነው። ብስክሌተኞቹ የተለያዩ ከተሞችን በማቋረጥ አስመራ ለመድረስ ያሰቡት በሳምንቱ እሑድ ነው። ይኽንኑ ጉዞ በተመለከተ የኢትዮጵያ ብስክሌት ፌዴሬሽን ዳይሬክተር አቶ ግዛቸው መኮንን ለDW በስልክ በሰጡት ማብራሪያ  በአንዳንድ የመገናኛ ብዙኃን እንደተገለጠው ውድድር አለመኾኑን ተናግረዋል።

ትናንት ጉዞውን ከጀመረው የኢትዮጵያ ብስክሌት ቡድን ጋር በመጓዝ ዛሬ ደሴ የገቡትን የአዲስ አበባ ብስክሌት ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ረዘነ በየነንም በስልክ አነጋግረናቸዋል። ስለ ጉዞው ዓላማ በመግለጥ ይንደረደራሉ።

ኤርትራ መዲና አስመራ ውስጥ ትናት በተከናወነው በአይነቱ የመጀመሪያ የኾነው የአፍሪቃ ብስክሌት ፌዴሬሽን ውድድር ላይ የኢትዮጵያ ቡድን በሦስተኛ ደረጃ አጠናቋል። ውጤቱ የተገኘው በሴት ተወዳዳሪዎች ሲኾን፤ በአዋቂዎችም ኾነ ከ23 ዓመት በታች በሁለቱም ጾታዎች በተደረገው ውድድር ኤርትራውያን አንደኛ ወጥተዋል። የኹለተኛ ደረጃውን ደቡብ አፍሪቃ አግኝታለች።

ምስል Reuters/T. Mukoya

በደቡብ አሜሪካ ውስጥ ትናንት ሊከናወን ቀጠሮ ተይዞለት የነበረው የኮፓ ሊበርታዶሬስ የፍጻሜ ግጥሚያ በደጋፊዎች ኹከት ላልተወሰነ ጊዜ በድጋሚ ተራዝሟል። ውድድሩ በአርጀንቲናዋ መዲና ቦነስ አይረስ ከተማ ውስጥ ሊከናወን ቀጠሮ ተይዞለት የነበረ ሲኾን፤ ግጥሚያውም በሪቨር ፕሌት እና ቦካ ጁኒየርስ መካከል ነበር። ኾኖም የቦካ ጁኒየርስ ተጨዋቾችን አሳፍሮ የነበረው አውቶቡስ ላይ በተቀናቃኝ ቡድን ደጋፊዎች በተወረወሩ ድንጋዮች እና ቁሳቁሶች ተጨዋቾች የመፈንከት እና በመስታወት ስብርባሪ ጉዳት ደርሶባቸዋል።

የፍጻሜ ጨታው ለቅዳሜ ተይዞ በነበረው ውጥረት እና በቦካ ጁኒየርስ ቡድን ጥያቄ ለእሁድ ተላልፎ ነበር። እሁድ እለት ግን የሪቨር ፕሌት ደጋፊዎች ጥቃት በመሰንዘራቸው በመላው ዓለም በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው ግጥሚያ ላልተወሰነ ጊዜ መራዘሙ ተገልጧል።  ኮፓ ሊበርታዶስ (የነጻነት ዋንጫ) በደቡብ አሜሪካ ዘንድ ልክ እንደ አውሮጳው ሻምፒዮንስ ሊግ የሚቆጠር የእግር ኳስ ፍልሚያ ነው። ኹለቱ ቡድኖች ከበፊትም ጀምሮ በጠላትነት የሚተያዩ ሲኾን፤ ቀደም ሲል ባደረጉት ግጥሚያ 2 ለ2 ነበር የተለያዩት።

በጀርመን ቡንደስሊጋ ባየር ሙይንሽን የወትሮ ኃያልነቱን እና የበላይነቱን ለቦሩስያ ዶርትሙንድ አስረክቧል። ባየር ሙይንሽን በደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ 17ኛ ላይ ከሚገኘው ፎርቱና ዱስልዶርፍ ጋር ቅዳሜ እለት ባደረገው ግጥሚያ ባልተጠበቀ መልኩ ሦስት እኩል መውጣቱ በርካቶችን አስደምሟል። በእለቱ ማይንትስን 2 ለ1 የረታው ቦሩስያ ዶርትሙንድ በደረጃ ሰንጠረዡ አንደኛ ላይ ሰፍሮ ባየር ሙይንሽንን በ9 ነጥብ ርቆታል። አምስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ባየር ሙይንሽን 21 ነጥብ አለው።

ምስል Getty Images/Bongarts/T. Kienzle

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ቅዳሜ እለት ዌስትሀም ዩናይትድን 4 ለ 0 ያንኮታኮተው ማንቸስተር ሲቲ በ35 ነጥብ አንደኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ዋትፎርድን 3 ለ0 ያሸነፈው ሊቨርፑል 33 ነጥብ ይዞ ማንቸስተር ሲቲን ይከተላል። ቶትንሀም በ30 ነጥብ ሦስተኛ ቸልሲ በ28 አራተኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ። ትናንት በርመስን 2 ለ1 ያሸነፈው አርሰናል አምስተና ደረጃ ላይ ይገኛል። ከኤቨርተን ዝቅ ብሎ በ7ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ማንቸስተር ዩናይትድን በስድስት ነጥብ ይበልጠዋል።

በስፔን ላሊጋ ትናንት ቫላዶሊድን 1 ለምንም ያሸነፈው ሴቪላ በደረጃ ሰንጠረዡ በ26 ነጥብ ቀዳሚ ነው። ቅዳሜ እለት ከአትሌቲኮ ማድሪድ ጋር አንድ እኩል በመለያየት ነጥብ የጣለው ባርሴሎና በ25 ይከተላል። አትሌቲኮ ማድሪድ በ24 ነጥብ ሦስተኛ ነው። ሪያል ማድሪድ 20 ነጥብ ይዞ ስድስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።  

ትናንት አቡዳቢ ላይ በተጠናቀቀው የፎርሙላ አንድ የመኪና ሽቅድምድም የብሪታንያው አሽከርካሪ ሌዊስ ሐሚልተን በመርሴዲስ ተሽከርካሪው አሸናፊ ኾኗል። ዘንድሮ በተጠናቀቀው የውድድር ዘመንም 408  ነጥብ በመሰብሰብ ኃያልነቱን አስመስክሯል። የፌራሪ አሽከርካሪው ጀርመናዊ ተፎካካሪ ሠባስቲያን ፌትል በ320 አጠቃላይ ነጥብ በኹለተኛነት አጠናቋል። የሦስተኛ ደረጃውን ያገኘው ኪሚ ራይኮነን ሲኾን፤  251 ነጥብ መሰብሰብ ችሏል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ኂሩት መለሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW