1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ስፖርት፤ ኅዳር 22 ቀን፣ 2012 ዓ.ም

ሰኞ፣ ኅዳር 29 2012

የባየር ሙይንሽን ጊዜያዊ አሰልጣኝ ዲተር ሐንሲ ፍሊክ ዋና አሰልጣኝ ሊኾኑ እንደሚችሉ የቡድኑ ፕሬዚደንት ዛሬ ዐስታወቁ። በጀርመን ቡንደስ ሊጋ ፉክክሩ ተጠናክሯል። በአንጻሩ በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ሊቨርፑል በመሪነት ለብቻው ርቆ እየገሰሰ ነው።

1. Bundesliga VfL Wolfsburg vs Werder Bremen | Tor (1:2)
ምስል Imago Images/J. Huebner

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

This browser does not support the audio element.

የባየር ሙይንሽን ጊዜያዊ አሰልጣኝ ዲተር ሐንሲ ፍሊክ ዋና አሰልጣኝ ሊኾኑ እንደሚችሉ የቡድኑ ፕሬዚደንት ዛሬ ዐስታወቁ። በጀርመን ቡንደስ ሊጋ ፉክክሩ ተጠናክሯል።  በአንጻሩ በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ሊቨርፑል በመሪነት ለብቻው ርቆ እየገሰሰ ነው። በ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ የሩጫ ውድድር አዲስ ክብረ-ወሰን ተሰብሯል። ዓለም አቀፉ ጸረ ኃይል ሰጪ መድኃኒት ኩባንያ ሩስያ ላይ ርምጃ ለመስወሰድ ቀጠሮ ይዟል። ርምጃው ምን ያኽል ብርቱ ይኾናል? ጥያቄ አጭሯል።  በዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማኅበራት ፌዴሬሽን (FIFA)ኢትዮጵያ ደረጃዋን በአምስት አሻሽላለች። 

እግር ኳስ

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ቅዳሜ ዕለት ብራይተንን 2 ለ1 ያሸነፈው ሊቨርፑል ነጥቡን 40 አድርሶ የመሪነት ደረጃውን ተቆናጧል። ትናንትኤቨርተንን በተመሳሳይ 2 ለ1 ድል ያደረገው ላይስተር ሲቲ ሊቨርፑልን በ8 ነጥብ ርቆ ይከተለዋል። አንድ ሰሞን የሊቨርፑል ዋና ተፎካካሪ ኾኖ የነበረው ማንቸስተር ሲቲ ቅዳሜ ዕለት ከኒውካስል ጋር ባደረገው ግጥሚያ ኹለት እኩል ተለያይቶ ነጥብ በመጣሉ በደረጃ ሰንጠረዡ ከሊቨርፑል ጋር ተራርቋል። ማንቸስተር ሲቲ እስካሁን ባደረጋቸው 14 ግጥሚያዎች 29 ነጥብ መሰብሰብ ችሏል። በሊቨርፑል በ11 ነጥብ ተበልጧል። ቸልሲ በበኩሉ 26 ነጥብ ይዞ አራተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ትናንት ከአስቶን ቪላ ጋር ኹለት እኩል በመለያየት ነጥብ የተጋራው ማንቸስተር ዩናይትድ 18 ነጥብ ይዞ 9ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።  ከማንቸስተር ዩናይትድ በአንድ ነጥብ እና በአንድ ደረጃ ከፍ ብሎ የሚገኘው አርሰናል ትናንት ከኖርዊች ጋር 2 እኩል ተለያይቷል።

ምስል AFP/F. Walschaerts

በጀርመን ቡንደስ ሊጋ አራተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ባየር ሙይንሽን ጊዜያዊ አሰልጣኝ የዘንድሮ የውድድር ክፍለ-ዘመን እስኪጠናቀቅ ድረስ ዋና አሰልጣኝ ኾነው እንደሚቀጥሉ ተገልጧል። ይኽ የተገለጠው ዛሬ ለንባብ በበቃው ኪከር የተሰኘው በጀርመንኛ ቋንቋ የሚቀርብ የድረገጽ ጋዜጣ ነው። ኪከር ከባየር ሙይንሽን የቀድሞ የረዥም ጊዜ አሰልጣኝ ጋር እሁድ ዕለት አድርጎ ዛሬ ባወጣው ዘገባው፦ «ሐንሲ ፍሊክ ዋና አሰልጣኝነቱን ለቦታው ምቹ በመኾናቸው የዘንድሮ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ እስኪጠናቀቅ አስቀድመው አረጋግጠውታል» ማለታቸውን አትቷል።

የባየር ሙይንሽን የሥራ ኃላፊ ካርል ሐይንትስ ሩመኒገ በበኩላቸው ለሐንሲ ፍሊክ አድናቆታቸውን ገልጠዋል። ትናንት በቡንደስ ሊጋው በባየር ሌቨርኩሰን 2 ለ1 ቢሸነፉም በትናንቱ አጨዋወታቸው የሚቀጥሉትን ግጥሚያዎች አሸንፈው ቡድናችንን ወደ መሪነቱ ከፍ እንደሚያደርጉት አልጠራጠርም ብለዋል። ኾኖም ሩመኒገ ቀደም ብለው በሰጡት በዚሁ ቃለ መጠይቅ ጊዜያዊ አሰልጣኙ በቡድኑ የዋና አሰልጣኝነት ቦታ የማግኘታቸው ነገር ጊዜ እንደሚያስፈልገው ጠቁመዋል።

በጎርጎሪዮሱ የ2019 ዓመት ውድድር እስኪጠናቀቅ ድረስ ያሉትን ጨዋታዎቹንም መመልከት ይሻሉ። የባየር ሙይንሽን ፕሬዚደንት እና ዋና ሥራ አስኪያጅ የሚገኙበት አመራር ሐንሲ ፍሊክ በቡድኑ ውስጥ ያጫሩት የቡድን መንፈስ እና የአሰለጣጠን ስልታቸውን ወዶላቸዋል።

ምስል Getty Images/Bongarts/S. Widmann

ሐንሲ ጀርመን የ2014ቱን የዓለም ዋንጫ በበላችበት ወቅት የጀርመን ብሔራዊ ቡድን ዋና አሠልጣኝ ዮአሒም ሎይቭ ረዳት ነበሩ።  በባየር ሙይንሽንም የቀድሞው አሰልጣኝ ኒኮ ኮቫች ልክ የዛሬ ወር በአይንትራኅት ፍራንክፉርት የ5 ለ1 ከባድ ሽንፈት ገጥሟቸው እስኪባረሩ ድረስ ረዳት አሰልጣኝ ኾነው ሠርተዋል።

ሐንሲ ፍሊክ ብቃታቸው ተደብቆ የቀረ አሰልጣኝ ናቸው ሲሉ የባየር ሙይንሽን አመራርም ኾኑ በርካታ የጀርመን ዕውቅ ተጨዋቾች አድናቆታቸውን ገልጠዋል። እስካሁን በቡንደስሊጋው እና በሻምፒዮንስ ሊግ ግጥሚያ አራት ጊዜ ሲያሸንፉ፤ ሽንፈት የገጠማቸው ትናንትና ብቻ ነው። ሐንሲ ፍሊክ ትናንት እስከተሸነፉበት ጊዜ ድረስ ባደረጓቸው አራት ግጥሚያዎች አንድም ግብ ሳይቆጠርባቸው 16 ግቦችን አስቆጥረዋል። ቦሩስያ ዶርትሙንድ እና ዱይስልዶርፍን በቡንደስ ሊጋው በተመሳሳይ 4 ለዜሮ ድል ሲያደርጉ፤ በሻምፒዮንስ ሊግ ደግሞ የግሪኩን ፕሬውስ 2 ለ0 አሸንፈዋል። ባለፈው ማክሰኞ በሻምፒዮንስ ሊጉ ግጥሚያ ደግሞ የሠርቢያው ሮተር ሽተርን ቡድንን በሜዳው ቤልግሬድ ውስጥ ግን እጅግ አሸማቀው 6 ለ0 ነበር ያደባዩት።  

ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማኅበራት ፌዴሬሽን (FIFA) በየዓመቱ በሚሰጠው የሃገራት ደረጃ ኢትዮጵያ እንደ ጎርጎሪዮሱ አቆጣጠር ካለፈው የ2018 ዓመት ዘንድሮ የአምስት ደረጃዎችን ማሻሻል ችላለች። ፊፋ ባለፈው ሳምንት ረቡዕ ባወጣው ደረጃ መሰረት የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ዘንድሮ ከ151ኛ ወደ 146ኛ የተሻሻለው። ለመኾኑ ይኽ ምን ያሳያል፤ ይበል የሚያሰኝ ነው ወይንስ ገና ብዙ የሚቀር ነገር አለ? የእግር ኳስ ስፖርት ጋዜጠኛ ዖምና ታደለ «አምስት ደረጃዎች ማሻሻል ማለት በጨዋታ ውጤት ተመስርቶ የመጣ ስለኾነ አስገራሚ ላይኾን ይችላል» ብሏል። ይልቁንስ ብሔራዊ ቡድኑ በተደጋጋሚ ወደ አፍሪቃ ዋንጫ መሳተፍ የሚችልበትን ስልት ነድፎ ፌዴሬሽኑ እና ቡድኖችን ማጠናከር እጅግ አስፈላጊ መኾኑን ዖምና አክሏል። 

አትሌቲክስ

ኡጋንዳዊው አትሌት ጆሹዋ ቼፕቴጊ በ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ የዓለም ክብረ-ወሰን መስበር ችሏል። አዲስ ያሻሻለው ክብረ-ወሰን በ26 ደቂቃ ከ38 ሰከንድ ተመዝግቦለታል። የ23 ዓመቱ ወጣት አትሌት ከዚህ ቀደም እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2010 በኬንያው ሯጭ ሌዎናርድ ኮሞ ተይዞ የቆየውን ክብረ-ወሰን በስድስት ሰከንዶች ማሻሻል ችሏል። አትሌት ጆሹዋ ቼፕቴጊ ባለፈው ጥቅምት ወር ዶሃ ውስጥ በተከናወነው የዓለም አትሌቲክስ ፌደሬሽኖች ማኅበር (IAAF) የ10 ሺህ ሜትር ውድድር አሸናፊ ነበር። ብርቱ ፉክክር በታየበት በዚያ የዓለም አትሌቲክስ ውድድር ኢትዮጵያዊው አትሌት ዮሚፍ ቀጀልቻ የሁለተኛነት ደረጃን አግኝቷል።  

ምስል Imago Images/Agencia Efe/J.C. Cardenas

ሩስያ አትሌቶቿ የኃይል ሰጪ ንጥረ ነገር እንዲጠቀሙ በመንግስት ዕውቅና ድጋፍ ይደረግላቸው ነበር በሚል ከማንኛውም የስፖርት አይነት ለአራት ዓመት ልትታገድ ጫፍ ደርሷል። ዓለም አቀፉ ጸረ ኃይል ሰጪ ንጥረ ነገር ኩባንያ (WADA)የፊታችን ሰኞ በሚያደርገው ስብሰባ ሩስያ ላይ ውሳኔ ለማስተላለፍ ቀጠሮ ይዟል። የአራት ዓመት እገዳው ጉዳይ ሩስያን ከወዲሁ እጅግ አሳስቧታል። የሩስያ ጸረ ኃይል ሰጪ ንጥረ ነገር ኩባንያ (RUSADA) ኃላፊ ዩሪ ጋኑስ የሀገሪቱ ፕሬዚደንት ቭላድሚር ፑቲን እጃቸውን አስገብተው ጉዳዩን የምር እንዲከታተሉት ጠይቀዋል። «ፕሬዚደንት ፑቲን ጣልቃ ሊገቡ ይገባል። በእውነቱ ያ ይኾናል ብዬ እጠብቃለሁ» ብለዋል። ዓለም አቀፉ ጸረ ኃይል ሰጪ ንጥረ ነገር ኩባንያ ሩስያ ላይ የአራት ዓመት ቅጣት ሊተላለፍ ይገባል የሚል ሐሳብ ያቀረበው ባለፈው ሳምንት ሰኞ ነበር። ዋዳ የፊታችን ሰኞ ሲሰበሰብ ቀደም ሲል ባቀረበው ሐሳቡ ጸንቶ ሩስያን ከቀጣዩ የ2020 የኦሎምፒክ ጨዋታዎች ጨምሮ ከማንኛውም ስፖርት ለሚቀጥሉት አራት ዓመታት ያግዳት ይኾን? የበርካቶች ጥያቄ ነው።  

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ኂሩት መለሰ

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW