ስፖርት
ሰኞ፣ ነሐሴ 23 2008 በፎርሙላ አንድ የቤልጂየም ግራንድ ፕሪ የመኪና ሽቅድምድም ጀርመናዊው አሽከርካሪ ኒኮ ሮዝበርግ ድል ቀንቶታል። የብሪታንያው ሌዊስ ሐሚልተን በሦስተኛነት አጠናቋል። በካናዳ በተከናወነው የኩቤክ የማራቶን ሩጫ አሸናፊው ኢትዮጵያዊ አትሌት ኤቢሳ መርጋ እጅጉ እንደ ኦሎምፒክ ባለድሉ ፈይሳ ሊሌሳ እጆቹን ግራና ቀኝ በማነባበር ተቃውሞውን አሳይቷል።
ካናዳ ውስጥ ትናንት በተከናወነው የኩቤክ የማራቶን ሩጫ ውድድር ኢትዮጵያዊው ኤቢሳ መርጋ እጅጉ 2:30:40 በመሮጥ ውድድሩን በአንደኛነት አጠናቋል። ኤቢሳ ውድድሩን ሲያጠናቅቅ ሁለት እጆቹን ወደ ላይ ከፍ በማድረግ ግራ እና ቀኝ በማነባበር የገዢው ፓርቲ መቃወሙን ካናዳ ውስጥ የሚገኘው የስፖርት ድረ-ገጽ (http://runningmagazine.ca) ዘግቧል። ድረ-ገጹ «የኩቤክ ማራቶን አሸናፊ የኦሎምፒክ ባለሜዳሊያው የፖለቲካ ተቃውሞን ደገመው» ሲልም ነው ለዘገባው ርእስ የሰጠው። ተመሳሳይ ምልክት ከአንድ ሳምንት በፊት ኢትዮጵያዊው ፈይሳ ሊሌሳ የብር ሜዳሊያ ባገኘበት የሪዮ ኦሎምፒክ የማራቶን ፉክክር ማሳየቱ የሚታወስ ነው። ድረ-ገጹ አትሌት ኢብሳ መርጋ እጅጉ ካናዳ ውስጥ በሚደረጉ ውድድሮች በተደጋጋሚ ተሳታፊ መሆኑን ጠቅሷል። ከሰኔ 18 ቀን 2008 ዓም አንስቶም አትሌት ኤቢሳ የመኖሪያ አድራሻው ቶሮንቶ ከተማ ውስጥ እንደሆነም ድረ-ገጹ አትቷል።
ሦስተኛ ሳምንቱን በያዘው የእንግሊዙ የፕሬሚየር ሊግ የግር ኳስ ውድድር ማንቸስተር ሲቲ ትናንት ዌስት ሐም ዩናይትድን 3 ለ1 በመርታት ጥንካሬውን አሳይቷል። በቀድሞው የባየር ሙይንሽን አሰልጣኝ ፔፕ ጓርዲዮላ የሚመራው ማንቸስተር ሲቲ 9 ግቦች አስቆጥሮ 3 ተቆጥሮበታል። ቸልሲ 7 ግቦች አሉት። 2 የግብ ዕዳ አለበት። 6 ግቦችን ከመረብ ያሳረፈው ማንቸስተር ዩናይትድ የግብ ዕዳው 1 ብቻ ነው። አርሰናል እና ሊቨርፑል አንድ አንድ አሸንፈው ቀሪውን ሁለት ጨዋታዎች በሽንፈት እና በአቻ አጠናቀዋል። ከ20ዎቹም ቡድኖች ነጥብ የሌለው አንድም ቡድን የለም።
ለማንቸስተር ሲቲ ራሂም ስተርሊንግ ሁለት ግቦችን ሲያስቆጥር፤ ፈርናንዲኒሆም በኬቪን ደ ብሩውይነ ቅጣት የተመታችውን ኳስ በጭንቅላት ገጭቶ ከመረብ አሳርፏል። መደበኛው 90 ደቂቃ አልቆ በጭማሪው ሰአት ራሂም ስተርሊንግ ግብ ጠባቂው እና ተከላካዩ ላይ ተዝናንቶ በእርጋታ ነበር ግብ ያስቆጠረው። የመጀመሪያውም ግብ ብትሆን ከመሀል ሜዳ አንስቶ በድንቅ የኳስ ቅብብል የታጀበች ነበረች።
የጀርመን ቡንደስሊጋ የእግር ኳስ ጨዋታ የዘንድሮ የዙር ውድድር ባሳለፍነው ሳምንት ማሳረጊያ ላይ ተጀምሯል። በቡንደስ ሊጋው የሚወዳደሩ ቡድኖችን ይዘው ብቅ ያሉ አሰልጣኞች በአጠቃላልይ ዘንድሮም የቡንደስ ሊጋው ዋንጫ የባየር ሙይንሽን እንደሚሆን ተናግረዋል። በበርካታ ደጋፊዎች፣ ዳጎስ ባለ የማስታወቂቃ ገቢ እንዲሁም ከፍተኛ ተከፋይ ተጫዋቾችን ያካተተው ባየር ሙይንሽን ሙዳዩ በዩሮ የተትረፈረፈ ነው።
በእርግጥ በቡንደስ ሊጋው ተሳታፊ የሚሆኑ ቢድኖች በአጠቃላይ ከዓመት ዓመት ገቢያቸው ከፍ ያለ ነው፤ ባየር ሙይንሽን ላይ የሚደርስ ባይኖርም ማለት ነው። የጀርመን እግር ኳስ ሊጋ ሥራ አስኪያጅ ክርስቲያን ዛይፈርት « እንደው ለመሆኑ ከጀርመን ምጣኔ በአጠቃላይ በተረጋጋ መልኩ ዐሥር እጅ ልቆ የሚገሰግሰው ማን ነው?» ሲሉ የቡንደስ ሊጋው ገቢ በየጊዜው መጨመሩን ተናግረዋል። ዴሎይት በተሰኘው ኩባንያ የስፖርት ንግድ የሚያከናውኑ ቡድኖች አማካሪ ክፍል ኃላፊ የሆኑት ካርስተን ሆላሽም ተመሳሳይ ሐሳብ ነው ያላቸው።
«የሁሉንም የእግር ኳስ ሊጎች በተለይ ቡንደስ ሊጋውን የሚመለከት በእርግጥም ለረዥም ጊዙ በተረጋጋ መልኩ ያለማቋረጥ ዕድገት መኖሩን ያስተውላል።»
ይኽ የጀርመን እግር ኳስ ገቢ እጅግ መዳጎስ በለም አቀፍ ደረጃም ላቅ ያለ ነው። በዓለም አቀፍ ደረጃ የጀርመን ቡንደስ ሊጋ ከእንግሊዙ ፕሬሚየር ሊግ ቀጥሎ በገቢ ደረጃ የሚስተካከለው የለም።
«አጠቃላይ ገቢውን ወስደን ከሌሎች ሊጋዎች ጋር ብናነጻጽረው የቡንደስ ሊጋው ገቢ በሁለተኛ ደረጃ ላይ ነው የሚገኘው። ከፕሬሚየር ሊግ ቀጥሎ ማለት ነው። የፕሬሚየር ሊግ አጠቃላይ ገቢ ባለፈው የጨዋታ ዘመን 4,4 ቢሊዮን ዩሮ ደርሶ ነበር። ከዚያ ጋር ሲነጻጸር ቡንደስ ሊጋው 2,4 ቢሊዮን ዩሮ ደርሷል።»
ይኽ በገቢ ደረጃ ብቻ ሳይሆን በተመልካች ብዛትም በተለይ በአፍሪቃ ሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ቡንደስ ሊጋ ውድድር የስርጭት አድማሱን እያሰፋ ይገኛል። በዶይቸ ቬለ የሐውሳ እና ኪስዋሂሊ ቋንቋ ክፍሎች የቡንደስ ሊጋ ውድድሮችን በሬዲዮ ከዚህ ከቦን ከተማ በቀጥታ ማሰራጨት ጀምረዋል።
በኪስዋሂሊ ክፍል ጋዜጠኛ የሆነው ጆሴፋት ቻሮን ወደ ኪስዋሂሊ ክፍል በማቅናት በስቱዲዮዋቸው አነጋግሬው ነበር። ጆጤፋት ቀደም ሲል የኪስዋሂሊ ቋንቋ ሥርጭት ከቡንደስ ሊጋ የሚላክለትን አጫጭር የቪዲዮ ዘገባዎች እየተረጎመ ለአድማጮቹ ያቀርብ እንደነበር ጠቅሷል። ደቡብ አፍሪቃ ከተኪያሄደው የዓለም ዋንጫ በተለይ ደግሞ ጀርመን ካዘጋጀችው የ2006ቱ ውድድር ወዲህ በርካቶች ለቡንደስ ሊጋ ፍቅር እንዳደረባቸውም ተናግረዋል። የቡንደስ ሊጋ እግር ኳስ ጨዋታ በኪስዋሂሊ ክፍል መተላለፍ የጀመረው ባለፈው ቅዳሜ ነበር። ወዲያውኑ ከአድማጮች የተገኘው ምላሽ አስደሳች እንደነበር ጆሴፋት ተናግሯል።
«ከአድማጮች ያገኘነው ምላሽ እጅግ በጣም ደስ የሚል እና የሚያበረታታ ነው። በፌስቡክ ገጻችን በርካታ አስተያየቶች ደርሰውናል። ሰዎች ይኽን ዕድል ስለሰጠናቸው ምስጋናቸውን ለግሰውናል። አድናቆታቸውንም ገልጠውልናል። ለመጀመሪያ ጊዜ የቡንደስ ሊጋ ጨዋታዎችን ከጀርመን በቀጥታ ማስተላለፍ ጀምረናል።»
የቀጥታ ስርጭቱ ከቅዳሜ ባሻገር እሁድም ቢኖር ሲሉ አስተያየት ሰጪዎች መጠየቃቸውን ጆሴፋት ቻሮ ገልጧል። በውሉ መሰረት ጨዋታው ከመጀመሩ 5 ደቂቃ አንስቶ አጠቃላዩን ጨዋታ እንዲሁም የመሀል ዳኛው ፊሽካውን ከነፋበት አንስቶ ለ5ደቂቃ በአጠቃላይ በትንሹ 100 ደቂቃዎች የቀጥታ ስርጭት ያከናውናሉ። ስርጭቱ ከመደበኛው የኪስዋሂሊ የሬዲዮ ስርጭት ውጪ የሚከናወን ነው። በቀጥታ ከቦን ስቱዲዮ እየተላለፈ የኪስዋሂሊ ቋንቋን ከዶይቸ ቬለ ተቀብለው መልሰው በሚያስተላልፉ አፍሪቃ ውስጥ በሚገኙ ጣቢያዎች ላይም ይሰማል። የዶይቸ ቬለ የአማርኛ ክፍል ስርጭቶቹን ኢትዮጵያ ውስጥ እየተቀበለ መልሶ የሚያስተላልፍለት ጣቢያ ከዚህ ቀደም ቢያፈላልግም ሁኔታዎች ግን አመቺ አልሆኑም። የኪስዋሂሊው ጋዜጠኛ የመጀመሪያው የሆነውን የእግር ኳስ በቀጥታ የመዘገብ ዕድል በማገኘቱ የተሰማውን ስሜት እንዲህ ይገልጣል።
«በእውነቱ ለእኔ በጣም ነበር የደነቀኝ። ከዚህ ቀደም በሕይወቴ ሙሉ እግር ኳስን በቀጥታ ስርጭት ዘግቤ አላውቅም። እናናም ለመጀመሪያ ጊዜ ቡንደስሊጋን በቀጥታ እንዲዘግቡ ዕድሉ ለኪስዋሂሊ እና ሐውሳ ቋንቋ ክፍሎች ሲሰጥ ደስ ነበር ያለኝ። ስልጠናም ተሰጥቶናል። ለአለቃዬ ይኼን መሞከር አለብኝ ስለው ትንሽ ተጠራጥሮ ነበር። አንዳንድ ባልደረቦቼም ተመሳሳይ ሐሳብ ነበራቸው። ምክንያቱም የስፖርት ሰው አይደለሁም።»
ሆኖም ጆሴፋት ከባልደረባው ጋር ባለፈው ቅዳሜ ያቀረቡት የቡንድስ ሊጋ የእግር ኳስ የቀጥታ ዘገባ በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነትን እንዳገኘ አንዳንዶች እንደውም እሁድም ይደገምልን ማለታቸውን ጠቅሷል።
በፎርሙላ አንድ የቤልጂየም የግራንድ ፕሪ የመኪና ሽቅድምድም የመርሴዲስ አሽከርካሪው ኒኮ ሮዝበርግ አሸናፊ ኾኗል። በተመሳሳይ ለመርሴዲስ ቡድን የሚወዳደረው ሌዊስ ሐሚልተን ከኋላ ተነስቶ ሦስተኛ መውጣት ችሏል። የሬድ ቡል አሽከርካሪው ዳንኤል ሪካርዶ ሁለተኛ ወጥቷል። በአጠቃላይ ድምር ውጤት ግን አሁንም መሪው ሌዊስ ሐሚልተን ነው። ሌዊስ እስካሁን 232 ነጥቦችን ሰብስቧል። ኒኮ ሮዝበርግ 223 ነጥቦች ይዞ በሁለተኛነት ይከተላል። ዳንኤል ሪካርዶ 151 ነጥብ ይዞ ሦስተኛ ነው።
ማንተጋፍቶት ስለሺ
አዜብ ታደሰ