1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ስፖርት፤ ነሐሴ 28 ቀን፣ 2010 ዓ.ም

ሰኞ፣ ነሐሴ 28 2010

የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ለአፍሪቃ ዋንጫ ማጣሪያ ጳጉሜ 4 ከሴራሊዮን ጋር ይጋጠማል፤  ከቡሩንዲ አቻው ጋር ባደረገው የወዳጅነት ጨዋታ በሜዳው አቻ ተለያይቷል። የእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግና የጀርመን ቡንደስሊጋ ጨዋታዎችን ቃኝተናል። «የኢትዮጵያ ስፖርት አወቃቀርና ማኅበራት ከጀርመን ልምድ እይታ» የሚል ጽሑፍ ላይ ቃለ-መጠይቅ ይኖረናል።

Fußball Bundesliga RB Leipzig - Fortuna Düsseldorf
ምስል Getty Images/AFP/R. Michael

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

This browser does not support the audio element.

የኢትዮጵያ ብሔራዊ  የእግር ኳስ ቡድን ለአፍሪቃ ዋንጫ ማጣሪያ ጳጉሜ 4 ከሴራሊዮን ጋር ይጋጠማል፤  ከቡሩንዲ አቻው ጋር ባደረገው የወዳጅነት ጨዋታ በሜዳው አቻ ተለያይቷል። በሳምንቱ ማሳረጊያ በተደረጉ የእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ጨዋታዎች፦ ሊቨርፑል፣ ሳውዝሐምፕተን፣ ቸልሲ፣ ማንቸስተር ሲቲ፣ አርሰናል፣ ማንቸስተር ዩናይትድ፣ ዋትፎርድ እና ዎልቭስ ድል ቀንቷቸዋል።  በጀርመን ቡንደስሊጋ ባየር ሙይንሽን እና ሆፈንሀይም በሰፋ ልዩነት አሸንፈዋል። ጀርመን ነዋሪ የኾኑት ዶር ጸጋዬ ደግነህ፦ «የኢትዮጵያ ስፖርት አወቃቀርና ማኅበራት ከጀርመን ልምድ እይታ» በሚል ያቀረቡት ጽሑፍ ላይ በመንተራስ ቃለ-መጠይቅ አድርገንላቸዋል። ልምዳቸውን ያካፍሉናል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን የ2019 የአፍሪቃ ዋንጫ የምድብ ማጣሪያ ጨዋታውን የፊታችን እሁድ በሀዋሳ ዓለም አቀፍ ስታዲየም ከሴራሊዮን ጋር ያከናውናል። ሴራሊዮን ኢትዮጵያ በመጨረሻ ደረጃ በምትገኝበት ምድብ  3 ነጥብ ይዞ በሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። የኢትዮጵያ ቡድን በትናንትናው እለት በሀዋሳ ስታዲየም ባደረገው የወዳጅነት ጨዋታ ከቡሩንዲ አቻው ጋር አንድ እኩል ተለያይቷል።

በእሁዱ ጨዋታ ከምድቡ ሦስተኛ ደረጃ ላይ የምትገኘው ኬንያ አንደኛ ደረጃ ላይ ያለችውን ጋናን ታስተናግዳለች። ምድቡን ጋና በ3 ነጥብ እና 5 የግብ ክፍያ ትመራለች። ሴራሊዮን በተመሳሳይ 3 ነጥብ ኾኖም በ4 የግብ ክፍያ ተበልጣ በሁለተኛነት ትከተላለች። ኬንያ እና ኢትዮጵያ ነጥብ ሳይኖራቸው በ4 የግብ ክፍያ እዳ ይበላለጣሉ።

ምስል picture-alliance/dpa

ወደ እንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ እና የጀርመኑ ቡንደስ ሊጋ ጨዋታዎች ከማለፋችን በፊት  አንድ ቃለ መጠይቅ ይኖረናል። ቃለመጠይቁን ያደረግነው ከዶ/ር ጸጋዬ ደግነህ ጋር ነው። በአሁኑ ወቅት የአፍሪቃ ጂጁትሱ ፌዴሬሽን ስፖርት ምክትል ፕሬዚደንት ናቸው። እንዲሁም ዶ/ር ጸጋዬ የዓለም አቀፍ ጂጁትሱ ፌዴሬሽን የስነምግባር ኮሚሽን ምክትል ፕሬዚደንት ኾነው በማገልገል ላይ ይገኛሉ። «የኢትዮጵያ ስፖርት አወቃቀርና  ማኅበራት ከጀርመን ልምድ እይታ» በሚል ርእስ ዘለግ ያለ ጽሑፍ ለፌዴራል ወጣቶች እና ስፖርት ሚንሥትር  ልከዋል። ዶክተር ጸጋዬ መሰል ጽሑፎችን በተለያዩ ጊዜያት ለተለያዩ ባለሥልጣናት መላካቸውን ይናገራሉ።  አሁን ከላኩት ጽሑፍ በመንደርደርም የኢትዮጵያ የስፖርት አወቃቀር ምን ይመስላል? ምንስ መስተካከል አለበት ይላሉ በሚል ላቀረብንላቸው ጥያቄ «አኹን ያለው የስፖርት አሠራር እንግዲህ ሶሻሊስታዊ መሰል አሠራር ነው» ብለዋል።  «ስፖርቱ እስካሁን ባላደገበት ኹኔታ ላይ ነው ያለው» ሲሉም አክለዋል።

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ እስካሁን አራት ዙር ጨዋታዎች የተከናወኑ ሲኾን፤ ሊቨርፑል ምድቡን ይመራል። ቸልሲ እና ዋትፎርድ ከሊቨርፑል ጋር ተመሳሳይ 12 ነጥብ ይዘው በግብ ልዩነት ይከተላሉ። ሦስቱም ቡድኖች በሳምንቱ መገባደጃ ላይ ባደረጋቸው ግጥሚያዎች ድል ቀንቷቸዋል። ሊቨርፑል ቅዳሜ እለት ላይስተር ሲቲን ገጥሞ 2 ለ1 ያሸነፈ ሲኾን፤ ለቀያዮቹ እና ለጀርመናዊ አሰልጣኛቸው ዬርገን ክሎፕ የዘንድሮው የጨዋታ ዘመን እስካሁን ድንቅ የሚባል ነው።

ምስል Reuters/A. Yates

ሊቨርፑል ጨዋታው በተጀመረ ገና በአምስተኛው ደቂቃ ላይ ነበር ድንቅ ሙከራ በማድረግ የበላይነቱን ማሳየት የጀመረው። ጆን ሔንደርሰን በቀኝ በኩል ለሮቤርቶ ፊርሚኖ ያቀበለውን ኳስ ሮቤርቶ በቀጥታ ወደ ግብ ይልካታል። ግብ ጠበቂው ሙከራዋን ያጨናግፋል፤ በፍጥነት ሳላህ ወደ ግብ ቢልካትም ኳሷ ግን ዒላማዋን ስታ ወደ ውጭ ወጥታለች። ግብጻዊው አጥቂ ብቃት ከኾነ ሌላ ጊዜ ዐይኑን ጨፍኖ እንኳን ሊያገባት ይችል ነበር ።

ከዚህች ሙከራ ከአምስት ደቂቃ በኋላ ሊቨርፑል ዳግም ማጥቃቱን ቀጠለ። በዚህ ጊዜ በግራ በኩል ነው ጫናውን የፈጠረው። የስኮትላንድ ብሔራዊ ቡድን ተከላካይ በላይስተር ሲቲ ግብ ክልል በግራ በኩል ተጨዋቾችን አታሎ በቀጥታ የላካትን ኳስ ሳዲዮ ማኒ በግራ እግሩ መቶ ከመረብ አሳትርፏታል። ምንም እንኳን በአንድሪው ተጠናቃ የተላከች ኳስ ብትሆንም ይህች ግብ ለሳዲዮ ማኒ በአራተኛ ጨዋታ አራተኛ ግብ ኾና ተመዝግባለታለች።

ጨዋታው ከተጀመረ አንስቶ በአብዛኛው በመከላከል ላይ ያተኮሩት ላይስተር ሲቲዎች በ24ኛው ደቂቃ ላይ አንሰራርተው ሙከራ ቢያደርጉም ኳሷ በብራዚል ብሔራዊ ቡድኑ ግብ ጠባቂ አሊሰን ቤከር ተጨናግፋለች። የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ ሲል በቀኝ በኩል የተሻማችውን ኳስ ሮቤርቶ ፊርሚኖ በተረጋጋ ኹናቴ በጭንቅላት ገጭቶ ከመረብ አሳርፏታል። በዘንድሮ የጨዋታ ዘመን የመጀመሪያው ግብ ኾና ተመዝግባለታለች። 63ኛው ደቂቃ ላይ ላይስተር ሲቲ ባደረገው ጫና ኳስ ግብ ጠባቂው አሊሰን ጋር ብትደርስም አሊሰን ኳሷን አታልላሁ ብሎ በሠራው ጥፋት ተነጥቋል። እናም  ራሂድ ጊዛል በዜሮ ከመውጣት ያዳናቸውን ግብ ለላይስተር ሲቲ አስቆጥሯል።

ምስል picture-alliance/AP Photo/M. Meissner

በዕለቱ ሳውዝሐምተን ክሪስታል ፓላስን፤ እንዲሁም ቸልሲ በርመስን 2 ለ0 አሸንፈዋል። ማንቸስተር ሲቲ ኒውካስልን 2 ለ1 ሲሸኝ፤ ዌስትሀም በዎልቭስ 1 ለ0 ተረትቷል። ብሪንግቶን ከፉልሀም 2 እኩል፤ እንዲሁም ኤቨርተን ከሁደርስፌልድ አንድ እኩል ተለያይተዋል።  ትናንት አርሰናል ካርዲፍ ሲቲን 3 ለ2፤ ማንቸስተር ዩናይትድ በርንሌይን 2 ለ0 አሸንፈዋል። ዋትፎርድ ቶትንሀምን 2 ለ1 ድል አድርጓል።

የጀርመኑ ቡንደስሊጋ የዘንድሮ ውድድር ከተጀመረ ሁለተኛ ዙር ጨዋታዎች በሳምንቱ መጨረሻ ላይ ተከናውነዋል። ከምድቡ ባየርን፤ ቮልፍስቡርግ እና ትናንት ሻልከን 2 ለ 0 ያሸነፈው ሄርታ ቤርሊን በ6 ነጥብ ቀዳሚ ኾነዋል። ቦሩስያ ዶርትሙንድ እና ሞይንሽንግላድባህ በ2 ነጥብ ዝቅ ብለው ይከተላሉ። ባየር ሙይንሽን ቅዳሜ ዕለት ሽቱትጋርትን የሸኘው 3 ለ0 በኾነ ልዩነት ነው። ቮልፍስቡርግ በበኩሉ ባየር ሌቨርኩሰንን ቅዳሜ ዕለት 3 ለ1 ማሸነፍ ችሏል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አዜብ ታደሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW