1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ስፖርት፤ ነሐሴ  29 ቀን፣ 2009 ዓ.ም. 

ሰኞ፣ ነሐሴ 29 2009

በሩስያ አዘጋጅነት ከሰኔ 7 እስከ ሐምሌ 8 ቀን 2010 ዓም ለሚከናወነው የዓለም ዋንጫ የእግር ኳስ ጨዋታ ለማለፍ በመላው ዓለም የሚገኙ ሃገራት እየተፋለሙ ነው። በአውሮጳ በተከናወኑ የማጣሪያ ጨዋታዎች መካከል ወደ 200 የሚጠጉ የጀርመን ደጋፊዎች ቼክ ሪፐብሊክ ውስጥ ያሳዩት የዘረኝነት ምልክት እና ያሰሙት መዝሙር ጥያቄ አጭሯል።

WM Qualifikation - Deutschland gegen Tschechische Republik - Deutschland Fans
ምስል Reuters/D. W. Cerny

የስፖርት ዘገባ፦

This browser does not support the audio element.

ለዓለም ዋንጫ የእግር ኳስ ጨዋታ ማጣሪያ የአፍሪቃ እና የአውሮጳ ሃገራት ያደረጓቸውን ግጥሚያዎችን እንቃኛለን። በፎርሙላ አንድ የሚኪና ሽቅድምድም ጀርመናዊው ሰባስቲያን ፌትል በጥቂት ነጥቦች ተበልጦ የአንደኛነት ደረጃውን ለብሪታንያዊው አሽከርካሪ ሌዊስ ሐሚልተን አስረክቧል። በ10 ሺህ ሜትር የጎዳና ሩጫ ውድድር ሰንበሬ ተፈሪ አንደኛ በመውጣት ትናንት አሸናፊ ኾናለች።  ከዛው ከአትሌቲክስ ውድድር ሳንወጣ ከአትሌት ሙክታር እድሪስ እና ከዮሚፍ ቀጄልቻ ጋር ስዊዘርላንድ ውስጥ የተደረገ ቃለ መጠይቅ ክፍል ሁለት ይኖረናል። 

በሩስያ አዘጋጅነት ሐሙስ ሰኔ 7 ቀን 2010 ጀምሮ  እሁድ ሐምሌ 8 ቀን 2010 ዓም ልክ በአንድ ወሩ ለሚጠናቀቀው የዓለም ዋንጫ የእግር ኳስ ጨዋታ ለማለፍ በመላው ዓለም የሚገኙ ሃገራት እየተፋለሙ ነው። በአውሮጳ በተከናወኑ የማጣሪያ ጨዋታዎች መካከል ወደ 200 የሚጠጉ  የጀርመን ደጋፊዎች ቼክ ሪፐብሊክ ውስጥ ያሳዩት የዘረኝነት ምልክት  እና ያሰሙት መዝሙር ጥያቄ አጭሯል። ዝርዝሩን የአውሮጳ ሃገራት ማጣሪያ ጨዋታዎችን ስንቃኝ ወደ በኋላ ላይ እንመለስበታለን። በቅድሚያ የአፍሪቃ ሃገራት ያከናወኑትን የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ግጥሚያዎች እንመልከት።

ምስል picture-alliance/AA/F. Kotb

የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ በአፍሪቃ

የአፍሪቃ ሃገራት ባከናወኑት የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎች መካከል የሴኔጋል ቡድንን ለመግጠም መዲናዪቱ ዳካር ውስጥ ወደሚገኘው የሌፖልድ ሴዳር ሴንጎር ስታዲየም ያቀናው የቡርኪናፋሶ ብሔራዊ ቡድን ግብ ሳይቆጠርበት አቻ በመውጣቱ ነጥብ ተጋርቶ ተመልሷል። አይቮሪ ኮስት በበኩሉ ሊብሬቪል ከተማ ውስጥ የጋቦን አቻውን በሜዳው እና በደጋፊው ፊት 3 ለ0 አደባይቶ ኩም አስብሏል። ብሔራዊ የጀግኖች ስታዲየም በተሰኘው ሜዳ ላይ አልጀሪያን በሀገሯ ያስተናገደችው ዛምቢያ ድል ቀንቷት 3 ነጥብ ማግኘት ችላለች። ዛምቢያ አልጀሪያን በመዲና ሉሳካ በማሸነፍ ደጋፊዎቿን ጮቤ ያስረገጠችው 3ለ1 ድል በማድረግ ነው።  የማጣሪያ ጨዋታዎቹ ቀጥለው ዛሬ ካሜሩን በደጋፊዎቸ ፊት ያውንዴ ከተማው ውስጥ ከናይጀሪያ ጋር ስትገጥም፤ ከሁለት ሰአት ልዩነት በኋላ ደግሞ ጊኒ እና ሊቢያ የቱኒዚያዋ ሞናስቲር ከተማ ውስጥ ይገናኛሉ። ነገ ጥቋቁር ከዋክብቱ የጋና ተጨዋቾች ወደ ብራዛቪል ከተማ ተጉዘው ኮንጎን ይገጥማሉ።

የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ በአውሮጳ

በአውሮጳ ሃገራት መካከል በተደረጉ የዓለም ዋንጫ የማጣሪያ ግጥሚያዎች መካከል ደግሞ፦ ዛሬ ማታ ከሚከናወኑ 9 ግጥሚያዎች መካከል እንግሊዝ ስሎቫኪያን ስትገጥም ጀርመን ኖርዌይን ታስተናግዳለች። የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን ተጨዋቾች ለብሔራዊ ቡድኑ ጥልቅ ፍቅር የላቸውም ሲሉ ደጋፊዎች በማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች ተችተዋል። በተለይ የእንግሊዝ ቡድን የማልታ አቻውን ዐርብ እለት 4 ለ0 ባሸነፈበት ጨዋታ ደጋፊዎች ቅሬታቸውን በጩኸት ሲገልጡ ነበር።  

ምስል Reuters/D. Cerny

በስኬታማው አሰልጣኝ ዮኣሂም ሎይቭ የሚመራው የጀርመን ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ምሽቱን ሽቱትጋት ከተማ ውስጥ የኖርዌይ ቡድንን ያስተናግዳል። ጀርመን የዛሬውን ግጥሚያ ካሸነፈች እና በሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው የሰሜን አየርላንድ ቡድን ቼክ ሪፐብሊክን መርታት ከተሳነው፤ ጀመርን ስምንት ተከታታይ ጨዋታዎችን በማሸነፍ ለዓለም ዋንጫ ማለፏን ከወዲሁ ታጋግጣለች። 

የጀርመን ቡድን ከቼክ ሪፐብሊክ አቻው ጋር ለመግጠም ወደ ቼክ መዲና ፕራኅ ሲያመራ አብረው ያቀኑ ወደ 200 የሚጠጉ ጽንፈኛ ደጋፊዎች ባሰሙት የዘረኝነት መፈክር የጀርመን እግር ኳስ ፌዴሬሽን ኃላፊ በአውሮጳ እግር ኳስ ማኅበራት ኅብረት (UEFA)ቀርቦ እንዲያብራራ ተጠይቋል። የጀርመን እግር ኳስ ማኅበር ፕሬዚዳንት ራይንሀርድ ግሪንድል ኪከር ለተሰኘው የስፖርት መጽሄት ዛሬ እንደተናገሩት ከሆነ የስታዲየም መግቢያ ቲኬት ሽያጭ ላይ መፍትኄ ሊበጅ ይገባል ብለዋል።  «በመላው አውሮጳ የቲኬት ግዢ ጉዳይን የበለጠ ቁጥጥር ስለሚደረግበት መንገድ ከአውሮጳ ማኅበራት ጋር በአንድነት መነጋገር ያስፈልገናል» ብለዋል። እንደ ጀርመን ቡድን  ሥራ አስኪያጅ  ዖሊቨር ቢርሆፍ  መግለጫ በዘረኝነት የተሳተፉት የጀርመን ደጋፊዎች የስታዲየም መግቢያ ቲኬት የገዙት ከጀርመን ፌዴሬሽን ዕውቅና ውጪ መኾኑን አስገንዝበዋል። ፖሊስ በዘረኝነት ከተሳተፉት ደጋፊዎች መካከል 13 ያኽሉ ከድሬስደን ከተማ መኾናቸውን በመግለጥ ሁለቱ ከፖሊስ ማስጠንቀቂያ የተሰጣቸው እንደነበር ገልጧል። በዐርቡ ግጥሚያ የጀርመን ቡድን የቼክ አቻውን ያሸነፈው 2 ለ1 ነበር።

ምስል Reuters/M. Rossi

አትሌቲክስ
ትናንት ሆላንድ ቲልቡርግ ከተማ ውስጥ በተከናወነው የ10,000 ኪሎ ሜትር የሩጫ ውድድር ኢትዮጵያዊቷ ሰንበሬ ተፈሪ በአንደኛነት አጠናቃለች። ሠንበሬ ውድድሩን ለማጠናቀቅ የፈጀባት ጊዜ 30 ደቂቃ ከ38 ሰከንድ ነው። ሠንበሬ ከሆላንዱ ውድድር በፊት ሦስተኛ የወጣችበትን የብራስልሱ የዲያመንድ ሊግ የሩጫ ፉክክር ያከናወነችው ዐርብ እለት ነበር። በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ ሌላ ድል ማስመዝገቧ የአትሌቷን ብቃት የሚያሳይ ኾኗል። 

የመኪና ሽቅድምድም 
በፎርሙላ አንድ የጣሊያን ግራንድ ፕሪ የመኪና ሽቅድምድም  የብሪታኒያው ተፎካካሪ ሌዊስ ሐሚልተን በአንደኛነት ሲያጠናቅቅ ጀርመናዊው ተፎካካሪው ሰባስቲያን ፌትል በሦስተናነት ጨርሷል። ሌዊስ ሐሚልተን በትናንቱ ፉክክር ሁለተኛ የወጣው ቫልተሪ ቦታስን የቀደመው በ4 ደቂቃ ልዩነት ነው። ሁለቱም የመርሴዲስ አሽከርካሪዎች ናቸው። ሌዊስ ሐሚልተን በትናንቱ ድል በአጠቃላይ ነጥብ ሰባስቲያን ፌትልን ለጥቂት በልጦ የአንደኛነቱን ስፍራ ተረክቧል። እስካሁን በተደረጉ ውድድሮች ሌዊስ ሐሚልተን 238    ነጥቦችን ሲሰበስብ፤ የፌራሪው አሽከርካሪ ሰባስቲያን ፌትል 235 ነጥቦች አሉት። 

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሰ


 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW