1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጥቅምት 19 ቀን፣ 2016 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ጥቅምት 19 2016

በቤጂንግ ማራቶን የወንዶች ፉክክር ኢትዮጵያውያኑ ድል ሲቀናቸው፤ በሴቶች ውድድር ኬንያውያቱ ከ1ኛ እስከ 3ኛ በመግባት አሸንፈዋል። የደቡብ አፍሪቃ የራግቢ ብሔራዊ ቡድን በፓሪስ የዐለም ራግቢ ፍፃሜ ኒውዚላንድን ድል አድርጎ ዋንጫውን ለ4ኛ ጊዜ ወስዷል ። ማን ዩናይትድ በሜዳው ኦልትራፎርድ በማንቸስተር ሲቲ ጉድ ሆኗል ።

ቡንደስ ሊጋ፦
ቡንደስ ሊጋ፦ ቦሁም ከማይንትስ ሲጋጠምምስል Hesham Elsheri/Eibner-Pressefoto/Imago Images

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

This browser does not support the audio element.

በቤጂንግ ማራቶን የወንዶች ፉክክር ኢትዮጵያውያኑ ድል ሲቀናቸው፤ በሴቶች ውድድር ኬንያውያቱ ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ተከታትለው በመግባት አሸንፈዋል ። የኢትዮጵያሴቶች ብሔራዊ ቡድን በፓሪስ ኦሊምፒክ የማጣሪያ ጨዋታዎች የሁለተኛ ዙር የመልስ ግጥሚያውን ነገ ያከናውናል ።  ቡድኑ ትናንት ወደ ናይጀሪያ ዋና ከተማ አቡጃ አቅንቷል ። ማን ዩናይትድ በሜዳው ኦልትራፎርድ በማንቸስተር ሲቲ ጉድ ሆኗል ። የደቡብ አፍሪቃ የራግቢ ብሔራዊ ቡድን በፓሪስ የዐለም ራግቢ ፍፃሜ ኒውዚላንድን ድል አድርጎ ዋንጫውን ለአራተኛ ጊዜ ወስዷል ። በከባድ ሚዛን ቡጢ ፍልሚያ ታይሰን ፉሪ በዝረራ ማሸነፌ እርግጥ ነው ያለበት ግጥሚያ ከገመተው በላይ ብርቱ እንደነበር ተናገረ ። የቅዳሜው ግጥሚያ በጠበበ የነጥብ ልዩነት ነበር የተጠናቀቀው ። 

አትሌቲክስ

በቻይና የቤጂንግ ማራቶን ሩጫ የወንዶች ፉክክር ኢትዮጵያዊው አትሌት ደሬሳ ገለታ አሸነፈ ። በሴቶች ተመሳሳይ ፉክክር ኬንያዊቷ ቪቢያን ቼፕኪሩይ አንደኛ ወጥታለች ። ትናንት በነበረው የማራቶን ሩጫ ፉክክር፦ አትሌት ደሬሳ ለድል የበቃው  ሁለት ሰአት ከሰባት ደቂቃ ከዐርባ አንድ ሰከንድ በመሮጥ ነው ። ሌላኛው ኢትዮጵያዊ አትሌት ይሁንልኝ አዳነ ለጥቂት በአንድ ሰከንድ ብቻ ተቀድሞ የሁለተኛ ደረጃ አግኝቷል ። ኬኒያዊው ፌሊክስ ኪፕኮይች ሦስተኛ ደረጃ ሲያገኝ፤ የገባበትም 2:07:44 ሆኖ ተመዝግቧል ። በሴቶች ፉክክር ኬንያዊቷ ቪቢያን ቼፕኪሩይ ያሸነፈችው 2:21:57 በመሮጥ ነው ። የሴቶቹን ፉክክር ሁለተኛ እና ሦስተኛም ኬንያውያት በማሸነፍ ጠቅልለው ወስደውታል ። የቻያናዋ ሯጭ ሉ ይንግ፦ ጃኔት ሩጉሩ እና ሔላ ኪፕሮፕን ተከትላ የአራተኛ ደረጃ አግኝታለች ። 

አትሌቲክስ፦ ሯጮች ሲሮጡ ። ፎቶ ከማኅደርምስል Charlie Neibergall/AP/picture alliance

እግር ኳስ

የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ለመልስ ጨዋታ ትናንት የናይጀሪያ ዋና ከተማ አቡጃ ናምዲ አዚክዌ ኢንተርናሽናል አየር ማረፊያ ገብቷል ። ቡድናችን ከናይጄርያ ጋር የመልስ ጨዋታውን ነገ፣ ጥቅምት 20 ቀን፣ 2016 ዓም ያከናውናል።  ባለፈው ሳምንት ረቡዕ በነበረው የመጀመሪያው ግጥሚያ የኢትዮጵያ ቡድን አዲስ አበባ ውስጥ ከናይጀሪያ ቡድን ጋር አንድ እኩል ነው የተለያየው ። በወቅቱ ለኢትዮጵያ፦ በ6ኛው ደቂቃ ላይ ብርቄ አማረ ስታስቆጥር፤ ናይጀሪያ አቻ የምታደርገውን ግብ 51ኛው ደቂቃ ላይ ያገኘችው በራሺዳት አጂባዴ ነው ።  ከኢትዮጵያ እና የናይጄሪያ ኦሊምፒክ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን የነገ አሸናፊ ወደ ቀጣዩ ዙር ያልፋል ።  

ፕሬሚየ ርሊግ፦

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ የሳምንቱ መጨረሻ ግጥሚያዎች በአጓጊ ሁኔታ ተጠናቀዋል ። በበርካቶች ዘንድ በከፍተኛ ደረጃ ሲጠበቅ በነበረው የማንቸስተር የአንድ ከተማ ቡድኖች ግጥሚያ ማንቸስተር ዩናይትድ በገዛ ሜዳው ኦልትራፎርድ ትናንት በቸልሲ ብርቱ ሽንፈት ገጥሞታል ።  ኧርሊንግ ኦላንድ ለማንቸስተር ሲቲ ሁለት ግቦችን በማስቆጠር እና አንድ ለግብ በማመቻቸት የግብ አዳኝነቱን አስመስክሯል ።  

የጥቅምት 12 ቀን፣ 2016 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

በዕለቱ ብርቱ ብቃቱን ያስመሰከረው የማንቸስተር ዩናይትድ ግብ ጠባቂ አንድሬ ኦናና የኦላንድን ግብ ሊሆን የሚችል ሙከራ በድንቅ ሁኔታ ማጨናገፍ ችሏል ። ሆኖም በሁለተኛው የጨዋታ አጋማሽ በተመሳሳይ ሁኔታ እና ቦታ ላይ ሆኖ ኖርዌጂያዊው አጥቂ በጭንቅላት የገጨውን ኳስ ግን ኦናና ግብ ሲሆን ከመመልከት ውጪ ምንም ማድረግ አልቻለም ። ፊል ፎደን 80ኛ ደቂቃ ላይ ሦስተኛዋን ግብ በማስቆጠር ማንቸስተር ሲቲ ማንቸስተር ዩናይትድን በሜዳው 3 ለ0 ኩም አድርጎታል ። በውጤቱም የአሰልጣን ፔፕ ጓርዲዮላው ማንቸስተር ሲቲ እንደ አርሰናል ሁሉ 24 ነጥብ ሰብስቦ የሦስተኛ ደረጃን መያዝ ችሏል ። ተጋጣሚው ማንቸስተር ዩናይትድ በ15 ነጥብ ስምንተኛ ደረጃው ላይ ተወስኗል ። 

የማንቸስተር ሲቲው አጥቂ ኧርሊንግ ኦላንድ የግብ ቀበኛነቱን እያስመሰከረ ነውምስል ARIS MESSINIS/AFP

ከማንቸስተሮች ግጥሚያ ጥቂት ቀደም ብሎ ሊቨርፑል በአራት ጨዋታዎች አራተኛ ድሉን አጣጥሟል ። ሊቨርፑል ተጋጣሚው ኖቲንግሀም ፎረስትን ትናንት በተመሳሳይ 3 ለ0 ማሸነፍ ችሏል ። በሰበሰበው 23 ነጥቡም ሁለተኛ ደረጃ ላይ ከሚገኘው አርሰናል በአንድ ነጥብ ብቻ ተበልጦ የአራተኛ ደረጃን ይዟል ።  ለሊቨርፑል ግቦቹን ያስቆጠሩት ዲዬጎ ጆታ ፤ ዳርዊን ኑኔዝ እንዲሁም ሞ ሣላህ  ናቸው ። በጭማሪው የባከነ ሰአት ኮዲ ጋክፖ ያስቆጠረው አራተኛ ግብ ከጨዋታ ውጪ በሚል ተሰርዟል ። 

የፕሬሚየር ሊግ የደረጃ ሰንጠረዡን ከዐሥረኛ ግጥሚያ በኋላ በ26 ነጥብ የሚመራው ቶትንሀም ጆትስፐር ነው ። ኤዲ ንኬቲያህ ቅዳሜ ዕለት ሼፊልድ ዩናይትድ ላይ ሦስት ኳሶችን ከመረብ በማሳረፍ ሔትትሪክ የሠራለት አርሰናል ቶትንሀምን በሁለት ነጥብ ብቻ ርቀት ይከተላል ። መድፈኞቹ ሼፊልድን 5 ለ0 ድባቅ ሲመቱ ሌሎቹን ሁለት ግቦች ያስቆጠሩት ፋቢዮ ቪዬራ እና ታኬሂሮ ቶሚያሱ ናቸው ። ሼፊልድ ዩናይትድ በ1 ነጥብ ተወስኖ የደረጃ ሰንጠረዡ መጨረሻ 20ኛ ላይ ይገኛል ። በርንሌይ እና ሉቶን ታውን በአራት እና አምስት ነጥብ ሼፊልድን አስከትለው ወራጅ ቀጣና ውስጥ ይገኛሉ ። 

ባለፈው ሳምንት በ86 ዓመቱ በሞት ለተለየው የእንግሊዝ የቀድሞ ብሔራዊ ቡድን ተጨዋች ሠር ቦቢ ቻርልተን መታሰቢያ ተጨዋቾች ጥቁር ጨርቅ ክንዳቸው ላይ አስረው ነበር ።

ቡንደስሊጋ

የጥቅምት 5 ቀን፣ 2016 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

የጀርመን ቡንደስሊጋ ቅዳሜ ዕለት ሠርከስ መስሎ ነበር ማለት ይቻላል ። ከታችኛው ዲቪዚዮን ያደገው ዳርምሽታድት ቡድን በባዬርን ሙይንሽን 8 ለ0 የግብ ጎተራ ሲሆን ግቦቹን ከመቁጠር ውጪ ምንም ማድረግ አልቻለም ። የጀርመን ብሔራዊ ቡድን የምንጊዜም ምርጡ ግብ ጠባቂ ማኑዌል ኖየር ከ300 ቀናት በኋላም መሰለፍ ችሏል ። ኪሚሽ የዳርምሽታድትን ተጨዋች ፍጹም ቅጣት ክልል አቅራቢያ ደጋግሞ በመጎተት በመጣሉ በቀይ ካርድ ከሜዳ ተሰናብቷል ። 

ቡንደስ ሊጋ፦ ባየርን ሙይንሽን ማይንትስ ላይ ሲያስቆጥር፦ ፎቶ ከማኅደርምስል Arne Dedert/dpa/picture alliance

የዳርምሽታድቱ ክላውስ ጃዙላ በሠራው ጥፋት በተመሳሳይ በቀይ ካርድ ተሰናብቷል ። እንደ ባየርን ሙይንሽን በ10 ተጨዋች የተወሰነው ዳርምሽታድት ፍጹም ቅጣት ምት መቃረቢያ ላይ በማቴይ ማጅሊካ ድጋሚ በሠራው ጥፋት ሁለተኛ ተጨዋቹ ቀይ ካርድ ዐይቶ በ9ኝ ተጨዋች ተወስኗል ።  የመጀመሪያው አጋማሽ የተጠናቀቀው ያለምንም ግብ ነበር ። ከዚያ በኋላ ግን በሔሪ ኬን የተጀመረው የመጀመሪያ ግብ ስምንተኛውም በራሱ ተደምድሟል ። ሌሮይ ሳኔ እና ጃማል ሙሳይላ ሁለት ሁለት ግብ አስቆጥረዋል ። ቶማስ ሙይለር እና ጆሹዋ ኪሚሽም አንድ አንድ ከመረብ አሳርፈዋል ። 
በሌሎች ግጥሚያዎች፦  ላይፕትሲሽም ኮሎኝን 6 ለ0 አሸንፏል ። ቦሩስያ ዶርትሙንድ ከአይንትራኅት ፍራንክፉርት ጋ ትናንት ሦስት እኩል ወጥቷል ። ሆፈንሃይም ሽቱትጋርትን 3 ለ2 ሲያሸንፍ፤ ሐይደንሀይደም በቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅ 2 ለ1 ተሸንፏል ። ቬርደር ብሬመን ዑኒዮን ቤርሊንን 2 ለ0፤ አውግስቡርግ ቮልፍስቡርግን 3 ለ2 አሸንፈዋል ። ቦሁም እና ማይንትስ ሁለት እኩል ተለያይተዋል ። 

ራግቢ

የደቡብ አፍሪቃ የራግቢ ብሔራዊ ቡድን በፓሪስ የዐለም ራግቢ ፍፃሜ ኒውዚላንድን በማሸነፍ ለ4ኛ ጊዜ ዋንጫ አነሳ ። ደቡብ አፍሪቃ እጅግ ልብ ሰቃይ በነበረው የፍፃሜ ግጥሚያ ጨዋታ ከትናንት በስትያ የኒውዚላንድ ቡድንን ድል ያደረገው 12 ለ 11 በሆነ ተቀራራቢ ውጤት ነው ። 
የራግቢ ግጥሚያ ኢትዮጵያ ውስጥ እምብዛም ዐይታወቅም ። ሆኖም ዋንጫውን ያሸነፈችው ደቡብ አፍሪቃ እና የፍጻሜ ግጥሚያው የተከናወነባት ፓሪስ ከተማን ጨምሮ በተለያዩ የውጭ ሃገራት የሚኖሩ በርካታ ኢትዮጵያውያን ራግቢን በቅርበት ይከታተላሉ ። በተለይ ደግሞ ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ራግቢ ከእግር ኳስም በበለጠ ተወዳጅ ስፖርት ነው ። 
ብዙውን ጊዜ ዓለም አቀፍ እግር ኳስ ጨዋታዎችን ስታስተናግድ ብጥብጥ የማያጣት የፓሪስ ከተማ ቅዳሜ ዕለት በራግቢው የፍጻሜ ግጥሚያ ድባቡ ምን ይመስል ነበር? የፓሪስ ወኪላችን ሐይማኖት ጥሩነህ በምትኖርበት ከተማ የነበረውን ድባብ ደማቅ እንደነበር ገልጻለች ።

የመስከረም 28 ቀን 2016 ዓ/ም የስፖርት ዝግጅት

በፓሪስ የዐለም ራግቢ ፍፃሜ ኒውዚላንድን በማሸነፍ ለ4ኛ ጊዜ ዋንጫ ያነሳው የደቡብ አፍሪቃ የራግቢ ብሔራዊ ቡድን ደጋፊዎች በካፕሽታድት ምስል sa Alexander/REUTERS

ሰሞኑን እሥራኤል እና ጋዛ ውስጥ ካለው ከባድ ሁኔታ አንጻር የተለያዩ የአውሮጳ ሃገራት የፀጥታ ጥበቃቸውን እጅግ አጥብቀዋል ። ዓለም አቀፍ የራግቢ የፍጻሜ ውድድር የተካሄደባት የፈረንሳይ ዋና ከረማ ፓሪስ የፀጥታ ጥበቃስ ምን ይመስል ነበር? ፍጻሜውስ በሰላም ተጠናቀቀ? ሐይማኖት ተጨማሪ አላት ። 

ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማኅበር ፌዴሬሽን (FIFA) የስፔን የቀድሞ የእግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚደንት ሉዊ ሩቢያልን ለሦስት ዓመታት ማገዱን ዛሬ ይፋ አድርጓል ። የ46 ዓመቱ ሉዊ የታገዱት ከሀገር ውስጥም ሆነ ከዓለም አቀፍ የእግር ኳስ ጉዳዮች ነው ።  ስፔናዊው የታገዱት የሀገሪቱ ብሄራዊ ቡድን ተጨዋች ጄኒፈር ሔርሞሶን ላይ ከሥነ ምግባር የወጣ ተግባር ፈጽመዋል በሚል ነው።  ስፔን ሲድኒ ውስጥ ከእንግሊዝ ጋ የነበራትን የዓለም ዋንጫ የፍጻሜ ጨዋታ በድል እንዳጠናቀቀች ተጨዋቿን ጭንቅላቷን ይዘው ከንፈሯን በመሳማቸው ነው ብሏል ዓለም አቀፉ ማኅበር ።  ፊፋ ሉዊ ሩቢያልን ለሦስት ዓመት ከማገዱ በፊት የ90 ቀናት እገዳ ጥሎባቸው ነበር ። 

ቡጢ፥

እንግሊዛዊው የከባድ ሚዛን ቡጢ ተፋላሚ ታይሰን ፉሪ ፈረንሳዊው ተጋጣሚው ፋራንሷ ንጋኑን ያለጥርጥር በዝረራ አሸንፈዋለሁ ሲል ዝቶ ነበር ። ሆኖም ሳዑዲ ዓረቢያ ውስጥ ቅዳሜ በነበረው ፍልሚያ ዳኞች 96 ለ93 እና 95 ለ94 የሆነ ጠባብ የነጥብ ልዩነት ሰጥተው ነበር ታይሰን አሸናፊ መሆን የቻለው ። እንደውም ፍራንሷ ታይሰንን በቡጢ መሬት ላይ ዘርሮት ነበር ። ፍልሚያው ታይሰን በእርግጥም ካሰበው እና ከገመተው በላይ ከባድ እንደነበር ተናግሯል ።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ኂሩት መለሠ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW