ስፖርት፤ የካቲት 07 ቀን፣ 2008 ዓ.ም
ሰኞ፣ የካቲት 7 2008በስፖርቱ ዓለም በተለይም በአትሌቲክሱ ዘርፍ ለረዥም ጊዜ ብቃታቸውን እንደጠበቁ የሚቀጥሉ አትሌቶች ጥቂቶች ናቸው። አትሌት መሠረት ደፋር ከነዚያ ጥቂቶች መካከል የምትደመር ናት። በወሊድ ምክንያት ከስፖርቱ ዓለም ርቃ ብትቆይም፤ ዛሬም የቀድሞው አቋሟ አብሯት እንዳለ ማስመስከር ችላለች። የስፖርት ተንታኞች ስለአትሌቷ የሚሉን ይኖራል። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ሊቨርፑል አስቶን ቪላን አንደ መኸር ወቅት ገለባ አበራይቶታል። ቸልሲ ኒውካስልን ድባቅ መትቷል። ላይስተር ሲቲ እና ማንቸስተር ሲቲ ሽንፈት ቀምሰዋል። በጀርመኑ ቡንደስ ሊጋ ኃያሉ ባየር ሙይንሽን የሚያቆመው አልተገኘም። በስፔን ላሊጋ ባርሴሎና ሴልታቪጎን የግብ ጎተራ አድርጎታል።
በመጀመሪያም አትሌቲክስ
አትሌት መሠረት ደፋር ትናንት ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ታላቅ ድል ተቀዳጅታለች። የሁለት ጊዜያት የኦሎምፒክ ውድድር አሸናፊዋ መሠረት ደፋር እሁድ ባለድል የኾነችው በቦስተን የቤት ውስጥ የሩጫ ውድድር ነበር። መሠረት ከሁለት ዓመት ከመንፈቅ ቆይታ በኋላ ወደ ስፖርት ውድድር ተመልሳ እሁድ እለት ያሸነፈችው በ3000 ሜትር ፉክክር ነው። መሠረት ደፋር ወደፊት ተጨማሪ ሜዳሊያዎችን የማሸነፍ ዕቅድ እንዳላትም ተናግራለች። በኤፍ ኤም 96.3 ፕላኔት ስፖርት የሬዲዮ ፕሮግራም ዋና አዘጋጅ እና አቅራቢ ጋዜጠኛ ምሥጋናው ታደሰ መሠረት በእርግጥም ተጨማሪ ድሎችንም ልታገን ትችላለች ብሏል።
አትሌት መሠረት ደፋር አሸናፊ የኾነችው አሜሪካዊቷ ተፎካካሪ አቢይ ዲ አጎስቲኖን በ5.94 በመቅደም በ8 ደቂቃ ከ30.83 ሰከንድ ጊዜ በመግባት ነው። የዓለም አቀፍ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማኅበር የኢትዮጵያ ዜና ዘጋቢ ኤልሻዳይ ነጋሽ በበኩሉ መሠረት የተቀዳጀችው ድል ከዚህ ቀደም የነበራት አቋም በአኹኑ ወቅት አለመዋዠቁን የሚያሳይ ነው ብሏል።
ሌላኛዋ የ19 ዓመት ወጣት ኢትዮጵያዊት አትሌት ዳዊት ስዩምም የ1500 ሜትር የሩጫ ውድድሩን በ4 01 87 አጠናቃ በመግባት አንደኛ ወጥታለች። ይኽ ውጤቷ አንድ ወር ከ15 ቀን ባስቆጠረው የጎርጎሪዮስ 2016 ዓመት ፈጣኑ ሰአት ተብሎ ተመዝግቦላታል።
በዚሁ የቦስተን የሩጫ ፉክክር በወንዶች የ3000ሜትር ውድድር ደጀን ገብረመስቀል አንደኛ በመኾን አሸንፏል። ደጀን ባለፉት ኹለት ሦስት ዓመታት በጉዳት እና በብቃት መዋዠቅ ሲጠበቅበት የነበረበትን ውጤት ማስመዝገብ ሳይችል ቀርቶ ነበር። የትናንቱ ውጤት በለንደኑ 2012 ኦሎምፒክ ውድድር ላይ ከሞ ፋራህ ጋር ተፎካክሮ ኹለተኛ ከወጣ በኋላ ያስመዘገበው ድል ተብሎለታል።
ፕሬሚየር ሊግ
በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ሊቨርፑል ትናንት በግብ ተንበሽብሾ ነው የወጣው። በ16ኛው ደቂቃ ላይ ከግራ በኩል የተሻማችውን ኳስ ዳንኤል ስቱሪጅ በጭንቅላት ከመሬት አጋጭቶ ከመረብ በማሳረፍ የጀመረው ግብ ሌሎች አምስት ግቦችን አስከትሏል። ጨዋታው ሲጠናቀቅ አስቶን ቪላ ስድስት ግቦችን በማስተናገዱ አንገት ከመድፋት ውጪ ምንም አማራጭ አልነበረውም።
በትናንቱ ድል ሊቨርፑል ነጥቡን 38 አድርሶ አምስተኛ ደረጃ ላይ ከሚገኘው ማንቸስተር ዩናይትድ ጋር ልዩነቱን ወደ ሦስት አጥብቧል። በሰንደርላንድ ቅዳሜ እለት 2 ለ1 የተረታው ማንቸስተር ዩናይትድ በማንቸስተር ሲቲ በስድስት ነጥብ ይበለጣል። ትናንት መሪው ላይስተር ሲቲን 2 ለ 1 የረታው አርሰናል 51 ነጥብ ይዞ ሦስተኛ ደረጃውን አስከብሯል። ላይስተር ሲቲ ትናንት ነጥብ በመጣሉ 53 ነጥብ ላይ ተወስኗል። ማንቸስተር ሲቲን 2 ለ1 ያሸነፈው ቶትንሐም ሆትስፐር በ51 ነጥብ ሁለተኛ ነው። ከአርሰናል ጋር የሚለያቸው የግብ ልዩነት ነው።
በጀርመን ቡንደስ ሊጋ ትናንት ባየር ሙይንሽን አውስቡርግን 3 ለ1 ረትቷል። ለባየር ሙይንሽን ፖላንዳዊው አጥቂ ሮበርት ሌቫንዶቭስኪ ሁለት ግቦችን ሲያስቆጥር፤ የጀርመኑ አጥቂ ቶማስ ሙይለር አንድ አግብቷል። ባየር ሙይንሽን በ56 ነጥብ እየመራ ነው።ሐምቡርግ የመልስ ጨዋታውን ከቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅ ጋር አድርጎ 3 ለ2 ማሸነፍ ችሏል። ቦሩስያ ዶርትሙንድ ከሐኖቨር ጋር ተገናኝቶ እንደምንም ባገባት አንድ ግብ አሸንፎ ወጥቷል። በ48 ነጥብ ሁለተኛ ነው። ባየር ሌቨርኩሰን 35 ነጥብ ይዞ ሦስተኛ ነው።
በስፔን ላሊጋ ካምፕኑ ስታዲየም ውስጥ ባርሴሎና እና ሴልታቪጎ ያደረጉት ጨዋታ በባርሴሎና 6 ለ1 የኾነ ሰፊ ልዩነት ተጠናቋል። ሊዮኔል ሜሲ በቅጣት ምት ያስቆጠራት የመጀመሪያዋ ግብ እጅግ አስደማሚ ነበረች። ሉዊስ ሱዋሬዝ ሦስት ግቦችን ከመረብ በማሳረፍ ሄትትሪክ ሠርቷል። ሌሎቹ ግቦች የኢቫን ራኪቲች እና የኔይማር ናቸው። ሪያል ሶሴዳድ ግራናዳን 3 ለባዶ፤ ሴቪላ ላፓልማን እንዲሁም አይበር ሌቫንቴን 2 ለምንም አሸንፈዋል። ጌታፌ በአትሌቲኮ ማድሪድ 1 ለባዶ ተሸንፏል።
በሜዳ ቴኒስ የሴቶች ውድድር የስዊዘርላንዷ ታዳጊ ቤሊንዳ ቤንቺክ የሰበሰበችው ነጥብ ከዐሥሩ የዓለማችን ምርጥ ተወዳዳሪዎች ተርታ አስገብቷታል። 9ኛ ላይ የምትገኘው ቤሊንዳ ከዓለም ምርጧ አሜሪካዊት ሴሬና ዊሊያምስም እህት ቬኑስ ዊሊያምስ ልቃለች። ቬኑስ 12ኛ ደረጃ ላይ ነው የምትገኘው። እህቷ ሴሬና በከፍተኛ ነጥብ እየመራች ትገኛለች።
የኢትዮጵያ የከፍተኛ ሊግ የእግር ኳስ ውድድር ትናንት በተለያዩ የኢትዮጵያ ከተሞች ተከናውኗል። ትናንት ብቻ 16 ጨዋታዎች ተደርገዋል። በምድብ «ሀ» አዲስ አበባ ፖሊስ በ15 ነጥብ እና በ5 ንጹህ የግብ ክፍያ ደረጃውን ይመራል። በምድብ «ለ»ም በተመሳሳይ በ15 ነጥብ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እየመራ ይገኛል። 9 ንጹህ ግቦች አሉት።
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ኂሩት መለሰ