1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ስፖርት፤ የካቲት 13 ቀን፣ 2009 ዓ.ም.

ሰኞ፣ የካቲት 13 2009

አዲስ የተሾሙት የኢትዮጵያ እግር ኳስ  ብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝ፦ «ቡድኑን ለአፍሪቃ ዋንጫ ማሳለፍ ብቻ ሳይሆን» የመጨረሻው ዕቅዳቸው ቢያንስ ሩብ አለያም ግማሽ ፍጻሜ ማድረስ እንደኾነ ለዶይቸ ቬለ ተናግረዋል። ቅዱስ ጊዮርጊስ ትናንት ከሲሸልስ ቡድን ጋር አድርጎ የተቋረጠውን ጨዋታ ዛሬ አሸንፏል።

UEFA Champions League | Benfica Lissabon vs Borussia Dortmund Torhüter Ederson
ምስል picture-alliance/AP Photo/A. Franca

ስፖርት፣ የካቲት 13፣ 2009 ዓም

This browser does not support the audio element.

አዲስ የተሾሙት የኢትዮጵያ እግር ኳስ  ብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝ፦ «ቡድኑን ለአፍሪቃ ዋንጫ ማሳለፍ ብቻ ሳይሆን» የመጨረሻው ዕቅዳቸው ቢያንስ ሩብ አለያም ግማሽ ፍጻሜ ማድረስ እንደኾነ ለዶይቸ ቬለ ተናግረዋል። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የብሄራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ አድርጎ የሾመው ባለፈው ሳምንት መመረጣቸው የተነገረላቸው የአዳማ ከነማ አሠልጣኝ አቶ አሸናፊ በቀለን ነው።

ቅዱስ ጊዮርጊስ ትናንት ከሲሸልስ ቡድን ጋር አድርጎ የተቋረጠውን ጨዋታ ዛሬ አሸንፏል። በሳምንቱ መጨረሻ ላይ በተደረጉ ጨዋታዎች የጀርመኑ ቦሩስያ ዶርትሙንድ ድል ቀንቶታል። ደረጃውንም ወደ ሦስተኛነት ማሻሻል ችሏል። በስፔን ላሊጋ በሊዮኔል ሜሲ የመጨረሻ ሰአት ግብ ባርሴሴሎና ማሸነፍ ችሏል።  የሻምፒዮንስ ሊግ ግጥሚያ ቀጥሎ ነገ እና ከነገ በስትያ አራት ጨዋታዎች ይከናወናሉ። የስፔን ቡድኖች ከጀርመን እና ከእንግሊዝ ቡድኖች ጋር ይገጥማሉ። የፈረንሳይ፣ የጣሊያን እና የፖርቹጋል ቡድኖችም ተፋላሚዎች ናቸው።  

ለአፍሪቃ ሻምፒዮንስ ሊግ ክለቦች የቅድመ ማጣሪያ ውድድር ቅዱስ ጊዮርጊስ ዛሬ የሲሸልሱን ኮት ዶር 3 ለ0 አሸንፏል። በአጠቃላይ ድምር ቅዱስ ጊዮርጊስ 5 ለ0 አሸናፊ መኾን ችሏል። ትናንት በነበረው ከባድ ዝናም ምክንያት ተቋርጦ የነበረው ጨዋታ የተጠናቀቀው ዛሬ ረፋዱ ላይ ነበር። ለቅዱስ ጊዮርጊስ ግቦቹን ያስቆጠሩት ሳህላዲን ሰዒድ፣ አስቻለው ታመነ እና አዳነ ግርማ ናቸው።

ምስል DW/G. T. Aile-Giorgis

በአንጻሩ ለአፍሪቃ ኮንፌዴሬሽን ክለቦች ውድድር የመልስ ጨዋታውን ቅዳሜ ዕለት ያደረገው መከላከያ በካሜሩኑ ዮንግ ስፖርት አካዳሚ 2 ለ0 ተሸንፏል። መከላከያ የመጀመሪያውን ጨዋታ 1 ለባዶ አሸናፊ በመኾኑ በአጠቃላይ ድምር ዮንግ ስፖርት 2 ለ1 አሸንፏል።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌፌሬሽን  የአዳማ ከነማ ቡድን አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለን የብሔራዊ ቡድኑ ዋና አሠልጣኝ አድርጎ መምረጡን ይፋ አድርጓል። አሰልጣኙ የመጨረሻ ዕቅዳቸው «ቡድኑን ለአፍሪቃ ዋንጫ ማሳለፍ ብቻ ሳይሆን»  ቢያንስ ለግማሽ ወይንም ለሩብ ፍጻሜ ማድረስ እንደኾነ ለዶይቸ ቬለ ተናግረዋል። 

አሠልጣኝ አሸናፊ በቀለ፦ «አዲስ የአጨዋወት ስልት በማጥቃት እና በመከላከል ወቅት የምንጠቀምበት መርኆዎች ይኖራሉ ብዬ አስባለሁ» ብለዋል። «የተጨዋቾች አዳዲስ ለውጥ ሊኖርም ላይኖርም ይችላል» ያሉት አዲሱ አሰልጣኝ «ግን አብዛኞቹ ልምድ ያላቸው ተጨዋቾች» በብሔራዊ ቡድኑ እንደሚካተቱ አስታውቀዋል።  «ውስን አዳዲስ ተጨዋቾች ይካተታሉ፤ ውጤታማ ሊያደርጉን የሚችሉ። ያሉትን ደግሞ ባሉበት ኹኔታ እናስኬዳቸዋለን ብዬ አስባለሁ» ብለዋል። በአሰልጣኝነት ዘመናቸው ዋነኛ ግባቸው ምን እንደኾነ ተጠይቀው ሲመልሱም፦ «ቡድኑን የአፍሪቃ ዋንጫ ማሳለፍ ብቻ ሳይሆን የመጨረሻው ጣራ ዕቅድ አድርጌ የምገምተው ቢያንስ 4 ወይንም 8 ውስጥ የሚገባ ቡድን እንሠራለን ብዬ ነው» ሲሉ ለዶይቸ ቬለ ተናግረዋል።  

አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ የብሔራዊ ቡድኑ ዋና አሠልጣን ኾነው ቢመረጡም ገና ውል እንዳልፈረሙ ግን ተናግረዋል። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ጁነዲ ባሻ በትዊተር ማኅበራዊ መገናኛ ገጻቸው የአዳማ ከነማ ቡድን አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ በዋና አሠልጣኝነት መመረጣቸውን በመግለጥ በአጭር ጊዜ  ጋዜጣዊ መግለጫ እንደሚሰጥ አስታውቀዋል።

ምስል Farouk Batiche/AFP/Getty Images

ባለፈው ሳምንት አስገራሚ ውጤቶች የታዩበት የሻምፒዮንስ ሊግ ግጥሚያ ነገ እና ከነገ በስተያም ይከናወናል። በነገው እለት የጀርመኑ ባየር ሌቨርኩሰን ከስፔኑ አትሌቲኮ ማድሪድ ጋር ይጋጠማል። ባየር ሌቨርኩሰን በጀርመን ቡንደስ ሊጋ 30 ነጥብ ይዞ ስምንተኛ ደረጃ ላይ ነው የሚገኘው። በአንጻሩ አትሌቲኮ ማድሪድ በስፔን ላሊጋ በ45 ነጥብ አራተኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ቡድን ነው። 51 ነጥብ ይዞ 2ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ባርሴሎና ትናንት በላሊጋ ግጥሚያው  ሌጋንስን 2 ለ1 ድል አድርጓል። ዛሬ ማታ ከፓልማ ጋር ይጋጠማል።

የባየር ሌቨርኩሰኑ አምበል ላርስ ቤንደር ለሻምፒዮንስ ሊግ የሩብ ፍጻሜ የመልስ ግጥሚያ ለመድረስ  መቻሉ አጠራጣሪ ነው። የመሀል ተከላካዩ ላርስ በዛሬው የመጨረሻ ልምምድ ተሳታፊ እንዳልነበር ታውቋል። ይልቁንስ ልምምድ ያደረገው በግሉ ነው ተብሏል። 

ከአውስቡርግ ጋር በነበረው ጨዋታ በጡንቻ መሸማቀቅ የተቀየረው ላርስ ቤንደርስ በሌላ ተጨዋች ይተካ እንደኾን ተጠይቀው የባየር ሌቨርኩሰን አሠልጣኝ ሮጀር ሽሚድት ያ በጨዋታው ዕለት የሚወሰን ነው ብለዋል።  ሁለት የቡንደስሊጋ ጨዋታዎችን ማሸነፍ የቀናቸው ባየር ሌቨርኩሰኖች ለነገው ጨዋታ በወኔ ወደ ሜዳ እንደሚገቡ ተናግረዋል። የቡድኑ የክንፍ ተጨዋች ካሪም ቤላራቢ፦ «በራሳችንን እንተማመናለን፤ ማክሰኞ በወኔ ነው የምንገባው» ብሏል። ጨዋታው ነገ ማታ ነው የሚከናወነው።

በተመሳሳይ ሰአት የእንግሊዙ ማንቸስተር ሲቲ ከፈረንሳዩ ሞናኮ ጋር ይጋጠማል። ማንቸስተር ሲቲ በፕሬሚየር ሊጉ 52 ነጥብ ይዞ 2ኛ ደረጃ ላይ ሲገኝ ሞናኮ በ59 ነጥብ የፈረንሳይ ሊግን እየመራ ይገኛል።

ረቡእ ዕለት በተመሳሳይ ሰአት የፖርቹጋሉ ፖርቶ ከጣሊያኑ ጁቬንቱስ እንዲሁም የስፔኑ ሴቪያ ከእንግሊዙ ላይስተር ሲቲ ይገናኛሉ።  ፖርቶ በፖርቹጋል ሊግ 53 ነጥብ ይዞ ከመሪው ቤኔፊካ የሚበለጠው በአንድ ነጥብ ብቻ ነው። የጣሊያኑ ጁቬንቱስ በሴሪኣው 63 ነጥብ ይዞ ያለተቀናቃኝ የሚገሰግስ ጠንካራ ቡድን ነው። በሁለተኛነት ከሚከተለው ሮማ በ7 ነጥብ ርቆ ይገኛል።

ምስል FADEL SENNA/AFP/Getty Images

ላይስተር ሲቲን የሚገጥመው ሴቪያ በስፔን ላሊጋ 49 ነጥብ ይዞ ደረጃው 3ኛ ነው።  የሻምፒዮንስ ሊግ የረቡዕ ተጋጣሚው ላይስተር ሲቲ በአንጻሩ በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ 21 ነጥብ ይዞ ቁልቁል 17ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

የጀርመን እግር ኳስ ብሔራዊ ቡድን ዋና አሠልጣኝ ዮኣሒም ሎይቭ  በአኹኑ ወቅት ትግል ላይ በሚገኙት ማሪዮ ጎይትስ እና ቶማስ ሙይለር እንደሚተማመኑ ዛሬ ተናገሩ። ሁለቱ የጀርመን ልምድ ያካበቱ አማካይ ተጨዋቾች ይዞታቸው ጥሩ ስለሆነ በብሔራዊ ቡድኑ ይቆያሉ ሲሉ አሠልጣኙ ዛሬ ለታተመው ኪከር የስፖርት መጽሄት ተናግረዋል።

ማሪዮ ጎይትስ  በአሁኑ ወቅት ጉዳት ስለደረሰበት ለቦሩስያ ዶርትሙንድ መጫወት አልቻለም። ቦሩስያ ዶርትሙንድ በቡንደስ ሊጋው  ከትናንት በስትያ ቮልፍስቡርግን 3 ለ0 አሸንፏል። ቶማስ ሙይለር በበኩሉ በዘንድሮ የቡንደስ ሊጋው የጨዋታ ዘመን ባየር ሙይንሽን ቡድን ውስጥ ብዙውን ጊዜ በተቀያሪነት ነው በመሰለፍ ላይ የሚገኘው። ኾኖም የብሔራዊ ቡድኑ አሠልጣኝ ዮኣሒም ሎይቭ  ባለፈው የዓለም ዋንጫ የፍጻሜ ግጥሚያ ወቅት አርጀንቲና ድል የተነሳችበትን ወሳኟን ግብ በማስቆጠሩ የ24 ዓመቱ ማሪዮ ጎይትሰ ምንጊዜም የማይዘነጋ ተጨዋች መኾኑን አስታውቀዋል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አርያም ተክሌ

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW