1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ስፖርት፤ የካቲት 26 ቀን፣ 2010 ዓ.ም. 

ሰኞ፣ የካቲት 26 2010

ሊዮኔል ሜሲ ትናንት 600ኛ ግቡን አስቆጥሯል። ባየርን ሙይንሽን ለብቻው ወደ ድል ጎዳና እየገሰገሰ ነው። ተከታዮቹን በ20 ነጥብ ርቋል። በሻምፒዮንስ ሊግ ነገ ሊቨርፑል እና ሪያል ማድሪድ የፖርቹጋል እና የፈረንሳይ ቡድኖችን ይገጥማሉ። ማንቸስተር ዩናይትድ የዛሬውን ግጥሚያ ካሸነፈ በፕሪሚየር ሊጉ የሁለተኛ ደረጃውን ከሊቨርፑል ይረከባል። 

China Beijing 2015 IAAF Weltmeisterschaft Genzebe Dibaba
ምስል picture-alliance/dpa/S. Suki

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

This browser does not support the audio element.

በቢርሚንግሐሙ የዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክ ውድድር ኢትዮጵያ በአጠቃላይ የሜዳሊያ ብዛት ከዩናይትድ ስቴትስ ቀጥላ በሁለተኛ ደረጃ አጠናቃለች። ገንዘቤ ዲባባ በሁለት የውድድር ዘርፍ ሁለት የወርቅ ሜዳሊያ አግኝታለች።  ኢትዮጵያዊው አትሌት በልምምድ ወቅት በኤሌክትሪክ አደጋ  ሕይወቱ ማለፉ በተነገረ በማግስቱ ጣሊያናዊው እግር ኳስ ተጨዋች ሆቴል መኝታ ክፍሉ ውስጥ ሞቶ ተገኝቷል። ሊዮኔል ሜሲ ትናንት 600ኛ ግቡን አስቆጥሯል። ባየርን ሙይንሽን ለብቻው ወደ ድል ጎዳና እየገሰገሰ ነው። ተከታዮቹን በ20 ነጥብ ርቋል። በሻምፒዮንስ ሊግ ነገ ሊቨርፑል እና ሪያል ማድሪድ የፖርቹጋል እና የፈረንሳይ ቡድኖችን ይገጥማሉ። ማንቸስተር ዩናይትድ የዛሬውን ግጥሚያ ካሸነፈ በፕሪሚየር ሊጉ የሁለተኛ ደረጃውን ከሊቨርፑል ይረከባል። 

አትሌቲክስ 
ታላቋ ብሪታንያ ቢርሚንግሐም ውስጥ ካለፈው ረቡዕ አንስቶ እስከ ትናንት ድረስ ለአራት ቀናት በተከናወነው የዓለም የቤት ውስጥ የአትሌቲክስ ፉክክር ኢትዮጵያ በሁለተኛነት አጠናቃለች። 4 የወርቅ እና አንድ የብር ሜዳሊያ በመሰብሰብ በአጠቃላይ በአምስት የሚዳሊያ ድምር ነው ዩናይትድ ስቴትስን በመከተል በሁለተኛነት ያጠናቀቀችው። 

ኢትዮጵያ ከሰበሰበቸው አምስት ሜዳሊያዎች ሁለቱ ወርቆች በሴቶች የ1500 እና የ3000 ሜትር የሩጫ ውድድሮች በአትሌት ገንዘቤ ዲባባ የተገኙ ናቸው። በወንዶች ውድድር ሣሙኤል ተፈራ በ1500 ሜትር እንዲሁም ዮሚፍ ቀጄልቻ በ3000 ሜትር ቀሪዎቹን ወርቆች አስገኝተዋል። ብቸኛዋ የብር ሜዳሊያ ዮሚፍን ተከትሎ በገባው ሠለሞን ባረጋ የተገኘች ናት። 

አትሌት ዮሚፍ ቀጄልቻ ከሁለት ዓመት በፊት በፓሪስ ዳያመንድ ሊግ በ3000 ሜትር ሲያሸነፍምስል picture-alliance/AP Photo/M. Euler

በአጠቃላይ ውድድሩ ዩናይትድ ስቴትስ 6 የወርቅ፣ 10 የብር እና 2 የነሐስ በድምሩ 18 ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ አንደኛ ወጥታለች። ኢትዮጵያን ተከትላ የሦስተኛ ደረጃን ያገኘችው ፖላንድ 5 ሜዳሊያዎችን አሏት፤ ሁለቱ የወርቅ አንዱ የነሐስ ነው። አስተናጋጇ ብሪታንያ በ2 የወርቅ በ1 የብር እና በ4 የነሐስ በድምሩ በ7 ሜዳሊያዎች በአራተኛነት አጠናቃለች። አንድ የነሐስ ሜዳሊያ ብቻ ያገኘችው ጎረቤት ኬንያ እጅግ ደካማ በሚባል ኹናቴ የመጨረሻ 24ኛ ደረጃ  ከያዙት 9 ሃገራት ተርታ ተመድባለች።  1 የብር እና 2 የነሐስ ሜዳሊያዎችን ያገኘችው ጀርመን በአንጻሩ 15ኛ ደረጃን አግኝታለች። 

ከዚሁ ከአትሌቲክሱ ዜና ሳንወጣ ኢትዮጵያዊው የማራቶን ሯጭ አትሌት ጫላ አዱኛ በልምምድ ወቅት ባጋጠመው የኤሌክትሪክ አደጋ  ሕይወቱ ማለፉ ተዘግቧል። አትሌቱ ዐርብ ጠዋት ልምምድ እያደረገ እንደነበር ተገልጧል። አትሌት ጫላ ከአንድ ወር በፊት ማራካሽ ከተማ ሞሮኮ ውስጥ በተከናወነው የማራቶን ሩጫ 2 ሰአት ከ11 ደቂቃ ከ47 ሰከንድ በመሮጥ ሁለተኛ መውጣት የቻለ አትሌት ነበር። እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2015 ሐኖቨር ጀርመን ውስጥ በተከናወነው ውድድር ያጠናቀቀበት የ2 ሰአት ከ09 ደቂቃ ከ42 ሰከንድ ጊዜ የግሉ ምርጥ ሰአት ተብሎ ተመዝግቦለታል። ከድሎቹ መካከል በ2014 ፈረንሳይ ውስጥ ያስገኘውም ይጠቀሳል። 

በሌላ ዜና፦ የጣሊያን ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ተሰላፊው ዳቪድ አስቶሪ ትናንት ሆቴሉ ውስጥ ሞቶ መገኘቱ ተዘግቧል። ለጣሊያን ብሔራዊ ቡድን ለ14 ጊዜ ተሰልፎ መጫወት የቻለው ዳቪድ ሕይወቱ ያለፈችው የልብ ምቱ በመቋረጡ እንደሆነ የጣሊያን ባሥልጣናት አስታውቀዋል።  በአንደኛ ዲቪዚዮን የሚገኘው ፍሎሬንቲና ቡድን አምበል የነበረው የ31 ዓመቱ ዴቪድ ሞቶ የተገኘው ኡዲኔዜ በተባለችው ከተማ ነው። 

ሴሪ ኣ

በጣሊያን የእግር ኳስ ፌዴሬሽን ውስጥ የታቀፉ ቡድኖች በሚያደርጓቸው ጨዋታዎች የተጨዋቹን ድንገተኛ ሞት በማሰብ የሐዘን መግለጫ ምልክት ክንዳቸው ላይ ማሰር ጀምረዋል። እድሜያቸው ከ19 ዓመት በታች የኾኑ ተጨዋቾች በሚሳተፉበት ውድድር ትናንት የጣሊያን የሴቶች እግር ኳስ ቡድን ከኖርዌይ አቻው ጋር ሲገጥም ተጨዋቾቹ የኅሊና ጸሎት በማድረግ የሐዘን መግለጫ ጥቁር ጨርቅ ክንዳቸው ላይ አስረዋል። የሴቶች ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድኑ ዛሬ ከፊንላንድ ጋር በሚያደርገው ጨዋታም በተመሳሳይ ምልክት ሐዘኑን ይገልጣል። ዴቪድ የ2 ዓመት ሕጻን ሴት ልጅ አለችው።

ፍሎሬንቲና በጣሊያን ሴሪአ በ10ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ዐርብ እለት ላትሲዮን 1 ለ0 ያሸነፈው ጁቬንቱስ በ68 ነጥቡ በሴሪአው ደረጃው ሁለተኛ ነው። 

የሆቴሉ መኝታ ክፍል ውስጥ ሞቶ የተገኘው የፍሎሬንትሱ ተከላካይ ዳቪድ አስቶሪምስል Imago/ZUMA Press/G. Maffia

ጁቬንቱስ ከእንግሊዙ ቶትንሀም ጋር ከነገ በስትያ በሻምፒዮንስ ሊጉ ይጋጠማል።  በተመሳሳይ ቀን እና ሰአት ረቡዕ ማታ የእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ መሪ ማንቸስተር ሲቲ ከስዊትዘርላንዱ ባዝል ጋር ይጋጠማል።  ነገ ማታ በሚደረጉ ሁለት የሻምፒዮስ ሊግ ግጥሚያዎች ደግሞ የስፔኑ ሪያል ማድሪድ ከፈረንሳዩ ፓሪስ ሴን ጀርሜይ ጋር ሲጫወት፤ የእንግሊዙ ሊቨርፑል የፖርቹጋሉን ፖርቶ ይፋለማል።  

ፕሬሚየር ሊግ

ሊቨርፑል በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ከመሪው ማንቸስተር ሲቲ በ18 ነጥብ ተበልጦ በሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።  ትናንት ቸልሲን 1 ለ0 ያሸነፈው መሪው ማንቸስተር ሲቲ 78 ነጥብ አለው። ቸልሲ በ53 ነጥቡ ተወስኖ ደረጃው አምስተኛ ነው።  ቶትንሀምን በአንድ ነጥብ በልጦ ሦስተኛ ደረጃ ላይ የሰፈረው ማንቸስተር ዩናይትድ ዛሬ ማታ ከክሪስታል ፓላስ ጋር ተስተካካይ ጨዋታውን ያከናውናል። ማንቸስተር ዩናይትድ የዛሬውን ጨዋታ ካሸነፈ በሚኖረው 62 ነጥቡ የሁለተኛ ደረጃውን ከሊቨርፑል ይረከባል። ሊቨርፑል 60 ነጥብ አለው። 

በበርናርዶ ሲልቫ ብቸኛ ግብ ትናንት ድል የተመታው የአንቶኒዮ ኮንቴ ቸልሲ አራተኛ ደረጃ ላይ ከሚገኘው ቶትንሀም በአምስት ነጥብ ይበለጣል። አሠልጣኝ አንቶኒዮ ኮንቴ በአምስት የሊጉ ጨዋታዎች አራት ጊዜ ሽንፈት ከቀመሰው ቡድናቸው ጋር የሚኖራቸው የወደፊት እጣ ፈንታ አጠያያቂ ኾኗል። ከአርሰናል ቸልሲን በቅርቡ የተቀላቀለው ኦሊቨር ዢሩ ቡድናቸው የገጠመውን ተደጋጋሚ ሽንፈት በተመለከተ ሲናገር፦ «ቀውስ አይደለም የገጠመን» ብሏል። ከአርሰናል ጋር ሦስት የኤፍ ኤ ካፕ ዋንጫዎችን ማግኘት የቻለው የፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድን ተሰላፊው ኦሊቨር ዢሩ ኤሚሬትን ለቆ ከወር በፊት ወደ ስታምፎርድ ብሪጅ የመጣው በ18 ሚሊዮን ፓውንድ ስምምነት ነው። 

ምስል Getty Images/AFP/R. Michael

ቡንደስ ሊጋ

በጀርመን ቡንደስ ሊጋ የመጨረሻ ደረጃ ላይ የሚገኘው ኮሎኝ ወሳኝ እድሉን ትናንት አምክኗል። 17 ነጥብ ይዞ በ18ኛ ደረጃ ወራጅ ቃጣና ውስጥ ያለው ኮሎኝ ትናንት የማሸነፍ እድሉን ቢጠቀም ኖሮ ወራጅ ቃጣናው ጠርዝ ላይ ከሚገኘው ማይንትስ በ5 ነጥብ ብቻ ይበለጥ ነበር። ሐምቡርግን በ7 ነጥብ በልጦ 16ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ማይንትስ 25 ነጥብ አለው። ትናንት በሽቱትጋርት 3 ለ2 የተሸነፈው ኮሎኝ ቡድን አሰልጣኝ ሽቴፋን ሩተንቤክ ቡድናቸው አንድም ግብ ሳይቆጠርበት በሰፋ ልዩነት ማሸነፍ ይችል እንደነበር በቁጭት ገልጠዋል። 

«ለ44 ደቂቃ ያኽል ድንቅ ጨዋታ አከናውነናል። በእውነቱ 2 ለ0 ወይንም 3 ለ0 ማሸነፍ ይገባን ነበር። ወደፊት ፈጽሞ ሊኾን በማይገባው የግል ስህተት ተመልሰን ወደ ኃላ ተንሸራተናል። በጨዋታው ሁለተኛ አጋማሽ ትንሽ ግራ ተጋብተናል። ግን ደግሞ ወዲያው ነበር ጨዋታውን የተቆጣጠርነው። ከነበሩት እድሎች አንጻር የማሸነፍ በርካታ እድሎች ነበሩን። ያም በመኾኑ ያስቆጫል፤ ግን ደግሞ ማለቃቀስ አይገባንም። ያው የወደፊቱን በመመልከት ብሬመን ላይ ነጥብ መያዝ ነው እንግዲህ።»

በትናንቱ ግጥሚያ በሜዳው የተጫወተው ኮሎኝ በክላውዲዮ ፒዛሮ ግብ መሪነቱን ጨብጦ የነበረው ጨዋታው በተጀመረ በ7ኛው ደቂቃ ላይ ነበር። የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ ጥቂት ሲቀረው በ44ኛው እና በባከነው ሰአት ጭማሪ 2 ደቂቃ ላይ ማሪዮ ጎሜዝ በተከታታይ ሁለት ግቦችን በማሳረፉ ሽቱትጋርት መሪነቱን ከኮሎኝ ነጠቀ። ከእረፍት መልስ በ57ኛው ደቂቃ ላይ አንድሪያስ ቤክ ማሳረጊያዋን ከመረብ አሳርፏል። ሚሎሽ ጆጂች በ86ኛው ደቂቃ ላይ ለኮሎኝ ቢያስቆጥርም ኮሎኝ በ50 000 ተመልካቾች ፊት መሪር ሽንፈቱን ቀምሷል። ተከታዩ ሻልከን በ20 ነጥብ የራቀው ባየር ሙይንሽን የአሸናፊነት ግስጋሴውን ለብቻው ተያይዞታል። ኃያሉ ባየር ሙይንሽን ፍራይቡርግን ትናንት 4 ለ0 በማንኮታኮት በ63 ነጥብ በደረጃው ተኮፍሷል።

ሊዮኔል ሜሲ በተደረደሩ ተከላካዮች አናት በድንቅ ኹኔታ ያስቆጠረው የቅጣት ምትምስል Getty Images/AFP/L. Gene

በስፔን ላሊጋ 
መሪው ባርሴሎና ትናንት ተከታዩ አትሌቲኮ ማድሪድን ባሸነፈበት ብቸኛ ግብ ሊዮኔል ሜሲ በጨዋታ ዘመኑ ለቡድኑ እና ለሀገሩ 600ኛ የኮነችውን ግቡን አስመዝግቧል።  በቶማስ ፓርቴ በተፈጸመበት ጥፋት የተገኘውን ፍጹም ቅጣት ምት 26ኛው ደቂቃ ላይ ራሱ ሜሲ በተደረደሩ ተከላካዮች አናት ልኮ በድንቅ ኹኔታ ከመረብ አሳርፏል። በዚህች ብቸኛ ግብ የተገኘው ሦስት ነጥብ ተደምሮ ባርሴሎና በ69 ነጥብ የደረጃ ሠንጠረዡን ይመራል። 11 ዙር ጨዋታዎች በሚቀሩት በዘንድሮው ላሊጋ ባርሴሎና አትሌቲኮ ማድሪድን በ8 ነጥብ በልጧል። በትናንቱ ጨዋታ አንድሬ ኢኔስታ በመጀመሪያው አጋማሽ በጡንቻ መሸማቀቅ ጉዳት ደርሶበታል። 

ትናንት በተከናወነ ሌላ ጨዋታ ሪያል ሶዴዳድ አላቬስን 2 ለ 1፤ ቫለንሺያ ሪያል ቤቲስን 2 ለ0 አሸንፈዋል። ላቫንቴ ከኢስፓኞላ አንድ እኩል ተለያይተዋል። ዛሬ ማታ ሴልታቪጎ ከላስ ፓልማስ ጋር ይጋጠማል። 

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አርያም ተክሌ
 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW