ስፖርት፤ የካቲት 5 ቀን፣ 2010 ዓ.ም.
ሰኞ፣ የካቲት 5 2010በካፍ የሻምፒዮንስ ሊግ ቅድመ ማጣሪያ እና ኮንፌዴሬሽን የእግር ኳስ ግጥሚያዎች የኢትዮጵያ ሁለት ቡድኖች ተሳክቶላቸዋል። በዓለም የክረምት ኦሎምፒክ ጨዋታዎች ውድድር ኤርትራ የካናዳ ዜግነት ባለው አትሌት የበረዶ ላይ ተንሸራታች ተካፋይ ናት። ካናዳዊው የወላጆቹ ሀገር ኤርትራን ወክሎ ሲሰለፍ የዘንድሮው የመጀመሪያው አይደለም። አሜሪካዊቷ የሜዳ ቴኒስ የዓለማችን ድንቅ ተጨዋች በወለደች በአምስት ወሯ ለውድድር ወደ ሜዳ ተመልሳለች። የፕሬሚየር ሊግ፤ ቡንደስሊጋ እና ላሊጋ ጨዋታዎችን የሚመለከቱ ዘገባዎችንም አካተናል።
ካፍ ኮንፌዴሬሽን ጨዋታ
በካፍ የአፍሪቃ ኮንፌዴሬሽን የእግር ኳስ ጨዋታ የቅድመ ማጣሪያ ውድድር ኢትዮጵያን ወክሎ የተሰለፈው ወላይታ ድቻ ከዛንዚባሩ አቻው ዚማሞቶ ጋር አንድ እኩል በመለያየት ነጥብ ተጋርቷል። ወላይታ ድቻ ከሀገር ውጪ ባከናወነው የመጀመሪያ ግጥሚያው ነጥብ በመጋራቱ ወደ ቀጣዩ ዙር ለማለፍ እድሉን አስጠብቋል። የመልሱን ጨዋታ የረቡዕ ሳምንት በደጋፊዎቹ ፊት ሐዋሳ ከነማ ስታዲየም ውስጥ ለሚያከናውነው ወላይታ ድቻ ነጥብ ተጋርቶ መምጣቱ እጅግ ይጠቅመዋል። ወላይታ ድቻ ወደ ማጣሪያው ማለፍ ከቻለ በመቀጠል የሚገጥመው በአፍሪቃ የሻምፒዮንስ ሊግ ፍልሚያ ኃያል ከሆነው የግብጹ ዛማሌክ ቡድን ጋር ነው። የማጣሪያ ጨዋታውም በደርሶ መልስ ቅዳሜ የካቲት 24 በደጋፊዎቹ ፊት እና መጋቢት 7 ግብጽ ውስጥ ይኾናል።
ካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ
በካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ ውድድር ትናንት ከደቡብ ሱዳኑ ዋ ሣላም ቡድን ጋር ሊጋጠም የነበረው ቅዱስ ጊዮርጊስ ቡድን በፎርፌ አሸንፏል። የደቡብ ሱዳኑ ቡድን ባለመምጣቱ በደንቡ መሰረት ሜዳ ውስጥ ለ15 ደቂቃ ልምምድ ያደረገው የቅዱስ ጊዮርጊስ ቡድን አሸናፊ መሆኑን ዳኞች ወስነዋል። የመልስ ጨዋታው የነገ ሳምንት ነው። የቅዱስ ጊዮርጊስ ቡድን ቀጣይ ጨዋታውን የሚያከናውነው ከዩጋንዳው ካምፓላ ሲቲ እና ከማዳጋስካሩ ሲናፕስ አሸናፊ ጋር ይኾናል። ካምፓላ ሲቲ ከትናንት በስትያ በሲናፕስ 2 ለ1 ተሸንፏል።
ፕሬሚየር ሊግ
በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ዛሬ ማታ አንድ ተስተካካይ ጨዋታውን ከዌስት ብሮሚች ጋር የሚያከናውነው ቸልሲ ከመሪው ማንቸስተር ሲቲ በ22 ነጥብ ርቀት ላይ ይገኛል። አምና በ93 ነጥብ ዋንጫውን የጨበጠው ቸልሲ የዘንድሮ ገስጋሹ ማንቸስተር ሲቲን በ15 ነጥብ ልቆ ነበር። በአንቶኒዮ ኮንቴ የሚመራው ቸልሲ የዛሬውን ጨዋታ አሸንፎ ቶትንሀምን በአንድ ነጥብ በመብለጥ የአራተኛ ደረጃውን መቀማቱ ብዙም የሚያጠራጥር አይደለም። 20 ነጥብ ይዞ የደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ ላይ 20ኛ ኾኖ የተዘረጋው ዌስት ብሮሚች ለቸልሲ ላይከብድ ይችል ይኾናል። እናም ቸልሲ በዛሬው ጨዋታ አሸንፎ 3 ተጨማሪ ነጥብ ማግኘት ቢችልም፤ በሦስተኛ ደረጃ ላይ ከሚገኘው ሊቨርፑል ግን በአንድ ነጥብ መበለጡ አይቀርም።
ሊቨርፑል ትናንት ሳውዝሀምፕተንን 2 ለ0 በማሸነፍ ነጥቡን 54 አድርሷል። ትናንት በኒውካስል የ1 ለ0 ሽንፈት የቀመሰውና በሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ማንቸስተር ዩናይትድንም በ2 ነጥብ ልዩነት ብቻ ደረስኩብህ እያለው ነው። በሊቨርፑል 2 ለ0 የተሸነፈው ሳውዝሀምፕተን 18ኛ ወራጅ ቃጣና ውስጥ ለመግባት ተገዷል። ሳውዝሀምፕተን እስካሁን ባደረጋቸው 27 ግጥሚያዎች ማሸነፍ የቻለው አምስት ጨዋታዎችን ብቻ ነው።
ከቸልሲ በአምስት ነጥብ ዝቅ ብሎ በ6ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው አርሰናል የቅዳሜ ሽንፈቱን የነገ ሳምንት በሚያደርገው ፍልሚያ ማካካሱ ያጠራጥራል። ቅዳሜ ዕለት በቶትንሀም 1 ለ0 የተረታው አርሰናል ሳምንት የሚጋጠመው ከመሪው ማንቸስተር ሲቲ ጋር ነው። ማንቸስተር ሲቲ እንደለመደው ማሸነፉን ተያይዞታል። ቅዳሜ ዕለት ላይስተር ሲቲን 5 ለ1 ነበር ያንኮታኮተው።
ቡንደስሊጋ
በጀርመን ቡንደስሊጋ መሪው ባየር ሙይንሽን የፊታችን ቅዳሜ ከቮልፍስቡርግ ጋር የሚያደርገው ግጥሚያ ይጠበቃል። ከተከታዩ ላይፕሲሽ በነጥብ ርቆ የሚገኘው ኃያሉ ባየር ሙይንሽን የቅዳሜ ድሉ ተጨምሮ እስካሁን 56 ነጥብ ሰብስቧል። ባየር ሙይንሽን ከትናንት በስትያሻልከን ድል ያደረገው 2 ለ1 ነበር። ላይፕሲሽ ዐርብ ዕለት አውስቡርግን 2 ለ0 ቢያሸንፍም በመሪው ባየር ሙይንሽን በ18 ነጥብ ይበለጣል። ሦስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ዶርትሙንድን የሚበልጠው ግን በአንድ ነጥብ ብቻ ነው። ዶርትሙንድ ከትናንት በስትያ ሐምቡርግን 2 ለ0 ድል በማድረግ ነጥቡን 37 አድርሷል። በቅዳሜው ጨዋታ ከስዊዘርላንድ በ20 ሚሊዮን ዩሮ ዝውውር የመጣው የኋላ መስመር ተከላካዩ ማኑኤል አካንጂ ተሰላፊ ነበር። ማኑኤል በስዊርላንዱ ባዘል ቡድን አለ የተባለ ተጨዋች ነበር።
ላሊጋ
በላሊጋው ዛሬ ሪያል ቤቲስ ከዲፖርቲቮ ላኮሩኛ ጋር ይጋጠማል። ሪያል ቤቲስ በ30 ነጥቡ ደረጃው 11ኛ ነው። እስካሁን 17 ነጥብ ብቻ መሰብሰብ የቻለው ተጋጣሚው ዲፖርቲቮ ላኮሩኛ 19ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። በደረጃ ሰንጠረዡ ወራጅ ቃጣና ግርጌ ከሚገኘው ማላጋ የሚበልጠውም በ4 ነጥብ ብቻ ነው።
እስካሁን በአንድም ጨዋታ ያልተሸነፈው መሪው ባርሴሎና ቅዳሜ ዕለት ከጌታፌ ጋር ያለምንም ግብ በመለያየት ነጥብ ተጋርቷል። ባርሴሎና 59 ነጥብ አለው። በ7 ነጥብ ዝቅ ብሎ በሁለተኛ ደረጃ የሚገኘው አትሌቲኮ ማድሪድ በበኩሉ ከትናንት በስትያ ባደረገው ግጥሚያ እንደምንም ነጥብ መጨበጥ ተሳክቶለታል። አትሌቲኮ ማድሪድ 1 ለ0 ያሸነፈው ወራጅ ቃጣናው ግርጌ ላይ የተዘረጋው ማላጋን ነው። ቫለንሺያ ትናንት በፍጹም ቅጣት ምት ያገኘውን ጨምሮ ሌቫንቴን 3 ለ 1 ድል አድርጓል፤ 43 ነጥብ አለው፤ ደረጃው ሦስተኛ ነው። 42 ነጥብ ይዞ አራተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ሪያል ማድሪድ ቅዳሜ ዕለት ከሪያል ሶሴዳድ ጋር ባደረገው ጨዋታ በግብ ተንበሽብሿል። ለሪያል ማድሪድ ክሪስቲያኖ ሮናልዶ 3 ግቦችን ከመረብ በማሳረፍ ሔትትሪክ ሠርቷል። ሮናልዶ ጨዋታው በተጀመረ አንደኛው ደቂቃ ላይ ለሉቃስ ቫስጌስ በግራ እግሩ ድንቅ በሚባል ኹናቴ በማሻማትም ግብ እንድትኾን ረድቷል። ቶኒ ክሮስ በበኩሉ ለሪያል ማድሪድ አንድ ግብ አስቆጥሯል።
ብስክሌት
ኪጋሊ ከተማ ውስጥ ከነገ በስትያ ጀምሮ እስከ እሁድ ለአምስት ቀናት በሚዘልቀው የሩዋንዳው የአፍሪቃ የብስክሌት ሽቅድምድም 15 የአፍሪቃ ሃገራት ተካፋይ ይሆናሉ፤ ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ተወዳዳሪዎችን ያሰልፋሉ።
ያለፈውን ዓመት የሩዋንዳ ብስክሌት ውድርር ያሸነፈው ሩዋንዳዊው ብስክሌተኛ አሬሩያ ጆሴፍ ነው። የኤርትራው ተወላጅ መትከል እዮብ በሁለተኛነት አጠናቋል። ካለፉት አራት ዓመታት አንስቶ የሩዋንዳ የብስክሌት ሽቅድምድም ድል ከሩዋንዳውያን እጅ መውጣት ግን አልቻለችም።
የክረምት ኦሎምፒክ ጨዋታዎች
ደቡብ ኮሪያ ፕዮንግቻንግ ውስጥ ከተጀመረ አራተኛ ቀኑን ባስቆጠረው 23ኛው የክረምት ኦሎምፒክ ጨዋታዎች ጀርመን በሜዳሊያ ብዛት እየመራች ትገኛለች። እስካሁን በተደረጉ ግጥሚያዎች ጀርመን አራት ወርቅ አንድ ብር እና ሁለት ነሐስ በድምሩ 7 ሜዳሊያዎችን አግኝታለች። 7 ሜዳሊያዎችን የሰበሰበችው ጎረቤቷ ኔዘርላንድ በሁለተኛነት ትከተላለች። ኔዘርላንድ ከጀርመን በሜዳሊያ ብዛት ብትስተካከልም የተበለጠችው 3 ወርቅ በማግኘቷ ነው። ሁለት መዳብ እና ሁለት ነሐስ ሜዳሊያዎችም አላት። ካናዳ በ2 ወርቅ፤ አራት ብር እና አንድ ነሐስ ሦስተኛ ስትሆን፤ ዩናይትድ ስቴትስ በ2 ወርቅ፤ አንድ ብር እና ነሐስ ሜዳሊያ አራተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።
በዘንድሮው የክረምት ኦሎምፒክ ጨዋታዎች ከቀድሞው በአራት አዳዲስ ጨዋታዎች ከፍ ብሏል። ቀደም ሲል 98 የተለያዩ ጨዋታዎች የነበሩ ሲኾን፤ ዘንድሮ የውድድር አይነቶቹ 102 ደርሷል። የተወዳዳሪ ሃገራት ቊጥርም በአራት ጨምሮ 92 ኾኗል። ስድስት ሃገራት ለመጀመሪያ ጊዜ ተወዳዳሪዎችን ማሰለፍ ችለዋል። ኤኳዶር፣ ኮሶቮ፣ ማሌዢያ፣ ሲንጋፖር እንዲሁም ከአፍሪቃ ናይጀሪያ እና ኤርትራ ተሳታፊ ኾነዋል። ኤርትራ በዘንድሮው የክረምት ኦሎምፒክ ጨዋታዎች የምትሳተፈው በበረዶ መንሸራተት ግጥሚያ ነው። ተወዳዳሪውም ከኤርትራዊ ቤተሰቦቹ ካናዳ ውስጥ ተወልዶ እንዳደገ የሚነገርለት ሻነን ኦግባኒ አቤዳ ነው። ካልጋሪ ከተማ ውስጥ ነዋሪ የኾነው ሻነን የካናዳ ዜግነት እንዳለውም ተዘግቧል።
የሜዳ ቴኒስ
በሜዳ ቴኒስ የሴቶች ውድድር የዓለማችን ቁጥር አንድ አሜሪካዊቷ ተጨዋች ሴሬና ዊሊያምስ ልጇን ከወለደች ከአምስት ወራት በኋላ በመፎካከር ብቃቷን አስመስክራለች። ዩናይትድ ስቴትስ ኖርዝ ካሮሊና አሽቪሌ ውስጥ ትናንት በተከናወነው ዓለም አቀፍ ጣምራ የሴቶች ቴኒስ ውድድር ግን ውጤት አልቀናትም። ሴሬና ዊሊያምስ እና እህቷ ቬኑስ ዊሊያምስ በፌድ ካፕ የትናንቱ ውድድር በኔዘርላንድ ቡድን 6 ለ 2 እና 6 ለ3 ተሸንፈዋል። እንዲያም ሆኖ ግን በዓለም የሜዳ ቴኒስ ውድድር ለ23 ጊዜያት በማሸነፍ አይበገሬነቷን ያስመሰከረችው ሴሬና ዊሊያምስ ወደ ውድድር በመመለሷ ተመልካቾች ከመቀመጫቸው በመነሳት በደማቅ ጭብጨባ አድናቆታቸውን ገልጠዋል። የ36 ዓመቷ ሴሬና ዊሊያምስ ልጇን ለማሳደግ በሚል የዘንድሮው የአውስትራሊያ ውድድር እንዲያልፋት አድርጋለች፤ በዘንድሮ ውድድር ላይ ተካፋይ አይደለችም።
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ሸዋዬ ለገሰ