1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ስፖርት፤ ግንቦት 19 ቀን፣ 2011 ዓ.ም

ሰኞ፣ ግንቦት 19 2011

በኦታዋ ማራቶን ኢትዮጵያውያቱ አትሌቶች ከአንደኛ እስከ  ሦስተኛ በመውጣት ድል ተቀዳጅተዋል። የፊታችን ረቡዕ ለአውሮጳ ሊግ ፍፃሜ እንዲሁም ቅዳሜ ዕለት ለሻምፒዮንስ ሊግ ትንቅንቅ አራት የእንግሊዝ ቡድኖች ከወዲሁ ተፋጠዋል።

DFB Cup - Final - RB Leipzig v Bayern Munich
ምስል Reuters/F. Bensch

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

This browser does not support the audio element.

በኦታዋ ማራቶን ኢትዮጵያውያቱ አትሌቶች ከአንደኛ እስከ  ሦስተኛ በመውጣት ድል ተቀዳጅተዋል። በአዲስ አበባ በርካታ ሰዎች የተሳተፉበት የጋራ ስፖርት ተከናውኗል። የስፖርት መድረኩ የፖለቲካ ተቃውሞ ተስተውሎበታል። የፊታችን ረቡዕ ለአውሮጳ ሊግ ፍፃሜ እንዲሁም ቅዳሜ ዕለት ለሻምፒዮንስ ሊግ ትንቅንቅ አራት የእንግሊዝ ቡድኖች ከወዲሁ ተፋጠዋል።  በፎርሙላ አንድ የመኪና ሽቅድምድም ያለፈው ዙር የዋንጫ አሸናፊ  ሌዊስ ሐሚልተን   የዘንድሮውን ዙር በድል ጀምሯል። በሜዳ ቴኒስ ፉክክር ሮጀር ፌዴሬር በፈረንሳይ መክፈቻ በሰፋ ልዩነት አሸንፏል።

ኃያሉ ባየር ሙይንሽን ጣምራ ዋንጫ ባነሳበት ሳምንት አንዳንድ ተጨዋቾቹ ስጋት ውስጥ ገብተዋል። ሊቨርፑል እና ቶትንሀም የሻምፒዮንስ ሊግ ፍጻሜ እስኪደርስ ተፋጠዋል። በአውሮጳ ሊግ ቸልሲ እና አርሰናል ለሞት ሽረት ፍልሚያ ተቃርበዋል። ከሌሎች ተጨማሪ የእግር ኳስ ዝውውር መረጃዎች ጋር ወደ በኋላ ላይ እንመለሳለን።  በቅድሚያም አትሌቲክስ

ካናዳ ውስጥ ትናንት በተከናወነው 45ኛው የኦታዋ ማራቶን የሩጫ ፉክክር ኢትዮጵያውያቱ አትሌቶች ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ተከታትለው በመግባት ድል ተጎናጽፈዋል። አትሌት ትእግስት ግርማ 2:26:34 በመሮጥ $30,000 ዶላር የሚያስገኘውን የአንደኛነት ደረጃ ተጎናጽፋለች። ቤቴልሔም ሞገስ 2:27:00 እንዲሁም እታፈራሁ ተመስገን 2:28:44 በመሮጥ ተከታትለው ሁለተኛ እና ሦስተኛ በመኾን ገብተዋል።

ምስል Colourbox

በወንዶቹም ውድድር ኬንያዊው አልበርት ኮሪርን በመከተል ኢትዮጵያውያኑ አበራ ኩማ እና ጽዳት አያና የኹለተኛ እና ሦስተኛ ደረጃ አግኘተዋል።  ከ32 ሺህ በላይ ሯጮች በታደሙበት የኦታዋ ማራቶን ከአበራ ኩማ ከባድ ፉክክር የገጠመው ኬንያዊ አትሌት ማሸነፉን በተመለከተ፦  «ይኽ ሕልም ነው» ሲል የፉክክሩን ጠንካራነት ገልጧል። ኬንያዊው አልበርት ኮሪር የገባበት ሰአት 2:08:03 ነው።  አበራ ኩማ 2:08:14 ሲሮጥ፤ ጽዳት አያና ሦስተኛ ኾኖ ለማጠናቀቅ ነው የፈጀበት 2:08:53 ነው።

በዚሁ በትናንቱ የማራቶን የሩጫ ፉክክር ከሙቀቱ እና ከልብ ኅመም ጋር በተያያዘ 11 ሰዎች ሐኪም ቤት ተወስደዋል። ሁለቱ አደገኛ ኹኔታ ላይ ይገኙ እንደነበር በሥፍራው የነበሩ የህክምና ባለሞያዎች ተናግረዋል። ዐሥራ አንዱ የማራቶን ሩጫ ተሳታፊዎች ሐኪም ቤት ሲገቡ ገሚሱ ከልብ ኅመም ጋር በተያያዘ የተቀረው ደግሞ በውኃ ጥም እና እጅግ በከባድ ድካም ተዝለፍልፈው እንደነበር ተገልጧል።

ከዚሁ ከአትሌቲክስ ስፖርት ዜና ሳንወጣ፦ አዲስ አበባ ውስጥም በሳምንቱ መጨረሻ ላይ የጋራ የስፖርት እንቅስቃሴ እና የሩጫ ውድድር ተከናውኗል። 16ኛ ዙር የዱላ ቅብብል ውድድር እሁድ ግንቦት 18 ቀን፤ 2011 ዓም ተከናውኗል። የትራፊክ አደጋን እንከላከል!» በሚል መሪ ቃል የተከናወነው ውድድር በተሳካ መልኩ መጠናቀቁን የታላቁ ሩጫ አዘጋጆቹ ገልጠዋል። በውድድሩ ስፍራ የተገኙ አንዳንድ ታዳሚዎች ግን የታሳታፊዎች ቊጥር አነስ ብሎ መታየቱን ተናግረዋል።   በ16ኛው የጎዳና ላይ የዱላ ቅብብል ውድድር በወንድም በሴትም አትሌቶች ኢትዮ ኤልክትሪክ አሸናፊዎች መኾኑ ተገልጧል። በውድድሩ ባንኮችን፣ ኢንሹራንሶችን፤ ሆቴሎችን የመሳሰሉ የተለያዩ ተቋማትም ተሳታፊ ነበሩ።

ምስል picture-alliance/dpa/B. Thissen

ሌላው በሳምንቱ መጨረሻ ላይ በርካታ ሰዎች የተሳፉበት የጋራ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ስፖርት መስቀል አደባባይ ላይ ተከናውኗል።  ውድድሩ በአዲስ አበባ ስፖርት ኮሚሽን አዘጋጅነት የተከናወነ ሲኾን፦ «ዘረኝነት ይብቃ» የሚል መርኅን አንግቧል። የጋራ ስፖርቱ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማም ይኽንኑ «ዘረኝነት ይብቃ» መፈክር የስፖርት ልብሳቸው ላይ አድርገው ታድመዋል። የጋራ ስፖርታዊ እንቅስቃሴው ሊበረታታ እንደሚገባ የገለጡ ሰዎች የመኖራቸውን ያህል የፖለቲካ ተቃውሞ ማንጸባረቂያ ያደረጉትም ነበሩ። የስፖርታዊ እንቅስቃሴው «ዘረኝነት ይብቃ» መፈክር እና በከተማዪቱ ውስጥ የሚከናወኑ አንዳንድ ድርጊቶችየሚጣረሱ መኾናቸውን በመግለጥም ተቃውሞዋቸውን አሰምተዋል።

በጋራ የአካል ብቃት እንቅስቃሴው ላይ ከ30 በላይ የተለያዩ የስፖርት ፌዴሬሽኖች ተሳታፊ መኾናቸው ተገልጧል። በከተማዪቱ ዐሥር ክፍለ-ከተሞችም የተከናወነው የጋራ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ወደፊት በተከታታይ እንደሚዘጋጅ ተነግሯል። 

የጀርመኑ ኃያል ባየር ሙይንይሽን በሳምንቱ ማሳረጊያ ላይ ሁለተኛ ዋንጫውን ሲያነሳ፤ የባየር ሙይንሽን የቁርጥ ቀን ተከላካይ ጄሮሜ ቦዋቴንግ እንደተከፋ የተቀያሪ አግዳሚ ወንበር ላይ እግሮቹን ዘርግቶ ተቀምጦ ነበር። የ30 ዓመቱ ተከላካይ ቦዋቴንግ ለመከፋቱ ምክንያት ነበረው።  የባየር ሙይንሽን ፕሬዚደንት ዑሊ ሆኔስ ለስምንት ተከታታይ የድል ዘመናት አብሯቸው የጨፈረው ጄሮሜ ቦዋቴንግ ሌላ አዲስ ቡድን ይፈልግ ማለታቸው ነበር የብሔራዊ ቡድኑ ተከላካይን ያስከፋው። 

የዘንድሮ አጀማመሩ ዋዣቂ የነበረው ባየር ሙይንሽን ላይፕትሲሽን  3 ለ0 ድባቅ መትቶ የጀርመን ዋንጫን ያነሳው በሮበርት ሌቫንዶቭስኪ እና ኪንግስሌይ ኮማን ግቦች ነው። በዚያም ባየርን የቡንደስ ሊጋውን እና የጀርመን ዋንጫዎችን ይዞ መጨፈር ችሏል።  በጣምራ ድሉ መላ ደጋፊዎችን ያስቦረቀው ባየር ሙይንሽን ጄሮሜ ቦዋቴንግን ሌላ ቡድን ፈልግ ሲለው ዐይኑን የፕሬሚየር ሊጉ አንድ ተጨዋች ላይ መጣሉ ተነግሯል። የባየር ሙይንሽን ሊቀ-መንበር ካርል ሐይንትስ ሩመኒገ ኃያላኑ አርየን ሮበንን እና ፍራንክ ሬበሪን የሚተካልንን አጥቂ ከወደ ማንቸስተር ሲቲ አግኝተናል ብሏል።  ያ ወጣት አጥቂ  ሌሮይ ሳኔ ነው። በእርግጥ የሌሮይ ሳኔ የማንቸስተር ሲቲ ውል ሊጠናቀቅ ገና ሁለት ዓመታት ይቀሩታል። እናስ ማንቸስተር ሲቲ ይህን ወሳን ተጨዋቹን የመሸጥ ውሳኔ ላይ ይደርስ ይኾን ግልጽ አልተደረገም። ለዚያም ይመስላል የባየር ሙይንሽኑ ሊቀ-መንበር ካርል ሐይንትስ ሩመኒገ፦ «ከማንቸስተር ሲቲ ጋር ገና የኹለት ዓመት ውል አለው፤ ያን መዘንጋት አያስፈልግም፤ እናም ተጨዋቾቻቸው ስለፈለጉ ብቻ ዝም ብለው አይሸጧቸውም» ብሏል። ሌሮይ ሳኔ ወደ ባየር ሙይንሽን የማምጣቱ ጉዳይ ከባድ ቢኾንም፦ «አጓጊው ነገር የሚተካቸው አርያን ሮበንን እና ፍራንክ ሬቤሪን ነው። ስለዚህ ይኼ ጥሩ ማበረታቻ ይመስለኛል» ሲል ሩመኒገ በእጅ አዙር ሌሮይ ሳኔን ወደ ባየርን እንዲመጣ አባብለዋል።

ምስል picture-alliance/dpa/G. Kirchner

ባርሴሎናንም ሪያል ማድሪድንም እርሷቸው፤ ይኼ ሳምንት የእንግሊዞች ነው ይላል የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ዘገባ። ለበርካታ ዓመታት የስፔን ቡድኖች በተከታታይ ድሎች የተምነሸነሹበት የአውሮጳ ሊግ እና የሻምፒዮንስ ሊግ ውድድሮች ዘንድሮ ለፍጻሜው ያሰለፉት የእንግሊዝ ቡድኖችን ብቻ ነው። ሁለቱም ታላላቅ የአውሮጳ የፍጻሜ ፍልሚያዎች  የሚከናወኑት በሊቨርፑል፤ ቶትንሀም፤ ቸልሲ እና አርሰናል ቡድኖች ነው። የፊታችን ረቡዕ ምሽት ላይ የአውሮጳ ሊግ ፍጻሜ ሲካሄድ የሚፋለሙት የእንግሊዞቹ አርሰናል እና ቸልሲ ናቸው። ከዚያም እጅግ በብዙዎች ዘንድ በጉጉት የሚጠበቀው የሊቨርፑል እና ቶትንሀም ዋናው የሻምፒዮስንስ ሊግ ግጥሚያ ቅዳሜ ምሽት ይከናወናል።

ምስል Getty Images/Bongarts/A. Hassenstein

የረቡዕ ግጥሚያ የ37 ዓመቱ የአርሰናል ግብ ጠባቂ ፔተር ቼክ ከጨዋታ ዓለም የሚሰናበትበት እንደኾነ ይጠበቃል። የአውሮጳ ሊግ እና የሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫዎችን የማሸነፍ ታላቅ ድል ከተጎናጸፈበት ቡድን ሲሰናበትም ማረፊያው ከነገ በስትያ ተቀናቃኙ ኾኖ ሜዳ ላይ የሚሰለፈው ቸልሲ ሊኾን ይችላል ተብሏል።  ፔተር ቼክ ወደ ቀድሞው ቡድኑ የስፖርት ኃላፊ ኾኖ ሊመለስ ነው ሲል ስካይ ስፖርት ያቀረበውን ዘገባ አላስተባበለም። የአውሮጳ ሊግ ፍጻሜ ተፋላሚው ቸልሲ በፍጻሜው አሸነፈም አላሸነፈ በቡድኑ ውስጥ መጠነ-ሰፊ ለውጥ እንደሚኖር እየተነገረ ነው። ኤደን ሐዛርድ ላይ በርካታ ቡድኖች ለዝውውር ዐይኖቻቸውን ጥለዋል። አሰልጣኙ ማውሪትሲዮ ሳሪ ምናልባት በሚቀጥለው የጨዋታ ዘመን የማሰልጠን ዕድሉን አያገኙም ይኾናል።

በፕሬሚየር ሊጉ ሦስተኛ ኾኖ መጨረስ በጥሩ መልኩ ሊታይ ይችላል፤ ዋንጫውን ለጥቂት አጥቶ በኹለተኛ ደረጃ ካጠናቀቀው ሊቨርፑል በ25 ነጥብ ልዩነት መጨረስ ግን አሰልጣኙን ለሰላ ትችት ዳርጓቸዋል። በኚሁ በሣሪ ዘምን ቸልሲ በማንቸስተር 6 ለ0 እንዲሁም ብዙም ልምድ በሌለው በርመስ ቡድን 4 ለ0 መንኮታኮታቸው ለረዥም ጊዜ የሚዘልቅ መጥፎ ትዝታ ነው። ከቡድኑ ጋር ውላቸው ሊጠናቀቅ ኩለት ዓመት የሚቀራቸው አሠልጣኝ ማውሪትሲዮ ሳሪ ግን ቡድናቸው በሳቸው ደስተኛ መኾን አለመኾኑን ለማየት ውላቸው ሲጠናቀቅ ቢናገሩ እንደሚሻል ገልጠዋል።  

ምስል Getty Images/D. Grombkowski

በሜዳ ቴኒስ የፈረንሳይ ውድድር የስዊዘርላንዱ ሮጀር ፌዴሬር በሰፋ ልዩነት ድል ተቀዳጅቷል። ተጋጣሚው ሮላንድ ጋሮስን 6-2 6-4 6-4 በኾነ ውጤት አሸንፎታል። የ37 ዓመቱ የሜዳ ተጨዋች በመቀጠል የሚገጥመው የጀርመኑ ኦስካር ኦቴን ነው።

በፎርሙላ አንድ የሞናኮ የመኪና ሽቅድምድም የብሪታንያው ሌዊስ ሐሚልተን ዘንድሮም ድል ተቀዳጅቷል። ለአምስት ጊዜያት የፎርሙላ አንድ ባለድል የነበረው ሌዊስ የዘንድሮውን ውድድር በድል ነው የጀመረው። በሞናኮው ሽቅድምድም፦ ሐሚልተን 1ኛ ሰባስቲያን ቬትል 2ኛ፤  እንዲሁም ቫለሪ ቦታስ 3ኛ ወጥተዋል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW