ስፖርት፤ ግንቦት 27 ቀን፣ 2010 ዓ.ም
ሰኞ፣ ግንቦት 27 2010ኢትዮጵያውያን በሳንዲያጎ የግማሽ ማራቶን በሳምንቱ ማሳረጊያ ድል ቀንቷቸዋል። የዓለም ዋንጫ የእግር የኳስ ፍልሚያ ሊጀመር በጣት የሚቆጠሩ ቀናት ብቻ ቀርተውታል። ጀርመን ባልተጠበቀ መልኩ ለዓለም ዋንጫ መሰናዶ ሽንፈት ገጥሟታል።
ዩናይትድ ስቴትስ ሳንዲያጎ ከተማ ውስጥ ትናንት በተከናወነው የግማሽ ማራቶን ሩጫ በሴቶች ፉክክር መሠረት ደፋር አሸንፋለች። በተመሳሳይ የሩጫ ዘርፍ በወንዶች የኦሎምፒክ የብር ሜዳሊያ ባለድሉ ኢትዮጵያዊው ፈይሳ ሊሌሳ የሁለተኛ ደረጃን አግኝቷል። በአምስት ሺህ ሜትር የሁለት ጊዜያት የኦሎምፒክ ባለድሏ አትሌት መሠረት ደፋር አንደኛ የወጣችበት ሰአት፦ 1 ሰአት ከ8 ደቂቃ ከ26 ሰከንድ ነው። የኬንያዋ ጄን ኪቢ 1 ሰአት ከ12 ደቂቃ በመሮጥ ተከትላ ገብታለች። በሦስተኛ ደረጃ ያጠናቀቀችው የኦሃዮዋ ካትሊን ጄምስ ናት። 1 ሰአት ከ13 ደቂቃ ከ54 ሰከንድ ፈጅቶባታል።
የሪዮ ኦሎምፒክ የብር ሜዳሊያ ባለቤቱ ፈይሳ ሊሌሳ ሁለተኛ ደረጃን ባገኘበት የእሁዱ ሩጫ ኬንያዊው ቲቱስ ኤኪሩ1 ሰአት ከ1 ደቂቃ ከ2 ሰከንድ በመሮጥ አሸንፏል። ፈይሳ ለጥቂት በ16 ሰከንዶች ነው የተቀደመው። የኬንያው ሯጭ ጆሴፋት ኪፕቺርቺር 1 ሰአት ከ02 ደቂቃ ከ21 ሰከንድ በመሮጥ የሦስተና ደረጃን አግኝቷል። የትናንቱ የሳንዲያጎ ግማሽ እና ሙሉ ማራቶን ሩጫ ውድድር ፖሊስ እግሩን በስህተት በጥይት በመምታቱ መጠናቀቅ ከነበረበት 10 ደቂቃ ዘግይቷል። ፖሊስ ጦር መሣሪያ የመዘዘበትን ተጠርጣሪ ለመያዝ ባደረገው ሙከራ ነበር የገዛ እግሩን በስህተት የመታው ተብሏል። በኋላ ላይ ተጠርጣሪው የመኪና ማቆሚያ ሥፍራ ጣሪያ ላይ በቁጥጥር ስር መዋሉም ተገልጧል።
አፋር ሠመራ ከተማ ውስጥ ትናንት በተከናወነው የአስመራጭ ጠቅላላ ጉባኤ አቶ ኢሳያስ ጂራ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ኾነው ተመርጠዋል፤ ኤ አዳራሹን ጥለው እስከውጣት ያደረሳቸውም ክስተት ተፈጥሮ ነበር። ኮሎኔል አወል አብዱራሂም ደግሞ ምክትል። የትናንቱ ምርጫ ተመራጮች እና ደጋፊዎቻቸው የጠቅላላ ጉባ
የአርሰናል ተቋምን ለመርዳት በሚል ትናንት በሳንቲያጎ ቤርናባው የሪያል ማድሪድ እና የአርሰናል የቀድሞ ዘመን ተጨዋቾች ባደረጉት ግጥሚያ ሪያል ማድሪድ አርሰናልን 2 ለ1 አሸንፏል። አዝናኝ በነበረው በትናንቱ ግጥሚያ ጨዋታው በተጀመረ በስድስተኛው ደቂቃ ላይ በጭንቅላት ገጭቶ ለሪያል ማድሪድ ቀዳሚዋን ግብ ያስቆጠረው የ40 ዓመቱ ራውል ጎንዛሌዝ ነበር። ሁለተኛዋን ግብ ጉቲ ከመረብ አሳርፏል። ለአርሰናል በባዶ ከመውጣት ያዳነውን ግብ ያስቆጠረው ቦዋ ሞርቴ ነው። የ45 ዓመቱ ፖርቹጋላዊ ሉዊስ ፊጎ፣ ሮናልዶ፣ ሮቤርቶ ካርሎስን የመሳሰሉ የቀድሞ ድንቅ ተጨዋቾች ዳግም ወደ ሜዳ ብቅ ብለው ታይተዋል።
ሩስያ ውስጥ በሚከናወነው የዓለም ዋንጫ ተሳታፊ የኾነችው ጀርመን ከትናንት በስትያ ባደረገችው የወዳጅነት ግጥሚያ በኦስትሪያ ባልተጠበቀ መልኩ 2 ለ1 ተሸንፋለች። በተመሳሳይ የግብ ልዩነት እንግሊዝ ናይጀሪያን አሸንፋለች። የጀርመን ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ዮኣሒም ሎይቭ የብሔራዊ ቡድኑ 23 ተሰላፊ ተጨዋቾችን ማንነት ዛሬ ይፋ አድርገዋል። አሠልጣኙ በቡድኑ ውስጥ ካላካተቷቸው ተጨዋቾች መካከል በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ከዋክብት ኾነው ብቅ ካሉት እንደነ ሌሮይ ሳኔ ያሉ ተጨዋቾች ይገኙበታል። በአውሮጳ በርካታ ግቦችን ያስቆጠረ ይኽን ወጣት ተጨዋች ለምን እንዳላካተቱ ግን ምንም ያሉት ነገር የለም። የባየር ሌቨርኩሰኑ ግብ ጠባቂ በርንድ ሌኖ እና ተከላካዩ ዮናታን ታህ እንዲሁም የፍራይቡርጉ አጥቂ ኒልስ ፔተርሰን ከቡድኑ ከተሰረዙ ተጨዋቾች መካከልም ይገኙበታል።
በሻምፒዮንስ ሊግ ለሦስት ተከታታይ ጊዜ ባለድል የኾነው የሪያል ማድሪድ አሰልጣኝ ፈረንሳዊው ዚነዲን ዚዳን ሐሙስ እለት የሪያል ማድሪድ አሰልጣኝነታቸው በፈቃዳቸው ማብቃቱን ማስታወቃቸው የቡድናቸውን ደጋፊዎች አስደንግጧል። አሰልጣኙ ሪያል ማድሪድን በአሰልጣንኝት ከተረከቡበት ጊዜ አንስቶ የላሊጋ፣ የስፔን የአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ እና ሦስት የቻምፒየንስ ሊግ ዋንጫዎችን ማሸነፍ ችለዋል። እሳቸው በገዛ ፈቃዳቸው ከአሰልጣኝነት እንደሚነሱ ሲገልጡ ሪያል ማድሪድን ማን ያሰልጥነው የሚለው ጥያቄ ተነስቷል። ምንም እንኳን ከቡድኖቻቸው ጋር ረዥም ውል የፈጸሙ ቢኾንም የሊቨርፑሉ ዬርገን ክሎፕ እና የቶትንሀም ሆትስፐሩ አሰልጣኝ ማርሲዮ ፖቼቲኖ ላይ ዐይን ተጥሏል። የቲያል ማድሪድ ተጨዋቾችም ቀጣዩ የውድድር ዘመን ከመጀመሩ በፊት የሚኖረው የዝውውር ጊዜ እስኪደርስ ድረስ ምን እንደሚመጣ እየተጠባበቁ ነው።
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ኂሩት መለሰ