የስፖርት ዘገባ
ሰኞ፣ ጥር 22 2009በኢትዮጵያ ፕሬሚየር ሊግ አዳማ ከነማ መሪነቱን ለቅዱስ ጊዮርጊስ አስረክቧል። ደደቢት ወደ ሦስተኛ ደረጃ ዝቅ ብሏል። በሜዳ ቴኒስ ሴሬና ዊሊያምስ አይበገሬነቷን አስመስክራለች። በወንዶች ውድድር ሮጀር ፌዴረር ከ10 ዓመት በኋላ ስፔናዊ ተቀናቃኙን ድል መንሳት ተሳክቶለታል። በስፔን ላሊጋ ሉዊስ ሱዋሬስ ባርሴሎናን ባለቀ ሰአት ታድጓል። ሪያል ማድሪድ መሪነቱን እንዳስጠበቀ ነው። በቡንደስ ሊጋው ቦሩስያ ዶርትሙን የማታ ማታ ድል ከእጁ ወጥቷል። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ቸልሲን የሚያስቆመው አልተገኘም። አርሰናል፣ቶትንሀም እና ሊቨርፑል ግን ተያይዘዋል። ነገ ማታ ሊቨርፑል ከመሪው ቸልሲ ጋር የሚያደርገው ጨዋታ ይጠበቃል።
የኢትዮጵያ የፕሬሚየር ሊግ
በ14ኛ ሳምንት ግጥሚያ ዛሬ ኢትዮጵያ ቡና ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር ተጋጥሞ 5 ለ2 ማሸነፉን ሶከር ኢትዮጵያ በድረ ገጹ ዘግቧል። በዚህም መሰረት ነገ ከአዲስ አበባ ከተማ ጋር የሚጋጠመው ቅዱስ ጊዮርጊስ የደረጃ ሰንጠረዡን በ25 ነጥብ እየመራ ይገኛል። አዳማ ከነማ በተመሳሳይ 25 ነጥብ ሆኖም በግብ ክፍያ ተበልጦ ሁለተኛ ነው። ደደቢት 24 ነጥብ ይዞ ወደ ሦስተኛ ደረጃ ዝቅ ብሏል። ኢትዮጵያ ቡና በ23 ነጥብ ከ7ኛ ደረጃ ወደ 4ኛ ከፍ ብሏል። በነገው ዕለት በርካታ ጨዋታዎች ይከናወናሉ። የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ 15 ግጥሚያዎችም በሳምንቱ ማሳረጊያ ተከናውነዋል።
የአፍሪቃ ዋንጫ
ጋቦን በምታስተናግደው የአፍሪቃ ዋንጫ ጋና፣ ካሜሩን፣ ቡርኪናፋሶ እና ግብጽ ለግማሽ ፍጻሜ መድረስ ችለዋል። በአፍሪቃ ዋንጫ የ7 ጊዜያት አሸናፊዋ ግብጽ በሩብ ፍጻሜው ሌላኛዋ የሰሜን አፍሪቃ ሀገር ሞሮኮን በባከነ ሰአት 1 ለ0 ድል አድርጋ ነው ወደ ግማሽ ፍጻሜው የገባችው። ግብጾች ሞሮኮን ያሸነፉት ሁለተኛ አጋማሽ መደበኛ የጨዋታ ክፍለ-ጊዜ ሊጠናቀቅ 3 ደቂቃዎች ሲቀሩት ነበር። ግብጽ እምብዛም ካልተጠበቀችው ቡርኪናፋሶ ጋር ከነገ በስትያ ረቡዕማታ ትጋጠማለች። ቡርኪና ፋሶ ቱኒዝያን በሩብ ፍጻሜው ቅዳሜ ዕለት 2 ለ0 በማሸነፍ ያሰናበተችው በመጨረሻዎቹ ዘጠኝ ደቂቃዎች ሁለት ግቦችን በማስቆጠር ነበር። ቡርኪናዎች ከግብጽ ጋር በሚኖራቸው ግጥሚያ ምን እንደሚፈጥሩ ግን አይታወቅም።
የኮንጎ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክን 2 ለ1 ያሸነፈችው ጋና ደግሞ በግማሽ ፍጻሜው ሐሙስ ማታ የምትጋጠመው ካሜሩንን ነው። ካሜሩን በበኩሏ በፍጹም ቅጣት ምት ሴኔጋልን 5 ለ 4 አሰናብታ ነው ለግማሽ ፍጻሜው የበቃችው።
የሁለት ምዕራብ አፍሪቃውያት ሀገራት ፍልሚያ። ለጋና ሁለት ግቦችን በማስቆጠር ጥቋቁር ከዋክብቱን ለድል ያበቁት ጆርዳን አየው እና ወንድምዬው አንድሬ አየው በአንበሶቹ ላይ ዳግም ድል ያስመዘግቡ ይሆን?
የሴኔጋል ብሔራዊ ቡድን በሩብ ፍጻሜ መሰናበቱ አጥቂው ሳዲዮ ማኔን ሐዘን ቢያጠላበትም ለሊቨርፑል ደጋፊዎች ግን እፎይታ ነው የሰጠው። ማኔ ለውድድር ወደ አፍሪቃ ካቀና ወዲህ ሊቨርፑል በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ያሸነፈው ለአንድ ጊዜ ብቻ ነው። ሊቨርፑል ከሊጉ ዋንጫ በማኔ የቀድሞ ቡድን ሳውዝሐምፕተን ድል ተነስቶ ወጥቷል። ከኤፍ ኤ ካፕም ቅዳሜ ዕለት በዎልቭስ ተሰናብቷል። ሊቨርፑል ከመሪው ቸልሲ ጋር ነገ ለሚያደርገው ጨዋታ ሴኔጋላዊው ማኔን ለማሰለፍ የግል አውሮፕላን ወደ ጋቦን ትናንት ልኮለት ነበር። ማኔ በፕሬሚየ ርሊጉ ዘንድሮ ለሊቨርፑል 9 ግቦችን ማስቆጠር የቻለ አጥቂ ነው። የሴኔጋላዊው አጥቂ አለመኖር ሊቨርፑልን እንደጎዳው ጀርመናዊው አሰልጣኝ ዬርገን ክሎፕ ተናግረዋል። ሊቨርፑል ከመሪው ቸልሲ በ10 ነጥብ ዝቅ ብሎ ይገኛል።
ቸልሲ 55 ነጥብ ሰብስቦ በቀዳሚነት ተኮፍሷል። አርሰናል በ47 ነጥብ ይከተላል።ቶትንሐም 46 አለው፤ 45 ነጥብ የያዘው ሊቨርፑልን አስከትሎ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ማንቸስተር ሲቲ በ43 ነጥብ አምስተኛ፤ እንዲሁም ማንቸስተር ዩናይትድ በ41 ነጥብ 6ኛ ደረጃ ላይ ናቸው።ማንቸስተር ዩናይትድ ከመሪው ቸልሲ በ14 ነጥቦች ይበለጣል።
በጀርመን ቡንደስሊጋ
ትናንት ቦሩስያ ዶርትሙንድ በባከነ ሰአት ድል ከእጁ ተፈልቅቃ ወጥታለች። ከቀድሞ ቡድናቸው ማይንትስ ጋር ዘንድሮ ለአራተኛ ጊዜ የተገናኙት የቦሩስያ ዶርትሙንድ አሰልጣኝ ቶማስ ቱሁል እና አንድሬ ሹርለ አጀማመራቸው የሰመረ ነበር። ያለ ማሪዮ ጎትሰ ወደ ሜዳ የገባው ቦሩስያ ዶርትሙንድ ገና ከመጀመሪያው ወደፊት በመግፋት ጠንካራ ጨዋታ አሳይቷል። ጨዋታው በተጀመረ ገና በሦስተኛው ደቂቃ ከአንድሬ ሹርለ የተላከለትን ኳስ ማርኮ ሮይስ ከመረብ ያሳረፈው በተረጋጋ ሁኔታ ነበር። 15ኛው ደቂቃ ላይ ማይንትስ ግብ ቢያስቆጥርም ከጨዋታ ውጪ በሚል ተሽሯል። ዳኛው በውሳኔያቸው ስህተት ፈጽመዋል። ከጨዋታ ውጪ አልነበረም። በ83ኛው ደቂቃ ላይ የቀድሞው የሻልካ አጥቂ ላትስ ቡድኑ ማይንትስን ከመሸነፍ ያዳነችውን ግብ በጭንቅላት ገጭቶ ከመረብ አሳርፏል። በዚህም ጨዋታው 1 ለ 1 በመጠናቀቁ የማይንትሱ አሰልጣኝ ማርቲን ሽሚት እፎይ ብለዋል። «ለዶርትሙንድ ሲበዛ አናዳጅ መሆኑ ግልጽ ነው፤ ባለቀ ሰአት ነውና የተቆጠረባቸው። ለእኛ ግን ባላጋራችን ብዙም ሰአት ሳይኖረው ባለቀ ሰአት አቻ መውጣታችን በጅቶናል»
በቡንደስ ሊጋው ቦሩስያ ዶርትሙንድ ነጥብ በመጣሉ ሦስተኛ ደረጃውን ለአይንትራኅት ፍራንክፉርት አስረክቧል። ቅዳሜ ዕለት ቬርደር ብሬመንን 2 ለ1 ያሸነፈው ባየር ሙይንሽን የደረጃ ሰንጠረዡን በ45 ነጥብ ይመራል። ላይፕትሲሽ በ42 ይከተላል። አይንትራኅት ፍራንክፉርት 32 ነጥብ ይዞ ሦስተኛ ነው። ዶርትሙንድን በአንድ ነጥብ ይበልጣል።
የስፔን ላሊጋ
በስፔን ላሊጋ ትናንት ሪያል ሶሴዳድን 3 ለባዶ የሸኘው ሪያል ማድሪድ እየመራ ነው። 46 ነጥብ ይዞ ተኮስፏል። ባለቀ ሰአት በሉዊስ ሱዋሬዝ ግብ ከመሸነፍ የዳነው ባርሴሎና 42 ነጥብ ይዞ ሁለተኛ ነው። በ90ኛው ደቂቃ ሱዋሬዝ ያስቆጠራትን ኳስ ሊዮኔል ሜሲ አመቻችቶለታል። በትናንቱ ጨዋታ ተደጋጋሚ ጥሩ የግብ ሙከራዎችን ሲያደርጉ የነበሩት ሪያል ቤቲሶች ቀዳሚዋን ግብ ያስቆጠሩት በ73ኛው ደቂቃ ላይ ነበር። የግብ መስመሮችን መለያ ካሜራ በሪያል ቤቲስ ስታዲየም አለመኖሩ ግብ ሊሆን የሚችል ኳስ በዳኛው ተዘሏል።
በላሊጋው ሉዊስ ሱዋሬዝ 16 ግቦችን ከመረፍ በማሳረፍ ቀዳሚ ነው። ሊዮኔል ሜሲ በ15 ይከተለዋል። የሪያል ማድሪዱ ክሪስቲያኖ ሮናልዶ እስካሁን 13 ግቦችን ከመረብ በማሳረፍ በሦስተኛ ደረጃ ይከተላል።
የሜዳ ቴኒስ
በዓለም የሜዳ ቴኒስ ፍልሚያ አሜሪካዊቷ ሴሬና ዊሊያምስ 7780 ነጥብ በመሰብሰብ ቀዳሚውን ስፍራ ይዛለች። ጀርመናዊቷ አንጄሊክ ክሬበር በ7115 ነጥብ ትከተላለች። በአውስትራሊያ የሜዳ ቴኒስ ፍጻሜ የሴቶች ውድድር በታናሽ እህቷ ድል የተነሳችው ቬኑስ ዊሊያምስ በ3530 ነጥብ 11ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች። ቬኑስ ከሴሬና ዊሊያምስ ነጥቧ በግማሽ ያህል ዝቅ ያለ ነው። ያም ብቻ አይደለም በቅዳሜው የአውስትራሊያ ፍጻሜ በታናሽ እህቷ ሴሬና ዊሊያምስ 6 ለ4 ተሸነፍለች። ሴሬና በሜዳ ቴኒስ ፍጻሜ ለ23ኛ ጊዜ ድል በማድረግ አይበገሬነቷን አስመስክራለች። «ዛሬ እዚህ የመቆሜ ምክንያቱ በእህቴ ነው። የዊሊያም ልጆች እህትትማማቾቹ እዚህ መድረሳቸውም ባንቺ ነው። ስላነቃቃሽኝም አመሰግናለሁ ቬኑስ።»
ቬኑስ እና የአንድ ዓመት ታናሿ ሴሬናን ገና ከልጅነታቸው ቴኒስ ያሰለጠኗቸው አባታቸው ናቸው። ገና የ10 ዓመት ልጅ ሳይሞሉ ስለልጆቻቸው የወደፊት ዕድል ሁሉም ነገር ግልጥ ብሎ የታያቸው አባት ጥረት ተደጋጋሚ ፍሬ አፍርቷል።
በወንዶች የሜዳ ቴኒስ ፍጻሜ በሮጄር ፌዴሬር የተሸነፈው ስፔናዊው ራፋኤል ናድል ከስፔን ዳቪስ ፍጻሜ ውድድር መውጣቱን ዛሬ ይፋ አድርጓል። በትናንትቱ ፍጻሜ ራፋኤል ናድል እጅግ ተበሳጭቶ ነበር። ከ10 ዓመታት በኋላ ራፋኤል ናድልን በፍጻሜው ውድድር ድል ያደረገው ሮጀር ፌዴሬር ተጋጣሚ ጓደናውን ሊያጽናናው ሞክሯል። «ቴኒስ አቻ የማትወጣበት ድንቅ ስፖርት ነው። ግን አቻ ቢኖር ኖሮ ዛሬ ማታ ያን ከራፋ ጋር መካፈሉ ባስደሰተኝ ነበር፤ የምር። »
አትሌቲክስ
ኢትዮጵያ ውስጥ ልምምድ እያደረገ የሚገኘው የብሪታንያው አትሌት ሞ ፋራህ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራም ሶማሌያውያን ወደ አሜሪካ አይገቡም በማለታቸው ስጋት ገብቶት እንደነበር አስታውቆ ነበር። ዶናልድ ትራምፕ 7 የሙስሊም ሃገራት ወደ ዩናይትድ ስቴትስ እንዳይገቡ ትእዛዝ ማስተላለፋቸው ይታወቃል። ከ7ቱ ሃገራት አንዷ ሶማሊያ ናት። ሞ ፋራህ ገና ከልጅነቱ አንስቶ ነዋሪነቱ በብሪታኒያ ሲሆን የሶማሊያ ዜግነት እንደሌለው ተዘግቧል። አሜሪካ ወደሚገኙት ልጆቹ እና ባለቤቱ ለማቅናት የነበረበት ስጋት መቀረፉንም ተናግሯል።
ማንተጋፍቶት ስሺ
ነጋሽ መሐመድ