1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ስፖርት፤ ጥር 25 ቀን፣ 2012 ዓ.ም

ሰኞ፣ ጥር 25 2012

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ሊቨርፑልን የሚያቆመው አልተገኘም። በኹለተኛነት ከሚከተለው ማንቸስተር ሲቲ በ22 ነጥብ ርቋል። በጀርመን ቡንደስሊጋ ባየር ሙይንሽን የደረጃ ሰንጠረዡ መሪነትን ከላይፕሲሽ ተረክቧል። አዲስ ባስፈረመው ታዳጊ አጥቂ የተነቃቃው ቦሩስያ ዶርትሙንድም በድንቅ ጨዋታ ደረጃውን ወደ ሦስት ከፍ አድርጓል።

Fußball UK Burnley vs. Manchester City
ምስል Getty Images/A. Livesey

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

This browser does not support the audio element.

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ሊቨርፑልን የሚያቆመው አልተገኘም። በኹለተኛነት ከሚከተለው ማንቸስተር ሲቲ በ22 ነጥብ ርቋል። በጀርመን ቡንደስሊጋ ባየር ሙይንሽን የደረጃ ሰንጠረዡ መሪነትን ከላይፕሲሽ ተረክቧል። አዲስ ባስፈረመው ታዳጊ አጥቂ የተነቃቃው ቦሩስያ ዶርትሙንድም በድንቅ ጨዋታ ደረጃውን ወደ ሦስት ከፍ አድርጓል። ዶርትሙንድ መከረኛው ዑኒዮን ቤርሊንን 5 ለ0 ሲያደባይ ኹለቱ ግቦች የታዳጊው አጥቂ ኧርሊንግ ብራውት ሐራልድ ነው።  በሴቶች የዓለም ዋንጫ እግር ኳስ ዕድሜያቸው ከ20 ዓመት በታች ግጥሚያ ኢትዮጵያ ቡሩንዲን በደርሶ መልስ 7 ለ1 ድል አድርጋ ለቀጣዩ ማጣሪያ አልፋለች። በአውስትራሊያ የሜዳ ቴኒስ የፍጻሜ ግጥሚያ ሰርቢያዊው ኖቫክ ጄኮቪች በማሸነፍ በዓለም የሜዳ ቴኒስ ባለሞያዎች ማኅበር ቀዳሚ መኾኑን አስመስክሯል።  ተጨማሪ ዘገባዎች ይኖረናል።  

እግር ኳስ

እድሜያቸው ከ20 ዓመት በታች የሴቶች ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን የቡሩንዲ አቻውን 2 ለ 1 በማሸነፍ በደርሶ መልስ ውጤት ደግሞ 7 ለ1 ድል አድርጎ ወደ ቀጣዩ ዙር ያለፈው በሳምንቱ መገባደጃ ላይ ነበር። ቡድኑ ቀደም ሲል ከኹለት ሳምንታት በፊት ቡሩንዲ ቡጁምቡራ ከተማ ውስጥ 5 ለ0 ነበር ያሸነፈው። ብሔራዊ ቡድኑ ቀጣይ ጨዋታውንም ከአንድ ወር በኋላ መጋቢት 11 ቀን የሚያከናውነው ከዚምባብዌ ጋር ነው። ዚምባብዌ በደርሶ መልስ ውድድር ማላዊን 2 ለ1 አሸንፏል።

ምስል DW/O. Tadele

ብሔራዊ ቡድኑ የዚምባብዌ ቡድን ላይ ተጨማሪ ድል ቀንቶት በደርሶ መልሱ ግጥሚያ አሸናፊ ከኾነ ወደ ዓለም ዋንጫ ማለፍ ይችላል። በነሐሴ ወር ኮስታሪካ እና ፓናማ በሚያዘጋጁት ፉክክር ላይ ተሳታፊ ከሚኾኑ 16 ዓለም አቀፍ ቡድኖች አንዱ ይኾናል። ዐሥራ ስድስቱ ቡድኖች በአራት ምድብ ተከፋፍለው ነው የሚጫወቱት።

በሴቶች እግር ኳስ ዩናይትድ ስቴትስ ከዓለም በአንደኛነት ደረጃ ላይ ትገኛለች። ጀርመን እና ሆላንድ ኹለተኛ እና ሦስተኛ ኾነው ይከታተላሉ። ኢትዮጵያ በአኹኑ ወቅት በዓለም ደረጃዋ 109ኛ ነው። የኮንጎ ሲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክን ከፊትዋ ዚምባብዌን ከዃላዋ አስከትላ ትገኛለች። ኢትዮጵያ ወደ ዓለም ዋንጫ ማለፍ አለማለፏ የሚወሰነው ዓርብ መጋቢት 18 ቀን፣ 2012 ዓ.ም ከዚምባብዌ ጋር በምታደርገው የመልስ ጨዋታ ውጤት ይኾናል።

ፕሬሚየር ሊግ

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ጀርመናዊው አሰልጣኝ ዬርገን ክሎፕ የሚመሩት ሊቨርፑልን የሚያስቆመው አልተገኘም። ሊቨርፑል ቅዳሜ ዕለት ሳውዝሐምፕተንን 4 ለ0 ድባቅ መትቷል።

በመጀመሪያው አጋማሽ ላይ ሊቨርፑል በርካታ ስህተቶችን ፈጽሞ ነበር። 43ኛው ደቂቃ ላይ ሳውዝሀምፕተን መሪ መኾን የሚያስችለውን ግብ ማስቆጠር ይችል ነበር። ኢንግስ ወደግብ የመታትን ኳስ በስህተት ያጨናገፈው የገዛ ቡድኑ አባል ሎንግ ነው። ከእረፍት መልስ 46ኛው ደቂቃ ላይ ግን ኦክስሌ ቻምበርሊንን የሚያስቆመው አልተገኘም። ከሳውዝሀምፕተን ግብ በስተቀኝ እየገፋ ያመጣትን ኳስ በድንቅ ኹኔታ ከመረብ በማሳረፍ ሊቨርፑልን መሪ አድሯል። ፊርሚኖ አመቻችቶ የሰጠውን ኳስ ሔንደርሰን ከመረብ ያሳረፈው በ60ኛው ደቂቃ ላይ ነው። 71ኛው ደቂቃ ላይም ሔንደርሰን ግሩም በሚባል ኹኔታ ለሞሐመድ ሳላኅ ያቀበለውን ኳስ ሳላህ በቀላሉ ከመረብ አሳርፏል።  90ኛው ደቂቃ ላይ ይኸው ግብ አዳኝ ሞሀመድ ሳላኅ ለሊቨርፑል አራተኛዋን ግብ አስቆጥሮ ሳውዝሀምፕተን በዜሮ ተሸንቷል። በዚህም መሠረት ሊቨርፑል ነጥቡን 73 ማድረስ ችሏል።

ምስል Reuters/Action Images/M. Childs

51 ነጥብ ይዞ በደረጃ ሠንጠረዡ ኹለተኛ ላይ የሚገኘው ማንቸስተር ሲቲ በቶትንሀም 2 ለ0 ተሸንፏል። በትናንቱ ጨዋታ 60ኛው ደቂቃ ላይ ኦሌክሳንደር ሲንቼንኮ በቀይ ካርድ ከሜዳ የተሰናበተበት ማንቸስተር ሲቲ አፍታም ሳይቆይ ነው ግብ የተቆጠረበት። በ63ኛው ደቂቃ ላይ ስቴቨን ቤርግዊጂን የመጀመሪያዋን፤ በ71ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ሶን ሆይንግ ሚን ኹለተኛዋን ግብ ለቶትንሀም ከመረብ አሳርፈዋል። ቶትንሀም ከትናንቱ ድሉ ጋር ተደምሮ ባሰባሰበው 37 ነጥብ 5ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ከመሪው ሊቨርፑል በ36 ነጥብ ይበለጣል። 49 ነጥብ ይዞ ሦስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ላይስተር ሲቲ ቅዳሜ ዕለት ከቸልሲ ጋር 2 እኩል ተለያይቷል። ቸልሲ 41 ነጥብ ይዞ አራተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ትናንት አርሰናል ከበርንሌይ ጋር ያለምንም ግብ ተለያይቷል፤ አርሰናል 31 ነጥብ ይዞ 10ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ማንቸስተር ዩናይትድም ከትናንት በስትያ ከዎልቨርሀምፕተን ጋር ባደረገው ግጥሚያ ያለምንም ግብ ነው የተለያየው፤ 35 ነጥብ ይዞ 7ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

በኤፍ ኤ ካፕ አራተኛ ዙር ግጥሚያ ሊቨርፑል ከሽሪውስበሪ ጋር ነገ ይጋጠማል። ካርዲፍ ከሪዲንግ፤ ኖርዝሀምፕተን ከደርቢ ኮንቲ፤ ኒውካስል ዩናይትድ ከኦክስፎርድ ዩናይትድ እንዲሁም ኮቨንትሪ ሲቲ ከቢርሚንግሃም ሲቲ ጋር የሚጫወቱት ነገ ነው። ረቡዕ ደግሞ ቶትንሀም ሆትስፐር ሳውዝሐምፕተንን ይገጥማል።

ቡንደስሊጋ

ምስል Getty Images/AFP/I. Fassbender

በጀርመን ቡንደስሊጋ ቅዳሜ ዕለት ዳግም ድል የቀናው ባየር ሙይንሽን በደረጃ ሰንጠረዡ የመሪነቱን ሥፍራ ከላይፕሲሽ ተረክቧል። ማይንትስን 3 ለ1 ያሸነፈው የአሰልጣኝ ዲተር ሐንሲ ፍሊክ ባየር ሙይንሽን ነጥቡን 42 ማድረስ ችሏል። ከቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅ ጋር ቅዳሜ ዕለት ተጋጥሞ ኹለት እኩል የተለያየው ላይፕሲሽ 41 ነጥብ አለው። ቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅ 39 ነጥብ ሰብስቦ አራተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ቦሩስያ ዶርትሙንድ ዑኒየን ቤርሊንን 5 ለ0 እንዳልነበረ በማድረግ ነጥቡን 39 ማድረስ ችሏል። ለቦሩስያ ዶርትሙንድ የፈረመው አዲሱ ተጨዋች ኧርሊንግ ብራውት ሐላንድ ድንቅ ብቃቱን አስመስክሯል። የ19 ዓመቱ አጥቂ ከሌላኛው ታዳጊ አማካይ ጃዶን ሳንቾ ጋር በመኾን ዑኒዮን ቤርሊን ላይ ተምነሽንሸዋል። ሳንቾ ቀዳሚዋን ግብ በ13ኛው ደቂቃ ላይ ሲያስቆጥር፤ ኧርሊንግ ብራውት 18ኛው እና 76ኛው ደቂቃ ላይ ኹለት ግቦችን ከመረብ ማሳረፍ ችሏል። አክሴል ዊትሴል የማሳረጊያዋን አራተኛ ግብ ያስቆጠረው በ70ኛው ደቂቃ ላይ ነው። ቦሩስያ ዶርትሙንድ በተለይ ኧርሊንግ ብራውትን በ45 ሚሊዮን ዩሮ ማዛወሩ በእርግጥም ትልቅ ውሳኔ መኾኑ ታይቶበታል ጨዋታው። ኖርዌጂያዊው ኧርሊንግ ብራውት ወደ ቦሩስያ ዶርትሙንድ የተዘዋወረው ከኦስትሪያው አር ቢ ዛልስቡርግ ቡድን ነው።

ትናንት ቮልፍስቡርግ ፓዴቦርንን 4 ለ2 አሸንፎ የፓዴቦርንን ተስፋ አጨልሟል። ፓዴቦርን 15 ነጥብ ይዞ ወራጅ ቃጣናው ግርጌ 18ኛ ላይ ተዘርግቷል። ኮሎኝ ፍራይቡርግን በድንቅ ኹኔታ 4 ለ0 አሸንፏል። በሜዳው እና ደጋፊዎቹ ፊት ያሸነፈው ኮሎኝ  23ነጥብ ይዞ 14ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ለጊዜውም ቢኾን ከወራጅ ቃጣናው በመጠኑ ርቋል። ቬርደር ብሬመን ቅዳሜ በአውስቡርግ 2 ለ1 ተረትቷል። ሆፈንሀይም ባየር ሌቨርኩሰንን 2 ለ1 አሸንፏል።  ፎርቱና ዱይስልዶርፍ ከአይንትራኅት ፍራንክፉርት ጋር አንድ እኩል ተለያይቷል።  ዐርብ ዕለት ሻልከ ከሔርታ ቤርሊን ጋር ያደረገው ግጥሚያ ያለምንም ግብ ተጠናቋል።

አትሌቲክስ

ምስል picture-alliance/dpa/B. Thissen

የፊታችን ቅዳሜ ቶሩን ፖላንድ ውስጥ በሚከናወነው የዓለም አትሌቲክስ ውድድር በ1500 ሜትር የሩጫ ፉክክር ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ የዓለማችን ዕውቅ አትሌቶች እንደሚሳተፉ ተዘግቧል። በዓለም ከቤት ውጪ የሩጫ ፉክክር የነሐስ ሜዳሊያ ተሸላሚዋ ጉዳፍ ጸጋይ በዘርፉ ፈጣን ሰአት ያላት ተፎካካሪ እንደኾነች ተገልጧል። ሌላኛው በቤት ውስጥ ፈጣን ሰአት ያላት ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ሐብታም ዓለሙም በውድድሩ ተሳታፊ ናት ተብሏል። አክሱማይት አምባዬም በቶሩን ውድድር የመጀመሪያ ድሏን ለማስመዝገብ የምትፋለም ይኾናል።         

ቻይና ውስጥ በተዛመተው የኮሮና ተሐዋሲ ምክንያት ቻይና በርካታ የስፖርት እንቅስቃሴዎችን ላልተወሰኑ ጊዜያት አዘዋውራለች። በዚህም መሠረት ከሦስት ሳምንት ግድም በኋላ ሊከናወን የነበረው የሀገሪቱ ከፍተኛ ሊግ የእግር ኳስ ግጥሚያ ተዘዋውሯል። የቻይና እግር ኳስ ፌዴሬሽን፦ «የመተንፈሻ አካላት ወረርሽኙን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር ይቻል ዘንድ» በሚል ጨዋታዎች ለጊዜው መሰረዛቸውን ዐስታውቋል።  በአትሌቲክሱ ዘርፍም ከአንድ ወር በኋላ ሊከናወን ቀጠሮ ተይዞለት የነበረው የናንጂንጉ የዓለም የቤት ውስጥ ውድድሮች ወደሚቀጥለው ዓመት መዛወሩ ተገልጧል። ከዚህ ባሻገር የዓለም የሴቶች እግር ኳስ፤ ቡጢ፤ የሴቶች የቅርጫት ኳስ የኦሎምፒክ ማጣሪያ ፉክክር፤ ብስክሌት፤ ጎልፍ፤ ፎርሙላ አንድ እና ሌሎች ውድድሮችም ተሰርዘዋል።

የሜዳ ቴኒስ

ምስል Getty Images/AFP/W. West

በአውስትራሊያ የሜዳ ቴኒስ ግጥሚያ ትናንት ድል የተቀዳጀው ሰርቢያዊው ኖቫክ ጄኮቪች የዓለማችን ቁጥር አንድ የሜዳ ቴኒስ ተጨዋችነቱን አስመሰከረ።  ኖቫክ ጄኮቪች በቴኒስ ባለሞያዎች ማኅበር (ATP)የነጥብ ውጤት መሠረት ስፔናዊው ራፋኤል ናዳልን ቀድሞ አንደኛ መኾን ችሏል። ኖቫክ ጄኮቪች የኦስትሪያው ተጨዋች ዶሚኒክ ቲየምን ትናንት ያሸነፈበትን ጨምሮ አኹን አጠቃላይ 9720 ነጥብ መሰብሰብ ችሏል። በትናንቱ የአውስትራሊያ የሜዳ ቴኒስ የፍጻሜ ግጥሚያ ሠርቢያዊው የኦስትሪያ ተጋጣሚውን ያሸነፈው ብርቱ ፉክክር በታየበት ግጥሚያ ነው። ኖቫክ ጄኮቪች እና ዶሚኒክ ቲየም ያደረጉት ግጥሚያ የተጠናቀቀው፦ 6-4፤ 4-6፤ 2-6፤ 6-3 እና  6-4 ነበር።  በቴኒስ ባለሞያዎች ማኅበር የዛሬው ውጤት መሠረት ኖቫክ ጄኮቪችን የሚከተለው ራፋኤል ናዳል 9395 ነጥብ አለው። ሦስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ስዊዘርላንዳዊው የሜዳ ቴኒስ ዝነኛ ሮጀር ፌዴሬር መሰብሰብ የቻለው 7,130 ነጥብ ነው።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አዜብ ታደሰ

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW