1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ስፖርት፤ ጥር 29 ቀን፣ 2009 ዓ.ም.

ሰኞ፣ ጥር 29 2009

በአፍሪቃ ዋንጫ የእግር ኳስ የፍጻሜ ፍልሚያ አንበሶቹ ካሜሮኖች ዋንጫውን ከፈርኦኖቹ ግብጾች ነጥቀው ወስደዋል። ካሜሩን በገንዘብ ክፍያ እሰጥ አገባ 8 ተጨዋቾቿ ጋቦን ሳይመጡ ቀርተውባታል። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ  ማንቸስተር ዩናይትድ ላይስተር ሲቲ ላይ ድል ሲቀዳጅ፤ ሊቨርፑል በደረጃ ሰንጠረዡ ወራጅ ቃጣና ውስጥ ለሚገኝ ቡድን እጅ ሰጥቷል።

Cameroon celebrate with the trophy after winning the African Cup of Nations
ምስል REUTERS

ስፖርት፤ ጥር 29 ቀን፣ 2009 ዓ.ም.

This browser does not support the audio element.

በአፍሪቃ ዋንጫ የእግር ኳስ የፍጻሜ ፍልሚያ አንበሶቹ ካሜሮኖች ዋንጫውን ከፈርኦኖቹ ግብጾች ነጥቀው ወስደዋል። ካሜሩን በገንዘብ ክፍያ እሰጥ አገባ ውጭ ሃገር ተሰልፈው የሚጫወቱ 8 ተጨዋቾቿ ጋቦን ሳይመጡ ቀርተውባታል። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ  ማንቸስተር ዩናይትድ ላይስተር ሲቲ ላይ ድል ሲቀዳጅ፤ ሊቨርፑል በደረጃ ሰንጠረዡ ወራጅ ቃጣና ውስጥ ለሚገኝ ቡድን እጅ ሰጥቷል። በስፔን ላሊጋ ላ ፓልማ የመጨረሻ ደረጃ ላይ ከሚገኘው ግራናዳ ጋር ዛሬ ይጋጠማል። በጀርመን ቡንደስ ሊጋ ቦሩስያ ዶርትሙንድ አጣብቂኝ ውስጥ ገብቷል፤ ባየር ሙይንሽን እየገሰገሰ ነው። 

ትናንት በተጠናቀቀው የአፍሪቃ ዋንጫ የእግር ኳስ ፍልሚያ የተጠበቀው ሳይሆን ያልተጠበቀው ተከስቷል። ግብጽ ዘንድሮ ብዙም ባልተጠበቁት ካሜሩኖች ድል ተነስታለች። ካሜሩን 8 የብሔራዊ ቡድን ተሰላፊ ተጨዋቾቿ ቡድኑን እንዲቀላቀሉ ያቀረበችላቸውን ጥሪ ባለመቀበላቸው ወጣቱ ብሔራዊ ቡድን እዚህ ይደርሳል ብሎ የገመተ ብዙም አልነበረም። ጋቦን ሊብረቪል ውስጥ ትናንት በተከናወነው የፍጻሜ ፍልሚያ ካሜሩን ግብጽን 2 ለ 1 ማሸነፏን እኚህ ካሜሩናዊት ደጋፊን ጨምሮ በእርግጥም ብዙዎች አልጠበቁም ነበር። «በጣም ደስተኞች ነን። እዚህ ይደርሳሉ ብሎ የገመተን አልነበረም። በጣም ደስ ብሎናል።  የማይታሰበውን ነው ያሳካነው። ብዙዎች የካሜሩን እግር ኳስ ሞቷል ብለው ነበር ያሰቡት። ግን ይኸው አለን!»

ቪንሰንት አቦባካር ካሜሩንን ለድል ያበቃችውን 2ኛ ግብ አስቆጥሮምስል Reuters/M. Hutchings

በትናንቱ የፍጻሜ ጨዋታ በአርሰናል አማካይ ሞሐመድ ኤልኔኒ ግብ 1 ለ0 እየመሩ የነበሩት ግብጾች ነበሩ። እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር ከ2010 ወዲህ በታደሙበት የአፍሪቃ ዋንጫም ድል የፈርኦኖች መስላ ነበር። ካሜሩኖች ወደፊት ገሰገሱ፤ ግብጾች አጥብቀው ተከላከሉ።  በ59ኛው ደቂቃ ላይ ካሜሩናዊው ኒኮላስ ንኮሉ የፈርኦኖቹን እንደ ፒራሚድ የጠነከረ የተከላካይ መስመር ደረመሰው። አንድ እኩል ኾኑ። የማታ ማታ ጨዋታው ሊጠናቀቅ 2 ደቂቃ ሲቀረው ቪንሰንት አቡበከር ኳሷን በድንቅ ኹኔታ ተቆጣጥሮ በግሩም ኹኔታ ከመረብ አሳረፈ። ለስምንተኛ ጊዜ የአፍሪቃ ዋንጫን ለመውሰድ የቋመጡት ግብጾች ኅልምም መክኖ ቀረ። ካሜሩኖች የአፍሪቃ እግር ኳስ ጀግኖች መኾናቸውን አስመሰከሩ። «የአፍሪቃ አሸናፊዎች ነን፤ ለማንም የማንበገር! ገና የዓለም ዋንጫን እናሸንፋለን።»

ግብጾች በፍጻሜው ግጥሚያ ድል ቢነሱም፤ የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት እና ጋዜጦች ሁለተኛ የወጣው ቡድናቸውን ዛሬ ሲያወድሱ ውለዋል። 2 ለ1 ተሸንፎ ዋንጫው ከእጁ ያመለጠው ብሔራዊ ቡድናቸውንም ባለድል ነው ሲሉ ጠርተውታል፤ «ክብር» ይገባዋልም ብለዋል። ግብጻዊው ሸሪፍ ኤክማራይ በጋቦን መዲና ሊብረቪል በተከናወነው የፍጻሜ ጨዋታ ሀገሩ ግብጽ ብትሸነፍም ወደፊት ሌላ የሰነቀው ተስፋ አለ። 

«በመጀመሪያ ለፍጻሜ በመድረሳችን እግዚአብሔርን አመሠግናለሁ። ስማችን በታሪክ መዝገብ እንዲሠፍር ምኞታችን ነበር፤ ግን ተጋጣሚህን አታውቀውም። ስለዚህ ካሜሮኖች ዋንጫውን በማሸነፋቸው እንኳን ደስ ያላችሁ ብለናል። ትልቁ ግባችን የዓለም ዋንጫ ተሳታፊ ለመሆን ነው፤ ያንን ግብ ለማሳካት ደግሞ ጠንክረን እንሠራለን።»

የፍጻሜ ውድድሩን የተመለከተው የዶይቸ ቬለ የምዕራብ አፍሪቃ ዘጋቢ አድሪያን ክሪሽ የካሜሩኖች ቁርጠኝነትን አድንቋል። የማሸነፍ መንፈሳቸውም ለድል እንዳበቃቸው ተናግሯል።

የአፍሪቃ ዋንጫ እግር ኳስ ዋንጫ አሸናፊዋ ካሜሩን ደጋፊዎችምስል Reuters/M. Hutchings

«ሲበዛ አስደናቂ ነው! ካሜሩኖች ይኽን የአፍሪቃ ዋንጫ ያሸንፋሉ ብሎ የጠበቀ የለም። ሌላው ቀርቶ የብሔራዊ ቡድኑ 7 ተጨዋቾች ከሀገራቸው ይልቅ አውሮጳ ለሚገኙ ቡድኖቻቸው ነው መጫወቱን የመረጡት። እናም ወጣቱ ቡድን በጋራ ቁርጠኛ ስሜት ምን ማድረግ እንደሚቻል አሳይቷል። ካሜሩኖች በተለይ በመከላከሉ ጠንካራ ተፎካካሪ የነበረው ግብጽን ማሸነፋቸው ይገባቸዋል። ካሜሩኖች የግብጽን የመከላከል አጥር ለሁለት ጊዜ ጥሰው፤ ሁለት ጊዜም ግብ በማስቆጠር በመጨረሻ ሰአት ባስቆጠሩት ግብ ማሸነፍ ችለዋል። እናም ካሜሩን ለአምስተኛ ጊዜ የአፍሪቃ ዋንጫን ወስዳለች። እናም በሚቀጥለው አስተናጋጅ ስትሆን ዋንጫዋን ላለማስነጠቅ ትፋለማለች ማለት ነው።»

የአፍሪቃ ዋንጫ አዘጋጅዋ ጋቦን ለአጠቃላይ የውድድሩ ዝግጅት ያወጣችው ገንዘብ ከተጠበቀው በታች እንደሆነ ተናግራለች። የውድድሩ አዘጋጅ ኮሚቴ አባል ክርስቲያን ኬራንጋል ዛሬ ከሊብረቪል ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፦ ለሦስት ሳምንት የዘለቀው ውድድር የተጠናቀቀው ከበጀት በታች ወጪ በማስወጣት ነው ብለዋል። ለዝግጅቱ 750  ሚሊዮን ዶላር መውጣቱን አስታውቀዋል።

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ውድድር አራት ምርጥ ቡድን ውስጥ ገብቶ ለመጨረስ የሚደረገው ፍልሚያ ተጠናክሯል። መሪው ቸልሲ በ9 ነጥብ ርቆ እየገሰገሰ ነው።  በሳምንቱ መጨረሻ የቸልሲ ተረኛ ተሸናፊ የነበረው አርሰናል ነበር። 3 ለ1 ድል ተነስቷል። በአሰልጣኝ አንቶኒዮ ኮንቴ የሚመራው ቸልሲ ዘንድሮ ዋንጫውን ለመውሰድ የሚያቆመው የሚገኝ አይመስልም። ሊጠናቀቅ 14 ጨዋታዎች በቀሩበት ውድድር  እስካሁን 59 ነጥብ ሰብስቧል። ቶትንሀም ማንቸስተር ሲቲን በአንድ ነጥብ በልጦ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ትናንት ስዋንሲ ሲቲን 2 ለ1 አሸንፎ ተጨማሪ ነጥብ የሰበሰበው ማንቸስተር ሲቲ  ነጥቡን 49 አድርሷል። በደረጃ ሰንጠረዡ  ወራጅ ቃጣና ውስጥ በሚገኘው ሁል ሲቲ 2 ለ0 የተሸነፈው እና ተደጋጋሚ ሽንፈት የገጠመው ሊቨርፑል በ46 ነጥቡ አምስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። አርሰናል በአንድ ነጥብ በልጦት አራተኛ ነው። ትናንት ላይስተር ሲቲን 3 ለ0 ያሸነፈው ማንቸስተር ዩናይትድ ሊቨርፑል ላይ ደረስኩብህ እያለው ነው። 45 ነጥብ ይዞ ስድስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።  

ካሜሩን ከግብጽ ለፍጻሜው ባደረገችው ግጥሚያ፥ የካሜሩን ደጋፊዎች በከፊልምስል Reuters/A.-A. Dalsh

በጀርመን ቡንደስሊጋ መሪው ባየር ሙይንሽን ዘንድሮ አጀማመሩ ጥሩ ባይሆንም በአራት ነጥብ ልዩነት ቀዳሚነቱን እንዳስጠበቀ ነው። ቅዳሜ በሜዳቸው ከሻልከ ጋር አንድ እኩል መውጣታቸውን ተከትሎ የቡድኑ አምበል ፊሊፕ ላም ባየር ሙይንሽን ግስጋሴውን ማፋጠን ይገባዋል ብሏል። በዶርትሙንድ 1 ለ0 የተሸነፈው ላይፕቲሽ በ42 ነጥብ ሁለተኛ ሆኖ ይከተላል። ቦሩስያ ዶርትሙንድ ምንም እንኳን ላይፕትሲሽን ቢያሸንፍም ከአይንትራኅት ፍራንክፉርት ዝቅ ብሎ አራተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። 34 ነጥብ ያለው ቦሩስያ ዶርትሙንድ በአይንትራኅት ፍራንክፉርት በአንድ ነጥብ ይበለጣል። ቦሩስያ ዶርትሙንድ አልበለጥ ያለው በኮከብ ግብ አግቢ አጥቂው ብቻ ነው። አጥቂው ፒየር ኤመሪክ ኦባማያንግ  ላይፕትሲሽ ላይ ያስቆጠራት አንድ ግብ ተጨምራ  እስካሁን 17 ኳሶችን ከመረብ በማሳረፍ ቀዳሚ ነው። የኮሎኙ አንቶኒ ሞዴስቴ እና የባየር ሙይንሽኑ ሮበርት ሌቫንዶቭስኪ 15 ግቦችን በማስቆጠር ይከተሉታል። 

በስፔን ላሊጋ 19 ጨዋታዎችን ያከናወነው ሪያል ማድሪድ ከቫለንሺያ ጋር ሳያደርግ የቀረውና የተራዘመበትን ጨዋታ ከሁለት ሳምንት በኋላ እንደሚያከናውን ዛሬ ተገልጧል። ሁለት ተስተካካይ ጨዋታዎች የሚቀሩት ሪያል ማድሪድ የደረጃ ሰንጠረዡን በ46 ነጥብ ይመራል። ባርሴሎና 45 ይዞ ይከተላል። ሴቪላ 43 ነጥብ አለው ሦስተኛ ነው። ሪያል ማድሪድ ትናንት ከሴልታ ቪጎ ጋር ሊያደርገው የነበረው ጨዋታ በመጥፎ የአየር ጠባይ የተነሳ የባላይዶ ስታዲየም ላይ ጉዳት እንዳይደርስ በሚል ለደኅንነት ሲባል ለሌላ ጊዜ ተሸጋግሯል። ዛሬ ማታ ግራናዳ እና ላፓልማ ተስተካካይ አንድ ጨዋታቸውን ያከናውናሉ። 28 ነጥብ ያለው ላፓልማ 11ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። የዛሬ ተጋጣሚው ግራናዳ በላሊጋው የደረጃ ሰንጠረዥ ጥግ 20ኛ ላይ ሰፍሯል።  እስካሁን 10 ነጥብ ብቻ ነው ማግኘት የቻለው። 

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ኂሩት መለሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW