የስፖርት ዘገባ
ሰኞ፣ ጥር 8 200928ኛውን የአፍሪቃ ዋንጫ ውድድር ከኢኳቶሪያል ጊኒ ጋር በመቀናጀት የዛሬ አምስት ዓመት አዘጋጅታለች፤ 31ኛውን የአፍሪቃ ዋንጫ ደግሞ ዘንድሮ ያሰናዳችው ለብቻዋ ነው፤ ምዕራብ አፍሪቃዊቷ ጋቦን። ቅዳሜ በጀመረው ውድድር እስካሁን አራት ጨዋታዎች ተከናውነዋል። በበርካታ የእግር ኳስ አፍቃሪዎች ዘንድ የሚጠበቁት አይቮሪኮስት፣ ጋና፣ ግብጽ እና ማሊ የሚጫወቱት ዛሬ እና ነገ ነው። በዛሬ እና በነገ ምሽቶች አራት ጨዋታዎች ይኖራሉ። ኡጋንዳ ከ39 ዓመት በኋላ ለጋቦኑ የአፍሪቃ ዋንጫ ማለፍ ችላለች፤ ነገ ጥቋቁር ከዋክብቱን ትገጥማለች። አትሌት ቀነኒሳ እና ፈይሳ ሊሌሳ የሚወዳደሩበት የለንደኑ ማራቶን በጉጉት ይጠበቃል።
31ኛው የአፍሪቃ የእግር ኳስ ፍልሚያ፤ ግዙፎቹን ናይጀሪያን እና ደቡብ አፍሪቃን በማጣሪያው ሸንቶ ነው የደረሰው። እንዲያም ሆኖ ግን ጠንካራ ተፎካካሪዎች በበቂ ሁኔታ ይገኙበታል። ያለፈው ውድድር የዋንጫ አሸናፊዋ አይቮሪኮስት እና ሁለተኛ ሆና ያጠናቀቀችው ጋና በዘንድሮው ውድድር ከሚጠበቁ ሃገራት ውስጥ ይገኛሉ። አይቮሪኮስት ከቶጎ ጋር የመጀመሪያ ግጥሚያዋን የምታከናውነው በነገው እለት ነው። ማክሰኞ ጋና ኡጋንዳን ትገጥማለች። በዕለቱ የማሊ እና የግብጽ ውድድርም የሚጠበቅ ነው።
አስተናጋጇ ጋቦን ዘንድሮ ለአፍሪቃ ዋንጫ ዝግጅት 700 ሚሊዮን ዩሮ በመገፍገፍ ጥድፊያ ቢታከልበትም ሰፊ ዝግጅት ለማድረግ ጥረት አድርጋለች። ቅዳሜ ዕለት ተጨዋቾቿ በመክፈቻው በደጋፊዎች ፊት ከጊኒ ቢሳዎ ጋር ያደረጉት ፍልሚያ ግን በድል አልተጠናቀቅም። ጋቦን በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ዩሮ ለዝግጅቱ ማፍሰሷ ላልተዋጠላቸው ደጋፊዎች በሜዳዋ አንድ እኩል ተለያይታ ነጥብ ለመጋራት መገደዷ ሳያንገበግባቸው አልቀረም።
ጨዋታው ከመጀመሩ በፊት ቃለ መጠይቅ የተደረገላቸው የሀገሪቱ የተቃዋሚ ፓርቲዎች እና አንዳንድ ነዋሪዎች ከሀገሪቱ ኢኮኖሚ አንጻር የፈሰሰውን ወጪ የተቹም አሉ። ጋቦን እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2012 የአፍሪቃ ዋንጫን አዘጋጅታ ምንም የተለየ ያተረፈችው ነገር የለም የሚሉም አልታጡም። በመዲናዪቱ ሊቭሬቪል ጎስቋላ መንደር ውስጥ ነዋሪ የሆኑት ፋኒ ከተቺዎቹ አንዷ ናቸው።
«ለእኔ ጋቦን የአፍሪቃ ዋንጫ ማዘጋጀቷ አይታየኝም። ከደረሰብን የገንዘብ ቀውስ እና የምርጫ ትርምስ ወዲህማ የማይታሰብ ነው። በ2012 ያዘጋጀነው ውድድር ራሱ አንዳችም የፈየደልን ነገር የለም። ለምን አዲስ እንዳዘጋጁ አይገባኝም።»
ጋቦን የዛሬ አምስት አመት በጣምራ ውድድሩን ባዘጋጀች በዓመቱ መስተንግዶውን የተረከበችው ደቡብ አፍሪቃ ነበረች። ዘንድሮ በጋቦን አልታደመችም። ደቡብ አፍሪቃን ተከትላ 30ኛውን የአፍሪቃ ዋንጫ ልታሰናዳ የታጨችው ሞሮኮ ነበረች። በወቅቱ በተቀሰቀሰው የኢቦላ ወረርሽ ሞሮኮ ከአስተናጋጅነቱ ራሷን በማግለሏ ከውድድሩ ታግዳ ከጋቦን ጋር በጣምራ ያሰናዳችው ኢኳቶሪያል ጊኒ 30ኛው የአፍሪቃ ዋንጫ ውድድርን ተረክባ አስተናገደች። ዘንድሮ አልታደመችም።
በዘንድሮው ውድድር በምድብ 1 አስተናጋጇ ጋቦን፣ ጊኒ ቢሳዎ፣ ቡርኪና ፋሶ እና ካሜሩን ይገኛሉ። በመጀመሪያ ግጥሚያቸውም አንድ እኩል በመለያየታቸው በምድቡ ሁሉም አንድ አንድ ነጥብ ይዘዋል።
በምድብ 2 አልጀሪያ፣ ዚምባብዌ፣ ሴኔጋል እና ቱኒዝያ ተመድበዋል። አልጀሪያ እና ዚምባብዌ ትናንት የተለያዩት 2 ለ2 ነው። ፖላንዳዊው ሲሞን ከፖላንድ ድረስ ወደ ጋቦን ያቀናው ቱኒዝያን ለመደገፍ ነበር። ምክንያቱ ደግሞ የቱኒዝያው አሰልጣኝ ፖላንዳዊ መሆናቸው ነው። በእርግጥ ሲሞን የአፍሪቃ እግር ኳስ ዋንጫ ጨዋታ ላይ መታደም የረዥም ጊዜ ፍልጎቱ ነበር።
«ለአፍሪቃ እግር ኳስ ጨዋታ መምጣት የሁል ጊዜ ምኞቴ ነበር። በስተመጨረሻም ተሳክቶልኛል። ቱኒዝያ እንድታሸንፍ ነው አጥብቄ የምሻው። ምክንያቱም አሠልጣኛቸው ፖላንዳዊ ናቸው። ስለዚህ ድጋፌ ለቱኒዚያ እና ለአስተናጋጇ ጋቦን ነው»
ፖላንዳዊው ሲሞን በቱኒዝያ ባይሳካለትም በአስተናጋጇ ጋቦን ግን ሳይጽናና አልቀረም። ጋቦን ከጊኒ ቢሳዎ ጋር ባደረገችው የመክፈቻ ጨዋታ የተለያየችው አንድ እኩል በመውጣት ነበር። ቱኒዝያ ግን ፍራንስቪሌ ስታዲየም ውስጥ ትናንት ለቴራንጋ አናብስት እጅ ሰጥታለች። ቱኒዝያ በሴኔጋል ብሔራዊ ቡድን 2 ለ0 ድል ተነስታለች።
ሴኔጋሎች ቱኒዝያውያኑን 2 ለ0 ባሸነፉበት ጨዋታ ሁለተኛዋን ግብ ከመረብ ያሳረፈው በጀርመናዊው የሊቨርፑል አሠልጣኝ ዬርገን ክሎፕ ተመራጭ የሆነው ሳዲዮ ማኔ ነው። በእንግሊዙ ፕሬሚየር ሊግ ለሊቨርፑል ተሰልፎ የሚጫወተው ሳዲዮ ማኔ የቴራንጋ አናብስትን አሸናፊ ያደረገችውን ግብ ሲያስቆጥር፤ ቡድኑ ሊቨርፑል ግን በፕሬሚየር ሊጉ ውድድር ነጥብ ጥሏል።
ሊቨርፑል ሳዲዮ ማኔ በሌለበት ትናንት ማንቸስተር ዩናይትድን ገጥሞ የማታ ማታ ዝላታን ኢብራሒም በጭንቅላት ገጭቶ ከመረብ ባሳረፋት ኳስ አንድ እኩል ለመለያየት ግድ ሆኖበታል። በጄምስ ሚልነር ፍጹም ቅጣት ምት ኦልትራፎርድ ስታዲየም ላይ ያገኘው የአሸናፊነት ዕድልም መክኗል።
የሊቨርፑሉ አሰልጣኝ ዬርገን ክሎፕ፦ ቡድናቸው በተቀናጀ መልኩ ጥሩ ኳስ እንደተጫወተ ማንቸስተር ዩናይትድ በአንጻሩ ረዥም ኳስ ላይ ማተኮሩን ተናግረዋል። «በማንቸስተር ዩናይትድ ሜዳ አቻ መውጣት የምትቀበለው ነው፤ ግን 98 ደቂቃውን ጨዋታ ላጤነ ማሸነፍ የነበረብን እኛ ነበርን» ሲሉ መጠነኛ ቁጭት በዋጠው ስሜት ተናግረዋል።
የማንቸስተር ዩናይትድ አሠልጣኝ ፖርቹጋላዊው ሆዜ ሞሪንሆ በበኩላቸው፦ «እኛ በማጥቃት ስንጫወት፤ ሊቨርፑሎች መከላከል ላይ አተኩረዋል» ብለዋል። በእርግጥ ሊቨርፑሎች «እንዴት ኳስ መጫወት እና መቆጣጠር እንደሚቻል በሚገባ ተክነውበታል» ሲሉም አክለዋል።
ማንቸስተር ዩናይትድ አቻ የምታደርገውን ግብ ያገኘው በ84ኛው ደቂቃ ላይ ነበር። ማንቸስተር ዩናይትድ ካለፈው ጥቅምት ወር አንስቶ አንድም ጨዋታ ባለመሸነፉ አሁን በደረጃ ሰንጠረዡ ስድስተኛ ላይ ከመሪው ቸልሲ በ12 ነጥብ ርቆ ይገኛል። በቶትንሐም ሆትስፐር በግብ ክፍያ ተበልጦ በ45 ነጥብ ሦስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ሊቨርፑል ከአርሰናል በአንድ ነጥብ ይበልጣል።
በምድብ 3 አይቮሪ ኮስት እና ከቶጎ እንዲሁም ሞሮኮ ከዲሞክራቲክ ኮንጎ ጋር የሚጫወቱት ዛሬ ነው። ነገ በምድብ 4 የሚገኙት ጋና እና ዩጋንዳ የመጀመሪያ ግጥሚያቸውን ያከናውናሉ። የሁለቱ ጨዋታ እንደተጠናቀቀም ማሊ ከግብጽ ጋር ትፋለማለች።
አትሌቲክስ
በብዙዎች ዘንድ በጉጉት የሚጠበቀው የለንደን ማራቶን የሩጫ ውድድር የፊታችን ሰኞ ይከናወናል። በውድድሩ ላይ በብዙ የአትሌቲክስ ስፖርት ተንታኞች ከፍተኛ ግምት የተሰጠው ኢትዮጵያዊው አትሌት ቀነኒሳ በቀለ እና በሪዮ ኦሎምፒክ ለኢትዮጵያ የብር ሜዳሊያ ያስገኘው አትሌት ፈይሳ ሊሌሳ ከፍተኛ ፉክክር ያሳያሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የአትሌት ቀነኒሳ በቀለ በግሉ ያስመዘገበው 2:03:03 ሰከንድ ሲሆን የፈይሳ ሌሊሳ የግል ምርጥ ሰአት ደግሞ 2:04:52 ነው። አትሌት ፈይሳ ሌሊሳ ዩናይትድ ስቴትስ ሂውስተን ከተማ ውስጥ ትናንት በተከናወነው የግማሽ ማራቶን የሩጫ ውድድር የዩናይትድ ስቴትሱን ሊዮናርድ ኮሪርን ተከትሎ በሁለተኛነት አጠናቋል። በውድድሩ ህዝቅኤል ተወልደ፤ ፍቃዱ ጻዲቅ እና ይግረም ደመላሽ ከ3ኛ እስከ አምስተኛ ደረጃ አግኝተዋል። ኤርትራዊው ሳምሶን ገብረ ዮሐንስ በ6ኛነት አጠናቋል።
በሳምንቱ ውስጥ ከተከሰቱ ስፖርታዊ ክንዋኔዎች መካከል በመሀመድ ሁሴን ዓሊ ዓላሙዲ ስም የተገነባው የወልዲያ ስታዲየም ምረቃ ይገኝበታል። ስታዲየሙ እጅግ ዘመናዊ እና እስከ ግማሽ ቢሊዮን ብር የፈሰሰበት እንደሆነ ተነግሮለታል። ነዋሪዎች ለስታዲየሙ በርካታ ሚሊዮን ገንዘብ እንዳዋጡ ተገልጧል። ስለ ወልዲያ ስታዲየም ወደፊት የስፖርት ተንታኝ አነጋግረን ዘገባ ለማቅረብ እንሞክራለን።
የጀርመን እግር ኳስ ዳይሬክተር ሐንሲ ፍሊክ ባልተጠበቀ ሁኔታ ሥራ መልቀቃቸውን አስታውቀዋል። የሐንሲን ቦታ የጀርመን ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ዋና አሠልጣኝ ዮአሒም ሎይቭ ተባባሪ የሆኑት ሆርስት ህሩቤሽ ይተካሉ ተብሏል። ዳይሬክተሩ ሥልጣናቸውን የለቀቁት ለቤተሰባቸው ጊዜ ለመስጠት እንደሆነ ተናግረዋል።
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ሸዋዬ ለገሰ