ስፖርት፤ ጥቅምት 26 ቀን፣ 2011 ዓ.ም
ሰኞ፣ ጥቅምት 26 2011የቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ቡድን ወደ ፕሬሚየር ሊጉ ባደገው የባህር ዳር ከተማ የእግር ኳስ ቡድን ትናንት በደጋፊው ፊት ሽንፈት ገጥሞታል። «በዛ ትልቅ ድባብ ውስጥ ውጤቱን ማጣቱ ነው በጣም ያናደደኝ» ሲሉ አሰልጣኙ ለDW ተናግረዋል። ዝርዝር ዘገባ ይኖረናል። ከኒውዮርክ ማራቶን አንስቶ ኢትዮጵያውያን በሳምንቱ መገባደጃ በመላው ዓለም በርካታ ድልችን አስመዝግበዋል። ለሻምፒዮንስ ሊግ ግጥሚያ ዐሥራ ስድስት የአውሮጳ ብርቱ ቡድኖች ቀጠሮ ይዘዋል። በነጋታው ረቡዕ በተመሳሳይ ስምንት ግጥሚያዎች ይኖራሉ። ቢሊየነሩ ቡጢኛ ፍሎይድ ማይዌዘር ከጃፓናዊው የቡጢርግጫ እና ቅይጥ የፍልሚያ ጥበብ ባለድል ጋር ሊጋጠም ቀጠሮ ተይዟል። የፍልሚያው አይነት ግን ቡጢ ይኹን ሌላ አይነት ገና አልታወቀም።
ትናንት በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች በተከናወኑ የማራቶን የሩጫ ውድድሮች ኢትዮጵያውያን ድል ቀንቷቸዋል። ለሁለት ጊዜያት የቦስተን ማራቶን ባለድል የነበረው አትሌት ሌሊሳ ደሲሳ ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በተከናወነው የኒውዮርክ ማራቶን የአንደኛነት ደረጃ ድልን ተቀዳጅቷል። አትሌት ሌሊሳ ደሲሳ አንደኛ በመውጣት ያሸነፈበት ጊዜ፦ 2:05:59 ነው። ከሁለት ሰከንዶች በኋላ በመግባት ሁለተኛ ደረጃ የተቀዳጀውም ኢትዮጵያዊው አትሌት ሹራ ቂጣታ ነው። ኬንያዊው አትሌት ጄኦፍሬይ ካምዎሮር የሦስተኛ ደረጃን አግኝቷል። ጄኦፍሬይን ሁለት ደቂቃ ከአራት ሰከንዶች በመከተል የገባው ኢትዮጵያዊው አትሌት ታምራት ቶላ የአራተኛ ደረጃን አግኝቷል። 2:08:30 አስመዝግቧል። አትሌት ታደሰ ያኤ 12ኛ፣ ግርማ በቀለ እና ብርሃኑ ዳሬ 19ኛ እና 20ኛ በመኾን አጠናቀዋል።
በተመሳሳይ የኒውዮርክ ማራቶን የሴቶች ውድድር ኬንያዊቷ ማሪ ኬታኒ ካለፉት አምስት ዓመታት አንስቶ ትናንት ለአራተኛ ጊዜ ድል በመቀዳጀት ሁለተኛዋ ሴት አትሌት ኾናለች። ማሪ ኬታኒ ዝነኛዋ አትሌት የሀገሯ ልጅ ቪቪያን ቼሩዮትን 3 ደቂቃ ከ13 ሰከንዶች በመቅደም ነው ያሸነፈችው። ሮጣ ያጠናቀቀችበት የ2:22:48 ጊዜ በታሪክ ሁለተኛው ፈጣን ሰአት ተብሎ ተመዝግቦላታል። እስካሁን የዓለማችን ፈጣኑ ጊዜ ተብሎ የተያዘው ሌላኛዋ ኬንያዊት አትሌት ማርጋሬት ኦኮዮ እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2003 የገባችበት 2:22:31 ሰከንዶች ጊዜ ነው።
በቻይና ሃንግዡ ማራቶን የሴቶች ውድድርም ኢትዮጵያውያቱ ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ደረጃ በማግኝት አሸንፈዋል። በውድድሩ ኂሩት ጥበቡ 2:25:09 በመሮጥ አንደኛ ስትወጣ፤ 2:27:33 የሮጠችው ፀሓይ ደሳለኝ የኹለተኛ ደረጃ አግኝታለች። የሦስተኛ ደረጃውን ሲፋን መላኩ 2:31:47 በመሮጥ አግኝታለች። ኬንያውያን ከአንደኛ እስከ አምስተኛ ደረጃውን ተከታትለው በያዙበት በሃንግዡው ውድድር፤ ኢትዮጵያውያኑ፦ መሥፍን ተሾመ እና ሁሴን መሐመድ ዓሚን ስድስተኛ እና ሰባተኛ በመኾን አጠናቀዋል።
የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የአንደኛ ሳምንት ቀሪ ጨዋታዎችና ሁለተኛ ሳምንት ግጥሚያዎች በሳምንቱ መገባደጃ በተለያዩ ከተሞች ተከናውነዋል። ትናንት አዲስ አበባ ውስጥ በተከናወነው የቅዱስ ጊዮርጊስ እና የባሕር ዳር ከተማ የእግር ኳስ ቡድኖች ግጥሚያ አንጋፋው ቡድን ወደ ፕሬሚየር ሊጉ ባደገ ቡድን ለሽንፈት ተዳርጓል።
የቅዱስ ጊዮርጊስ ቡድን ደጋፊዎች ቢጫ እና ቀይ ቀለማት ያላቸው መለያዎችን ስታዲየሙ ውስጥ በመያዝ በእንግሊዝኛ «SAVE TANA, LALIBELA» (ጣናን እና ላሊበላን እንታደግ) የሚል መልእክት አሳይተዋል። ደጋፊዎቹን እና እንግዳ ቡድኑን በደመቀ ኹኔታ የተቀበለው የቅዱስ ጊዮርጊስ ቡድን ጨዋታው ሲጠናቀቅ እንደአጀማመሩ የደመቀ ስሜት ይዞ አይደለም ከሜዳ የወጣው። ወደ ፕሬሚየር ሊጉ ባደገው የባህር ዳር ቡድን 1 ለ0 ሽንፈት ገጥሞታል። የቅዱስ ጊዮርጊስ ቡድን አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታን ውድድሩን በተመለከተ በስልክ ቃለ-መጠይቅ አድርገንላቸዋል። ለትናንቱ ጨዋታ ምን ያኽል ተዘጋጅታቹ ነበር ወደ ስታዲየሙ የሄዳችሁት? የመጀመሪያው ጥያቄ ነበር።
«እኛ የሚገባውን ማድረግ ያለብንን የሥልጠና መርሐ-ግብር ጨርሰን ወደ ስቴዲየም ሄደናል። ጥሩ ሥልጠና አድርገን፤ ጥሩ ነገር አስበንም ነበር የሄድነው። ስገባ የነበረው የደጋፊ ድባብ፤ [ልዩ ነበር።] የቅዱስ ጊዮርጊስ ኼሌም ልማድ እና ኹሌም የማየው ይኼን ነው። እኔ ትልቅ ማክበር እና እምወደው ደጋፊ ፊት ስጫወት ለራሴ ውስጤ የሚሰማን ነገር አለ፤ ትልቅ ነገር። ያንን ነገር ስንገባ እያየነው ነበር። ለእኔ በጣም እጅግ የተሰማን ነገር በደጋፊዎቼ እና በዚያ አይነት ትልቅ ድባብ ውስጥ ውጤቱን ማጣቱ ነው ውስጤን በጣም ያናደደኝ።»
የሻምፒዮንስ ሊግ በርካታ ግጥሚያዎች ነገ እና ከነገ በስተያ በተለያዩ የአውሮጳ ከተሞች ይከናወናሉ። በነገው እለት ምሽት ቀዳሚ ጨዋታቸውን የሚያከናውኑት የእንግሊዙ ሊቨርፑል እና የሠርቢያው የቤልግሬድ ቀይ ኮከብ ናቸው። በተመሳሳይ ሰአት የፈረንሳዩ ሞናኮ እና የቤልጅጉ ክለብ ብሩዥ ይፋለማሉ።
ሊቨርፑል በነገው እለት ወደ ሠርቢያ የሚያቀናው ትውልደ-አልባኒያ የስዊትዘርላንዱ አጥቂ ሼርዳን ሻቂሪን በቡድኑ ሳያካትት ነው። ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ ቀደም ሲል ለዓለም ዋንጫ ማጣሪያ የመጀመሪያ ዙር ስዊዘርላንድ ብሔራዊ ቡድን ከሠርቢያ ጋር ባደረገው ግጥሚያ የስዊትዘርላንድ ሠርቢያ ላይ ግብ ሲያስቆጥር አጥቂው ግራ እና ቀኝ የሚመለከቱ፤ ክንፎቻቸው የተዘረጉ አሞሮች ምስልን የሁለት እጆቹን ጣቶች ዘርግቶ በማጣመር በማሳየቱ በተነሳው ቁጣ ነው። ክንፋቸው የተዘረጉት አሞሮች ምስል የአልባንያ ዐርማ መለያ ነው።
ምንጫቸው ከኮሶቮ የኾኑት የአልባንያ ዝርያዎች እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ1999 የሰሜን አትላንቲክ ቃል ኪዳን አባል ሃገራት (የኔቶ) ጦር ጣልቃ እስኪገባ ድረስ በሠርቢያ ጦር ኃይላት ጭፍጨፋ ተከናውኖባቸው ነበር። ሼርዳን ሻቂሪን የአልባንያ ዓርማ የኾኑት ጥንድ አሞሮችን ምስል በእጆቹ በማሳየቱ 10,000 የስዊስ ፍራንክ በዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማኅበራት ፌዴሬሽን በእንግሊዝኛ ምኅፃሩ (FIFA) «ፊፋ» ተቀጥቶ ነበር። የሊቨርፑሉ አሰልጣኝ ዬርገን ክሎፕ ነገ ወደ ሠርቢያ ሲያቀኑ ሼርዳን ሻቂሪን ከቡድናቸው ጋር ቢያካትቱ እዛ ምን ሊጠብቃቸው እንደሚችል እንደማያውቁ ተናግረዋል። ኾኖም ግን ቡድናቸው ወደ ሠርቢያ የሚሄደው መቶ በመቶ እግር ኳስ ለመጫወት እንጂ ስለሌሎች ነገሮች ለማሰብ እንዳልኾነ ገልጠዋል። ይኽ ውሳኔያቸው ላይ ግን አንዳችም «የፖለቲካ መልእክት» እንደሌለው በአጽንዖት ተናግረዋል። ከወር በፊት ሊቨርፑል የሠርቢያው ሬድ ስታርን አስተናግዶ 4 ለ0 በረታበት ጨዋታ ለቡድኑ መሰለፍ የጀመረው ሼርዳን ሻቂሪ የተወለደው ዩጎዝላቪያ ውስጥ ሲኾን፤ እድገቱ ከቤተሰቦቹ ጋር በተሰደደበት ሀገር ስዊትዘርላንድ ነው።
በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ፉልሀም ከሁደርስፊልድ ጋር ዛሬ ይጋጠማል። 27 ነጥብ ይዞ ሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ቸልሲ ክሪስታል ፓላስን ትናንት 3 ለ1 ድል አድርጓል። ከትናንት በስትያ ቶትንሀም ዎልፍቭስን 3 ለ2፤ ኒውካስል ዋትፎርድን 1 ለ0 አሸንፈዋል። በቸልሲ በግብ ክፍያ ተበልጦ ሦስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ሊቨርፑል ከአርሰናል ጋር አንድ እኩል ሲለያይ፤ የደረጃ ሠንጠረዡን በ20 ነጥብ የሚመራው ማንቸስተር ሲቲ ሳውዝሐምፕተንን 6 ለ1 አደባይቷል።
ትናንት በጀርመን ቡንደስሊጋ ውድድር ማይንትስ ቬርደር ብሬመንን 2 ለ1 ድል አድርጓል። ቅዳሜ እለት ባየር ሙይንሽን ከፍራይቡርግ ጋር አቻ ሲለያይ በደረጃ ሰንጠረዡ በ24 ነጥብ መሪው ቦሩስያ ዶርትሙንድ ቮልፍስቡርግን 1 ለባዶ አሸንፏል። ባየርሙይንሽን እኩል 290 ነጥብ ይዞ በግብ ክፍያ በሞይንሽንግላድባኅ ይበለጣል፤ ሦስተኛ ደረጃ ላይም ይገኛል።
ቡጢ
የጎርጎሪዮሱ አዲስ ዓመት በሚጠባበት ዋዜማ ምሽት፦ ቢሊየነሩ ቡጢኛ ፍሎይድ ማይዌዘር ከጃፓናዊው የቡጢርግጫ እና ቅይጥ የፍልሚያ ጥበብ ባለድል ጋር ሊጋጠም ቀጠሮ ተይዞለታል። የ41 ዓመቱ ጎልማሳ ማይዌዘር ባለፈው ዓመት ኮኖር ማክ ግሬጎርን በማሸነፍ በሕይወት ዘመኑ 50ኛ ድሉን ያስመዘገበ ቡጢኛ ነው። ተፋላሚው የ20 ዓመቱ ወጣት ቴኒሺን ናሱካዋ በበኩሉ በቡጢርግጫ (kickboxing) ለ27 ጊዜ እንዲሁም በቅይጥ የፍልሚያ ጥበብ (mixed martial arts) ለአራት ጊዜያት አሸንፏል። እስካሁን አንድ ጊዜም አልተሸነፈም። ማይዌዘር ከእድሜው እኩሌታ ከሚያንሰው ጃፓናዊ ጋር በአዲስ ዓመት ዋዜማ የሚያከናውነው የፍልሚያ አይነት ግን ቡጢ ይኹን ሌላ ገና ዐልታወቀም።
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ተስፋለም ወልደየስ