1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ስፖርት

ሰኞ፣ ኅዳር 24 2005

በአውሮፓ ቀደምት የእግር ኳስ ሊጋዎች ውስጥ የመጀመሪያው ዙር ሊጠናቀቅ እየተቃረበ ሲሆን በላቲን አሜሪካ ደግሞ ሻምፒዮናው ቀስ በቀስ በመጠቃለል ላይ ነው።

ምስል AP

በአውሮፓ ቀደምት የእግር ኳስ ሊጋዎች ውስጥ የመጀመሪያው ዙር ሊጠናቀቅ እየተቃረበ ሲሆን በላቲን አሜሪካ ደግሞ ሻምፒዮናው ቀስ በቀስ በመጠቃለል ላይ ነው። በብራዚል አንደኛ ዲቪዚዮን ፍሉሚኔንዘ በቅርቡ ውድድሩ ሊጠቃለል ሶሥት ጨዋታዎች ቀርተው ሳለ ቀድሞ ሻምፒዮንነቱን ማረጋገጡ አይዘነጋም። በአርጄንቲና ሊጋ ደግሞ ቬሌዥ ሣርስፊልድ ትናንት ዩኒየን-ሣንታ-ፌን 2-0 በመርታት አንድ ጨዋታ ሲቀር ለዘጠነኛ ጊዜ የአገሪቱ ሻምፒዮን ሊሆን በቅቷል። ላኑስ ሁለተኛ ሲሆን ሶሥተኛው አትሌቲኮ ቤልግራኖ ነው። በዓለምአቀፍ ደረጃ በሰፊው የሚታወቁት ቀደምት ክለቦች ቦካ ጁኒየርስና ሬቨር ፕሌት በስድሥተኛና በስምንተኛ ቦታ ተወስነዋል።

በሜክሢኮ ደግሞ ቲሁዋና ትናንት ለመጀመሪያ ጊዜ የሜክሢኮ ሊጋ ሻምፒዮና ባለድል ሆኗል። ከአምሥት ዓመታት በፊት የተቋቋመው ክለብ በሜክሢኮ አንደኛ ዲቪዚዮን ውስጥ አንድ ዓመት ተኩል ብቻ ማሳለፉ ሲታሰብ ሻምፒዮንነቱ በጣሙን የሚያስደንቅ ነው። ቡድኑ ጠንካራ ተጋጣሚውን ቶሉሃን 2-0 ሲረታ በደርሶ መልስ ግጥሚያው አጠቃላይ ውጤት 4-1 አሸናፊ ሆኗል። ቶሉሃ በበኩሉ ለ 11ኛ ጊዜ የዋንጫ ባለቤት በመሆን ከጉዋዳላሃራ ለመስተካከል የነበረው ምኞት ዕውን ሳይሆንለት ቀርቷል።

በዩ ኤስ አሜሪካ የሴቶች እግር ኳስ ሻምፒዮና የሰሜን ካሮላይናው ክለብ ለ 21ኛ ጊዜ ሻምፒዮን መሆኑ ተሳክቶለታል። ክለቡ ለዚህ ክብር የበቃው ፔን ስቴትን 4-1 ካሸነፈ በኋላ ነው። በወንዶች የእንግሊዙ ኮከብ ተጫዋች ዴቪድ ቤክሃም ባለፈው ሰንበት ለሎስ አንጀለስ ጋላክሢይ ለመጨረሻ ጊዜ በመሰለፍ ከሊጋው የክብር ስንብት አድርጓል። የ 37 ዓመቱ ቤክሃም በዩ ኤስ ሶከር ሊጋ ውስጥ በቆየባቸው ዓመታት በችሎታው ታላቅ ትኩረትን ሲስብ የአሜሪካ እግር ኳስ ተመልካች ቁጥር እንዲያድግም ጠቃሚ አስተዋጽኦ ነው ያደረገው። በቀላሉ የሚረሣ አይሆንም።

ምስል gettyimages/AFP

በአፍሪቃ ላይ እናተኩርና ኡጋንዳ ውስጥ በሚካሄደው የማዕከላዊና ምሥራቅ አፍሪቃ ዋንጫ ውድድር በሶሥት የተከፈለው የምድብ ዙር አብቅቶ ወደ ጥሎ ማለፉ ዙር ያለፉት ሃገራት ማንነት ለይቶለታል። በምድብ-አንድ ኡጋንዳና ኬንያ በቀጥታ ሲያልፉ ኢትዮጵያም በጥሩ ሶሥተኝነት ከሱዳን በጎል በመላቅ ወደ ቀጣዩ ዙር ተሻግራለች። ደቡብ ሱዳን በመጀመሪያ የሤካፋ ተሳትፎዋ በዜሮ ነጥብ ከወዲሁ መሰናበቱ ግድ ሆኖባታል። ኢትዮጵያም በምድቡ ያሸነፈችው ይህችኑ አዲስ መጤ አገር ነበር።

ከምድብ-ሁለት ቡሩንዲና ታንዛኒያ ወደፊት ሲዘልቁ ሱዳንና ሶማሊያ ከወዲሁ ወድቀው ቀርተዋል። በመጨረሻው ምድብ-ሶሥት ደግሞ ሩዋንዳና ጂቡቲን የተካችው ማላዊ በቀጥታ ሲያልፉ ዛንዚባር እንደ ኢትዮጵያ በሶሥተኝነት ወደፊት ለመዝለቅ ችላለች። ኤርትራ በአራተኝነት ከውድድሩ ተሰናብታለች። በነገራችን ላይ 14 የሚሆኑት የኤርትራ ብሄራዊ ቡድን ዓባላት በውድድሩ አጋጣሚ በዚያው በኡጋንዳ መሰወራቸውን በዛሬው ዕለት ሮይተርስ ዜና አገልግሎት ዘግቧል።

በሩብ ፍጻሜው ግጥሚያ ዛሬ ሩዋንዳ ከታንዛኒያና ኢትዮጵያ ከኡጋንዳ የሚገናኙ ሲሆን በነገው ዕለት ደግሞ ቡሩንዲ ከዛንዚባር እንዲሁም ኬንያ ከማላዊ ይጋጠማሉ። ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ከአስተናጋጇ አገር ጋር የሚያደርገው ግጥሚያ በጣም ከባድ ነው የሚሆነው። ኡጋንዳ በምድቡ ዙር ኢትዮጵያን 1-0 ረትታ እንደነበር ይታወሳል።

ምስል picture-alliance/dpa

የአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋ

የያዝነው ሣምንት በአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋ ውድድር የምድብ-ዙር ነገና ከነገ በስቲያ የመጨረሻዎቹ ግጥሚያዎች የሚካሄዱበት ነው። ከምድብ አንድ ፓሪስ-ሣንት-ዠርማንና የፖርቱጋሉ ፖርቶ ወደ ሩብ ፍጻሜው ማለፋቸውን ከወዲሁ በማረጋገጣቸው ነገ እርስበርስ የሚያደርጉት ግጥሚያ ምንም የሚለውጠው ነገር አይኖርም። በምድብ-ሁለት፣ ሶሥትና አራትም ሁኔታው ተመሳሳይ ሲሆን የጀርመኑ ሻልከ፣ አርሰናል፣ የስፓኙ ማላጋ፣ ኤ ሲ ሚላን፤ እንዲሁም ዶርትሙንድና ሬያል ማድሪድ በነገ ግጥሚያቸው ቢሸነፉም ወደተከታዩ ዙር የሚያልፉ ናቸው።

በምድብ-አራት ውስጥ ሬያል ማድሪድ ከአያክስ አምስተርዳም የሚጋጠም ሲሆን ያለፈው የእንግሊዝ ሻምፒዮን ማንቼስተር ሢቲይ ማለፉ ቢቀርበት ከመጨረሻው ወደ ሶሥተኛው ቦታ ከፍ በማለት በአውሮፓ ሊጋ ውድድር ለመቀጠል የግድ የጀርመኑን ክለብ ዶርትሙንድን መርታት አለበት። እርግጥ ይህም የሚሳካለት ሶሥተኛው አያክስ ከተሸነፈ ወይም በእኩል-ለእኩል ውጤት ከተወሰነ ብቻ ነው።

በምድብ-አምሥት በአንጻሩ የኡክራኒያው ሻኽታር ዶንትስክ፣ የኢጣሊያው ጁቬንቱስና የእንግሊዙ ቼልሢይ ሶሥቱም ገና የማለፍ ዕድል ሲኖራቸው አንዱ በግድ በምድቡ ዙር መወሰኑ አይቀርለትም። በዚህ ምድብ ውስጥ ዶኔትስክ ከጁቬንቱስ ጠንካራው ግጥሚያ ሲሆን ቼልሢይን ቀለል ያለው የስካንዲኔቪያ ክለብ ኖርድስየላንድ ይጠብቀዋል። ምድብ-ስድሥት ውስጥ የስፓኙ ክለብ ቫሌንሢያና የጀርመኑ ባየርን ሙንሺን ወደ ጥሎ ማለፉ ዙር የተሻገሩ ሲሆን በፊታችን ረቡዕ በየፊናቸው የሚያደርጉት ግጥሚያ የአንደኝነቱን ቦታ ለመያዝ ካልሆነ በስተቀር ሌላ ትርጉም አይኖረውም።

በምድብ-ሰባት ውስጥ ባርሤሎናም ቀድሞ ማለፉን ሲያረጋግጥ ሤልቲክ ግላስጎውና ቤንፊካ ሊዝበን ለሁለተኝነት የሚያደርጉት ፉክክር በፊታችን ረቡዕ ምሽት ይለይለታል። ቤንፊካ ከባርሤሎና የሚጫወት ሲሆን የሤልቲክ ተጋጣሚ ደግሞ አራተኛ ሆኖ የቀረው ስፓርታክ ሞስኮ ነው። በምድብ-ስምንትም ማንቼስተር ዩናይትድ ወደ ሩብ ፍጻሜው ማለፉን ቀድሞ ሲያረጋግጥ ክሉጅና ኢስታምቡል ገና ለሁለተኛው ቦታ መታገል ይኖርባቸዋል። በአጠቃላይ ከየምድቡ አንደኛና ሁለተኛ የሚሆኑት 16 ክለቦች ወደ ሻምፒዮና ሊጋው ጥሎ ማለፍ ዙር ሲያልፉ የየምድቡ ሶሥተኛች ደግሞ መለስተኛውን የአውሮፓን ሊጋ ውድድር ይቀላቀላሉ።

ምስል AP

አትሌቲክስ

በትናንትናው ዕለት ጃፓን ውስጥ ተካሂዶ በነበረው የፉኩኦካ ዓለምአቀፍ ማራቶን ሩጫ ኬንያዊው ጆሴፍ ጊታው አሸናፊ ሆኗል። በዚያው በጃፓን የሚኖረው የ 24 ዓመት አትሌት 42ቱን ኪሎሜትር በሁለት ሰዓት ከስድሥት ደቂቃ 58 ሤኮንድ ጊዜ ሲያቋርጥ አገሬው ተወዳዳሪ ሂሮዩኪ ሆሪባታ ሁለተኛ፤ እንዲሁም ፖላንዳዊው ሄንሪክ ሾስት ሶሥተኛ በመሆን ከግባቸው ደርሰዋል። ከተሳታፊዎቹ መካከል የቀድሞው የዓለም ክብረ-ወሰን ባለቤት ሃይሌ ገ/ሥላሴም አንዱ ሲሆን ከ 32 ኪሎሜትር በኋላ ሩጫውን ማቋረጡ ግድ ነበር የሆነበት።

ሃይሌ ታፋው ላይ በተሰማው ሕመም መቀጠል እንዳልቻለና ሩጫውን ማቋረጥ እንደተገደደ ለጋዜጠኞች ገልጿል። የ 39 ዓመቱ ዕውቅ አትሌት በዚህ ሁኔታ ለምን ከውድድሩ መድረክ ስንብት እንደማያደርግ የሚጠይቁት ታዛቢዎች ጥቂቶች አይደሉም። የአሥር ሺህ ሜትር የኦሎምፒክና የዓለም ሻምፒዮን፤ ከዚያም የማራቶንን ክብረ-ወሰን ለመጀመሪያ ጊዜ ከሁለት ሰዓት አራት ደቂቃ በታች በማውረድ ታሪክ ያስመዘገበው አትሌት እንዳማረበት ከውድድሩ መድረክ ቢለይ ምንኛ በበጀው ነበር። ዘገየ ካልተባለ አሁንም ተገቢውን ጊዜ አውቆ መሰናበቱ ብልህነት ነው።

ምስል AP

እግር ኳስ

በአውሮፓ ቀደምት ሊጋዎች ውድድር ባርሤሎና አትሌቲክ ቢልባኦን 5-1 በመሸኘት በክንፈቱ ሲቀጥል ማንቼስተር ዩናይትድም ከሪዲንግ ጋር ባካሄደው ማራኪ ግጥሚያ 4-3 በማሸነፍ አመራሩን ከፍ ለማድረግ በቅቷል። ሰባቱም ጎሎች የተቆጠሩት በመጀመሪያው አጋማሽ 38 ደቂቃዎች ውስጥ ነበር። የስፓኙ ቀደምት ክለብ ኤፍ ሲ ባርሤሎና በበኩሉ በ 14 ግጥሚያዎች አንዴም ሳይሸነፍ 40 ነጥቦች ላይ በመድረስ በጥሩ የውድድር ጅማሮ የፕሪሜራ ዲቪዚዮኑን አዲስ ክብረ-ወሰን ለማስገንዘብ በቅቷል።

ሊዮኔል ሜሢ ሁለት ጎሎች በማስቆጠር ከቀድሞው የጀርመን አጥቂ ከጌርድ ሙለር የክለብና ብሄራዊ ቡድን የአንድ ውድድር ወቅት የ 85 ጎሎች ሬኮርድ ላይ ይበልጥ ሲቃረብ አሁን አንዲት ጎል ብቻ ናት የቀረችው። ሁለተኛው አትሌቲኮ ማድሪድ በሬያል ማድሪድ 2-0 ሲረታ ከባርሣ ጋር ያለው ልዩነት ወደ ስድሥት ከፍ ብሏል። ሬያል ማድሪድ ደግሞ በሶሥተኝነቱ እንደቀጠለ ነው።

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ያለፈው ወቅት ሻምፒዮን የማንቼስተር ሢቲይ ከኤቨርተን በ 1-1 ውጤት መለያየት በበኩሉ ግጥሚያ ያሸነፈው ማንቼስተር ዩናይትድ አመራሩን ወደ ሶሥት ነጥቦች እንዲያሰፋ ነው የበጀው። ቼልሢይም ዌስት-ሃም-ዩናይትድን 3-1 በማሸነፍ በሶሥተኝነቱ ሲቀጥል ቶተንሃምና አልቢዮን እኩል 26 ነጥብ ይዘው ይከተሉታል። አርሰናል በስዋንሢይ ሢቲይ 2-0 በመረታቱ ወደታች ይብስ በማቆልቆል አሁን አሥረኛ ነው።

ምስል picture-alliance/dpa

በጀርመን ቡንደስሊጋ በጉጉት የተጠበቀው ያለፉት ሁለት ዓመታት ሻምፒዮን የዶርትሙንድና የወቅቱ ሃያል ቡድን የባየርን ግጥሚያ ብዙም ባልደመቀ ሁኔታ 1-1 ሲያበቃ የሚዩኒኩ ክለብ በ 38 ነጥቦች ተዝናንቶ መምራቱን ቀጥሏል። ስምንት ነጥቦች ወረድ ብሎ ሁለተኛው ኑርንበርግን 1-0 ያሸነፈው ሌቨርኩዝን ነው። ዶርትሙንድ ሶሥተኛ፤ ሻልከ አራተኛ! ብሬመን ሆፈንሃይምን 4-1 በመርታት ወደ መጨረሻው ቦታ ሲሸኝ በበኩሉ ከ 12ኛው ወደ ስምንተኛው ቦታ ከፍ ማለቱ ተሳክቶለታል።

በኢጣሊያ ሶሥቱም ቀደምት ክለቦች ጁቬንቱስ፣ ናፖሊና ኢንተር ሚላን በየበኩላቸው ግጥሚያ ሲያሸንፉ በአመራሩ ቅደም ተከተል ላይ በሣምንቱ የተደረገ ለውጥ የለም። በፈረንሣይ ሊጋ በአንጻሩ ሊዮን በአመራሩ ቢቀጥልም ሁለተኛው ፓሪስ-ሣንት-ዠርማን በኒስ በደረሰበት የ 2-1 ሽንፈት ወደ አራተኛው ቦታ ወርዷል። ኦላምፒክ ማርሤይ ሁለተኛ ሲሆን በሶሥተኝነት የሚከተለው ሣንት ኤቲየን ነው። በኔዘርላንድ ሻምፒዮና የአይንድሆፈን መሸነፍ ትዌንቴ ኤንሼዴ አመራሩን እንዲይዝ መንገድ ከፍቷል። በአያክስ አምስተርዳም 3-1 የተረታው አይንድሆፈን ወደ ሶሥተኛው ቦታ ሲያቆለቁል አርንሃይም በወቅቱ ሁለተኛ ነው፤ አያክስ አራተኛ!

ምስል dapd

ቴኒስ

የዓለም ቴኒስ ማሕበር WTA አሜሪካዊቱን ሤሬና ዊሊያምስን የዓመቱ ድንቅ ቴኒስ ተጫዋች ብሎ ሰይሟል። ማሕበሩ ሤሬናን የመረጠው የ 31 ዓመቷ አሜሪካዊት ባለፈው የውድድር ወቅት ያሳየችውን ልዕልና በማጤን ነው። ሤሬና በዚህ ዓመት በታላላቆቹ ውድድሮች በዊምብልደንና በዩ ኤስ ኦፕን ጭምር ስታሸንፍ በለንደን ኦሎምፒክም በነጠላና ከእሕቷ ከቬኑስ ጋር በጥንድም ባለድል እንደነበረች ይታወሳል።

ከዚሁ ሌላ አሁን የዓመቱ መጨረሻ ሲቃረብ በኢስታምቡል የዓለም ሻምፒዮና አሸናፊ መሆኗም ተጨማሪ የጥንካሬዋ መለያ ነው። በምርጫው የመላው ዓለም ጋዜጠኞች ተሳትፈዋል። በሌላ የቴኒስ ዜና የስፓኙ ኒኮላስ አልማግሮ ትናንት ማያሚ ላይ በተካሄደው የቴኒስ ትርዒት ዋንጫ ፍጻሜ ግጥሚያ አሜሪካዊውን ኤንዲይ ሮዲክን በሁለት ምድብ ጨዋታ 6-4,7-5 በሆነ ውጤት ለማሸነፍ በቅቷል።

መሥፍን መኮንን

ሸዋዬ ለገሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW