1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሶማሊያቱ ወጣት የጀርመንን ሽልማት አሸነፈች

ማክሰኞ፣ ጥቅምት 10 2013

ድርጅቱ፣ «ጠመጃዉን አስቀምጡ፣ ብዕር ጨብጡ» ባለዉ መርሕ ብዙ የቀድሞ ልጅ ወታደሮችን ሕይወት ቀይሯል።በሴቶች ላይ የሚደርስ በደልን በተለይም አስገድዶ መድፈርን ለማስቀረትና ተበዳዮችን ለመርዳት ባደረገዉ ጥረትም ብዙ ሴቶችን ከጥቃት ማዳን፣ የተጠቁትን የተሰበረ ልብ መጠገን ችሏሏም።

Somalia Mogadischu Ilwad Elman
ምስል DW/A. Kriesch

 

ሶማሊያዊቷ የመብት ተሟጋችና በጎ አድራጊ ኢልዋድ ኤልማን ወጣት ነች።30 ዓመቷ።ዓላማ፣ ጥረት፣ ምግባር ዉጤቷ ግን  ለብዙዎች አብነት ሆኗል።ሶማሊያን ያወደመዉ ጦርነት ሲባባስ የ2 ዓመትዋ ሕፃን ከእናትዋ ጋር ወደ ካናዳ ተሰደደች።የኤሌክትሪክ መሐንዲስ (ኢንጂነር) አባቷ ኢልማን ዓሊ ግን በጦርነቱ የሚሳተፉ ወጣት ተዋጊዎችን ከሕብረተሰቡ እንዲቀየጡ ይረዱ ስለነበር እዚያዉ ሶማሊያ ቀሩ።እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር (እጎአ) በ1996 በታጣቂዎች ተገደሉ።

ኢልዋድ  አባትዋ በተገደሉ በ14ኛዉ ዓመት የአባትዋን ጅምር ከዳር ለማድረስ ወደ ሶማሊያ ተመለሰኝ።እናቷን ተከትላ ካገር እንደወጣች ሁሉ፣ ወደ ሐገር የተመለሰችዉም እናትዋን አስከትላ ነበር።እጎአ 2010።የ19ኝ ዓመቷ ወጣት ሞቃዲሾ ስትገባ  የትዉልድ ከተማዋ ወድማ፣ ምጣኔ ሐብቷ ደቅቆ፣ ያልተሰደዱ ነዋሪዎችዋ በታጣቂዎች ሲንገላቱ አገኘቻቸዉ።

ሐገሪቱን የሚቆጣጠረዉ የአክራሪዉ ደፈጣ ተዋጊ ቡድን የአሸባብ እርምጃ፣ ጫናና  ጭቆናም ቀላል አልነበረም።ተስፋ ግን አልቆረችም።የቤተሰቧ በተለይም የናትዋ የወይዘሮ ፋርቱና አደን ድጋፍና ማበረታቻ አልተለያትምም።ባባቷ ስም «የኤልማን የሠላም ማዕከል» ያለችዉን ድርጅት መሠረተች።

ድርጅቱ አባቷ የጀመሩትን ሥራ ቀጥሎ፣ የልጅ ወታደሮች እያስተማረ፣ በተለያየ ሙያ እያሰለጠነ፣ የስነ ልቡና ድጋፍም እያደረገ ከሕብረተሰቡ እንዲቀየጡ ይረዳል።ድርጅቱ፣ «ጠመጃዉን አስቀምጡ፣ ብዕር ጨብጡ» ባለዉ መርሕ ብዙ የቀድሞ ልጅ ወታደሮችን ሕይወት ቀይሯል።በሴቶች ላይ የሚደርስ በደልን በተለይም አስገድዶ መድፈርን ለማስቀረትና ተበዳዮችን ለመርዳት ባደረገዉ ጥረትም ብዙ ሴቶችን ከጥቃት ማዳን፣ የተጠቁትን የተሰበረ ልብ መጠገን ችሏሏም።

ምስል Thomas Trutschel/photothek/Imago Images

ኢልዋድ፣ በተለይ የተደፈሩ ሴቶችን የሚረዳና ለመብታቸዉ የሚታገለዉን የድርጅቷን ቅርንጫፍ «እሕት ሶማሊያ» ብላዋለች። በድርጅቱ ጥረት የሶማሊያ መንግስት ሴቶችን በሚደፍሩ ላይ ጠንካራ ቅጣት የሚያስጥል ሕግ አርቅቋል።ሕጉ ከተረቀቀ 2 ዓመት ቢሆነዉም የሐገሪቱ ምክር ቤት ግን እስካሁን አላፀደቀዉም።

የኢልዋድ ድርጅት ባሁኑ ወቅት 172 ሠራተኞች አሉት።በ8 ግዛቶች ፅሕፈት ቤቶች ከፍቷል።የወጣትዋ ምግባር ከአፍሪቃ ቀንድ አልፎ እስከ ማሊ እና በመላዉ የቻድ ሐይቅ አዋሳኝ ሐገራት አብነት ሆኗል።ኢልዋልድ ራስዋ እጎአ ከ2018 ጀምሮ የተባበሩት መንግሥታት  «የሠላም ግንባታ ድርጅት» ወጣት አማካሪም ናት።የጀርመኑ የአፍሪቃ ሸላሚ ድርጅት ለዘንድሮዉ (2020) ሽልማት ኢልዋድን የመረጠዉ ከ32 ብጤዎችዋ አወዳድሮ ነዉ።«ሽልማቱ ለቡድናችን ታላቅ ማበረታቻ ነዉ» አለች ኢልዋድ በቀደም።«በጣም ጠቃሚ ነዉ፣ ምክንያቱም ጀርመን ለብዙ መርሐ-ግብራችን አስተማማኝና ዘላቂ ደጋፊያችን ናትና።»

ምስል Getty Images for BET/E. Gibson

ሽልማቱን በሚቀጥለዉ ሳምንት በርሊን ዉስጥ በሚዘጋጅ ሥርዓት ትቀበላለች።

ኢልዋድ ከዚሕ ለመድረስ ብዙ ፈተናዎችን ማለፍ ነበረባት።ከጥቂት ወራት በፊት እንኳን እዚያዉ ሞቃዲሾ ዉስጥ እሕቷ በጥይት ተመታ ተገድላባታለች።የሶማሊያ መንግስት ባለስልጣናት  ልጅቱን የገደላት ጥይት ተባባሪ ነዉ ብለዉ አሟሟቷን በቅጡ አላጣሩም።ኢልዋድ ግን የባለስልጣናቱን ምክንያት የተቀበለችዉ አትመስልም።ቢሆንም «አልማአስ (እሕቷ)ን የምናስባት ለሰላም፣ለእርቅ ለእኩልነት የምናደርገዉን ትግል ስንቀጥል ብቻ ነዉ» ትላለች።ቀጥላለችም።

ነጋሽ መሐመድ

አዜብ ታደሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW