1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሶማሊያ፣እስላማዊዉ ቡድንና የሰላም ተስፋ

ረቡዕ፣ ግንቦት 30 1998

የሱማሊያ ዋና ከተማ በእስላማዊዉ እንጃ ቁጥጥር ስር መዋሏ ለአገሪቱ ሰላም ማግኘት አዲስ እድል ይከፍት ይሆናል የሚሉ አሉ።

ከተማዋን የተቆጣጠረዉ ቡድን
ከተማዋን የተቆጣጠረዉ ቡድንምስል AP

ዩናይትድ ስቴትስ ደግሞ ህግ አልባዋ ምድር ለአልቃይዳ እቅድና ዓላማ መስፋፋት ዓይነተኛ ምድራዊ ገነት ትሆናለች የሚል ስጋት አላት።

ቡድኑ ከተማዋን የመቆጣጠር እቅዱ ሲሳካ ወዲያዉ ነበር ለዓለም ዓቀፉ ህብረተሰብ መልዕክት ያስተላለፈዉ። ሽብርተኞች ሳንሆን ሰላም ፈላጊዎች ነንና ለሰላማዊ ሂደቱ ድጋፍ አድርጉልን የሚል።

አንዳንዶችም አካሄዱ ቀናና የታሊባኖች ዓይነት ሳይሆን የሱማሊያ ሙስሊሞች ፅንፈኞች አይደሉም ብለዋቸዋል።

ከሶስት ወራት የመንገድ ለመንገድ ዉጊያ የሸሪአ ህግን መመሪያዉ ያደረገዉ እስላማዊ ታጣቂ ቡድን መቋዲሾን መቆጣጠሩ ተሳክቶለታል።

ይህ እንጃ መንግስትና ህግ አልባ በሆነችዉ የሱማሌ ግዛት አምባ ገነኑ ዚያድ ባሬ ከተወገዱበት ከአዉሮፓዉያኑ 1991ዓ.ም ጀምሮ መቋዲሾን ተቆጣጥረዉ በጉልበት ሲገዙ የነበሩትን የጦር አበጋዞች አደብ አስገዝቷል።

ምንም እንኳን ዩናይትድ ስቴትስ ሶማሊያ የሽብርተኞች ምሽግ ትሆናለች የሚል ስጋት እንደያዛት ዲፕሎማቶች ቢናገሩም የእስላማዊዉ ታጣቂ ቡድን መሪዎች ምድሪቱን የሙስሊም መንግስት ለማድረግ ነዉ የዛቱት።

በሶማሊያ የሰላም ሂደት ረገድ እየሰሩ የሚገኙ ማንነታቸዉ እንዳይገለፅ የጠየቁ አዉሮፓዊ ዲፕሎማት ለሮይተርስ እንደገለፁት ሁኔታዉ በሶማሊያ መረጋጋትን የሚያመጣና መንገድ ከፋች ነዉ ብለዉ ያምናሉ።

ዲፕሎማቱ እንደተናገሩት አሳሳቢዉ ነገር ምዕራባዉያን መንግስታት የሸሪዓ ህግ የሚለዉን ሲሰሙ የሚያገናኙት ከሽብርተኝነት ጋር መሆኑ ነዉ።

መቋዲሾን የተቆጣጠረዉ ሸሪዓን የሚፈልገዉ እስላማዊ ቡድን ደግሞ ምንም እንኳን ከዋና መሪዎቹ መካከል አንዱ አዳን ሃሺ አይሮ ስልጠና የወሰዱት አፍጋኒስታን በመሆኑ ቡድኑን ያዉቃሉ በሚል ቢጠረጠሩም ከአልቃይዳ ጋር ግንኙነት እንደሌለዉ አስተባብሏል።

የደህንነት ጉዳይ ጠበብቶችና ዲፕሎማቶች በመቋዲሾ ከተማና አካባቢዉ የማሰልጠኛ ካምፕ እንዳለና በርካታ የአልቃይዳ እንቅስቃሴም እዚያዉ ይካሄዳል ይላሉ።

የዩናይትድ ስቴትስ የዉጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ሲያን ማኮርማክም ለCNN ቴሌቪዥን እንደገለፁት ሁኔታዉ ለሶማሊያ ህዝብ የሚበጅ ነገር ሊያስከትል ይችላል ብለዉ ቢያስቡም አካባቢዉ የሽብርተኞች መናኸሪያ ይሆናል የሚለዉ ስጋታቸዉ ግን ያይላል።

«ለሶማሊያ ህዝብ ችግር ምላሽ ሊሰጡ የሚችሉ ተቋማት መመስረታቸዉን ማየት የምንፈልገዉ ነገር ነዉ። ያም ማለት የእያንዳንዱን ግለሰብ ሰብዓዊ መብቶች የሚያከብሩ ዲሞክራሲያዊ ተቋማት መመስረት መቻላቸዉ አንድ ነጥብ ነዉ፤ በተጨማሪም አካባቢዉ ለሽብርተኞች ምድራዊ ገነት ሆኖ ለማየት አንፈልግም። እዚህ ላይ ከፍተኛ ስጋት አለን።»

የስላማዊ ቡድኑ ሊቀመንበር ሼኽ ሻሪፍ አህመድ ለዲፕሎማቶችና ለሮይተርስ በላኩት የኢሜይል መልዕክት «ከዓለም ዓቀፉ ህብረተሰብ ጋር በመከባበርና በጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረተ ሰላማዊ ግንኙነት መመስረት እንፈልጋለን። በማለት በሶማሊያ ሰላምን ለማስፈን በሚደረገዉ ሂደት እገዛ ጠይቀዋል።

ቡድኑን ከአልቃይዳ ጋር የሚያዛምደዉ የጋራ ዓላማም ሆነ አሰራር እንደሌለ፤ የሽብር ተግባርንም ለማራመድ ማንንም እንደማይተባበር በይፋ በመግለፅ ስጋቱን ለማረጋጋት ሞክረዋል።

በሶማሊያ የተቋቋመዉ መንግስት ወደመቋዲሾ ለመግባትና ሁኔታዎችን ለማረጋጋት እጅግ ደካማ
በመሆኑ እስላማዊ ቡድኑ ክፍተቱን ሞልቷል።

በጦር አበጋዞች ማን አለብኝ አስተዳደር ለዓመታት የተጨነቀዉ የመቋዲሾ ህዝብም በየጎሳዉ በሸሪዓዉ ስርዓት በተዋቀሩት ተቋማት አማካኝነት ደህንነቱን በመጠበቅ፤ ትምህርትም ሆነ መሰረታዊ ፍላጎቱን ለማሟላት ባደጉት ሙከራ ድጋፉን ሰጥቷቸዋል።

መዲናዋን ለመቆጣጠር ሲዋጉ ከከረሙት አራት የጦር አበጋዞችና ደጋፊዎቻቸዉ ጋርም በምድሪቱ ሰላም ለማስፈን የሚረዳ ስምምነት ለማድረግ ጥረቱ ተጀምሯል።

በርካቶች የዩናይትድ ስቴትስ ራሳቸዉን ፀረ ሽብርተኝነት በሚል ግንባር የፈጠሩትን የጦር አበጋዞች ከስለላ በጀቷ የገንዘብ ድጋፍ ታደርግላቸዋለች ብለዉ ያምናሉ።

ያ ደግሞ በመቋዲሾ የተካሄደዉ ዉጊያ በዋሽንግተንና በሽብር ላይ የሚካሄደዉን ጦርነት ሙስሊሞች ላይ የተከፈተ ዘመቻ አድርጎ በሚረዳዉ እስላማዊ ቡድን መካከል እንደተካሄደ አድርገዉ ይረጁታል።

ምንም እንኳን የገንዘብ ድጋፍ ማድረጓን ከማረጋገጥ ብትቆጠብም በሽብር ላይ ለከፈተችዉ ዘመቻ የሚተባበራት ቡድን ካለ አብራ ለመስራት ፈቃደኛ መሆኗን ዩናይትድ ስቴትስ ገልፃለች።

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW