1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሶማሊያ፣የሽብር ምድር

ሰኞ፣ ጥቅምት 21 2015

ቅዳሜ ነዉ። መይሙናም ያወ-እንደ ወትሮዋ ልጆቿን ምሳ አብልታ ደግሞ ለእራት ተፍ-ተፍ ትላለች። ከቀኑ 8 ሰዓት።የመኪና ድምፅ፣ የልጆች ጫጫታ፣ የሽማች-ሻጭ፣የሸቃይ-አምታቺ ትርምስ የሚያካልበዉ ያ መንደር በአስደንጋጭ ድምፅ ተናወጠ።የምፅአት መለከት፣የሽብር ፊሽካ።ቦምብ ነዉ።

A view shows smoke rising following a car bomb explosion at Somalia's education ministry in Mogadishu
ምስል ABDIHALIM BASHIR/REUTERS

ማብቂያ የለሽ ሽብር፣ ለቁጥር ያታከተ እልቂት-ሶማሊያ ግን እስከ መቼ?

This browser does not support the audio element.

የአዲስ አበባና የመቀሌ ተቀናቃኝ ፖለቲከኞች ፕሪቶሪያ ላይ በቃላት ይነታረካሉ።ሁለቱ ተቀናቃኞች የሚያዟቸዉ ኃይላት ትግራይ ዉስጥ በመድፍ፣አዳፍኔ፣ በታንክ-መትረየስ ይጠዛጠዘሉ።የንግግር ዉጊያዉ ተቃራኒ ሒደት ዉጤትን ግን ያዉ ዝም እንዳሉ ነዉ።ጭጭ።የመቃብር ላይ ፀጥታ።ሱዳኖች ርዕሰ ከተማ ካርቱምን ከመስሪያ፣ መኖሪያ መዝናኛነት ይልቅ መሰለፊያ፣ማዉገዢያ፣ መፈከሪያ፣ የሰልፈኛ ፀጥታ አስከባሪ መፋለሚያ ካደረጓት ዓመት ደፈኑ።ዉጤቱ ላሁኑ አለየም።ሶማሊያ ግን በዝም-ዝምታ አርምሞ የምትዉጠዉ፣ በይደር የምታልፈዉ ብዙ ሚስጥር የላትም።ርዕሰ ከተማይቱ ሳይቀር ቦምብ ያናጥርባታል፣መቶዎች ያልቁባታል፣ ብዙዎች ይጮኹ፣ፖለቲከኞች ይዝቱ-ይፎክሩባታል።ያዉ እንደ ድሮ፣ ሐቻምና አምናዉ ምናልባት ለሌላ ጥፋት ይዘጋጁባታል።ዝም ያሉትን ዝም ብለን ሞቃዲሾ አደባባይ በሰጣዉ አሳዛኝ  ሐቅ ላፍታ እንቆዝም።

መይሙና  መሐመድ የዞባ መንደር የሞቃዲሾ ነዋሪ፣ የስድስቶች እናት፣ባተሌ፣አዛኝ ፣ድንጉጥ፣ ከተፎ እና ፈጣን ናት» የሚያዉቋት እንደሚሉት።የዛሬ አምስት ዓመት መንደሯን ባወደመዉ ሽብር ያለቁ ጎረቤት፣ዘመድ ወዳጆችዋን ለመዘከር  በተዘጋጀዉ ድግስ ላይ ከኮከብ አስተጋጆች አንዷ ነበረች።የሐዘን-ዝክር፣የመታሰቢያ ሐዉልት ምረቃዉ ካበቃ ሁለት ሳምንት አለፈ።

ቅዳሜ ነዉ። መይሙናም ያወ-እንደ ወትሮዋ ልጆቿን ምሳ አብልታ ደግሞ ለእራት ተፍ-ተፍ ትላለች። ከቀኑ 8 ሰዓት።የመኪና ድምፅ፣ የልጆች ጫጫታ፣ የሽማች-ሻጭ፣የሸቃይ-አምታቺ ትርምስ የሚያካልበዉ ያ መንደር በአስደንጋጭ ድምፅ ተናወጠ።የምፅአት መለከት፣የሽብር ፊሽካ።ቦምብ ነዉ።

የሙታን የሰዉነት አካልምስል Farah Abdi Warsameh/AP/picture alliance

ሴትዮዋ ዘላ ከቤት ወጣች።«ልናቆማት ሞከረን ነበር አቃታን» አለ ባለቤቷ ትናንት።«ድሪዓዋን ወገቧ ላይ  ጎጎራዋ ዉስጥ ሽጣ ትሮጥ ገባች-ወደ ሞት ጥድፊያ።ቦምቡ ከፈነዳበት ስፍራ መድረስ አለመድሯሷ አይታወቅም።የሚታወቀዉ መኪና ላይ የታጨቀዉ ቦምብ በፈነዳ በደቂቃዎች ልዩነት ሁለተኛዉ መደገሙ ነዉ።

መይሙናም እንደወጣች ቀረች።

«እነዚሕ አሸባሪዎች ኢላማ ያደረጉት ከዚሕ ወደ አፍጎዬ ከተማ በየቀኑ የሚመላለሱ ሰዎችን፣ የምስክር ወረቀት ለመቀበል የመጡ ተማሪዎችን፣ ሆስፒታል የተኙ ሕመምተኛ ዘመዶቻቸዉን ጠይቀዉ የሚመለሱ ሰዎችን፣ ለርዳታ የመጡ ሰዎችን ነዉ።አሸባሪዎች ያጠቁት እነዚሕ ሰዎች ናቸዉ።እስካሁን ድረስ ከ100 በላይ ሰዎች ተገድለዋል።ከ300 በላይ ቆስለዋል።»

ፕሬዝደንት ሐሰን ሼክ ማሕሙድ ትናንት።ከሟቾቹ አንዷ መይሙና ናት።እሱ ደግሞ ከ300ዉ ቁስለኞች-አንዱ።«ዞባ አጠገብ፣ከሰላአም ባንክ ጎን ሱቅ አለኝ።ሱቄ ዉስጥ እያለሁ ያንን ከባድ ድምፅ ሰማሁ።ወዲያዉ ሱቁ፤ ዉስጥ በነበርነዉ ላይ ተደረመሰ።አራት ነበርን።እራሴን ስቼ ነበር።ስነቃ አካሌ በደም ተነክሮ አገኘሁት።አንዱ ክፉኛ ተጎድቷል።አካባቢዉም በእሳት፣ጢስና ፍርክስካሽ ተሽፍኖ አየሁት።»የምስራቅ አፍሪቃ ምስቅልቅል፣ የሱዳን አብነት

የሶማሊያዉ አምባገነን ገዢ መሐመድ ዚያድ ባሬ ከስልጣን ከተወገዱ ከ1991 በኋላ (ዘመኑ በሙሉ እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) ምስራቅ አፍሪቃዊቱን ሐገር ለማረጋጋት ቃል ያልገባ፣ ጦሩን ያለዘመተ፣ ሰላይ፣የርዳታ ሰራተኛዉን ያልላከ፣ገንዘቡን ያላወጣ የምዕራብ-ምሥራቅ፣ የአረብ-የአፍሪቃ መንግስት የለም።

አሜሪካኖች፣አዉሮጶች፣  ፓኪስታኖች፣ ሔይቲዎች፣ ኢትዮጵያዉያን፣ ኬንያ፣ ጅቡቲ፣ ዩጋንዳ፣ ቡሩንዲ  ሌሎችም እየፎከሩ ይዘምቱባታል፤ ገድለዉ ይሞቱባታል፤ እየሰለሉ ይሸሹ፣ ይባክኑባታል።የሶማሊያ ሕዝብን ግን በተፋላሚ ኃይላት ቦምብ ጥይት፣ በረሐብ፣ ሽብር ከማለቅ፣ አካል ደሙን ከማጣት፣ ከመሰደድ መፈናቀል ያዳነዉ ማንም የለም።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬሽ መጋቢት አጋማሽ 2017 ባይዶዎን ሲጎበኙ ከአምስት ዓመት በፊት (በ2011-2012) መቶ ሺዎችን ለሞት የዳረገዉ ረሐብ ሶማሊያ ዉስጥ እንዳይደገም ከማሳሰባቸዉ እኩል የመፃኤ ተስፋዋን ብሩሕነት ተንብየዉም ነበር።

ረሐብተኞችምስል Feisal Omar/REUTERS

«ይሕ የተስፋ ወቅትም ነዉ።የተስፋ ወቅት ነዉ።ምክንያቱም ሶማሊያ አዲስ ምዕራፍ ከፍታለች።አዲስ ፕሬዝደንት ተመርጧል።አዲስ ጠቅላይ ሚንስትር ተሾሟል።ፀጥታን ለማስከበርና ለሕዝቡ መሰረታዊ አገልግሎቶችን ለመስጠት የመንግስትን አቅም ለማጠናከር ግልፅ ቁርጠኝነት ይታያል።ይሕ በርግጥ የዓለም አቀፉን ማሕበረሰብ ድጋፍ ይፈልጋል።»

በረጅም ጊዜዉ ዉጊያ መሐል በ2011ን ሶማሊያን የመታዉ  ድርቅ ከ5ሚሊዮን የሚበልጥ ሕዝብን አስርቧል።ረሐቡ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እንዳስታወቀዉ ከ260 ሺሕ በላይ ሰዉ ገድሏል።ሚሊዮኖችን አሰድዷል።ጉተሬሽ ከአምስት ዓመት በኋላ በ2017 ሶማሊያን ሲጎበኙ ከ3.5 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ በምግብ እጥረት ይሰቃይ ነበር።

ዘንድሮ በአምስተኛ ዓመቱም ከ4 ሚሊዮን በላይ ሶማሊያዊ አስቸኳይ የምግብ ርዳታ ጠባቂ ነዉ።ከ1.5 ሚሊዮን የሚበልጡት በተለይም ሕፃናትና አቅመ ደጋሞች በረሐብና ረሐብ በሚያመጣዉ በሽታ በመኖርና አለመኖር መሐል እየተሰቃዩ ነዉ።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ ከባይዶዎ ለተረበዉ የሶማሊያ ሕዝብ ርዳታ፤ አዲስ ለተመሰረተዉ መንግስት ድጋፍ በጠየቁ፣ የሰላም ተስፋቸዉን በገለፁ በ6ኛ ወሩ ጥቅምት፣ የሶማሊያዉ አሸባሪ ቡድን አሸባብ አባላት በጭነት መኮኖች ያጨቁትን ቦምብ ሞቃዲሾ ዞባ መንደር ላይ ዘረገፉት።

የትምሕርት ሚንስቴር ዋና መስሪያ ቤት፣ባንኮች፣ሱቆች፣ ምግብ ቤቶች፤ሐኪም ቤቶች ፣የተገጠገጡበት ጉልቶች የሚሰጡበት ያመንደር 587 ሰዉ አለቀበት።ጥቅምት 14፣ 2017።አፍሪቃ ዉስጥ ባንድ ቀን፣አንድ ስፍራ በደረሰ የሽብር ጥቃት ይሕን ያሕል ሰዉ ሲገደል የሞቃዲሾዉ የመጀመሪያዉ-እስካሁን የመጨረሻዉም ነዉ።ያኔ አዲስ የተመረጡት፣ ጉተሬሽ ያወደሱ፣ ተስፋ የጣሉባቸዉ፣ የለንደን፣ዋሽግተን፣ብራስልስ መንስታት በግብዣ ያበሻበሿቸዉ ፕሬዝደንት መሐመድ አብዱላሒ መሐመድ አሸባብን አዉግዘዉ ነበር።                           

«በርግጥ በጣም ከባድ ጊዜ ነዉ።የትናንቱ የጭነት መኪና ላይ ቦምብ ጥቃት የብዙ ሰዎችን ሕይወት ያጠፋ ብሔራዊ አደጋ ነዉ።ጥቃቱ እነዚያ የአሸባብ አሸባሪዎች ጨካኝ፣ቁሻሻና ማንንም የሚግድሉ መሆናቸዉን የሚያረጋግጥ ነዉ።»

የቱርክ ጦር ያሰለጠናቸዉ የሶማሊያ ወታደሮች ምረቃምስል Sadak Mohamed/AA/picture alliance

በ2006 በ10 ሺሕ የሚቆጠር የኢትዮጵያ ጦር፣ ከ2008 ጀምሮ ደግሞ ከ22 ሺሕ የሚበልጥ የአፍሪቃ ሕብረት ጦር ሶማሊያ ዉስጥ ይርመሰመሳል።ዩናይትድ ስቴትስ ወታደራዊ አማካሪዎች፣አሰልጣኞች፣ ሰላዮች ይመላለሳሉ።የዩናይትድ ስቴትስ ልዩ ኮማንዶዎች ከምድር፣ ሰዉ አልባ የጦር አዉሮፕላኖች (ድሮኖች) ከሰማይ የሶማሊያን ጉጥ ስርጓጉጥ ያስሳሉ።«አሸባብ» የሚሉትን ይገድላሉ።

ከ2009 እስከ 2017 በዘለቀዉ በፕሬዝደንት ባራክ ኦባማ ዘመን የዩናይትድ ስቴትስ ሰዉ አልባ አዉሮፕላኖች የአሸባብ ይዞታና አባላት ያሏቸዉን አካባቢና ሰዎች 37 ጊዜ በሰዉ አልባ አዉሮፕላኖች ደብድበዋል።ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራም ስልጣን ላይ በቆዩበት  ከ2017 እስከ 2021 በነበረዉ አራት ዓመት ዉስጥ ብቻ የአሜሪካ ጦር 205 ጊዜ፣ ፕሬዝደንት ጆ ባይደን ስልጣን ከያዙ ወዲሕ ደግሞ 11 ጊዜ  ሶማሊያን ከአየር ደብድቧል።

የባይደን አስተዳደር በሌላ የአፍሪቃ ሐገራት ከሰፈረዉ የአሜሪካ ጦር 450 ወታደሮች  እዚያዉ ሶማሊያ ወይም አጎራባች ሐገራት ሰፍሮ አሸባብን እንዲያጠቃ ወይም የሶማሊያና የአፍሪቃ ሕብረት ጦርን እንዲያግዝ ወስኗል።

አሸባብ እንደሶማሊያዊ ድርጅት ከሶማሌ ፖለቲከኞች ጋር በሚደረግ ድርድር ሽብሩን እንዲያቆም የሚመክር-የሚዘክር ፖለቲከኛ፣ የፖለቲካ ተንታኝና ምሁር የለም።የዉይይት-ድርድር ሐሳብ የሚያነሳ እሱ ለአዓለም ዘዋሪዎች «አሸባሪ» ወይም «የአሸባሪ ተባባሪ» ነዉ።በለዉ ባይ ነዉ-ተሰሚዉ።አሸባብም ስፍራ፣ ጊዜ  እየቀያየረ ከረሐብ፣በሽታ፣ከፊት ለፊት ጦርነት የተረፈዉን ሰዉ ይገድላል።ያሸብራል።ሶማሊያ የክሽፈት አብነት፣ዉብ ምድር

ባለፈዉ ጥቅምት 3 የአሸባብ ታጣቂዎች የሒራን ክፍለ-ሐገር ርዕሰ ከተማ በልድወይን የሚገኘዉን የክፍለ ሐገሩን ዋና ፅሕፈት ቤት በቦምብ አጋዩት።

የሒራን ክፍለ ሐገር ምክትል አስተዳዳሪን፣የሒርሸበሌ ክፍለ ሐገርን የጤና ሚንስትርን ጨምሮ 12 የበታች ሹማምንታትንና ጉዳይ ለማስፈፀም የተሰበሰቡ ሰላማዊ ሰዎችን ገደሉ።ከጥቃቱ ከተረፉ  ባለስልጣናት አንዱ አናለቅስም አሉ-አንበቀላለን እንጂ።«እናለቅስም፣አንጮኽም።ግን እንበቀላለን።በዚሕ ጥቃት አንሸማቀቅም።አሸባሪዎችን ከመታገል አንገታም።እስከ መጨረሻዉ፣ እስክናሸንፋቸዉ ድረስ እንፋለማለን።»

አሸባብ ከሞቃዲሾ በስተሰሜን 300 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘዉን በለድወይንን ያጠቃዉ የአሜሪካ ሰዉ አልባ አዉሮፕላኖች አንድ ከፍተኛ ባለስልጣኑን መግደሉ በተዘገበ ሳልስት ነበር።የበልድወይኑ ሹም ዛቻ አስገምግሞ ሳያበቃ አሸባብ እንደገና የሶማሊያ ሁለተኛ ትልቅ ከተማ ኪስማዩን አጠቃ።

የአሸባብ አጥፍቶ ጠፊና ሶስት ታቂዎች  የመንግስት ባለስልጣናትና የሐገር ሽማግሌዎች የሚገኙበትን አንድ ሆቴል ወርረዉ 8 ሰዉ ገደሉ።ከ8 አምስቱ አንድም ባለስልጣን አለያም ፀጥታ አስከባሪዎችና የሐገር ሽማግሌዎች ናቸዉ።«ሶስት  ታጣቂዎች ወደ ሆቴሉ መግባት ችለዋል።የኛ ወታደሮች ታጣቂዎቹን ለማጥፋት ከታጣቂዎቹ ጋር እየተታኮሱ ነዉ።»

የጁባላንድ የፖሊስ አዛዥ መሐመድ ናስር ጉሌድ።ፖሊስ ሶስቱን ታጣቂዎቹ መግደሉ ተዘግቧል።ጥቅምት 24 ነበር።በሳምንቱ ቅዳሜ፣ ከአምስት ዓመት በፊት 600 ያሕል ሰዎች ያለቁበት የሞቃዲሾ ዞባ መንደር ተደገመ።ልክ እንደ ፕሬዝደንት መሐመድ አብዱላሒ ፎርማጆ ሁሉ፣ ፕሬዝደንት ሐሰን ሼሕ ማሕሙድም አሸባብን አወገዙ።

የአሸባብ ተዋጊዎች ወታደራዊ ትርዒትምስል Farah Abdi Warsameh/AP/picture alliance

የዋሽግተን-ለንደን ፖለቲከኞች፣ የኒዮርክ ብራስልስ-አዲስ አበባ  ዲፕሎማቶች አሸባብ እንደ ቡድን ከታወቀበት ጊዜ ጀምሮ ደጋግመን የሰማነዉን ዉግዘት አንቆረቆሩት።የሮማ ካቶሊካዊት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንስሲም ለኮሪያ መዝናኛ ስፍራ፣ ለሕንድ የድልድይ አደጋ ሰለቦች እንደፀለዩት ሁሉ፣ የሞቃዲሾ ሰለቦችንም ዘከሩ።«ክርስቶስ ሰይጣንና ሞትን ድል ያደረገበትን ስናከብር ሞቃዲሾ ዉስጥ በአሸባሪ ጥቃት ለተገደሉት ብዙ ሕፃንትን ጨምሮ ከ100 በላይ ሰዎች እንፀልይ።የአመፀኞቹን ልብ ፈጣሪ ይለዉጥ።»

ዉግዘት፣ዛቻ፣ ፉከራዉ ለስድስቶቹ እናትና ለ99 ብጤዎችዋ የሚተክረዉ መኖሩ  ሲበዛ አጠራጣሪ ነዉ።ፀሎቱስ?

ነጋሽ መሐመድ 

ሸዋዬ ለገሰ                      

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW