1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

“ሶማሊያ ለውክልና ጦርነት እድል አትሰጥም” የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ንግግር አንድምታ

ሥዩም ጌቱ
ሐሙስ፣ መስከረም 15 2018

የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ ሶማሊያ በአገራቸው በሰላም ማስከበር ላይ የሚሰማሩ የኢትዮጵያ እና የግብፅ ወታደሮች ወደ ግጭት ሊገቡ የሚችሉበት ምክንያት ወይም የውክልና ጦርነት ሊኖር የሚችልበት ሁኔታ እንደማይኖር አስረድተዋል። በሶማሊያ ምድር ሠራዊቶቻቸውን ያሰፈሩበት ቦታም ስለማይቀራረብ ለግጭት የሚያበቃ ዕድል የለም ሲሉም ተናግረዋል።

የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ ሞሐመድ
የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ ሞሐመድምስል፦ Annegret Hilse/REUTERS

“ሶማሊያ ለውክልና ጦርነት እድል አትሰጥም” የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ንግግር አንድምታ

This browser does not support the audio element.

የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ ሶማሊያ ልዩነቶቿን ከኢትዮጵያ ጋር በመነጋገር ከመፍታቷ በፊት በነበሩት በነዚያ ጊዜያት የነበራትን ሁኔታ ጨምሮ ከሰሞኑ ከቢቢሲ ጋር ለቃለምልልስ በተቀመጡበት ወቅት በሰጡት ማብራሪያ በአገራቸው በሰላም ማስከበር ላይ የሚሰማሩ የኢትዮጵያ እናየግብፅወታደሮች ወደ ግጭት ሊገቡ የሚችሉበት ምክንያት ወይም “የውክልና ጦርነት” ሊኖር የሚችልበት ሁኔታ እንደማይኖር አስረድተዋል።

ሁለቱ አገራት “በሶማሊያ ምድር” የሚያካሄዱት ጦርነት አይኖርም ያሉት፤ ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ በዚሁ ቃለ ምልልሳቸው ኢትዮጵያ እና ግብጽ በሶማሊያ ምድር ሠራዊቶቻቸውን ያሰፈሩበት ቦታ ተቀራራቢ ባለመሆኑ ለግጭት የሚያበቃበት ዕድል የለም ሲሉም በቃለ ምልልሳቸው አንስተዋል።

በሶማሊያ ውስጥ በሚገኙ ለሰላም አስከባሪነት ዓላማ በተሰማሩት የኢትዮጵያ እና የግብጽ ወታደሮች መካከል ግጭት የሚፈጠርበት አጋጣሚ ሊኖር ይችል ይሆን በሚል በዶይቼ ቬለ የተጠየቁት የዓለማቀፍ የሕግ እና ዲፕሎማሲ ተንታኝ አቶ ባይሳ ዋቅዎያ፤ “ለ30 ዓመታት በተለያዩ አገራት ሰላም አስከባሪ ኃይሎችን አይቻለሁኝ፤ ግን ለሰላም ማስከበር በሄዱባት ሶስተኛ አገር ውስጥ የተጋጩ የሁለት አገራት ሰላም አስከባሪ አይቼ አላውቅም” ብለዋል፡፡ በሶማሊያ ውስጥ የሚገኙትን የኢትዮጵያ እና ግብጽ ሰላም አስከባሪ ሠራዊቶችንም በማንሳት፤ ወታደሮቹ ጦርነት ውስጥ ሊገቡ የሚችሉበት ከባድ መሳሪያ አለመያዛቸው፤ ብሎም በሶማሊያው ፕሬዝዳንት በተገለጸው መልኩ የሁለቱ አገራት ሰራዊት በተለያዩ አከባቢዎች ሰፈሩ መሆናቸው የርሰበርሳቸው ግጭት መፍጠር እድልን ከወሬ የዘለለ አያደርገውም ነው ያሉት፡፡

የዶናልድ ትራምፕ ንግግር አንድምታ

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በተደጋጋሚ በሚያነሱትና በቅርቡም በደገሙት ንግግራቸው፤ “በኢትዮጵያ እና ግብጽ መካከል ልነሳ የነበረውን ጦርነት አስቆምኩ”ብለዋል፡፡ ትራምፕ ይህን ያሉትና አስቆምኩ ያሉት ጦርነቱን የማስቀረት ተግባር የከወኑም ለዳግም ፕሬዝዳንትነት ጥር ወር 2025 ላይ ነጩ ቤተመንግሰት ከተመለሱ በኋላ መሆኑ ነው፡፡

በቅርቡ የተመረቀው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ምስል፦ Luis Tato/AFP

ይህ ወቅት ደግሞ ኢትዮጵያ ከጎረቤቷ ሶማሊያ ጋር በአወዛጋሚው የኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ የወደብ አጠቃቀም የጋራ መግባቢያ ስምምነት ምክንያት የዲፕሎማሲ ሽኩቻ ውስጥ የገቡበትና፤ ኢትዮጵያ ከአባይ ውሃ አጠቃቀም ጋር በተያያዘ በጂኦ ፖለቲካው ከምትቃቃረው ግብጽ ጋር ወደ ጦርነት ሊገቡ ይሆን የሚል የግጭት ጥላ በቀጣናው ባጠላበት ወቅት መሆኑ ነው፡፡ የዓለማቀፍ ሕግና ዲፕሎማሲ አዋቂው አቶ ባይሳ ግን፤ ይህን የፕሬዝዳንቱን ንግግር ማመን ከብዶአቸዋል፡፡ “የፕሬዝዳንቱን ንግግር ከዲፕሎማሲ አንጻር እኔ ኮስተር ብዬ በቁምነገር የማየው አይደለም፤ በቂመረጃ ያላቸው ወይም በቂ መረጃ የሚሰጣቸው ያለ አይመስለኝም” በማለት “በሁለት መሳሪያ የያዘ ቡድን፤ በታሪካዊ ጠላትነት በሚፈራረጁት መካከል ፊትለፊት ቢገናኙ ጦር አይማዘዙም ብሎ ውርርድ መግባት ባይቻልም እስካሁን ድረስ ተደርጎ ስላላየን እድሉ ግን እጅግ ዝቅተኛ ነው” ሲሉም አስተያየታቸውን አክለዋል፡፡

ዘላቂ ሰላምና የትብብር መህርት በግብጽና ኢትዮጵያ መካከል እንዴት ይስፈን?

ግብጽ በቅርቡ በተመረቀው የታላቁ ህዳሴ ግድብ ላይ ተገኝተው ትልቁን የትብብር መልእክት ያስተላለፉትን የኬንያን ፕሬዝዳንት ወርፋለች፡፡ ካይሮ የናይሮቢው አለቃ በግድቡ ምርቃት ላይ በመገኘታቸውም ቅር መሰኘቷን ገልጻለች፡፡ ለመሆኑ የአዲስ አበባ እና ካይሮ ዲፕሎማሲያዊ ሽኩቻ ዘመን ተሻጋሪ ውዝግቡን በመልቀቅ ወደ ትብብር የሚሸጋገሩ እንዴት ባለ መንገድ ይሆን፤ የዓለማቀፍ ሕግ ባለሙያና የቀጣናው ዲፕሎማሲያዊ ሁናቴን የሚከታተሉት አቶ ባይሳ፤ “ክርስትና ወደ ኢትዮጵያ ከመጣበት ጊዜ ጀምሮ በታሪክ ኢትዮጵያን ለመጉዳት በምትሰራቸው ተግባራት የምትከሰሰው ግብጽ፤ እንደ ታሪካዊ ጠላት” መታየቷ እንደሚታመንም አንስተው አሁን ላይ ግን ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከመጠናቀቁ ጋር ተያይዞ የሚፈጠር አዲስ ነገር አለመኖሩን ጠቁመዋል፡፡ ይልቅ ግድቡ አደጋ ደርሶበት ጎርፉ በታችኛው ተፋሰስ አገራትላይ ጉዳት እንዳያስከትል ግብጽ ከኢትዮጵያ ጋር በደህንነቱ እጅና ጓንት ሆና መስራት አለባት የሚሉት ባለሙያው በሶማሊያ በኩልም ግብጽ ለኢትዮጵያ ደህንነት ስጋት የምትሆንበት እድል እጅግ ጠባብ እየሆነ መምጣቱን አስገንዝበዋል፡፡

የሶማሊያ መንግሥት በአፍሪካ ኅብረት የሶማሊያ ድጋፍ እና ማረጋጋት ተልዕኮ ውስጥ የሚሳተፉ አገራት 11,000 ወታደሮች እንደሚያዋጡ በተገለጸበት ባለፈው ዓመት በስምሪቱ የሚሳተፉ ወታደሮች ድልድል የተወሰነው በሁለትዮሽ ስምምነት እንደሆነ መገለጹ ይታወሳል።

ስዩም ጌቱ 

ኂሩት መለሰ

ታምራት ዲንሳ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW