ሶማሊያ፣ ሕዝቧ ድምፅ አልጠም፤ መሪ ግን ተመረጠላት
ማክሰኞ፣ ግንቦት 9 2014ዉድቅት ነዉ።ትናንት።አብዛኛዉ የሞቅዲሾ ነዋሪ ግን አልተኛም።ለነገሩ ሶማሌ «ቀኑን ለሠራዊት ሌቱን ለአራዊት» ብሎ አባባልን ከረሳ ስንት ዘመኑ? ከ1990ዎቹ ጀምሮ (ዘመኑ በሙሉ እንደጎርጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) እንቅልፍ ነሺዉ ሚርቃና፣ሥራ፣ፀሎት-ስግደት አይደለም።ብዙ ነዉ።የመንግስትና ያማፅያን ዉጊያ፣ የዩናይትድ ስቴትስ፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጦርና የአይዲድ ሚሊሺያ፣የጦር አበጋዞች ዉጊያ፣የኢትዮጵያ ጦርና የሸርዓ ፍርድ ቤቶች ዉጊያ፣ የአሸባብ ቦምብ፣ የአሸባብና የአፍሪቃ ሕብረት ጦር ዉጊያ ሌላም፣ ሶማሌን በወጉ አስተኝተዉት አያዉቁም።ትናንት ዉድቅት ግን ሞቃዲሺ፣ ዉጊያ፣ፍንዳታ፣ ሽብር ግድያ ዋይታዉ ለቅፅበት ገለል ቀለል ሲልላት አብዛኛ ነዋሪዋ እንቅልፍ የነሳ ሁነት-ሆነባት።ምርጫ።እና የድል ብስራት።የሶማሊያ ምርጫና ዉጤቱ መነሻ፣ የፖለቲካ ፀጥታዋ ምስቅልቅል ማጣቀሻ፣ ተስፋዋ መድረሻችን ነዉ።
ሶማሊያ የቀድሞ ፕሬዝደንቷን ሐሰን ሼሕ ማሕሙድን የወደፊት ፕሬዝደንቷ እንዲሆኑ መረጠች።ትናንት ለዛሬ አጥቢያ።ሞቃዲሾም ጨፈረች።ደስታ።«ምን ያሕል እንደተደሰትኩ በቃላት መግለፅ አልችልም።ኢንሻአላሕ ዛሬ በጣም፣ በጣም ደስተኛ ነኝ።ሐሰን ሼኽ መሐሙድ እወድሐለሁ።I love You.»
አለ ከጨፋሪ፣ ዘፋኝ-ዘማሪዎቹ አንዱ።ደስታ ጭፈራዉ የሁሉም ሶማሌ ወይም የመላዉ ሞቃዲሾ ይሆን? «ሁሉም የከተማዋ ነዋሪ ደስተኛ ነዉ ማለት አንችልም» ይላል።የጀርመኑ ዜና አገልግሎት DPA የሞቃዲሾ ዘጋቢ መሐመድ አድዎ።
«በዕዉነቱ፣ባሁኑ ወቅት ሕዝቡ ማለት ሁሉም የከተማዋ ነዋሪ ደስተኛ ነዉ ማለት አንችልም።ምክንያቱም ሰዉዬዉን ከዚሕ ቀደም ያዉቁታል።በዚያን ጊዜ ጥሩ ሰዉ አልነበሩም።ምክንያቱም (መንግስታቸዉ) ከፍተኛ ሙስና አድርሷል።የፀጥታዉ ችግርም በጣም ተባብሶ ነበር።ነገር ግን ባሁኑ ወቅት ሕዝቡ ከእሱ (ከፕሬዝደንቱ) ብዙ ይጠብቃል።ደስታዉም እሱዉ ነዉ።»
ሐሰን ሼክ ማሐሙድ።66 ዓመታቸዉ ነዉ።ከትላልቆቹ የሶማሊያ ጎሳዎች አንዱ የሆነዉ የሐዉያ ጎሳ አባል።ጃላላቂሲ ከተማ ሒራት ተወለዱ።ሞቃዲሾ አደጉ፣ ሶማሊያ ብሔራዊ ዩኒቨርስቲ ቴክኒካዊ ምሕንድና ተማሩ።አስተማሪ ሆኑ።ሁለተኛ ዲግሪያቸዉን ሕንድ ሐገር ከተማሩ በኋላ በትምሕርት ሚኒስቴር የአስተማሪዎች የሰልጠና ጉዳይ ኃላፊ ሆኑ።
በ1991 የሶማሊያ ማዕከላዊ መንግስት ሲፈርስ የዩኒሴፍ የትምህርት ጉዳይ ባልደረባ ሆኑ።የሶማሊያ ማዕከላዊ መንግስት ከፈረሰ በኋላ የመጀመሪያዉን የአንደኛ ደረጃ ትምሕርት ቤት የከፈቱትም ያኔ ነበር።1995።የሚያዉቋቸዉ እንደሚሉት ዝምተኛ፣ ታጋሽ፣ ቁጥብ፣ ለዘብተኛ ኃይማኖተኛ፣ ሰላማዊም ናቸዉ።ሐገራቸዉ በጦርነት ስትተራመስ ዕዉቅ የሰላም አቀንቃኝ ሆኑ።ፖለቲካዉን ሲቀየጡ የመሰረቱት የፖለቲካ ፓርቲም «አንድነት ወይም ሕብረት ለሶማሊያ ሰላምና ልማት» የተሰኘ ነዉ።
በ2012 በተደረገዉ ምርጫ 8ኛዉ ፕሬዝደንት ሆነዉ ተመረጡ።ብዙዎች በተለይ ምዕራባዉያን ብዙ ጠብቀዉ ነበር።ለጠበቁት ብዙ ስኬትም የዩናይትድ ስቴትስ፣የብሪታንያና አብዛኞቹ የአዉሮጳ ሕብረት አባል መንግስታት በየርዕሰ ከተሞቻቸዉ ጋበዟቸዉ።ከሶማሊያ ጋር አቋርጠዉት የነበረዉን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ጀመሩ።
ይሁንና ሹመኞቻቸዉ በሙስና ሲዘፈቁ፣ በርዳታ የተገኘ ሕብትና ገንዘብን ሲቦጠቡጡ፣የሐገሪቱን ብሔራዊ ባንክ ሳይቀር ሲያራቁቱ ዝምተኛዉ ፖለቲከኛ ዝም አሏቸዉ።በአፍሪቃ ሕብረት ጦርና በምዕራባዉያን ወታደራዊ ሥልጠናና ገንዘብ የሚደገፈዉ ጦራቸዉና መንግስታቸዉ ከአሸባብ ጋር በገጠመዉ ዉጊያም ሽንፈት እንጅ ድል አልነበረም።
በ2017 በተደረገዉ ምርጫ ተሸነፉ።ትናንት ግን እንደገና ተመረጡ።10ኛዉ ፕሬዝደንት።«ሐሰን ሼሕ ማሕሙድ የሶማሊያ ፌደራል ሪፐብሊክ ፕሬዝደንት እንዲሆኑ ተመረጠዋል።»
የሰላም አራማጁ ፖለቲከኛ የምረጡኝ ዘመቻ ዐበይት ርዕሶች ሰላም ማስፈን፣ ሙስናን መዋጋት፣ልማትና አንድነትን ማጠናከር የሚሉ ናቸዉ።ከድል በኋላም በተለይ አንድነትን እንደሚያጠናክሩ፣ ሕግ እንደሚያስከብሩ ቃል ገቡ።
«የትኛዉም ዓይነት ቂምና ቁርሾ ካመረቀዘ፣ እጩነቴን ባወጅኩበት ሰዓት እንዳልኩት ችግሩን ለመፍታት እራሴን አዘጋጅቻለሁ።ማንንም ለማጥቃት ያለመ ፖለቲካዊ ክትትልና ብቀላ አይኖርም።ሐገሪቱ በቂ ደንቦችና ሕጎች አሏት።ልዩነት ከተፈጠረ ሐገሪቱ ያፀደቀቻቸዉን ሕጎች ገቢር እናደርጋለን።»
ይሳካላቸዉ ይሆን?አይታወቅም።የሚታወቀዉ ሶማሊያዊ ጋዘጠኛ መሐመድ ኦዶዎ እንዳለዉ ሐሰን ሼክ ማሕሙድ ያለፈ ስሕተታቸዉን ለማረም ሁለተኛ ዕድል ማግኘታቸዉ ነዉ።
«እንደሚመስለኝ አሁን ብዙ ነገር መስራት ይችላሉ።ምክንያቱም ብዙ ልምድ አላቸዉ።ብዙ ሰዎችም የሚያስቡት ያለፈ ልምዳቸዉን በመጠቀም ብዙ ችግሮችን ያቃልላሉ ብለዉ ነዉ።እድሉ ተሰጥቷቸዋል።»
18 ሚሊዮን የሚገመተዉን የሶማሊያ ሕዝብ የወደፊት ዕጣ ፈንታ እንዲወስኑ ወይም እንዲመሩ በጋዜጠኛዉ ቋንቋ «እድሉን የሰጣቸዉ» ግን በምርጫ ደንብ እንደሚታወቀዉ አብዛኛዉ የሶማሊያ ሕዝብ አይደለም።ሶማሊያ «አንድ ሰዉ አንድ ድምፅ» የሚባል ምክር ቤታዊ ምርጫ ያስተናገደችዉ መጋቢት 1969 ነበር።በዚያዉ ዓመት ጥቅምት ጄኔራል ዚያድ ባሬ የተመረጠዉን መንግስት በመፈንቅለ መንግስት አስወግደዉ ሥልጣን ያዙ።
እርግጥ ነዉ ዚያድ ባሬ እንደ ሶሻሊስቱ ወግ ብቻቸዉን ለተወዳደሩበት «ምርጫ» መሰል ድግስ የሶማሊያ ሕዝብ ድምፅ ሰጥቶ ያዉቃል።ለመድብለ-ፓርቲ ወይም ፖለቲከኞች ለሚፎካከሩበት ምርጫ ግን የሶማሊያ ሕዝብ እንደራሴዎችቹን የመረጠዉ አንዴ ነዉ።በ1969።
ከሼክ ሸሪፍ ሼክ አሕመድ እስከ ሐሰን ሼክ ማሕሙድ የተፈራረቁት መሪዎች ስልጣን የያዙትም ከ300 ብዙም የማበልጡ የምክር ቤት አባላት በሰጡት ድምፅ ነዉ።ሒደቱ እንዲሕ ነዉ፣- 135 የጎሳና የማሕበረሰብ መሪዎች 14 ሺሕ 25 ተወካዮችን ይሰይማሉ።ተወካዮቹ በፋንታቸዉ 275 የሕዝብ ምክር ቤት (ሕግ-መምሪያ) አባላትንና 54 የሕግ መወሰኛ እንደራሴዎችን (ሴናተሮችን) ይሰይማሉ።የሁለቱ ምክር ቤቶች አባላት ፕሬዝደንቱንና ጠቅላይ ሚንስትሩን ይመርጣሉ።
ጎሳ፣አካባቢ፣ወገን ድርድርና መጠቃቀምን መሰረት ያደረገዉ ምርጫ ብዙ ጊዜ በጉቦና ምልጃ የጎደፈ ነዉ።ዘገባዎች እንደሚጠቁሙት በ2017 በተደረገዉ ምርጫ ከ20 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገንዘብ ለጉቦ ወጥቷል።አብዛኛዉ ገንዘብ የተገኘዉ ከሐብታም የአረብ ሐገራት ነዉ።በዚሕም ምክንያት የፖለቲካ ተንታኝ አብዲ አየንቴ እንደሚለዉ የመጨረሻዉ ዉጤት እስኪታወጅ ድረስ አሸናፊዉን አስቀድሞ መገመት ሲበዛ ከባድ ነዉ።
«የሚኖረዉን ትብብርና የአሸናፊዉን ማንነት ለመገመት አሁን አስቸጋሪ ነዉ።ብዙ የጓዳ ዉስጥ ድርድሮች፣ የጠረጴዛ ስር ስምምነቶችና የአጉርሰኝ ላጉርስሕ ዉሎች ይደረጋሉ።እስከ መጨረሻዉ ድረስ፣ እስከ ዕሁድ ማለዳ ድረስ ድርድርና ስምምነቱ ይቀጥላል።»
በጉቦ፣በድርድር ስምምነትም ሆነ በቀጥታ ድምፅ ሐሰን ሼኽ ማሕሙድ 38 ተፎካካሪዎችን አሸንፋዋል።ሴቷ አንዲት ብቻ ነበሩ።
ምርጫዉን ከአንድ ዓመት በላይ ያዘገየዉ የፕሬዝደንት መሐመድ አብዱላሒ መሐመድ (ፎርማጆ)ና የጠቅላይ ሚንስትር መሐመድ ሁሴይን ሮብሌ የስልጣን ሽኩቻ አብቅቷል።ፕሬዝደንት መሐመድ አብዱላሒ መሐመድ ከፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂና ከጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ ጋር የመሰረቱት ትብብርም ዛሬ አበቃ።
ለአዲሱ ፕሬዝደንት ኢጋድ፣ ብሪታንያና ሌሎችም የሶማሊያ ረዳቶች ደስታቸዉን እየገለጡ ነዉ።ያቺ የርስ የርስ ፖለቲካዊ ሽኩቻ፣ ጦርነት፣ የአሸባሪዎች ጥቃት ሺዎችን የፈጁባት፣ ያቺ፣ ሙስናና ሥርዓተ አልበኝነት የሚያናጥርባት ሐገር ዘንድሮ ከግጭት፣ጦርነት ሽኩቻዉ በተጨማሪ ከ3.5 ሚሊዮን በላይ ሕዝቧ በረሐብ ይሰቃይበታል።
አሮጌዉ ፕሬዝደንት ባዲሱ ዘመነ ስልጣናቸዉ ዉስብስቡን ችግር ለማቃለል ቃል ገብተዋል።የዉጪ ደጋፊዎችዋ በተለይ የምዕራባዉያን ርዳታ ፀጥታ ለማስከበር ብቻ ሳይሆን ልማት ላይ እንዲያተኩርም ተማፅነዋል።
«ሶማሊያን የሚደግፉ በጣም በርካታ ምዕራባዉያን ወዳጆች አሉን።ይሁንና ድጋፉ በጣም በጠበበ አመለካከት በፀጥታ ላይ ብቻ ያተኮረ ነዉ።እኛ የምንለዉ፣ከፅንፈኝነት ሌላ፣ አማራጭ ኑሮን ወይም ሕይወትን የሚያመለክት ድጋፍ ያስፈልጋል ነዉ።ለርዕዮተ ዓለም ሳይሆን መኖር ስላቃታቸዉ ብቻ የፅንፈኞቹን ጎራ የተቀየጡ ሰዎች አሉ።እነዚሕን ወጣቶች ወደየቤታቸዉ ለመመለስ አብረን መስራት መጀመር አለብን።»
ፕሬዝደንት መሐመድ አብዱላሒ መሐመድ በ2017 ስልጣን ሲይዙ ሙስናንና አል ሸባብን ለማጥፋት፣አዲስ ሕገ-መንግስት ለማስረቀቅ፣ የ«አንድ ሰዉ አንድ ድምፅ» ምርጫን ገቢር ለማድረግ ቃል ገብተዉ ነበር።አንዱም አልሆነም።የሐሰን ሼኽ ማሕሙድ ቃል-ከቀዳሚያቸዉ የተለየ፣ የሩቅም ቢሆን ተስፋ ሰጪም ነዉ።ከተስፋ መዝለል አለመዝለሉን ግን ጊዜ ነዉ በያኙ።
ነጋሽ መሐመድ
ኂሩት መለሰ