1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሶማሊያ፤ ምርጫ፤ ተኩስና ሽብር

ነጋሽ መሐመድ
ረቡዕ፣ የካቲት 1 2009

ምርጫዉ  ከዉጊያ፤ ሽብር ሥጋት በተጨማሪ፤ መንበሩን ሞቃዲሾ ያደረገዉ የፀረ-ሙስና ተቋም እንደሚለዉ  ጉቦ፤ ምልጃ ፤ ማባበል፤ መወዳጅ፤ በጥቅም መደራደር የጎላበት ነዉ።አንድ ድምፅ እስከ 30 ሺሕ ዶላር መሸጡ ተዘግቧል።

Somalia Präsidentschaftswahl
ምስል picture-alliance/AP Photo/F. Abdi

Somalia Wahl - MP3-Stereo

This browser does not support the audio element.

ሶማሊያ ዉስጥ ዛሬ በተደረገዉ የመጀመሪያ ዙር ፕሬዝደንታዊ ምርጫ በሥልጣን ላይ የሚገኙት ፕሬዝደንት ሐሰን ሼኽ ማሕሙድ አሸነፉ።ይሁንና ለሙሉ አሸናፊነት የሚያበቃቸዉን ሁለት ሰወስተኛ ድምፅ ባለማግኘታቸዉ በሚቀጥለዉ ዙር ምርጫ መፎካከር አለባቸዉ።በሶማሊያ የምርጫ ሕግ መሠረት በመጀመሪያዉ ዙር ምርጫ ከአንድ እስከ አራት ያለዉን ደረጃ ያገኙ ዕጩዎች በቀጣዩ ዙር ይፎካከራሉ።በዛሬዉ ምርጫ ዋዜማ ትናንት ርዕሠ-ከተማ ሞቃዲሾ በመድፍ ተደብድባለች።ዛሬ ጠቃት ደግሞ ቦሳሶ በሚገኝ አንድ ሆቴል ላይ ታጣቂዎች በከፈቱት ተኩስ ቢያንስ ስድስት ሰዉ ገድለዋል።

እንደ ሠላሙ ወግ ምርጫ፤ እንደ ረጅም ጊዜ ልምዷ  ዉጊያ፤ ተኩስ ግድያም እያስተናገደች ነዉ።ሶማሊያ።የሠላም-ጦርነት ቅይጥ ምድር።ትናንት በምርጫዉ ዋዜማ ርዕሠ-ከተማ ሞቃዲሾ በሞርታር አረር ስትርድ ነበር።በትንሽ ግምት አምስት ሰዉ ቆስሏል።ዛሬ ሲነጋጋ ቦሳሶ በጥይት ተኩስ፤ በቦምብ ፍንዳታ ተናዉጣለች።የአክራሪዉ ደፈጣ ተዋጊ ቡድን የአሸባብ አባላት ናቸዉ የተባሉ ሁለት ታጣቂዎች ቦሳሶ ሆቴል ላይ በከፈቱት ተኩስ ስድስት ሰዉ ገድለዋል።እራሳቸዉም ተገድለዋል።

 

ሞቃዲሾ ግን ዛሬ እስከ ማምሻዉ ሠላም ነች።ምርጫ አስተናግዳለች።የምርጫዉ ሥርዓት ሒደቱና  ሥፍራዉ ግን ሐገሪቱ ከሰላም ይልቅ ጦርነት ያረበበባት መሆንዋን የሚያረጋግጥ ነዉ።ሕዝብ መሪዉን አይመርጥም።መራጮቹም በሕዝብ አልተመረጡም።በሕዝብ ያልተመረጡት የምክር ቤት አባላት ፕሬዝደንቱን የሚመርጡበት ሥፍራ ራሱ ለጦርነት የተዘጋጀ የአየር ኃይል ጦር ሰፈር ነዉ።

መራጭ-ተመራጮች ጦር ሠፈር፤ የሞቃዲሾ ነዋሪ ደግሞ በየቤቱ ተዘግቶበታል።ግን ቴሌቪዥን ያያል።የዶቼ ቬለዉ ተባባሪ ዘጋቢ መሐመድ ዑመር ሐሰን ሺኔ እንደሚለዉ ሞቃዲሾ አዉራ መንገዶች ላይ ከመንግሥት እና ከፀጥታ አስከባሪዎች መኪኖች በስተቀር ዝር የሚል የለም።እግረኛም አይንቀሳቀስም።«የከተማይቱ ከንቲባ ዩሱፍ በዳሌ ከሁለት ቀናት በፊት ባወጡት መግለጫ በከተማይቱ ዉስጥ ዛሬ ከመንግሥት መኪኖች በስተቀር የግል መኪኖች እንዳይንቀሳቀሱ አግደዋል።የንግድ እንቅስዋሴም የለም።ነዋሪዎች ከየቤታቸዉ አልወጡም።በዚሕም ምክንያት በሞቃዲሾ መንገዶች የሚንቀሳቀስ የለም።ከተማይቱ ዉስጥ ሰዉ አይታይም።»

ምስል Reuters/F. Omar

ዛሬ የተጀመረዉ ምርጫ ካለፈዉ ነሐሴ ጀምሮ በፀጥታ ችግር ምክንያት በተደጋጋሚ ሲገፋ ነበር።ፀጥታዉ ብዙም ለዉጥ አላሳየም።ምርጫዉ ግን ቢያንስ የመጀመሪያዉ ዙር በሰላም ተጠናቅቋል።ድምፅ ከመሰጠቱ በፊት በርካታ ታዛቢዎች እንዳሉት ከ22ቱ ዕቹዎች በሥልጣን ላይ ያሉት ፕሬዝደንት ሐሰን ሼኽ ማሕሙድ እና የቀድሞዉ የሽግግር ፕሬዝደንት ሸሪፍ ሼኽ አሕመድ በግንባር ቀደምትነት ይፎካከራሉ።

                            

«በሥልጣን ላይ የሚገኙት ፕሬዝደንት ሐሰን ሼኽ ማሕሙድ ለተጨማሪ ዘመነ-ሥልጣን ይመረጣሉ የሚል አስተያየት አለ።ብዙ የምክር ቤት አባላት እሳቸዉን ይደግፋሉ የሚሉ አሉ።የዚያኑ ያክል የቀድሞዉ ፕሬዝደንት ሸሪፍ ሼኽ አሕመድ ከፍተኛ ድጋፍ አላቸዉ የሚል ጠንካራ አስተያየት አለ።በዚሕም ብሎ በዛ ቀጣዩ ፕሬዝደንት ከነዚሕ ከሁለቱ አንዳቸዉ ሳይሆን አይቀርም የሚለዉ ግምት ጠንከራ ነዉ።ሁለቱም አብጋል የተሰኘዉ የሐዉያ ንዑስ ጎሳ አባላት ናቸዉ።»

በመጀመሪያዉ ዙር ምርጫ ፕሬዝደንት ሐሰን ሼኽ ማሕሙድ 89 ድምፅ በማግኘት አንደኛ ሆነዋል።ሁለተኛዉ የቀድሞዉ ጠቅላይ ሚንስትር መሐመድ አብዱላሒ ፎርማጆ ናቸዉ።72 ድምፅ።ብዙ የተጠበቁት የቀድሞዉ ፕሬዝደንት ሸሪፍ ሼሕ አሕመድ ሰወስተኛ ናቸዉ።45።ያሁኑ ጠቅላይ ሚንስትር ዑመር አብዲረሺድ ዓሊ ሸርማርኬ 35 ድምፅ።አራተኛ።አራቱ ፖለቲከኞች በቀጣዩ ዙር ይወዳደራሉ።

ምስል Reuters/F. Omar

ምርጫዉ  ከዉጊያ፤ ሽብር ሥጋት በተጨማሪ፤ መንበሩን ሞቃዲሾ ያደረገዉ የፀረ-ሙስና ተቋም እንደሚለዉ  ጉቦ፤ ምልጃ ፤ ማባበል፤ መወዳጅ፤ በጥቅም መደራደር የጎላበት ነዉ።አንድ ድምፅ እስከ 30 ሺሕ ዶላር መሸጡ ተዘግቧል።ጠቅላይ ሚንስትር ዑመር አብዲረሺድ ሸርማርኬ በበኩላቸዉ አጎራባች ሐገራት የሚሽቱን ዕጩ ለማስመረጥ በምርጫዉ  ጣልቃ ገብተዋል በማለት ወቅሰዋል። ሸርማርኬ «ጣልቃ ገባ» ያሉትን ጎረቤት ሐገር በሥም አልጠቀሱም።

ነጋሽ መሐመድ

ኂሩት መለሰ

 

 

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW