1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሶማሊያ፤ አዲስ መንግሥት አሮጌ ፖለቲከኞች

ሰኞ፣ ነሐሴ 14 2004

«የሽግግር» እንደተባለ ስምንት ዓመት ሊደፍን ወራት የቀሩት መንግሥት ባለሥልጣናት ግን በአፍሪቃ ጦር እየተጠበቁ በአብዛኛዉ ከምዕራባዉያን፥ በጥቂቱ ከአረብ ሐገራት የሚገኘዉን ርዳታ እየተቀራመቱ ከመቀማጠል ባለፍ ለሶማሊያ ሕዝብ የተከሩት ብዙም የለም።

In a photograph taken Wednesday, Aug. 1, 2012 and released by the African Union-United Nations Information Support team Thursday Aug. 2., 2012. A man waves the Somali national flag ahead of the arrival of Somali President Sheik Sharif Sheik Ahmed (not seen) in Balad town, Somalia, in Middle Shabelle region approx. 40km north east of the capital Mogadishu. Balad was until recently, under the control of the Al-Qaeda-affliated terrorist group Al Shabaab until an offensive by the Somali National Army (SNA) supported by the African Union Mission in Somalia (AMISOM) forces on 26 June drove out the extremists, liberating the town and its people, and bringing the area under the control of the UN and internationally-backed Transitional Federal Government (TFG) whose mandate expires on 20 August. (AP Photo/AU-UN IST / Stuart Price).
ምስል dapd


ዓለም ከኦሎምፒኩ ቱማታዉ ማግስት፣ በሶሪያዉ እልቂት ጦርነት በዲፕሎማሲዉ እንኪያ ሰላንታ፣ በዩሮ ዉድቀት-ትንሳኤዉ ወከባ፣ በድርቅ ረሐብ መቅሰፍቱ መሐል ወደ ሞቃዲሾ ሲያማትር ጉደኛይቱ ሐገር የሐሃያ ዓመት እድፍ-ጉድፏን ባዲስ ሥም-ተስፋ ልትጆቡን ስትባትል አገኛት ዛሬ።የሶማሊያ የጎሳ መሪዎች ዉሳኔ፣ የፖለቲከኞችዋ ሥልት የኒዮርክ-ብራስልስ፣ የአዲስ አበባ-ካይሮ ዲፕሎማቶችን ማስደሰቱ፥የካምፓላ-ቡጁምቡራ፥ የአዲስ አበባ ናይሮቢ መሪዎችን ማኩራቱ፥ የዋሽግተን-ለንደን፥ የፓሪስ ሮም፣ የሪያድ-አንካራ ፖለቲከኞችን ማርካቱ እየናኘ ነዉ።ሶማሊያና ሶማሌዎቹስ? ላፍታ አብረን እንጠይቅ።


አብኩዋር ሼክ ዓሊ ከሞቃዲሾ ወደ ኬንያ ከተሰደደ፥ ኢስቲሌኽ-ናይሮቢ መኖር፣ መስራት ከጀመረ ዓመታት አስቆጠረ።በመሠደዱ ከበረ-ነሰረ እንጂ አልተቸገረም። እሱና ወደ መቶ የሚጠጉ የቤተሰቡ አባላት ናይሮቢ፣ ጀቡቲ፣ ዱባይ፣ ሶማሊላንድ፣ ደቡብ ሱዳንና ዩጋንዳ ዉስጥ ትላልቅ ሆቴሎችና የተለያዩ የንግድ ተቋማትን ከፍተዉ ይሥራሉ።

እሱ ናይሮቢ የሚገኘዉ አንድ መቶ አስራ-አራት ክፍል ያሉት ሆቴል ሥራ አስኪያጅ ነዉ።ኑሮዉ የቅምጥል ነዉ።አዱኛም በሽ።የሐብቱ ብዛትም ሆነ የኑሮዉ ድሎት ልቡን ወደ ትዉልድ ሐገሩ ከመሸፈት አልገታዉም።አብኩዋርና ቤተ-ሠቡ ከሶማሊያ ዉጪ እየኖሩ፥ሶማሊያን ርቀዉ አልራቋትም። ሶማሊያ ዉስጥ እንደማያተርፉ ምናልባትም እንደሚከስሩ እያወቁ ዉጪ ያፈሩትን ሐብት ወደ ሞቃዲሾ መላካቸዉን አላቋረጡም።

«ሞቃዲሾ ዉስጥ ከዚሕ የበለጠ ትልቅ ሆቴል አለን።በጣም ትልቅ ነዉ። አሁን ግን ታዉቃለሕ አይሰራም።ምክንያቱም የኢትዮጵያ ወታደሮች አፍርሰዉ ሥለነበር።ያም ሆኖ እንደገና አሠርተነዉ ነበር።ግን አልከፈትነዉም።ምክንያቱም በአካባቢዉ አሁንም ቢሆን እኛ የምንፈልገዉን ያክል አስተማማኝ ሠላም የለም።»

የሼክ ዓሊ ቤተሰብ ሆቴሉን ለማደስ ከአስራ-ስድስት ሚሊዮን ዶላር በላይ ከስክሷል። አብኩዋርና ቤተ-ሠቡ ሶማሊያን ርቀዉ፥ ሥለ ሶማሊያ የሚያስቡ፥ ሠላም ደሕንነቷን የሚመኙት በየተሰደዱበት ሐገር ነግዶ ማትረፉ፥ ሠርቶ መኖሩ ከብዷቸዉ አይደለም።የዜግነት ክብር፥ የወገን ፍቅር፥ የሐገር ናፍቆት ገፋፍቷቸዉ እንጂ።

አምባገነኑ የጄኔራል ዚያድ ባሬ መንግሥት በ1991 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ) ከተወገደ ወዲሕ ሶማሊያን ያተረማመሰዉ የጎሳ ግጭት፥ የዉጪ ሐይላትና የጦር አበጋዞች ጦርነት፥ ከድርቅና ረሐብ ጋር ተዳምሮ ሚሊዮኖችን ፈጅቷል።እነ አብኩዋርን ጨምሮ ብዙ ሚሊዮኖችን በመላዉ ዓለም በትኗል።

2000 ማብቂያ ላይ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ድጋፍ ጁቡቲ ላይ ተሰብስበዉ የነበሩት የጦር አበጋዞችና የጎሳ ተጠሪዎች ዶክተር አብዱልቃሲም ሳላድ ሐሰን የሚመሩት የሽግግር መንግሥት ሲመሠርቱ ምሥራቅ አፍሪቃዊቱን ሐገር ያደቀቀዉን፥ ሕዝቧን የፈጀ፥ ያሰደደዉን ጦርነት የማቆሚያዉ ጅምር ተስፋ ተደርጎ ተወድሶ፥ተሞግሶ ነበር።

የተስፋ ዉዳሴ ሙገሳዉ ቃል በመላዉ ዓለም ለተበተዉ ሶማሊያዊ ተዳርሶ ሳያበቃ ሶማሊያ ከዘጠኝ ዓመት በፊት በጀመረችዉ የእልቂት ፍጅት ጉዞዋ ቀጠለች።ሶማሌ ግን ተስፋ አይቆርጥም።አብኩዋር ሶማሌ ነዉ።

«ምንጊዜም ቢሆን አሁን ካለዉ የተሻለ ነገር መምጣቱ አይቀርም።ይሁንና ሕዝቡ የሚፈልገዉ አይነት ጥሩ ነገር አይጠበቅም።ምክንያቱም ከመንግሥት አልባነት መጥፎም መንግሥት መኖሩ ጥሩ ነዉ።»

የሳላድ መንግሥት ከተሽመደመደ በኋላ አዲስ መንግሥት ለመመሥረት አስራ-አራቴ ተሞክሮ አስራ-በአምስተኛዉ ሙከራ ሰምሮ ጥቅምት 2004 ናይሮቢ ላይ የሽግግር መንግሥት ሲመሠረት ከሽግግር መንግሥቱ መሪዎችና ከደጋፊዎቻቸዉ የተንቆረቆረዉ ተስፋ ግን የእነ አቡኩዋርን ጥርጣሬ አስወግዶ፥ የሶማሊያን ምሥቅልቅል ነቅሎ የሚጥል መስሎ ነበር።

የሽግግር መንግሥቱን የሚደግፉት የዋሽንግተን፥ የብራስልስ፥ የአዲስ አበባ፥ የናይሮቢና የመሰሎቻቸዉ መንግሥታትና ማሕበራት መሪዎች ለዓለም በጣሙን ለሶማሊያ ሕዝብ የገቡት ቃል-ተስፋ ግን ፕሬዝዳት አብዱላሒ የሱፍና ተከታዮቻቸዉን ባይዶዎ ከመደበቅ ማዳን አልቻለም።በ2006 ማብቂያ በዩናይትድ ስቴትስ ድጋፍ ሶማሊያ የዘመተዉ የኢትዮጵያ ጦር የእነአቡኩዋርን ሆቴል እየደረመሰ የሶማሊያ የሸርዓ ፍርድ ቤት ሕብረትን መነቃቅሮ ቪላ ሞቃዲሾን ለፕሬዝዳት አብዱላሒ የሱፍ ማስረከቡ፥ የአብዱላሒ የሱፍ መንግሥት ለመጠናከር ጥሩ መሠረት መስሎ፥ ከአዲስ አበባና ከባይዶዎም በሰፊዉ ተነግሮለት ነበር።


የኢትዮጵያ ጦር ዘመቻ፥ እስከዚያ ጊዜ ድረስ ብዙም የማይታወቀዉን አሸባሪ ቡድን አሸባብን አጠናክሮ ሶማሊያን ጦርነቱ አልበቃ ያላት ይመስል ለሽብር ማጋለጡ እንጂ ድቀቱ።የሶማሊያ የሽግግር መንግሥት ፕሬዝዳት የነበሩት የአብዱላሒ የሱፍ በሁለት ሺሕ ዘጠኝ በቀድሞዉ የሸሪዓ ፍርድ ቤት ሕብረት መሪ በሼክ ሸሪፍ ሼኽ አሕመድ ተለዉጠዋል።ከጠቅላይ ሚንስትር መሐመድ ዓሊ ጌዲ በሕዋላ ስድስት ጠቅላይ ሚንስትሮች ተቀያይረዋል።

በሐያላኑ መንግሥታት የሚደገፉት ዩጋንዳ፥ ብሩንዲ፥ ኬንያ እና ኢትዮጵያ ያዘመቱት ጦር የሶማሊያዉ አክራሪ ደፈጣ ተዋጊ ቡድን አሸበባን አዳክመዉ፥ ከሞቃዲሾ፥ ከባይደዋና ከሌሎችም ከተሞች አባረዉታል።«የሽግግር» እንደተባለ ስምንት ዓመት ሊደፍን ወራት የቀሩት መንግሥት ባለሥልጣናት ግን በአፍሪቃ ጦር እየተጠበቁ በአብዛኛዉ ከምዕራባዉያን፥ በጥቂቱ ከአረብ ሐገራት የሚገኘዉን ርዳታ እየተቀራመቱ ከመቀማጠል ባለፍ ለሶማሊያ ሕዝብ የተከሩት ብዙም የለም።

የሽግግር ዘመኑ ዛሬ ያበቃል ተብሎ ነበር።ኤርፉርት ጀርመን በሚገኘዉ በማክስ-ፕላንክ የጥናት ተቋም የሶማሊያ ጉዳይ አስተንታኝ ማርኩስ ሆነ እንደሚሉት የሽግግር መንግሥቱ መኖሩም ሆነ መተካቱ ለሶማሊያ ብዙም ለዉጥ አያመጣም።

«እስካሁን ያለዉ የሽግግር መንግሥት በሁለት እግሩ ለመቆም ስምንት አመት ያደረገዉ ሙከራ አልሆለትም።እርግጥ ነዉ በዉጪ ጦር ድጋፍ በጣም በትንሹ ፀጥታ ማስከበር ችሏል።አሁን ሶማሊያ የሚታየዉ ፀጥታ በአብዛኛዉ የተከበረዉ ግን በዉጪ ጦር ነዉ።ባጭሩ ሐገሪቱ ልክ እንደከዚሕ ቀደሙ ሁሉ አሁንም ጦርነት ላይ ናት።ባለፉት አስርታት የታየዉ ቀዉስ ሕዝቡ በፖለቲከኞቹ ላይ እምነት እንዲያጣ አድርጎታል።የጦር አበጋዝ ይሁን፥ የሽግግር ፕሬዝዳት ይሁን፥ እስላማዊ መሪ ይሁን ሁሉንም ሕዝቡ ከልቡ ይቀበለዋል ማለት አጠራጣሪ ነዉ።እና አሁን ያለዉ የዉጪዎች ፍላጎት ይመስላል።ይሕ ማለት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሶማሊያዉ ትርምስ ማቆም አለበት፥ የሽግግር ዘመኑ ማብቃት አለበት በማለት ወስኗል።በዚሕም ሰበብ ነዉ የሽግግር ዘመኑ ነሐሴ ሃያ ማብቃት አለበት ተብሎ የተቆረጠዉ።ለዚሕም ነዉ ብዙ ሰዎች ለዉጡ የሶማሊያን ችግር ለማቃለል አይረዳም የሚሉት።»

የአፍሪቃ ሕብረት፥የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፥ የአዉሮጳ ሕብረትና የአረብ ሊግ ዲፕሎማቶችና ምዕራባዉያንና የአካባቢዉ መንግሥታት በተደጋጋሚ እንዳስታወቁት የሽግግር መንግሥቱ ባዲስ ቋሚ መንግሥት ሲቀየር የሶማሊያ ችግር በአብዛኛዉ ይቃለላል።ይሕን ከግብ ለማድረስም የሶማሊያ ጉዳይ ያገባናል የሚሉ መንግሥታት፥ ማሕበራትና የሽግግር መንግሥቱ ባለሥልጣናት ባለፉት ስድስት ወራት ሲባትሉ ነዉ-የከረሙት።

ባለፈዉ ነሐሴ አንድ የሶማሊያ የሕገ-መንግሥት አፅዳቂ ሸንጎ አዲስ የተረቀቀዉን ሕገ-መንግሥት አፅድቋል።የሕገ-መንግሥቱ ረቂቅ እንደ ሕገ-መንግሥት ደንብና ወግ ጥልቅ ዉይይትና ክርክር አልተደረገበትም።በሕዝብ ድምፅ አልፀደቀመምም።

የልማቷም፣ የጥፋቷም መሠረት የሆኑት የጎሳ መሪዎች የወከሏቸዉ የሸንጎ አባላት ብዙ ሳይከፋፈሉ፣ በአሸባብ ጥቃትና ዛቻ ሳይደናገጡ ረቂቁን ማፅደቃቸዉ ግን ሠነዱን ላስረቀቁት፣ ወጪዉን ለሸፈኑት፣ ቋሚ መንግሥት እንዲመሠረት ለሚጥሩት መንግሥታትና ማሕበራት ታላቅ ድል፣ ለነአብኩዋር ምኞት ጭላንጭል ተስፋ ፈንጣቂነቱ አላጠያየቅም።

በዚሕ ሕገ-መንግሥት መሠረት የሚሠራዉን የምክር ቤት አባላት ለመሰየም የጎሳ መሪዎች በተከታታይ ባደረጉት ስብሰባ ሁለት መቶ የሕግ መምሪያ ምክር ቤት እንደራሴዎችን ሰይመዋል።ሰባ አምስቱ ገናናቸዉ። ምክር ቤቱ ዛሬ የሐገሪቱን ፕሬዝዳት፥ አፈ ጉባኤና ሁለት ምክትል አፈ-ጉባኤዎችን መርጦ የሽግግር መንግሥቱ ዘመን ማብቃቱን ያዉጃል ተብሎ ነበር።

ግን አልሆነም።ፕሬዝዳትና አፈ-ጉባኤዎችን ለመምረጥ ለዛሬ የተያዘዉ ቀጠሮ ለሌላ ጊዜ ተላልፏል። የምክር ቤት አባላትን የሚመርጠዉ የጎሳ መሪዎች ስብስብ ቴክኒካዊ አማካሪዎች እንዳሉት ግን በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት ዉስጥ አዲሶቹ መሪዎች መመረጣቸዉ አይቀርም።

አይ ኤስ ኤስ በሚል ምሕፃረ ቃል የሚጠራዉ ጥናት ተቋም ባልደረባ ኢማኑኤል ኪሳንጋኒ ግን የወደፊቶቹን የሶማሊያ መሪዎች «አዲስ» መባላቸዉን አይፈቅዱትም።

«እስካሁን በሥልጣን ላይ የነበሩት ሰዎችን አሁን ብንመለከት ሥልጣናቸዉን እንደያዙ ለመቀጠል ሲፍጨረጨሩ እናያለን።እና ይሆናል ተብሎ ሊገመት የሚቻለዉ በሙስና የሚወቀሱ የሽግግር መንግሥቱ ባለሥልጣናት ሥልጣን እንደያዙ ሲቀጥሉ እናይ ይሆናል።»

የሶማሊያ የሽግግር መንግሥት የገንዘብ ሚንስትር ሁሴይን ሐለኔ «አንድ ጊዜ ከቀድሞዉ ጠቅላይ ሚንስትር ጋር ወደ አረብ ኤሚሬቶች ሔደን ነበር» አሉ።«ጠቅላይ ሚንስትሩ ከአረብ ኤሚሬቶች መሪዎች አምስት ሚሊዮን ዶላር ተቀበሉ።» ቀጠሉ የገንዘብ ሚንስትሩ፥ ከዚያስ «ለግላቸዉ ወሰዱት።»

በሁለት ሺሕ ዘጠኝና አስር መሐል የነበረዉን የሶማሊያን የሽግግር መንግሥት የገንዘብ አጠቃቀም ያጠኑት አብዱረዛቅ ፋርታአግ እንዳስታወቁት ባንድ ወቅት የሽግግር መንግሥቱ ረሐብተኞችን እንዲረዳበት፥ የባሕር ላይ ወንበዴዎችንና አሸባሪዎችን እንዲከላከልበት ሰባ-አምስት ሚሊዮን ዶላር ከዉጪ በርዳታ አገኘ።አምስት ሚሊዮኑ በርግጥ ለታለመለት አገልግሎት ዋለ።የተቀረዉ ሰባ ሚሊዮን ግን በየባለሥልጣናቱ ኪስ ገባ።

ሶማሊያ የማይሆን የለም።ባለፈዉ ነሔሴ መጀመሪያ የሽግግሩን ፕሬዝዳት ሸክ ሸሪፍን ጨምሮ የሶማሊያን ባለሥልጣናት ያነጋገሩት የዩናይትድ ስቴትስዋ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ሒላሪ ክሊንተን ቢያንስ ፕሬዝዳንቱ የያዙትን ሥልጣን እንደያዙ እንዲቀጥሉ በተዘዋዋሪ መንገድ ያረጋገጡ መስለዋል።

ጀርመናዊዉ የፖለቲካ አዋቂ ማርኩስ ሆነ እንደሚሉት ግን የሽግግር መንግሥቱ ባለሥልጣናት በቋሚዉ መንግሥትም ዉስጥ ቀጠሉ አልቀጠሉ እስካሁን የነበረዉ ሂደት ከምርነቱ ይልቅ ቧልትነቱ ነዉ የሚያመዝነዉ።

«ካለፉት ወራቶች ምናልባት ለግማሽ ዓመት የነበረዉና አሁን ወደ መጠናቀቁ የተቃረበዉ ሒደት እንዲያዉ ቧልት ብጤ ነዉ።ዉጤቱም የተለየ ነዉ ሊባል አይቻልም።እኔ የማየዉ ብዙ ባልደረቦቼም ጉዳዩን የሚመለከቱት በጣም በመነመነ ተስፋ ነዉ።በድጋሚ በግልፅ መታየት ያለበት አጠቃላይ ሒደቱ በሙሉ አሁንም በጦርነት በምትመሠቃቀል ሐገር ነዉ የሚከናወነዉ።የብዙ ሐገር ጦር በሠፈረባት ሐገር ነዉ።የሐገር ዉስጦቹ ሸማቂዎች ወይም እስላማዉያኑ የአሸባብ ተዋጊዎች ገና ባልተሸነፉበት ሐገር ነዉ።»

ግን የተገመተዉ እየሳተ-ያልተጠበቀዉ፥ የታቀደዉ እየፈረሰ ያልታቀደዉ የተገባዉ ቃል እየታጠፈ ያልተሰማዉ በሚፈፀምባት ሐገር ሁሉም ሊሆን-ላይሆንምም ይችላል።ነጋሽ መሐመድ የሚሆነዉን ሲሆን ለመስማት ያብቃን።

የባሕር ላይ ወንበዴዎችን የሚወጋዉ ጦርምስል AP
ሞቃዲሾ ገበያምስል AP
የሶማሊያ ፖሊስምስል dapd
ሼክ ሸሪፍና ክሊንተንምስል AP

ነጋሽ መሐመድ

ሸዋዬ ለገሠ




ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW