1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሶማሊያ፤ ዉዝግብ፤ የጌዲ ስንብት

ማክሰኞ፣ ጥቅምት 19 2000

በሶማሊያ የሽግግር መንግስት ፕሬዝደንት አብዱላሂ ዩሱፍና በጠቅላይ ሚኒስትር አሊ ሞሃመድ ጌዲ መካከል የተፈጠረዉ አለመግባባት ገፍቶ ጌዲ ከስልጣን እንዲለቁ አብቅቷል።

አሊ ሞሐመድ ጌዲ
አሊ ሞሐመድ ጌዲምስል AP

ባለፉት ሳምንታት በአገር ዉስጥም ሆነ በዉጪ አግባቢዎች የተሞከረዉ የማስማማት እቅድም የተጠናቀቀዉ ጌዲ ከስልጣን መልቀቃቸዉን የሚያመለክት ደብዳቤ ዛሬ ጠዋት ለፕሬዝደንቱ፤ ቀጥለዉም ለምክር ቤቱ ካቀረቡ በኋላ ነዉ። ከስልጣን ስንብታቸዉን ምክር ቤቱ በደስታ ነዉ የተቀበለዉ።


አሊ ሞሃመድ ጌዲ ባይደዋ የተቀመጠዉ የሽግግር መንግስት በአዉሮፓዉያኑ 2004ዓ.ም ኬንያ ላይ ሲመሰረት ነዉ ወደፖለቲካዉ መድረክ ብቅ እንዳሉ የሚነገረዉ። ቀደሞ በፖለቲካዉ መደረክ በፓርላማ ተመራጭነት እንኳን አለማገልገላቸዉ የሚታወቀዉ ጌዲ የዉጪ ኃይሎች በተለይም የኢትዮጵያ ድጋፍ አላቸዉ ይሏቸዋል።

ከፕሬዝደንት አብዱላሂ ዩሱፍ ጋ መግባባታቸዉ ቀርቶ አለመስማማታቸዉ ጎልቶ የወጣዉ ደግሞ የኢትዮጵያ ወታደሮች ወደሶማሊያ ምድር ዘልቀዉ በመግባት አቅም ካልነበረዉ የሽግግር መንግስቱ ኃይል ጋ መቃዲሾን ከጦር አበጋዞች በመንጠቅ ኃይል መስሎ የታየዉ እስላማዊ ሸንጎ ተበታትኖ ሳለ መዲናይቱን ማረጋጋት ሲሳን ነዉ።

በአገሪቱ የሚገኙ ጠንካራ ጎሳዎች በስልጣን ለማካተት በታለመዉ መሰረት ነበረ ከሃዉዬ ጎሳ የተገኙት ጌዲ ጠቅላይ ሚኒስትር፤ ከዳሮድ የሚወለዱት ዩሱፍ ደግሞ ፕሬዝደንትነቱን የተሰየሙት። ሃዉዬዎች በመንግስት የስልጣን ርከን ፕሬዝደንትነቱ በዳሮድ መያዙ ጥርጣሬ ፈጥሮባቸዋል። ጌዲም ቢሆኑ ከሃዉዬ ጎሳ ይገኙ እንጂ የሃዉዮዎች ምርጫ እንዳልሆኑ ደግሞ ዉስጥ አዋቂዎች ይገልፁታል። ይህም ከመነሻዉ ሃዉዬዎች ከሽግግር መንግስቱ በተቃራኒ እንዳቆማቸዉ ይታሰባል።

ምንም እንኳን ጌዲ የሃዉዬዎችን ድጋፍ መቃዲሾ ላይ ለማግኘት ቢጥሩም ሁሉን ያካተተ ይሁንታ አልተሳካላቸዉም። ከአዲስ አበባ ድጋፍ ስለነበራቸዉ ዩሱፍም ሆኑ ጌዲ ከመነሻዉ አብረዉ ሲሰሩ ታይተዋል። በያዝነዉ የአዉሮፓዉያኑ ዓመት መጀመሪያ ግን በየፊናቸዉ የሶማሊያን ነዳጅ ዘይት ሊያወጡ ከሚፈልጉ የተለያዩ ኩባንያዎችን ለመደገፍ ባደረጉት ሙከራ ታምቆ የከረመዉ ልዩነት እየሰፋ መምጣቱ ታየ። ልዩነታቸዉ እየጎላ ሲሄድም የማግባቢያ ዉይይቶች በአገር ዉስጥም ሆኑ በዉጪ ተሞከሩዉ ዉጤት አልባ መሆናቸዉ ዛሬ ጌዲ ስልጣናቸዉን መልቀቃቸዉን በደብዳቤ ለፕሬዝደንቱ፤ ለምክር ቤቱም በአካል ቀርበዉ ሲያሳዉቁ ተገለጠ።

ጌዴ ጠቅላይ ሚኒስትር በነበሩበት ወቅት ቃል አቀባያቸዉ እንደሆኑ የገለፁት አብዱላሂ ሙህዲን ኦብካ ጌዲ ለሶማሊያ ህዝብና መንግስት ደህንነት ሲባል ከዉጪ በተደረገባቸዉ ግፊት ነዉ ስልጣት የለቀቁት፤
«የአዉሮፓ ህብረት፤ ዩናይትድ ስቴትስ፤ ኢትዮጵያ፤ የአፍሪቃዉ ህብረትና የምስራቅ አፍሪቃ የልማት በይነ መንግስታት IGAD በተለይም ደግሞ ዩናይትድ ስቴትስ፤ ኢትዮጵያና ሳዉዲ አረቢያ።»


ለመቃዲሾ መረጋጋትና ለሶማሊያ ሰላም ሲባል ጌዲ በዉጪዉ ዓለም ጫና ስልጣን መልቀቃቸዉን የገለፁት ሙህዲን በሁለቱ መካከል ለተፈጠረዉ አለመግባባት የአገር ዉስጡን መሰረታዊ ችግር ለመንገር ፈቃደኛ አልሆኑም። የአፍሪቃ ቀንድ ተንታኝ የሆኑት ጀርመናዊቷ አኔታ ቨበር ጉዳዩን በቅርበት እንደማወቃቸዉ የሚሉት አለ፤


«እንደሚመስለኝ በአሁኑ ሰዓት ለችግሩ ማሳበቢ ነገር እየተፈለገ ነውናም ጌዲ አሁን ምን እንኳን ከኢትዮጵያ በኩል ጠንካራ ድጋፍ እንደነበራቸዉ ቢታወቅም የነበረዉ ትስስር ደከም ያለ ይመስላል፥ አሁን ተሰሚነት ያላቸዉ አብዱላሂ ዩሱፍ በመሆናቸዉ እሳቸዉን ደስተኛ ለማድረግና ላለፉት አስራአንድ ወራት እየተባባሰ ለመጣዉ የደህንነት ችግር እሳቸዉን ላለመኮነን የተደረገ ይመስላል። በተለይ ደግሞ በሳምንቱ መጨረሻ የታቀደዉና የሰላም ድርድር በመክሸፉ የግድ አንድ ሰዉ መሰናበት ይኖርበታል ጥፋቱን ለመሸከም።»
ችግሩ እየተባባሰ በሄደባት በሶማሊያ ጌዲ ስልጣኑን ይልቀቁት እንጂ በማን ሊተኩ እንደሚችል ገና አልታወቀም።

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW