1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሶማሊያ የሚገኙ የኢትዮጵያ ወታደሮች

ማክሰኞ፣ የካቲት 19 2005

ባለፉት ጥቂት ወራት ከሶማሊያ ከደርሱን አጫጭር የስልክ መልዕክቶች መካከል አብዛኞቹ ፣ በሶማሊያ የሚገኘው የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ኃይል መች ወደ ሀገር እንደሚመለስ የሚጠይቁ ሲሆኑ፣ ወታደሮቹ ላይ ደረሰ ስለተባለ እሮሮም ያወሳሉ።

ምስል AP

የኢትዮጵያ መንግስት ግን ጥያቄው ተጨባጭነት የለውም ብሏል። ደረሰ የተባለው እሮሮም አሉባልታ ነው ሲል አጣጥሏል። ከጥቂት ወራት ወዲህ ከሶማሊያ በአጭር የመልዕክት ማስተላለፊያ መሥመራችን በኩል(SMS ) ለዶቼቬሌ የሚላኩ አብዛኞቹ መልዕክቶች የሚመጡት በሶማሊያ ካሉ የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ኃይል ወታደሮች ነው። አብዛኞቹ መልዕክቶች በሶማሊያ የሚገኘው የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ኃይል መች ወደ ሀገር እንደሚመለስ የሚጠይቁ ናቸው። ወታደሮቹ ላይ ደረሱ ስለተባሉ ችግሮችም ያወሳሉ፣

«አልሸባብ ተደምስሷል። የቀረው የሶማሊያ መንግስት ጦር ነው እና ከማን ጋ ነው የምንዋጋው?»

«የኢትዮጵያ መንግስት ብቁ ሠራዊት አለኝ እያለ ያልሆነ ፕሮፖጋንዳ ይነዛል። እኛ ግን በቁማችን ሞተናል። ኧረ የኢትዮጵያ ህዝቦች ሆይ አትጨክኑብን?»

«ለሀገራችን ዘብ የምንቆም የህወሃት ሠራዊት እኛ ብቻ ነን? ከሁለት ዓመት በላይ በጦርነት ማነቆ ውስጥ ነን። ለምን አይቀይሩንም።»

ምስል PETER DELARUE/AFP/Getty Images

«ኧረ አልሸባብ ማነው?መሪ ተብለው ተቀምጠው እየበዘበዙን ነው። ሌላው ቀርቶ የራሽን ብር አልቀረም። እባካችሁ እኛ የምንፈልገው ከሶማሊያ መውጣት ነው።»

«እኛ በሶማሊያ የምንገኝ ኢትዮጵያውያን ወታደሮች ወገን የለንም ወይ ፣ከህዝቡ አይደለም የተፈጠርነው?!። እባካችሁን ለኢትዮጵያ ህዝብ አሰሙልን ግፍ እየተሰራብን ነው። » እነኝህና የመሳሰሉ መልዕክቶች ነበሩ ከሶማሊያ የደረሱን ።

የኢትዮጵያ መንግስት እአአ በታህሳስ 2011 ጦሩን ወደ ሶማሊያ መልሶ ሲያስገባ ዋና ዓላማው አል-ሸባብን ከሶማሊያ ማውጣት መሆኑ ይነገራል። አልሸባብ ከሶማሊያ ጨርሶ ባይጠፋም አሁን የመዋጋት አቅሙ መዳከሙ ተነግሯል። የኢትዮጵያ ውጭ ጉይይ ሚኒስቴር ቃለ አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ፣ የኢትዮጵያ መንግስት ዓላማ የሶማሊያ ጸጥታ እንዲጠናከር መርዳትና አልሸባብ መልሶ እንዳያንሠራራ ማድረግ እንደሆነ ተናግረዋል። ስለ ወታደሮቹ በሶማሊያ መቆየት የቀረበው ቅሬታ ግን ተጨባጭ አይደለም ብለዋል።

ወታደሮቹ ይደርስብናል ያሉትን እሮሮም አምባሰደሩ ያልተረጋገጠ አሉባልታ ሊሆን ይችላል ነዉ ያሉት። የኢትዮጵያ መንግስት መች ከሶማሊያ እንደሚወጣ በግልጽ የተቀመጠ ቀነ ገደብ የለም። የሶማሊያ ጸጥታ እንዲጠናከርና አልሸባብ እስኪያንሠራራ በሶማሊያ እንደሚቆይ ቢናገርም፣ መንግስት ሽብርተኝነትን በመዋጋት ስም ከምዕራባውያን ሀገራት የሚያገኘውን እርዳታ ለማስቀጠል እንደሚፈልግም ይነገራል።

ገመቹ በቀለ

አርያም ተክሌ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW