1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሶማሊያ የክሽፈት አብነት፣ዉብ ምድር

ሰኞ፣ የካቲት 1 2013

የሶማሊያ ፖለቲከኞች ለስልጣን ሲሻኮቱ፣ የሞቃዲሾና የናይሮቢ መሪዎች በግዛት ሲወዛገቡ አሸባብ ሁለቱንም ሐገራት እያደባ ያሸብራል።ባንድ ቀን ባንዴ ጥቃት 12 የስለላ ባለሙያዎች መገደላቸዉ የሶማሊያ ፖለቲከኞችን በጋራ የሚያቆም፣ የአፍሪቃ ጎረቤቶቻቸዉን ለርዳታ የሚያሽቀዳድም በሆነ ነበር።

Somalia Mogadischu Parlament
ምስል STRINGER/AFP/Getty Images

ሶማሊያ የዉዝግብ፣ሽኩቻ፣ የክሽፈት ሐገር

This browser does not support the audio element.


የሶማሊያ ሕዝብ በ1961 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) ነፃ ከወጣ በኋላ ነፃና ትክክለኛነቱ ቢያጠራጥርም መሪዉን በድምፁ መርጦ ነበር።በ1969 ጄኔራል መሐመድ ዚያድ ባሬ የመሪነቱን ስልጣን ከተቆጣጠሩ ወዲሕ አጠራጣሪዉ ምርጫም ቀረ።ዚያድ ባሬ ከስልጣን ከተወገዱ ከ1991 እስከ 2009 በነበረዉ 28 ዓመት ደግሞ በሕዝብ የተመረጠ ዓይደለም አንድነቷን የሚያስከብር መሪም አልነበራትም።በ2017 በተደረገዉ ተዘዋዋሪ ምርጫ መሐመድ አብዱላሒ መሐመድ (ፎርማጆ) ሥልጣን ከያዙ ወዲሕ የሞቃዲሾ ፖለቲከኞች፣ የኒዮርክ፣ ብራስልስ፣አዲስ አበባ ዲፕሎማቶች ቃል ተስፋ ሶማሊያ ዘንድሮ «አንድ ሰዉ አንድ ድምፅ» በሚባለዉ ሥርዓት የሚመረጥ መሪ ይኖራታል የሚል ነበር።ዛሬ ሶማሊያ ሕጋዊ ፕሬዝደንት የላትም።አሸባብ እያሰለሰ ይገድልባታል።የአፍሪቃ ሕብረት ጦር ይተራመስባታል።ኬንያም ቁስሏ ትጓጉጥባታለች።ሶማሊያ የክሽፈት አብነት።
                                 
የአሻባብ ጥቃት፣ የጦር አበጋዞች ሥጋት፣ የመራጩ ሕዝብ ንቃት፣ የጎሳ መሪዎች ክፍፍልና የምርጫ ማስፈፀሚያ ገንዘብ እጥረት ሠበብ-ምክንያት ሆነዉ የሶማሊያ መሪዎች ምርጫ በተዘዋዋሪ እንዲሆን በ2009 ተወሰነ።በዉሳኔዉ መሰረት የጎሳ መሪዎች 51 ተወካዮችን ይሰይማሉ።የጎሳ መሪዎቹ ተወካዮች አብዛኛዉን ጎሳ ያሰባጠረ የምክር ቤት አባላትን ይመርጣሉ።የምክር ቤቱ አባላት የሐገሪቱን ፕሬዝደንት ይመርጣሉ።በዚሕ ስልት ሼሕ ሸሪፍ ሼኽ አሕመድ እና ሐሰን ሼኽ ማሕሙድ ተመርጠዉ ለአራት-አራት አመት ሐገሪቱን መርተዋል።በ2017 መሐመድ አብዱላሒ መሐመድም የተመረጡት በዚሁ ስልትና ዉሳኔ መሰረት ነዉ።
የመሐመድ አብዱላሒ መሐመድ ዘመነ-ሥልጣን ዛሬ ከማብቃቱ በፊት ሐገሪቱ «አንድ ሰዉ አንድ ድምፅ» የሚባለዉን የቀጥታ ምርጫ ሥርዓትን ገቢር እንደምታደርግ  ፖለቲከኞች ቃል ገብተዉ ነበር።የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ የአዉሮጳ ሕብረት፣ የአፍሪቃ ሕብረትም የሶማሌ ፖለቲከኞቿ ቃል ገቢር እንዲሆን በገንዘብ፤ በዲፕሎማሲና ፀጥታን በማስከበር እንደሚተባበሩ አስታዉቀዉ ነበር።
ሁሉም ግን ዛሬ ያዉ ነበር የዘከር የበነነ ቃል ሆኗል። ጋዜጠኛ መሐመድ ዑመር ሁሴይን (ሺኔ) እንደሚለዉ ፕሬዝደንት መሐመድ የዘንድሮዉ ተዘዋዋሪ ምርጫ ተራዝሞ ሐገሪቱ አንድ ሰዉ አንድ ድምፅ ለሚባለዉ ሥርዓት እድትዘጋጅ ፈልገዉ ነበር።ፕሬዝደንቱ ከፌደራል ክፍለ-ግዛቶች ገዢዎች ጋር ሰሞኑን ባደረጉት ዉይይትም ይሕንኑ ሐሳብ አንስተዉ ነበር።
                                 
«ፕሬዝደንቱና የፌደራል ክፍለ-ግዛቶች መሪዎች በተደጋጋሚ ሲወያዩ ነበር።በዉይይቱ ከተነሱት ነጥቦች አንዱና ዋናዉ ፕሬዝደንቱ የያዙት ስልጣን እንዲራዘምላቸዉ መጠየቃቸዉ ነበር።ፕሬዝደንቱ በመሰረቱ ዘመነ-ሥልጣናቸዉ እንዲራዘም የጠየቁት አንድ ሰዉ አንድ ድምፅ ለሚባለዉ ምርጫ ለመዘጋጀት ብለዉ ነበር።የተቀባላቸዉ ስላልነበረ ዉይይቱ ተቋረጠ።»
ፕሬዝደንቱ ድፍን 4 ዓመት ሳይዘጋጁበት ወይም ችላ ብለዉት ዘመነ-ሥልጣናቸዉ ሲያልቅ አሁን የቀጥታ ምርጫ ጉዳይን ማንሳታቸዉ፣ ስልጣናቸዉን ለማራዘም ማማኻኛ ከመፈለግ በስተቀር በርግጥ ሌላ ሊባል አይችልም።ለተቀናቃኞቻቸዉ ደግሞ አንድ የምክር ቤት እንደራሴ ባለፈዉ ቅዳሜ እንዳሉት ግልፅ ማጭበርበር ነዉ።«ምርጫዉ እንዳይደረግ ዋናዉ እንቅፋት ፕሬዝደንቱ ራሳቸዉ ናቸዉ።ለችግሮቹ ሁሉ ተጠያቂዉ የፌደራል መንግሥቱ ፕሬዝደንት መሆኑ ምንም ጥያቄ የለዉም።ምክንያቱም ምርጫዉን ማጭበርበር ፈልገዋል።»
የተቃዋሚዎቻቸዉ ዉግዘት፣የፌደራል ክፍለ-ግዛቶች መሪዎች ቅሬታ፣ የምክር ቤት አባላት ጥርጣሬ ሲያይል ፕሬዝደንቱ ከአራት ዓመት በፊት የተመረጡበት የዉክልና ምርጫ እንዲደረግ ፈቀዱ።ይሁንና በምርጫዉ ሒደት በተለይም የጎሳ ተወካዮቹን ብዛት ለመወሰን ፕሬዝደንቱ ከክፍለ-ግዛት አገረ ገዢዎች ጋር መነጋገር ግድ ነበረባቸዉ።
ፕሬዝደንቱ ከሚደራደሯቸዉ የክፍለ-ግዛት አገረ-ገዢዎች ከሁለቱ ጋር የነበራቸዉ የቆየ የስልጣን ሽኩቻ ያቋረዉ ቂም ቁርሾ በድርድሩ ሒደት አደባባይ ወጣ።የጁባ ላንድ ክፊል ራስ ገዝ ግዛት አገረ ገዢ አሕመድ መሐመድ ኢስላን (መዶቤ በቅፅላቸዉ) በ2018 ከፕሬዝደንት መሐመድ ጋር ከተጋጩ ወዲሕ  የናይሮቢ መሪዎችን ሙጥኝ እንዳሉ ነዉ።
ኬንያ ድንበር ተሻግረዉ የሚያጠቋትን አሸባሪዎች ለመዉጋት በሚል ሰበብ 4ሺሕ ጦሯን ሶማሊያ ግዛት በተለይም አሕመድ መዶቤ በሚገዙት ጁባ ላንድ አስፍራ ከተደላደለች በኋላ «ሶማሊያ ወስዳብኛለች» የምትለዉን ግዛት ለመቆጣጠር መቃዲሾን የሚፈረካክስ እሳት በተጫረ ቁጥር አቀጣጣይ ቤንዚን ጠብ ማድረጓ አልቀረም።መዶቤንም በአዲስ አበቦች አገላለፅ «በእጇ» አስገብታለች።
ፑንት ላንድ የተባለችዉን ክፍለ ግዛት እንደ ነፃ ሐገር መግዛት የሚፈልጉት አገረ-ገዢ ሰዒድ አብደላ መሐመድ የሞቃዲሾዎች «ወዳጅ» ባሆኑም የመዶቤ ግን ተቀናቃኝ ነበሩ።ፕሬዝደንት መሐመድ አብዱላሒ ከኢትዮጵያና ከኤርትራ መሪዎች ጋር ፍቅራቸዉ ጠንቶ ከአዲስ አበባ፣ ጎንደር አስመራ ሲመላለሱ፣ ናይሮቢዎች  የቀድሞ የጁባላንድ ባላንጦችንና የፑንት ላንድ ገዢዎችን አስማምተዉ በሞቃዲሾዉ መሪ ላይ አሳምፀዉ ጠበቋቸዉ።
ሶስቱም የዳሮድ ጎሳ አባል ናቸዉ።ሶስቱም የጦር አበጋዞችን ያወግዛሉ።ሶስቱም የአክራሪ አሸባሪዎች  ጠላት ናቸዉ።ሥልጣንና ጥቅም ሲሆን ግን ሞዶቤ እና ሰዒድ አብደላሕ ከፕሬዝደንት መሐመድ ይልቅ ለዑሁሩ ኬንያታ አድረዉ የናይሮቢ-ኪስማዩ-ጋሮዉ የጋራ ግንባር መሠረቱ።
«አሕመድ መዶቤ፣ ፕሬዝደንት ፎርማጆ እና የፑንትላንዱ መሪ ሶስቱም የአንድ ጎሳ አባላት ናቸዉ።ሶስቱም ዳሮድ ናቸዉ።የኬንያ ጦር ፑንትላንድ ከሰፈረ ጊዜ ጀምሮ መዶቤ ከኬንያዎች ጋር ጥብቅ ግንኙነት መፍጠራቸዉን ፕሬዝደንቱ ይጠረጥሩ ነበር።ፕሬዝደንቱ፣ መዶቤን የሚቃነቀኑትን የኪስማዩ (የጁባ ላንድ ዋና ከተማ) ፖለቲከኞችን ይደግፉ ነበር።ኋላ ግን የኬንያዉ ኡሁሩ ኬንያታ የጁባላንድንም  የፑንትላንድንም ተቀናቃኞች አስማሙና የፎርማጆ አንድ ጠላት ሆኑ።»

ምስል Mohamed Odowa
ምስል Getty Images/AFP/M. Haji Abdinur

ፕሬዝደንት መሐመድ አብዱላሒ ቀጥታ ምርጫ ለማድረግ እንዘጋጅ በሚል ሰበብ ዘመነ-ስልጣናቸዉን ለማራዘም ያደረጉት ሙከራ ከከሸፈ በኋላ፣ የሶማሊያ የፌደራልና የክፍለ-ግዛት መሪዎች በምርጫ ጉዳይ ብቻ ሶስቴ ተወያይተዋል።አልተስማሙም።ለአራተኛ ጊዜ ለመነጋገር በቀጠሮ እንደተለያዩ ግን ጋዜጠኛ መሐመድ ዑመር ሁሴይን እንደሚለዉ የጁባ ላንዱ አገረ-ገዢ አሕመድ መዶቤ ማንዴራ ወደ ተባለችዉ አካባቢ ጦር አዘመቱ።
ከማንዴራ ባጭር ርቀት ላይ በምትገኘዉ ቡልሐዋ ዉስጥ የፌደራሉ መንግሥት ጦር ሠፍሯል።ሁለቱም አካባቢዎች ኬንያ ከሶማሊያ ቀምታ ከግማደ ግዛትዋ ለመቀየጥ የምትፈልገዉ ግዛት አካል ነዉ።የሶማሊያ የፌደራልና የክፍለ-ግዛት መሪዎች ሥለምርጫ ለመነጋገር ለ4ኛ ጊዜ ያደረጉት ስብሰባ፣ የሞቃዲሾና የኪስማዩ ገዢዎች በሁለቱ አካቢዎች ባሰፈሩት ጦር ምክንያት ሲነታረኩ ቆይተዉ ተበተነ።አርብ።
                                  
«የጁባ ላንድ ግዛት ጦሩን ኬንያ ድንበር አጠገብ ማንዴራ ዉስጥ አስፈሯል።የሶማሊያ መንግሥትም ጦሩን ቡልሐዋ ዉስጥ አስፍሯል።ስለምርጫዉ ለመነጋገር በተደረገዉ ስብሰባ ላይ ፕሬዝደንቱ ቡልሐዋ የሰፈረዉን ጦር ወደ ሞቃዲሾ እንዲስቡ (እነ መዶቤ) ጠየቋቸዉ።ፕሬዝደንቱ ግን ቡልሐዋ የሶማሊያ አካል በመሆኑ እዚያ የሰፈረዉ ጦር እይነሳም አሉ።አሕመድ መዶቤ ፕሬዝደንቱን በመቃወማቸዉ ስብሰባዉ ከሸፈ።» 
ለዛሬ ተይዞ የነበረዉ ፕሬዝደንታዊ ምርጫም ቀረ።ፕሬዝደንት መሐመድ አብዱላሒ (ፎርማጆ) ለምርጫዉ መሠረዝ  ከሐገር ዉስጥ ተቃዋሚዎቻቸዉ አልፈዉ በስም ባይጠቅሷትም ኬንያን ተጠያቂ አድርገዋል።
«ዱሰመረብ የተደረገዉ 4ኛዉ ዙር የምርጫ ጉዳይ ዉይይት ፍሬ ያፈራል ብዬ ጠብቄ ነበር።እንዳለመታደል ሆኖ አልተሳካም።ዉይይቱ የከሸፈበትን ምክንያት ታዉቁታላችሁ።ማስታወቂያ ሚንስትሩም  ትናንት ተናግረዉታል።አሁን የምነግራችሁ በብሔራዊ ምርጫችንም ሆነ ባጠቃላይ በሶማሊያ የዉስጥ ጉዳይ የዉጪ ኃይላት ጣልቃገብነት አለ።»
የሶማሊያና የኬንያ ዉዝግብ ተካርሯል።ባለፈዉ ወር ጀቡቲ ላይ የተሰበሰቡት የምስራቅ አፍሪቃ የልማት በይነ-መንግስታት (ኢጋድ) አባል ሐገራት መሪዎች ሁለቱን ሐገራት ለማስታረቅ ሞክረዉ ነበር።ይሁንና መሪዎቹ እግረ-መንገዳቸዉን የገቡበት ሽምግልና ጠቡን ማለዘብ አልቻለም።
ወትሮም የጀቡቲዉ መሪ በመገለል ስሜት እየቆዘሙ፣የሱዳኑ ከኢትዮጵያ አቻቸዉ ጋር እየተጓሸሙ ከካሜራ ታይታ ባለፍ ሞቃዲሾን ከናይሮቢ የሚያስታርቁበት መሠረት፣ አቅም፣ ሞራልም ሊኖራቸዉ አይችልም ነበር።ናይሮቢና ሞቃዲሾ አምባሰደሮቻቸዉን ወደየሐገራቸዉ ጠርተዋል።ለኬንያ በየወሩ በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር የሚያስገባዉ የኬንያ ጫት (ሚራ) ወደ ሶማሊያ አይገባም።
የሶማሊያ ፖለቲከኞች ለስልጣን ሲሻኮቱ፣ የሞቃዲሾና የናይሮቢ መሪዎች በግዛት ሲወዛገቡ አሸባብ ሁለቱንም ሐገራት እያደባ ያሸብራል።ባንድ ቀን ባንዴ ጥቃት 12 የስለላ ባለሙያዎች መገደላቸዉ የሶማሊያ ፖለቲከኞችን በጋራ የሚያቆም፣ የአፍሪቃ ጎረቤቶቻቸዉን ለርዳታ የሚያሽቀዳድም በሆነ ነበር።ሥልጣን ለመያዝና የያዙትን ላለመልቀቅ የሚራኮቱት የሶማሊያ ፖለቲከኞች ግን የሰላዮቻቸዉን መገደል ከቁብ የቆጠሩት አይመስሉም። ከ20ሺሕ በላይ ጦር ሶማሊያ ዉስጥ ያሰፈረዉ የአፍሪቃ ሕብረትም የምሥራቅ አፍሪቃዊቱ መስራች አባል ሐገር ፖለቲከኞች ሲጠላለፉ፣ በከጎረቤቶቻቸዉ ግራ-ቀኝ ሲላጉ፣ በምርጫ ሲወዛገቡ በቅርብ ርቀት ያንኮራፋል።ምናልባት የዋሽግተን-ለንደኖች ትዕዛዝ ከዕንቅልፉ ይቀሰቅሰዉ ይሆናል?  

ምስል Mohammed Odowa/DW
ምስል AFP

ነጋሽ መሐመድ

አዜብ ታደሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW