1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሶማሌላንድ ነገ ረቡዕ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ታካሂዳለች

ማክሰኞ፣ ኅዳር 3 2017

ሶማሌላንድ ነገ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫን ታካሂዳለች። እአአ ከ1991 ጀምሮ እራሷን እንደ ነፃ ሀገር የምትቆጥረው ሶማሌላንድ የራሷ ገንዘብ፣ ፓስፖርት እና የጦር ሠራዊት ቢኖራትም፣ እስካሁን ከዓለም ሀገራት እውቅና አላገኘችም። አዲስ ተመራጩ ፕሬዚዳንት ሃገሪቱ ዓለምአቀፍ እዉቅናን እንድታገኝ ብሎም ስራ አጥነትና የዋጋ ግሽበት ለመቅረፍ ይሰራሉ።

የሶማሌላንድ ሰንደቅ ዓላማ
የሶማሌላንድ ሰንደቅ ዓላማ ምስል Eshete Bekele/DW

ሶማሌላንድ ነገ ረቡዕ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ታካሂዳለች

This browser does not support the audio element.

በራስ ገዝ አስተዳደር የምትመራዉ ሶማሌላንድ ነገ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫን ታካሂዳለች። እንደ ጎርጎረሳዉያኑ ከ1991 ጀምሮ እራሷን እንደ ነፃ ሀገር የምትቆጥረው ሶማሌላንድ የራሷ ገንዘብ፣ ፓስፖርት እና የጦር ሠራዊት ቢኖራትም፣ እስካሁን ከዓለም ሀገራት እውቅና አላገኘችም። የፖለቲካ ተንታኞች አዲስ ተመራጩ ፕሬዚዳንት  ሃገሪቱ ዓለም አቀፍ እዉቅናን እንድታገኝ ብሎም በግዛቲቱ የሚታየዉን ስራ አጥነት እና የዋጋ ግሽበት ለመቅረፍ ይሰራል ሲሉ ተስፋ አድርገዋል።

ከሶማሊያ ተገንጥላ በራስ ገዝ አስተዳደር የምትመራው እና በዲፕሎማሲያዊ ውጥረት ውስጥ የምትገኘው ሶማሌላንድ፣ በቀጠናዉ ውጥረት በነገሰበት በአሁኑ ወቅት ነገ ረቡዕ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫን ለማካሄድ ዝግጅቷን አጠናቃለች። ከጎርጎረሳዉያኑ 1991 ጀምሮ እራሷን እንደ ነፃ ሀገር የምትቆጥረው እና በሰሜን ምዕራብ ሶማልያ ክልል ግዛት የምትገኘው ሶማሌላንድ፤ ከተቀረው የሶማልያ ክፍል እጅግ የተረጋጋና ሰላማዊ ሆና የዘለቀች መሆኗ ይነገርላታል። ይሁንና ሶማሌላንድ በኢትዮጵያ እና በሶማልያ መካከል ለተነሳዉ ከፍተኛ ዉዝግብ እና ተቃርኖ ምክንያትም ሆናለች። አለመረጋጋት በሚታይበት በአፍሪቃዉ ቀንድ ግጭት ሊቀሰቀስ ይችላል ሲል ዓለም አቀፍ ስጋትም ቀስቅሷል። ይሁንና ሶማሌላንድ ነገ ይምታካሂደዉ ምርጫ ወሳኝ እና እጅግ አስፈላጊ መሆኑን የሶማሌላንድ ተቃዋሚ ፖለቲከኛ ፕሮፌሰር ሙባሪክ አብዱላሂ  ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል።

« የሶማሌላንድ ጉዳይ በአፍሪካ ቀንድም ይሁን ከአብዛኛው አፍሪካ የተለየ ነው። ስለዚህ ይህ ምርጫ ለሶማሌላንድ ዴሞክራሲያዊነት የበለጠ ማረጋገጫ ይሆናል።  ከዚህ በተጨማሪ በዓለም አቀፉ መድረክ የሶማሌላንድን ገጽታ ይቀይራል። እንዲሁም ለሁለት ዓመታት የዘለቀውን የፖለቲካ አለመረጋጋት እና በመንግሥት እና በተቃዋሚዎች መካከል ያለውን ፖለቲካዊ ልዩነት ያበቃል። ስለዚህ ይህ ምርጫ በእውነቱ እጅግ በጣም አስፈላጊ ነው።» ሶማሌላንድ የራሷ የመገበያያ ገንዘብ፣ ፓስፖርት እና የጦር ሠራዊት ቢኖራትም፣ እስካሁን ከዓለም ሀገራት እውቅናን አላገኘችም። ነዋሪዎችዋ ምርጫዉን ለመታዘብ ለገቡ ጋዜጠኞች እና የዉጭ ዜጎች እዉቅናንን እንሻለን ሲሉ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ መልክት አስተላልፈዋል።

«ፕሬዚዳንታዊ ምርጫዉ ኢትዮጵያ እና ሶማሌላንድ ለተፈራረሙት ሰነድ ማሻሻያ ያመጣል»

የሶማሌላንድ ፕሬዝዳንት ሙሴ ቢሂ ታህሳስ 22 ቀን ፤ 2016 ዓም ከኢትዮጵያዉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር በተፈራረሙት ስምምነት፣ 20 ኪሎሜትር ርዝመት ያለው የቀይ ባህር ዳርቻ የባህር በር ለሌላት ኢትዮጵያ ለመስጠት ቃለ መግባታቸዉ ይታወቃል። በምትኩ ኢትዮጵያ ለሶማሌላንድ እውቅና እንደምትሰጥ ነዉ የተናገሩት። ይህ ስምምነት ግን ከአዲስ አበባ በኩል አልተረጋገጠም። ሙሉ ዝርዝሩም ለህዝብ ይፋ አልተደረገም። የመግባቢያ ስምምነቱ ግን ጎረቤት ሶማሊያን አስቆጥቷል። በሁለቱ ሃገራት መካከል የቃላት እና ወታደራዊ ፍጥጫ መጨመር ዓለም አቀፉን ማህበረሰብ አሳስቧል። ሶማሌላንድ ነገ የምታካሂደዉ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ፤ኢትዮጵያ እና ሶማሌላንድ ለተፈራረሙት ሰነድ ማሻሻያ ነዉ ሲሉ ተቃዋሚ ፖለቲከኛዉ ፕሮፌሰር ሙባረክ አብዱላሂ ተናግረዋል።  

«በሶማሌላንድ ሀገርነት ላይ በሶማሊያ እና ሌሎች አካባቢዎች የሚንቀሳቀሱ አሸባሪ እና አክራሪ ኃይሎችን ጨምሮ የሶማሌላንድ ጠላቶች  በላስ አኖድ አካባቢ በከፈቱት ጦርነት ምክንያት ሶማሌላንድ በወሳኝ ሁኔታ ላይ የምትገኝ በመሆኑ እጅጉን ጠቃሚ ነው። ከዚህ በተጨማሪ ዓለም አቀፍ እውቅና ለማግኘ ት የመጀመሪያው እርምጃ ሆኖ ሊያገለግል በሚችል እና ሶማሌላንድ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በተፈራረመችው የመግባቢያ ሥምምነት እውቅና ለማግኘት ጥረት የምታደርግበት ወቅትም በመሆኑ ጠቃሚ ነው።  ምክንያቱም የመግባቢያ ሥምምነቱ የተሟላ ሥምምነት ከሆነ እና ኢትዮጵያ ለሶማሌላንድ እውቅና ከሰጠችሌሎች በአፍሪካ እና ከዚያ ባሻገር ያሉ ሀገሮች ተመሳሳይ እርምጃ ይወስዳሉ ብለን ተስፋ እናደርጋለን።»

የሶማሌላንድ ፕሬዝዳንት ሙሴ ቢሂ ታህሳስ 22 ቀን ፤ 2016 ዓም ከኢትዮጵያዉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር የመግባብያ ስምምነት ተፈራረሙምስል TIKSA NEGERI/REUTERS

እንደታቃዋሚ ፖለቲከኛዉ ፕሮፊሰር ሙባረክ ምናልባትም ምርጫዉን ፕሬዝዳንት ሙሴ ቢሂ ዳግም ሳያሸንፉ አይቀሩም። የቡሂ ተፎካካሪ ሆነዉ የቀረቡት አብዲራህማን ሞሐመድ አብዱላሂ እና ፋይሳል አሊ ዋራቤ፣ ሃገሪቱ ከኢትዮጵያ ጋር በተፈራረመችዉ መግባቢያ ሰነድ ላይ ምንም ቅሬታን አላቀረቡም። ይሁንና ቢሂን በራስገዝዋ ግዛት ለሚታየዉ የስራ አጥነት እና የዋጋ ግሽበት ተጠቂ ያደርጓቸዋል።

«አዲስ ተመራጩ ፕሬዚደንት ስራ አጥነት እና የዋጋ ግሽበትን ይጋፈጣሉ»

«ቀጣዩ ፕሬዝደንት የላስ አኖድን የጸጥ ችግር እና ጦርነት መፍታት አለባቸው። ከጥቂት ቀናት በፊት ባበቃው የተካረረ የምረጡኝ ዘመቻ የተበላሸውን  ማኅበራዊ መስተጋብርን ማሻሻል፤ ዓለም አቀፍ እውቅና ማግኘት፤ ከፍተኛ ደረጃ የደረሰውን ሥራ አጥነት እና የዋጋ ግሽበት መፍትሔ ማበጀት  ቀጣዩ ፕሬዝደንት መፍትሔ ሊያፈላልጉላቸው የሚገቡ ጉዳዮች ናቸው።» 

አብዛኛ የሶማሌላንድ ነዋሪዎች ነገ አዲስ ፕሬዚዳንታቸዉን ለመምረጥ የለዉጥ ተስፋን በሙሉ እምነት ሰንቀዉ ተነስተዋል። «ምርጫዉ ለዴሞክራሲና ለለውጥ፣ የኤኮኖሚ ዕድገት፣ በሀገሪቱ ፖለቲካዊ መረጋጋት፣ እና የተሻለ ፀጥታ ሁኔታን ያመጣል።»  ከጎርጎረሳዉያኑ 2017 ጀምሮ በስልጣን ላይ የሚገኙት የ76 ዓመቱ የሶማሌላንድ ፕሬዚዳንት ሙሴ ቢሂ፤ «ኩልሚዬ» የተሰኘዉ ፓርቲያቸዉ በድጋሚ ቢመረጥ ራስገዝዋ ሶማሌላንድ፣ ከኢትዮጵያ ጋር የገባችዉ የስምምነት ሰነድ ይሻሻላል ሲሉ ቃል ገብተዋል።

አዜብ ታደሰ

እሸቴ በቀለ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW