1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሶሪያ ተቃዉሞ:ግጭት:ምርጫና ሽብር

ሰኞ፣ ግንቦት 6 2004

የአልጄሪያዉ ጠቅላይ ሚንስትር አሕመድ ኦያሒድ «የአረብ አብዮት ተብዬዉ» አሉ ባለፈዉ ሳምንት ኢራቅን ከቅኝ ተገዢዎች እጅ የጣለ፥ ሊቢያን ያጠፋ፥ ሱዳንን ለሁለት የከፈለ፥ ግብፅን ያዳከመ ወረርሺኝ ነዉ።» ቀጠሉ።ሶሪያስ? ወረፋ እየጠበቀች ነዉ-እንበል ይሆን

Demonstrators protest against Syria's President Bashar Al-Assad in Al Habeet, near the northern province of Idlib May 11, 2012. Picture taken May 11, 2012. REUTERS/Shaam News Network/Handout (SYRIA - Tags: CIVIL UNREST POLITICS) FOR EDITORIAL USE ONLY. NOT FOR SALE FOR MARKETING OR ADVERTISING CAMPAIGNS. THIS IMAGE HAS BEEN SUPPLIED BY A THIRD PARTY. IT IS DISTRIBUTED, EXACTLY AS RECEIVED BY REUTERS, AS A SERVICE TO CLIENTS
ተቃዉሞ ሠልፍምስል REUTERS



አስራ-አራት ወራት ያስቆጠረዉ ግጭት-ዉዝግብ፣ የተቃዉሞ ሠልፍ-ዉግዘት ግመትን ከድክመቱ ከማፈራረቁ ባለፍ ለሶሪያ በርግጥ አዲስ አይደለም።የግጭት ዉዝግቡን ግመት ሥጋት ከድክመቱ፣ ምናልባትም ከመቆሙ ተስፋ የቀየጠዉ የኮፊ አናን የሰላም ሐሳብ ለወር በመለመዱ-እንግዳ አይደለም።ምርጫ ግን ምርጫን ከስም ባለፍ ለማታዉቀዉቀዉ ሐገር ከስም ባለፍ ማስተዋወቁ ቢያጠራጥርም አዲስ ነበር።ሰኞ ምርጫ ነበር።ማክሰኞ-የኮአናን አስጊ ማስጠንቀቂያ።የሰላም ተስፋ የፈነጠቀዉ የአናን ዕቅድ-ገቢር የሆነበት አንደኛ ወር ሐሙስ ሲዘከር ሽብር።ሶሪያ።ፖለቲካዊ ቀዉሳ መነሻ፥ ምክያንት እድምታዉ መድራሽን ነዉ ላፍታ አብራችሁን ቆዩ።


ሶሪያዊዉ ፈላስፋ፣ የሥነ-ማሕበረሰብ አጥኚ፣ የታሪክ ምሑርና የአረብ ብሔረተኛ ዘኪ አል-አርሱዚ ለተማሪ ተከታዮቻቸዉ ያስጠኑት ፖለቲካዊ ፍልስፍና አረብ የባሕል፣ ሐይማኖቱን ልዩነት፣ የታሪክ፣ የጎሳ ዳራዉን ብዙነት የአሰፋፈሩን ርቀት አቻችሎ በአረብነቱ ብቻ አንድነቱን እንዲጠብቅ፣ የጋራ ጥቅሙን እንዲያስከብር እንጂ ኋላ የሆነዉ እንዲሆን አስበዉ ነበር ማለት ሲበዛ ከባድ ነዉ።

ክርስቲያኑ ሚካኤል ኢፍላቅ፣ ከሙስሊሙ ሳላሕ አል-ዲን አል-ቢተር ጋር ከሚንስቶቹ ከሐይማኖት አጥባቂዎቹ ጋር በ1947 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎሮጎሳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ) የአረብ ሶሻሊሲት በአዝ ፓርቲን የመሠረቱት አረብነታቸዉን መሠረት፣ የአርሱዚን ፍልስፍና መመሪያ አድርገዉ እንጂ በጎሳ-ሐይማኖት አንድ ሆነዉ አልነበረም።

አርሱዚ በሕይወት ቢኖሩ ኖሮ ከሁለት ሳምንት በሕዋላ አንድ መቶ አስራ-ሰወተኛ አመት ልደታቸዉን ባከበሩ ነበር ።ፍልስፍናቸዉ በተለይ በ1943 The Genius of Arabic in its Toung በሚል ርዕሥ ባሳተሙት መፅሐቸዉ የተነተኑት የአረብ ብሔረተኝነት በእነ-ኢፍላቅ መሪነት በፖለቲካ ፓርቲነት ከተደራጀ ባለፈዉ ወር ስልሳ-አምስተኛ አመቱን ደፈነ።

የአርሱዚን ልደት፣ የእነ-ኢፍላቅ ፓርቲ የተመሠረተበት ዕለት ለሶሪያዎች በተለይም በአርሱዚ ፍልስፍና ሥም፣ በበአዝ ፓርቲ ሽፋን ለሚገዙት ለደማስቆ መሪዎች የትልቅ ድግስ-ፌስታ በሆነ ነበር።የአረብን ብሔረተኝነት በሚሰብከዉ ፍልስፍና አፍላቂ አንድ-መቶ አስራ-ሰወስተኛ ልደት ዋዜማ፣ የአረብን ብሔረተኝነት በሚያራምደዉ ፖርቲ ስልሳ አምስተኛ አመት ማግስት የደማስቆ ገዢዎች ሥጦታ የብዙዉ አረብ አይደለም የአንዲቷ ሶሪያ ክፍፍል መርዶ፥ የዉጊያ ዛቻ እና ፉከራ ነበር።

«ከታጠቁ፥ ሁከትና ትርምስን ከሚያቀጣትሉ አሸባሪዎች ጋር፥ ከዉጪ ሐይላት ጋር ተመሳጥረዉ በገዛ ሐገራቸዉና ሕዝባቸዉ ላይ ከሚያሴሩ ሐይላት ጋር እርቅ የለም።»

ፕሬዝዳት በሽር አል-አሰድ።ምርጫ ቨጠሩበት ዕለት ዋዜማ።


የተቃዋሚዎቻቸዉ አፀፋም፥ የሶሪያ ብሔራዊ ምክር ቤት የተሰኘዉ ስብስብ ቃል አቀባይ ሎዋይ ሳፊ እንዳሉት የመጠፋፋት ዉግዘት ነበር።«በጣም አሳፋሪ ነዉ።ገሚስ ሐገሪቱ በጦርነት ተዘፍቃ፥ ጦር ሐይሉ ከተሞችን በቦምብ እየደበደበ ሰዉ እንዴት ምርጫ ይደረጋል።»

ባለፈዉ የካቲት በተሻሻለዉ ሕገ-መንግሥት መሠረት በተደረገዉ ምርጫ ከ1966 ጀምሮ ሥልጣን ላይ የሚገኘዉን የባዕዝ ፓርቲን የሚቃወሙ ጥቂት የፖለቲካ ማሕበራት ተሳትፈዋል።ሁለት መቶ ሐምሳ መቀመጫዎች ላሉት ምክር ቤት የተደረገዉ ምርጫና መርሑ አነሰም በዛ በሶሪያ የአርባ ስድስት ዘመን ታሪክ አዲስ ክስተትነቱ በርግጥ አለነጋገረም። ምርጫዉ የሕዝብ ጥያቄ፥ የዋነኛ ተቃዋሚዎችን እንቅስቃሴ ለማፈን ፥ የዉጪዉን ዓለም ግፊት ለማደናገር ያለመ የመሆኑን ያክል፥ የምርጫዉ ሒደት አስራ-አራት ወራት ባስቆጠረዉ ግጭት-ዉጊያ መጀቦኑ እንጂ ያዲስ-አሮጌነቱ ድቀት።

ምርጫዉ የደማስቆ ገዢዎች እንዳለሙት የገጠማቸዉን ተቃዉሞ-ገፊት ማፈን እንደማይችል፥ ወይም ባደባባይ እንዳሉት የተሐድሶ ለዉጥ መሠረት እንደማይሆን ለብዙዎች ገና ሲታቀድ ግልፅ ነበር።ተፋላሚ ሐይላት፥ የዉጪ ደጋፊዎችም የቀድሞዉን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ የኮፊ አናን የሠላም ዕቅድ የደገፉትም የማፈን-ማደናገሩ ሙከራ፥ የአስራ-አራት ወራቱ ዉጊያ ለዉጤት እንደባይበቃ ሥለተረዱት ነዉ-ነበር ተስፋ እምነቱ።የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የተፋላሚዎችን የተኩስ አቁም ዉል ገቢራዊነት ለመከታተል ታዛቢ ቡድን ማሠፈሩ በጎ ተስፋ-እምነቱን የሚያጠናቅር ነበር።

የታዛቢ ቡድን ቃል አቀባይ ኒራጅ ሲንጌሕ እንዳሉትም የቡድናቸዉ አላማ-ምግባር ተስፋ ሰጪነቱን ጠቋሚ ነበር።

«የእኛ ተልኮ እዚሕ (ያለዉ) ግጭት በሙሉ ቅርፅና በሁሉም ወገን መቆሙን በማረጋገጥ ላይ ያተኮረ ነዉ።በተጨባጭ የሚደረገዉን በመከታተልና በመዘገብ ሒደት ላይ ነን።የቡድኑ አባላት ብዛት አስካሁን ድረስ ሰባ ነዉ።ከነዚሕ መካካል ሰላሳ-ዘጠኙ ወታደራዊ ታዛቢዎች ሲሆኑ የተቀሩት ሰላማዊ ድጋፍ ሰጪ ሠራተኞች ናቸዉ።»

በሶሪያ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የታዛቢዎች ቡድን ዋና አዛዥ ሜጄር ጄኔራል ሮበርት ሙድ ወደ ዳራዕ የተጓዙት ቃል አቀባይ ኒራጅ ሲንጌሕ የሰማነዉን ባሉ በሳልስቱ ነበር።ኖርዌያ-ዊዉ ጄኔራል አስራ-አንድ ባልደረቦቻቸዉን አስከትለዉ በሶሪያ መንግሥት ወታደሮች ታጅበዉ ደራዕ ከተማ ሲቃረቡ ጄኔራሉና ባልደረቦቻቸዉ የተሳፈሩባቸዉን መኪኖችን የሚመሩት መኪኖች በፈንጅ ጋዩ።

የታዛቢዉ ቡድን ባልደረቦች የደረሰባቸዉ ጉዳት የለም።እነሱት ያጀቡት አስር የሶሪያ ወታደሮች ግን ቆስለዋል።ገሚሶቹ ክፉኛ ተጎድተዋል።ዋና ሸምጋይ ኮፊ አናን በጄኔራል ሙድና በባልደረቦቻቸዉ ላይ የተቃጣዉን ጥቃት አልሰሙም፥ የሶሪያን የምርጫ ሒደት አልተከታተሉም ማለት አይቻልም። ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት በሰጡት ማብራሪያ ግን የታዛቢዉን ቡድን ያገጠመዉን አደጋ ግን አልጠቀሱም።

ሥለምርጫዉ ሒደት በጎ መጥፎነት ያሉት የለም።ባለፉት ሰላሳ ቀናት እንደተለመደዉ ዲፕሎማሲያዊ ወግ የሰላም ተስፋ የሚያጭር አልነበረም።የሥጋት ማስጠንቀቂያ እንጂ።

«ሐገሪቱ ወደ ሙሉ የርስ በርስ ጦርነት ትገባለች የሚል ሥጋት አለ።የዚሕ እንድምታ ደግሞ አስፈሪ ነዉ።ይሕ እንዲሆን ልንፈቅድ አንችልም።ወታደራዊ እንቅስቃሴዉ በሆነ ደረጃ ቀንሷል።ግጭቱን ለማስቆም የተደረገዉ ሥምምነት ግን በተደጋጋሚ እየተጣሰ ነዉ።የግጭቱ መጠንና ስምምነቱን የማወኩ ደረጃ ተቀባይነት የለዉም።»

ተቀባይነት የለዉም። ግን ቀጥሏል።የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንደሚለዉ በሶሪያዉ ግጭት ዉጊያ ከዘጠኝ ሺሕ በላይ ሰዎች ተገድለዋል።በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ ቆስለዋል።አሜሪካ መራሹ ጦር ኢራቅን ከወረረበት ከሁለት ሺሕ ሰወስት ሚዚያ እስከቅርብ ጊዜ ድረስ በርካታ የኢራቅ ስደተኞችን በማስተናገድ ሶሪያን የሚወዳደር ሐገር አልነበረም።

ወረራ፥ ጦርነት ሽብር ከሐገሩ ካሰደደዉ አራት ሚሊዮን ያክል ኢራቃዊ ከአንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ለሚበልጠዉ መጠለያ የሰጠችዉ ሶሪያ እንጂ የኢራቅን ሕዝብ ከአምባገነኖች ነፃ ለማዉጣት፥ ለማበልፀግና ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ለማስረፅ ጦር አዘመትን ያሉት ሐያላን አልነበሩም።ሶሪያ የተጠለሉት ኢራቃዉያን ወደ ሐገራቸዉ ተመለሰዉ ሳያበቁ አስተናጋጆቻቸዉ ራሳቸዉ ይሰደዱ ገቡ።

ዛሬ በብዙ መቶ ሺሕ የሚቆጠሩ ሶሪያዉን የቱርክ፥ ዮርዳኖና የኢራቅን ድንበሮች እያጨናነቁ ነዉ።ባለፈዉ ሳምንት ለሶሪያ እንዳዲስ የታየዉ ምርጫ የአዲስ አረጌነቱ እንዴትነት፥ የዓለም አቀፉ ድርጅት ታዛቢዎች ተልዕኮ እስከየትነት፥ የአናን ማስጠንቀቂያ ምክንያት ምንነት ሲያነጋግር-ደማስቆ ተሸበረች።


ቦምብ።የሰዉ ልጅ ጥንታዊ ስልጣኔ መሠረቲ፥ የሐይክሶሶቿ ጥንስሰ፥ የዑመያዶች መናገሻይቱ፥ የአይቡዶች መናኸሪያ፥ የመምሉኮች መግዢያቱ፥ ዉብ ከተማ እንደገና በደም በሰዉ ደም ጨቀየች።ሐሙስ።

ፋርሶች፥ አረቦች፥ አባሲዶች፥ቱርኮች፥ፈረንሳዮች፥ አይሁዶች እገነቡ ያፈረሷት፥ እየገደሉ ነግሰዉ፥ እየተገደሉ የወደቁባት ጥንታዊት ከተማ በነዋሪዎችዋ አካል-አስከሬን ጎደፈች።በቋሚዎቿ ዋይታ ጩኸት ደፈረሰች።ዲማሽቅ።

የሰዉ ልጅ ያለማቋረጥ ለረጅም ጊዜ ከነረባቸዉ አካባቢዎች የመጀሪያዋ ትልቅ ከተማ ካለፈዉ ታሕሳስ ጀምሮ በቦምብ ስትሸበር የሐሙሱ ስድስተኛዋ ነዉ።የሐሙሱ ግን ባንዴ ሁለት ቦምብ ያደረሰዉ ጥፋትም ከቀዳሚዎቹ ሁሉ ከባድ ነበር።ወደ ሥልሳ ያሕል ሰዎች ገድሏል።ከአራት መቶ በላይ አቁስሏል።ግን ለምን-ደግሞስ ማነዉ።ብዙዎች ብዙ ጊዜ ጠይቀዉታል።ብዙዎች እንደመሰላቸዉ መልሰዉታል።

መመለስ ከነበረባቸዉ ዋንኞቹ የሶሪያ መንግሥትና ተቃዋሚዎቹ አንዱ ሌላዉን ለመወንጂያነት ከመጠቀም ባለፍ ትክክለኛዉን መልስ አልሰጡትም።የደማስቆ ገዢዎች ከዚሕ ቀደም እንደሚሉት ሁሉ የሐሙሱን የቦምብ ጥቃትም ሶሪያን ለማጥፋት በሚሹት «በፅዮናዉያንና በአሜሪካዉያን የሚደገፉ» ያላቸዉን የመንግሥት ተቃዋሚዎች ወንጅሏል።

የመንግሥት ጦር የሚወጉ ታጣቂዎችንና ተቃዋሚ ፖለቲከኞችን የያዘዉ የሶሪያ ብሔራዊ ምክር ቤት የተሰኘዉ ስብስብ የበላይ ቡርሐን ጋሊዩን ባንፃሩ መንግሥትን ተጠያቂ ያደርጋሉ።

«ይሕ የቦምብ ጥቃት በደረሰበት ወቅት የነበሩ ሒደቶችን ማጤን ያሻል።ጥቃቱ የተፈፀመዉ በአናን የሠላም እቅድ መሠረት ሥርዓቱ ከባድ የጦር መሳሪያዎቹንና ጦሩን ከየከተሞቹ እንዲያስወጣ ግፊት በሚደረግበት ወቅት ነዉ።በእኛ እምነት ይሕ ግፊትና ጥቃቱ በቅጡ የተያያዙ ናቸዉ።»

ደማስቆ ስትሸበር እዚያዉ የነበሩት የሊባኖስ ጡረተኛ ጄኔራል ሐሺም ጀባር የሶሪያ ተፋላሚ ሐይላት የሚወነጃጀሉበትን ሰበብ ምክንያት አይቀበሉትም።

«ሶሪያ ዉስጥ ያለዉ እዉነተኛ ሥጋት የተለመደዉን አይነት ዉጊያ የሚያደርጉት አማፂያን (የሶሪያ ነፃ ጦር ይባል ወይም ሌላ) ያደርሱታል የሚባለዉ አይደለም።ዋነኛዉ ፍርሐት ይሕን መሠሉ የቦምብ ወይም የአጥፍቶ ጠፊዎች ጥቃት ነዉ።የሶሪያ መንግሥት ሐገሪቱን መቆጣጠር ያቃተዉ መስሎ መታየት አይፈልግም።እነሱ ደማስቆ እንደወትሮዉ ሰላም መሆኗን ሙሉ በሙሉ እንደሚቆጣጠሯት ማሳየት ነዉ የሚሹት።ሥለዚሕ መንግሥት ከእንዲሕ አይነቱ ጥቃት ሥለማይጠቀም የመንግሥት እጅ አለበት ብዬ አላስብም።»


በሽር አል-አሰድ ከደማስቆ ሲዝቱ፥ ተቃዋሚዎቻጨዉን ሲወነጅሉ፥ ቡርሐን ጋሊዩኒ ከኢስታንቡል፥ ኮሎኔል ሪያድ አል-አሰድ ከተደበቁበት ይፎክራሉ።ኮፊ አናን ከዤኔቭ ድርድር ዉይይት ሲሉ የቀጠር፥ የሪያድ ነገስታት፥ የአንካራ መሪዎች የደማስቆ ገዢዎችን ለማስጥፋት ይዝታሉ።ዋሽግተኖች ደማስቆን ሲያወግዙ ሞስኮዎች የደማስቆ ተቃዋሚዎችን ይተቻሉ።

አንዳቸዉም ግን የሶሪያ ሕዝብን መከራ-ሰቆቃ ያባሰዉን ያሁኑንም ሆነ የእስካሁኑን የሽብር ጥቃት ያደረሰዉን ወገን ማንነት አልጠቆሙም።የዓለም አቀፉ የታዛቢ ቡድን አባል ጀርመናዊዉ ሐገን ፔንከርት ግን አል-ቃኢዳን ይጠረጥራሉ።

«በተከታታይ የደረሱት የአጥፍቶ ጠፊዎች የቦምብ ጥቃቶች ይዘት አል-አቃኢዳ በሆነ ደረጃ ቢሆን የተሳተፈባቸዉ ሳይሆኑ እንዳልቀሩ ያመለክታሉ።» የፔንከርትን ሐሳብ የተጋሩ ብዙዎች ናቸዉ። የብሪታንያዉ ማሰራጪያ ጣቢያ ባለፈዉ ቅዳሜ እንደዘገበዉ ግን አደጋዉን ያደረሰዉ አል-ኑስራ የተሰኘ አዲስ ፅንፈኛ ቡድን ነዉ።

«ባለፈዉ መግለጫችን ሥርዓቱ በብዙ የሶሪያ አዉራጃዎች በቤተሰቦች፥ በሴቶች፥ በሕፃናትና በአዛዉንቶች ላይ የፈፀመዉ ግድያ እንደምንበቀል ቃል ገብተን ነበር።እነሆ አሁን ቃላችንን ገቢር አደረግን» ይላል-ቢቢሲ የጠቀሰዉ የቡድኑ የቪዲዮ መግለጫ።የእልቂት አዋጅ።

ጄኔራል ሐፊዝ አል-አሰድ የመሯቸዉ የጦር መኮንኖች በአዝ-ፓርቲ ሽፋን በ1966 የደማስቆ ቤተ-መንግሥት ከተቆጣጠሩ ወዲሕ በ1940ዎቹ የአረብ-አንድነት፥ ብሔረተኝነት የተሰበከባት፥ በ1950ዎቹ ገቢራዊነቱ የተሞከረባት ሐገር-አናሳዎቹን አል-አዊት ሐራጥቃ አገዛዝ ነዉ የሰፈነባት።

በ1970ዎቹ ማብቂያ አገዛዙን በመቃዉም ብቅ ያለዉን የአብዛሐዉ የሱኒ እምነት ተከታይን አመፅ አገዛዙ ባፍታ ነበር የደፈለቀዉ።የኩርዶችን ጥያቄም እንዲሁ።ያም ሆኖ-አመፅ ተቃዉሞዉም ሆነ አፀፋዉ ያሁኑን ያክል ሕዝብ የሚፈጅ፥ የሚያሸብር ምናልባትም የጥንታዊቱን ሐገር አንድነት ከጥያቄ የጨመረ ነበር ማለት ያጠራጥራል።

የአልጄሪያዉ ጠቅላይ ሚንስትር አሕመድ ኦያሒድ «የአረብ አብዮት» ተብዬዉ አሉ ባለፈዉ ሳምንት ኢራቅን ከቅኝ ተገዢዎች እጅ የጣለ፥ ሊቢያን ያጠፋ፥ ሱዳንን ለሁለት የከፈለ፥ ግብፅን ያዳከመ አደገኛ ወረርሺኝ ነዉ።» እያሉ ቀጠሉ።ሶሪያስ? ወረፋ እየጠበቀች ነዉ-እንበል ይሆን።ነጋሽ መሐድ ነኝ ቸር ያሰማን።

ሽብርምስል Reuters
ስደትምስል Doris Bulau
ግድያምስል Reuters

ነጋሽ መሐድ

አርያም ተክሌ




















ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW