1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሶስት ሕዝበ-ውሳኔዎች፤ አራት ክልሎች፦ የደቡብ ጥያቄ ተመለሰ?

Eshete Bekele
ሰኞ፣ የካቲት 6 2015

ከሕዳር 2012 ጀምሮ የተካሔዱ ሶስት ሕዝበ-ውሳኔዎች የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልልን አራት ከፍለው ታሪክ ሊያደርጉት ነው። ክልሉን ወደ መፍረስ የገፉ ጥያቄዎች ምን ያክል ተመለሱ? ይኸ ውይይት የኢትዮጵያ መንግሥት የተከተለውን አካሔድ፣ ሕዝበ-ውሳኔዎቹን እና አዲሶቹ ክልሎች የነዋሪዎችን ህልም ለማሳካት የሚጠብቃቸውን ፈተና ይፈትሻል።

ሶስት ሕዝበ-ውሳኔዎች፤ አራት ክልሎች፦ የደቡብ ጥያቄ ተመለሰ?

This browser does not support the audio element.

ከሶስት ተከታታይ ሕዝበ-ውሳኔዎች በኋላ የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል ወደ አራት ተከፍሎ ታሪክ ሊሆን በሒደት ላይ ይገኛል። ደቡብን ታሪክ የሚያደርጉት ሕዝበ-ውሳኔዎች የተካሔዱት ራስን በራስ የማስተዳደርን ጨምሮ በተከታታይ ከተነሱ ዘርፈ ብዙ ጥያቄዎች እና ግፊቶች በኋላ ነው። አብዛኞቹ የደቡብ ክልል ዞኖች በየምክር ቤቶቻቸው ባሳለፏቸው ውሳኔዎች የየራሳቸውን ክልል በተናጠል ለማቆም ፈልገው የነበረ ቢሆንም የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት የተለየ መንገድ መርጧል። 

ባለፈው ጥር 29 ቀን 2015 ዓ.ም. የተካሔደው እና ውጤቱ "ደቡብ ኢትዮጵያ" የተባለ ክልል ያቋቁማል ተብሎ የሚጠበቀው ሕዝበ-ውሳኔ በዎላይታ፣ ጋሞ፣ ጎፋ፣ ኮንሶ፣ ደቡብ ኦሞ፣ ጌዴኦ ዞኖች እንዲሁም ኧሌ፣ ባስኬቶ አማሮ፣ ቡርጂ እና ደራሼ ልዩ ወረዳዎች የተካሔደ ነው። በደቡብ ክልል ሶስተኛ የሆነው ይህ ሕዝበ-ውሳኔ 410 ሚሊዮን ብር ገደማ የተበጀተለት ሲሆን ከሶስት ሚሊዮን በላይ ነዋሪዎች በ3371 የድምጽ መስጫ ጣቢያዎች ተሳትፈውበታል። ውጤቱም የካቲት 8 ቀን 2015 ዓ.ም. ይፋ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል። 

በሁለተኛው ሕዝበ-ውሳኔ ውጤት መሠረት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል በሕዳር 14 ቀን 2014 ዓ.ም. ተመስርቷል። በካፋ፣ ዳውሮ፣ ቤንች ሸኮ፣ ምዕራብ ኦሞ፣ ሸካ ዞኖች እና ኮንታ ልዩ ወረዳ ከደቡብ ክልል ወጥተው የራሳቸውን መስተዳድር ለማቋቋም ሕዝበ-ውሳኔ የተካሔደው መስከረም 20 ቀን 2014 ዓ.ም. ነበር። 

ከሁሉም ቀዳሚው ሕዳር 10 ቀን 2012 ዓ.ም የተካሔደው የሲዳማ ሕዝበ-ውሳኔ ነው። የሲዳማ ክልል ከነባሩ የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል ሥልጣን በይፋ የተረከበው ሰኔ 11 ቀን 2012 ዓ.ም. ነበር። 

ሶስቱ ሕዝበ-ውሳኔዎች በ1985 ዓ.ም. ደቡብ ክልልን ከመሠረቱት መካከል ጉራጌ እና በጉራጌ ዞን ሥር የሚገኙ እንደ ማረቆ ያሉ ብሔረሰቦች፤ ሐድያ፣ ስልጤ፣ ሐላባ እና ከምባታ ጠምባሮ ዞኖች እንዲሁም የም ልዩ ወረዳን ለብቻቸው ያስቀራቸዋል። የጉራጌ ዞን መንግሥት የተከተለውን አወቃቀር በጽኑ ሲቃወም ቢቆምይ ዞኖቹ እና ልዩ ወረዳዎቹ "ማዕከላዊ ኢትዮጵያ" የተባለ ክልል ያቋቁማሉ ተብሎ ይጠበቃል። 

ይኸ የውይይት መሰናዶ እነዚህ ሶስት ሕዝበ-ውሳኔዎች በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል የተነሱ ጥያቄዎችን ፈተው እንደሁ ያጠይቃል። ውይይቱ የካቲት 2 ቀን 2015 ዓ.ም. የተቀረጸ ነው። የፖለቲካ ተንታኙ አቶ ደያሞ ዳሌ፣ የጉራጌ ዞን ክልል ለመሆን ያቀረበውን ጥያቄ በቅርበት የሚከታተሉት አቶ መሐመድ አብራር፣ የዎላይታ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ግንባር ሥራ አስፈጻሚ አባል አቶ አሸናፊ ከበደ እና የዶይቼ ቬለ የሐዋሳ ዘጋቢ ሸዋንግዛው ወጋየሁ በውይይቱ ተሳትፈዋል። 

ሙሉ ውይይቱን ለማድመጥ የድምጽ ማዕቀፉን ይጫኑ

እሸቴ በቀለ
 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW